February 15, 2022

በሀኪሞች ቅጥር ዙሪያ እያወዛገበ ስላለዉ የቋንቋ ጉዳይ ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

City: Addis AbabaHealth

ታካሚዎች በተለያየ የቋንቋ ችሎታ ደረጃ ላይ ቢሆኑም የህመም ስሜቶችን ለመግለፅ አንድ ቋንቋ ይበልጥ ተመራጭ ይሆንላቸዋል።

Avatar: Ilyas Kifle
By Ilyas Kifle

Ilyas is a reporter at Addis Zeybe experienced in creative writing and content production.

በሀኪሞች ቅጥር ዙሪያ እያወዛገበ ስላለዉ የቋንቋ ጉዳይ ባለሙያዎች ምን ይላሉ?
Camera Icon

Credit: getty images

ከሰሞኑን የክልል ጤና ቢሮዎች የጠቅላላ ሀኪም የቅጥር ማስታወቂያ በስፋት አውጥተው ነበር። በክፍት የስራ ማስታወቂያዎቹ ላይ የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ የክልሉን የስራ ቋንቋ ማንበብ፣ መፃፍ እና መናገርን እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸው ብዙ ሲያነጋግር ሰንብቷል። አዲስ ዘይቤ በተለያዩ ክልሎች የስራ ቆይታ ያደረጉ የህክምና ባለሙያዎችን ስለጉዳዩ አነጋግራለች።

ዶክተር ሀብታሙ አውለው ‘ሀኪም’ በተሰኘው ከ235 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት የህክምና ጉዳዮች ገፅ ላይ “ሀኪም አለማቀፋዊ ባለሙያ ነው። አንድ ሀኪም የህክምና ትምህርት የሚማረው የራሱን ብሔር ብቻ መርጦ ለማከም ሳይሆን የሰው ዘርን በሙሉ በቋንቋ፣ በብሔር፣ በሀይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት... ወዘተ ሳይለይ ሁሉንም በእኩልነት ለማገልገል ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ ይህንን አለማቀፋዊ መርህ የሚፃረር ተግባር እየተፈጸመ ነው” የሚል መልእክት አስተላልፏል”።

ቋንቋ በህክምና ሙያ ውስጥ ያለው ሚና ምንድን ነው?

የኢትዮጵያ ሕክምና ህግ እና ሥነ ምግባር ማህበር መስራች የሆኑት ዶክተር መልካሙ መዓዛ እንደሚገልፁት “በህክምና ስራ ቋንቋ ከመግባባት ባለፈ ችግሩን ለመረዳት እና ለመፈወስ የሚያግዝ ቁልፍ ጉዳይ ነው። የአንድን ታካሚ ችግር ለማወቅ 75 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚወስደው በህክምና ባለሙያው እና በታካሚው መካከል የሚደረገው ንግግር እና የመረጃ ልውውጥ ነው። የተቀረው ሳይንሳዊ ምርመራ እርግጠኛ ለመሆን የሚደረግ ነው”።

ታካሚዎች በተለያየ የቋንቋ ችሎታ ደረጃ ላይ ቢሆኑም የህመም ስሜቶችን ለመግለፅ አንድ ቋንቋ ይበልጥ ተመራጭ ይሆንላቸዋል። 

እንደ ዶክተር መልካሙ ገለፃ “በሀኪምና ታካሚ መካከል ከሚፈጠሩ ቅራኔዎች ወይም አለመግባባቶች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ባለመግባባት የሚመነጩ ናቸው”

ሀሳቡን በፌስቡክ ላይ የገለፀው ዶ/ር ሀብታሙ አክሎም “እኔ 6 አመት በኦሮሚያ ክልል በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርቴን ስማር ፣ እንዲሁም የመጨረሻውን አንድ አመት ኢንተርንሺፕ ስሰራ ኦሮምኛ ቋንቋ አለመቻሌ ታካሚዎችን ለመመርመርም ሆነ የሚያስፈልጋቸውን ህክምና በወቅቱ ለመስጠት አንድም ቀን እንቅፋት ሆኖብኝ አያውቅም” ብሏል። 

የህክምና ባለሙያው እና ታካሚ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆኑ ምን ይደረጋል?

