ኅዳር 13 ፣ 2012

"የጃኪ ቻን ልጆች"

Lifestyle

"የጃኪ ቻን ልጆች"

"የጃኪ ቻን ልጆች"

ብዙው የሀገሬ ሰው ጃኪ ቻን ሀዋሳ ውስጥ ልጆች እንዳሉት አያቅም፡፡ ፍሬዎቹም አድገውና አብበው የዘመኑን መንፈስ እንደመሰሉ መረጃ ያለው አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ የሚከተለው ትርክት እነዚያ ከኔ ጋር ከ05 እስከ ጥቁር ውኃ፤ ከታቦር እስከ 01፤ ከኮምፖኒ እስከ ጎርጓዳ፤ ከከውቆሮ እስከ ሀረር፤ ከኦሲስ እስከ 5ኛ ካምፕ፤ ከወንዶ ጢቃ እስከ አሞራ ገደል፤ ከእርሻ ጣቢያ እስከ ሞኖፖል ሰፈር... ድረስ አብረን ክፉና ደጉን ስላሳለፉ 'ምናባዊ' ወጣቶች ነው፡፡

መጋቢት 2006 ዓ.ም በማላስታውሰው አንድ ቀን ጓደኛዬ ወሳኝ አክተር ሀዋሳ እንደሚመጣ አበሰረኝ፡፡፡ ቅዳሜና እሁድ በአርቲስት በሚሞላ ከተማ ለሚኖር ሰው ወሬው ልብ የሚያንጠለጥል አልነበረም፡፡ ወዳጄ ግን በቀላሉ አለቀቅኝም "ጃኪቻን! የልጅነት የሳቅ ምንጫችን፣ የጠራራ ወጣትነት መደበርያችን፣ የጭንቅ ጊዜ አማላጃችን...ዛሬ ከች ይላል" አለኝ።

እረ-ባክህ?

ከምር! የጆኒ ቪድዮ ቤት ትዝ አላለችህም፤ አረብ ሰፈር የነበረችው?

ጊዜ ካገኘሁ እሄዳለሁ ስለው

ጓደኛየ ጮኸ

ያምኸል እንዴ? ይሄኔ አሸዋርያ ብትመጣ ኖሮ እንደ እርግብ ትበር ነበር፡፡ እረ ለመሆኑ በጃኪ የሚጨክን አንጀት ከወዴት አገኘህ? ከመቼው ልጅነታችንን ለመርሳት እንዲህ ተጣደፍክ?... እና ሌሎች የቁጣና ምክር አዘል ቃሎችን አዝንቦብኝ ተለያየን፡፡

በርግጥ ጓደኛዬ ትክክል ነው፤ እርሱ ለቻይና ካራቴ ከቁርስ ዳቦው ላይ ቀንሶ ሶል ቪድዩ ቤት ይገባ ነበር፡፡ እርሱ ለጀት ሊ የማርሻል አርት ክትክት ስኪርቢቶ መግዛቱን ትቶ ወንዴ ፊልም ቤት ይታደም ነበር፡፡ የኔ ጸባይ ከዚህ ይለያል፤ ህንድ ፊልም ነፍሴ ነው! የሰፈሬ ልጅ ብረሀኑ እንደ ሆሊውዱ ቫንዳም እግሩን ሊፈለቅቅ ሲጥር እኔ ጸጉሬን እንደ አሚር ከምበል ደፋ አደርጋለሁ ብየ የእህቴን ዘኒት ቅባት ጨርሻለሁ፡፡

ከዓመታት በፊት ከወንደላጤ ሰርቪስ ቤት ፖስትር እስከ ማስቲካ ስቲከር ድረስ የቦሊውድ አክተሮች ፎቶ በከተማው ላይ ፈሶ ነበር፡፡ በ2000ዓ.ም መጀመርያ ላይ የነ ጌቾ ትርጉም ሲጀመር ሻህሩክ ካህን የቤተሰብ ያክል፤ ፕርያንካ ቾፕራ የዘመድ ያክል፤ የፕሪቲ ጆንስን ሙዚቃውን ደግሞ እንደራሳችን ባህል ቆጠርን (ጌቱ ኦማህሬ ትዝ ይለኛል)፡፡ እነዚህን ፊልሞች ከአሜሪካ ፊልም ጋር ቀላቅለው የሚያሳዩ የሳጣራ ቤት አስታውሳለሁ፡፡ የተጣመመ የእንጨት ወንበር፤ በክረምት ዝናብ እንዲሁም በበጋ የጸሀይ ጨረር የሚያስገባ ግርግዳ፤ በተቃቀፉ የህንድ ተዋናዩች የተለበደ ጭቃ፤ በራቸው በመጋረጃ ጨርቅ የተጋረደ፤ ቀጫጫ ሂሳብ ተቀባዩች ያሏቸው ቪድዩ ቤቶችን በሰፈሬ አይቻለሁ፡፡ በቀዳዳ ሱሪያቸው አፍር ላይ የተቀመጡ ህጻናት፤ ጸጉራቸውን የሚፈትሉ ታዳጊዎች፣ ጥፍራቸውን የሚነክሱ ወጣቶች፤ መኪናቸው ጋራጅ የገባባቸው ወያላዎች ጋር ዱቅ ብየ ኸርቲክ ሮሻን የሚሰራበት 'ክሪሽ' ሙቪ ተመልክቻለሁ፡፡ የሆነ ግዜ ጆሲ ቬንትለተር እና ጀላቲ ያለው ፊልም ቤት ከፍቶ ሰፈራችንን ከቴክኖሎጂ እና ከቅዝቃዜ ጋር አገናኛት፡፡ 

ዛሬ ቪድዩ ቤቶቹ በአብዘሀኛው ወደ DSTV እና ኪራይ ቤቶች ተቀይረዋል፤ የዛን ጊዜው ታዳጋዎችስ የት ደረሰው ይሆን?

የህልም-ዓለም ልጆች

ዳንኤል ሜንስ እኤአ በ2014 ለንባብ ባበቃውና Hope is Cut; Youth, Unemployment and the Future in Ethiopia በተሰኘ ጥናታዊ መጸሀፉ ጅማ ውስጥ የሚኖሩ ወጣችን የከሰዓት በኃላ እና ምሽት ህይወት ምን እንደሚመስል በዝርዝር ተመልክቷል፡፡ ከአመት በላይ ከነርሱ ጋር በማሳለፍ ምርምሩን በተጨባጭ መረጃና እውነታዊ ገጠመኝ እንዲሞላ ጥረት አድርጓል፡፡ በጽሁፉም ትምህርት ቀመስ የሆኑ ስራ አጥ ወጣቶች ጊዜያቸው በቪድዮ እና ጫት ቤቶች እንደሚያሳልፉ ያትታል፡፡ በይሉኝታ እና በምናባዊው ዓለም የሚዋልሉት ወጣቶቹ ከእጃቸው እያመለጠ ያለውንንና  የማይጨበጥ ነጋቸውን ሲኒማ በሚሰጣቸው ቀመር መሰረት ያሰላሉ፡፡ "ተምረናል፣ መስራትና መለወጥ እንፈልጋለን" የሚል ተደጋጋሚ ቃል እንዳጫውቱት የሚገልጸው ዳንኤል ይሁን እንጂ አዲስ ቀን በነጋ ቁጥር ጧት የስልክ እንጨት፤ ከሰዓት ቪዲዮ ቤት፤ ማታ ደግሞ ግሮሰሪ ተደግፈው እንደሚያያቸው ያስረዳል፡፡  