"በጋሞ ጎፋ ለስራ ተጉዤ አውቃለሁ” የሚሉት ባለሙያዉ “የአካባቢውን ቋንቋ በደንብ ባልናገርም ከታካሚዎች ጋር መግባባት አይከብደኝም ነበር፤ እንደውም ያለአስተርጓሚ ነበር ስራዬን የምሰራው። እዛ በነበረኝ የስራ ቆይታ ከባህሉ ጋር እራሱ ተቆራኝቼ ነዉ ያለሁት” ሲሉ ዶ/ር መልካሙ መአዛ ይናገራሉ። 

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለመዱ ሁለት አማራጮች አሉ የሚሉት ዶ/ር መልካሙ የመጀመሪያው ለህክምና ስራ ተብሎ በተለየ ሁኔታ የማስተርጎም ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ሲሆኑ ሌላኛው ደግሞ በታካሚ ዘመዶች ወይም አስታማሚዎች የሚደረግ ማስተርጎም መሆናቸውን ይገልፃሉ። 

ሁለቱም የየራሳቸው ጥቅምና ጉዳት አላቸው። የማስተርጎም ስራን የሚሰሩት ባለሙያዎች ሙያዊና የቋንቋ ክህሎት በጋራ ቢኖራቸውም  ሙሉ ሃሳብ ላይተላለፍ ይችላል። ታካሚው አስተርጓሚውን የማያውቀው በመሆኑ የጤና ችግሩን በዝርዝር ለማስረዳት ሲጠየቅ ምቾት አይሰጥም።

በቅርብ ዘመዶች እና አስታማሚዎች በኩል የሚደረገው የማስተርጎም ተግባር ደግሞ የቤተሰቡ አባል ወይም የታካሚው የቅርብ ሰው እንደመሆኑ ስሜትን እንደልባቸው እንዲገልፁ ያደርጋቸዋል። ግን ደግሞ ታካሚው ከሚናገረው በላይ የማጋነን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህ ክፍተቶች ቢኖሩባቸውም በመላው ዓለም ተግባራዊ የሚደረጉ አሰራሮች ናቸው።

እንደ  ዶ/ር መልካሙ ገለፃ "ቋንቋ የእኔነት ስሜትን በታካሚም ሆነ በህክምና ባለሙያው ላይ ይፈጥራል ግን ደግሞ ቋንቋ መስፈርት አድርጎ በሚወጡ ማስታወቂያዎች ልክ ባለሙያ ካልመጣ ማስታወቂያው ሊስተካከል ይችላል። ይሁን እንጂ በመጀመሪያው ማስታወቂያ ላይ ቋንቋ መስፈርት መደረጉ ባለሙያዎች የእኔነት ስሜት ተሰምቷቸው እንዳይመጡ ስለሚያደርግ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ቋንቋ ለህክምና ሙያ መስፈርት መሆን የለበትም። ስለዚህ መጀመሪያ ማስታወቂያ ራሱ “የአካባቢውን ቋንቋ ለመማር ዝግጁ የሆነ የሚል ቢሆን የተሻለ ይሆን ነበር”

የፋርማሲ ባለሙያ የሆነው ልዑል ሰለሞን ለሶስት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሰርቷል፤ አሁንም በአፋር ክልል በፋርማሲ ሙያ እያገለገለ ይገኛል። ከአንድ ዓመት በፊት ተመሳሳይ የስራ ማስታወቂያ ወጥቶ ለመቀጠር ሄዶ ከእዚህ በፊት በክልሉ መስራቱን ቢገልፅላቸውም ቋንቋው መስፈርት ስለሆነ መቀጠር አትችልም ተብያለሁ” ሲል ያስረዳል።  

በህክምና ስራ ቋንቋ መስፈርት እንዳይሆን የሚነሱት  ምክንያቶችስ? 

ሁለትና ከዚያ በላይ ቋንቋዎችን የሚናገሩ የህክምና ባለሙያዎች ተጨማሪ ጥቅም አላቸው። በኢትዮጵያ አንፃር ቋንቋ መስፈርት እንዳይሆን የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ባለሙያዎች ሲገልጹ፤ የቋንቋን ብዛት ከ85 በላይ ነው፣ የህክምና ባለሙያዎች እጥረት አለ፣ የተማረ የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል የሚመጣው ከከተማዎች መሆኑን ያነሳሉ።