ብርያን ላኪን በበኩሉ የናይጀርያ ወጣቶች እንዴት ማህበረሰቡ የከለከላቸውን የፍቅርና ወሲብ ተምኔት በቦሊውድ ፊልም አማካኝነት በአቋራጭ ለማገኘት ጥረት እንደሚያደርጉ  አኤአ በ1997 ባሳተመውእና Indian Films and Nigerian  Lovers በተሰኘ መጣጥፉ ይገልጻል፡፡ ወግ አጥባቂና በብዛት የእስልምና ሀይማኖት ተከታይ በሆነው የ'ሀውሳ' ማህበረሰብ ውስጥ ከልቁ የአሜሪካ ፊልም ይልቅ ቁጥቡ የህንድ ፊልም ተመራጭ ነው፡፡ ሆኖም እነዚህ የቦሊውድ ፊልሞች ራሳቸው በማይጨበጥ የፍቅር ታሪክና ወሲብ ቀስቃሽ በሆኑ የዳንስ ትዕይንቶች የተዋቀሩ ናቸው፡፡  ስለሆነም የ'ሀውሳ' ታዳጊዎች ማህበረሰቡ ካስቀመጣቸው እሴቶች እየተንሸራተቱ መምጣታቸውን እንዳረጋገጠ ላኪን በምርምር ስራው ይተንትናል፡፡ 'ለሂያጅ የለውም ወዳጅ' እንዲሉ አበው፤ ከሆሊውድ የባህል ወረራ ቢያመልጡም ያረፉት በሌላኛው የባህል ወራሪ ቦሊውድ እቅፍ ውስጥ ነው፡፡

እኔና ጓደኞቼም የዚሁ አዙሪት ሰለባ ነን፤ በርግጥ አሁን ወደ እንግሊዝ ኳስና ፌስቡክ ተሸጋግረናል፡፡ በምሳሌነት የተወሰኑትን ላንሳና እንዴት ራሳችንን እና ጊዚያችንን እንደተቀማን ላጫውታችሁ፡፡ ወዳጆቼ እንዳይቀየሙብኝ እውነተኛ ስማቸው ተቀይሯል፡፡

ያቆብ ገነሞ- በሰፈራችን ፎቶ ተነስተህ ምስሉ አልመች ሲለህ 'ከዚህስ የያዕቆብ ስዕል ይሻላል' ማለት የተለመደ ነበር፡፡ ያዕቆብ እርሳስ ጨብጦ ተወልዶ ላፒስ የሚጠባ ይመስል ያቺ ብርቱካናማ እንጨት ከጁ አትለየውም፡፡ በልጅነታችን ከጋሽ አስረስ 10 ማርክ እንዲሁም ከመስፍኔ ሱቅ ሁለት ሜንታ ከረሜላ የተሸለመው ሳያዩት ስሏቸው ነው፡፡ የእንቁጣጣሽ በዓል በሱ ይደመቃል፤ ከልብ ጎን የሚሞነጭራት ባለ እሾህ አበባ በያቆብ ትለሰልሳለች፡፡ ሀዋሳን ከነ 'ቀኃሷ' ቁጭ ሲድርጋት እጁን አገጩ ላይ ያልጣለ ጩጬ አልነበረም (የሀዋሳ ፕላን በ1950 ዎቹ ሲነደፍ ቀኃስ ወይም ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ የሚል ምህጻረ ቃል አለ ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ አንዳንዶች ታቦር ተራራ ላይ ወጥተን በአይናችን በብረቱ  ተመልክተናል ይላሉ፡፡ ሆኖም ይህ የተሳሳተ ሀሳብ እንደሆነ ራስ መንገሻ ስዩም አረጋግጠውልኛል)፡፡

የጆን ቪድዮ ቤት ሲከፈት ግማሹ ደብተሩን ጥሎ፣ እኛ ኳሳችንን ለግተን፣ ያቆብም እርሳሱን ወርውሮ ፕሮቫ ለማየት መጋፋት ጀመርን፡፡ በወቅቱ ሳንቲም ኔፕ ስለሆንን መቀፈል ለመድን፤ ማጭበርበር ቀጠልን፡፡ ክፉ ቀን ሲመጣም ከቡታጋዝ ነዳጅ ላይ መቀነስ፤ ከዳቦ ሂሳብ ላይ መቆንጠር፤ ደብተር ሰይጠፋን ጠፋ ብለን ከቤተሰብ ቦርሳ ብር መመንተፍ ስራችን ሆነ፡፡ አዲስ ልጆች ሆንን፤ አዲስ ባህሪ ተማርን፤ አዲስ ማንነት ወረስን፤ አዲስ አለም የፈጠርን መሰለን፡፡ መሰለን ያልኩት አንዳንድ ጊዜ የፊልሙ ዓለም እውነታና የምንኖረው ህይወት እውነታ አልገጣጣም ስለሚለን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ውስጣንን ይረብሸዋል፡፡ መበሳጨት ስለማንፈልግ ተምለሰን ወደ መደበቂያችን ጉድጓድ ዘለን እንገባለን፡፡ ያቺ ጉድጓድ 'ቪድዮ ቤት' ትባላለች፡፡