በተጨማሪም ያሉት የህክምና ባለሙያዎች ቁጥር ምን ያህሉን ህብረተሰብ ይወክላሉ የሚለውን ማገናዘብ ያስፈልጋል ይላሉ።

“ወገኑን ለማገልገል የሚችል ሀኪምን የኔን ቋንቋ መናገር ፣ ማንበብ እና መጻፍ ካልቻልክ እዚህ ክልል መስራት አትችልም በሚል ምክንያት ከፍተኛ የሀኪም እጥረት ባለባት አገር በርካታ ህሙማንን ማከም የሚችሉ ሀኪሞችን ያለ ስራ ቤት ሲቀመጡ ማየት አግባብ ይሆን?” ሲል ይጠይቃል ዶክተር ሀብታሙ አውለው።

"ተጨማሪ ቋንቋ ማወቅ በህክምና ትልቅ ጥቅም ቢኖረውም ቋንቋን መስፈርት ማድረግ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም ። ቋንቋ መስፈርት በሚሆንበት ወቅት የክልሉን ቋንቋ የሚናገሩ የህክምና ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ ከሆነ ፍላጎቱን አይሞሉም፤ በዛው ልክ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎች ቁጥር በሚገኝባቸው ክልሎች ደግሞ ስራ የማያገኝ ባለሙያ እንዲኖር ያደርጋል። በረጅም ጊዜ ታቅዶበት ካልተሰራ በስተቀር መሰል እርምጃ ክፍተት ይፈጥራል" ያሉት ደግሞ ዶ/ር መልካሙ መአዛ ናቸው።

የመፍትሔ ሀሳቦችስ? 

በኢትዮጵያ ብሔራዊ የስራ ቋንቋ እንደመኖሩ ሁሉ ክልሎች የራሳቸው የስራ ቋንቋ እንዲኖራቸው ህገ መንግስቱ ቢፈቅድም የስራ ማስታወቂያ በቋንቋ ክህሎት ከሚገደብ ለማስተማር ዝግጁ መሆን እና ለመማር የሚፈልጉ ባለሙያዎችን መቅጠር የተሻለ ነው። ምክኒያቱም ህገ መንግስቱ ራሱ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ተንቀስቅሶ ሰርቶ ሀብት የማፍራት መብት ቢሰጥም የቋንቋ መስፈርት ይህን ሊያግድ ይችላል ሲሉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። 

ዋናው ነገር በህክምና ስራ ውስጥ ቋንቋ መስፈርት ከማደረግ ይልቅ “የእኔነት ስሜት በሚፈጥር መልኩ መሰረታዊ የሆነውን የአካባቢው ቋንቋ እንዲለምዱ ከውጭ ሀገር ለሚመጡት እንደሚደረገው አጭር ስልጠና መስጠት በቂ ይመስለኛል” ሲሉ ዶ/ር መልካሙ ይመክራሉ። 

“ቋንቋን መልመድ ለግለሰብም ሆነ ለስራው ጥቅም አለው፤ ነገር ግን መስፈርት መሆን ያለበት ጉዳይ አይደለም፤ የህክምና ባለሙያን ለመመዘን በእኛ ሀገር ልምድና አቅም ብቻ ነው መመዘኛ መሆን የሚችለው”

ማስታወቂያው ያለቋንቋ መስፈርት ወጥቶ ነገር ግን በአካል ሲኬድ ቋንቋን የሚፈትኑበት ሁኔታ እንደገጠመው የሚገልጸው ልዑል “መሰረታዊ ነገር ማስተማር እንጂ ቋንቋን ግዴታ ከማድረግ ይልቅ የአካባቢውን ቋንቋ ለመልመድ የሚፈልጉ ቢባል ብዙሀኑ ፍላጎት ይኖረዋል ስለዚህ የተሻለ አማራጭ የሚሆነው ይሄ ነው፤ ቋንቋ እና ሙያን በእኛ ሀገር ሁኔታ ማገናኘት ተገቢ አይደለም”

የህክምና ባለሙያ የሚመዘነው በስራ ልምዱ፣ በተመረቀበት ዘርፍ በአጠቃላይ በወረቀት መሆን እንደሚገባው ባለሙያዎች ይስማማሉ። 

ከውጭ ሀገራት የሚመጡ የህክምና ባለሙያዎች አዲስ አበባ ሲገቡ የ3 ወራት የቋንቋ መሰረታዊ ስልጠና ይሰጣቸዋል። የትኛው ቋንቋ በስፋት ይነገራል እና ወደሚሰማሩበት አካባቢ የሚነገረውን ቋንቋን በተለየ ትኩረት ይሰለጥናሉ።