በቅርቡ ተመጦ እንደተጣለ ሾንከራ በዝንብ የተወረረ ወጣት ሸምሱ በለጮ ቤት ፊትለፊት አየሁ፡፡ በደረቀ የጫት እንጨት እግሩ ላይ ይሞነጫራል፡፡ ትካሻው ላይ በቢጫና በጥቁር ቀለም መኃል የሚዋልል አዳፋ ጃኬት ደርቧል፡፡ ጸጉሩ በስነስረዓት ተክርክሟል፡፡ ፊቱ አይታይም፤ ደግሞ  እንዳቀረቀረ ነው፡፡ አብሮኝ ያለው ጓደኛየ "ያቆብ እኮ ነው!"ብሎ በእጁ ሲጠቁመኝ ደነገጥኩ፡፡ አላመንኩም፤ በርግጥ ከተያያን ከ12ዓመት በላይ ሆኗል፡፡ በራሴ ሀፍረት ተሰማኝ፡፡ የማናገርበት ወኔ አጣሁ፡፡ መንፈሱ እንዳልረብሽበት ስል አለፍኩት፡፡ 

ምህረተአብ ዳንጊሶ - ህንድ ፊልም ባለፈበት እንድከተል፤ ቦሊውድ ባረፈበት እንድቀመጥ ምክኒያት ከሆኑት የልጅነት ጓደኞቼ ውስጥ ኪያ አንዱ ነው፡፡ የሆነ ጊዜ ካጀልን ካላገባሁ ብሎ እጁን በመርፌ ሲወጋ፤ ደሙን ፖስተሯ ላይ ሲቀባ፤ ራሱን እንደተመታ እባብ እጥፍጥፍ ብሎ 'ሁምኮ ሁሚሴ ቹራሎ' ሲዘፍን የትላንት ያህል ትዝ ይለኛል፡፡ እርሱ ከልቡ መተረክ ይችል ነበር፡፡ ፍቅር ገንዘብ በሚሉት መጋረጃ፤ እውቀት በሚሉት አጥር እና ሀገር በሚሉት መከላከያ በፍጹም እንማይወሰን ይሰብከናል፡፡ በወቅቱ ከሮዝና ንግስት መጽሄት ላይ የለቀማቸውን ጥቅሶች እየጨማማረ ሲያወራ አፋችንን ከፍትን ከማዳመጥ ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበረንም፡፡ እናም እርሱን ስንከተል መጀመርያ ምሳችንን፤ ከዚያ ቤታችንን በኃላም ትምህርታችንን መቅጣት ቀጠልን፡፡ 

በቀን ሶስት የህንድ ፊልም እናይ እኮ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ኪያ አረብ ሀገር ስሙን ባልነገረኝ የስራ ዘርፍ ተሰማርቶ የእውነታውን ዓለም ኑሮ ይገፋል፡፡ 

"አሁን የኔ አሟሟት አሟሟት ነው ወይ፤ 

ውቢቷን ካጀሌን አንድ ቀን ሳላይ"እያለ የሚቆዝም ይመስለኛ፡፡

ድብርታሞቹ

ጸጋየ ኃ/ማርያም 'የጨርቆስ ልጅ' የተሰኘ ግሩም መጸሀፍ በ2008 ዓ.ም አሳትሟል፡፡ የጨርቆስን ጓዳ-ጓድጓዳ፤ መልክና ጸባይ፤ ትላንትናና ዛሬ፤ ደግና ክፉ እንዲሁም ተስፋና ፍረሀት በመልክ በመልኩ ደርድሯል፡፡ ጸጋየ እንዲህ ሲል ስለ ፊልም ቤቶች ያጫውተናል፤

"በአስራ ሶስት ቀበሌ የማይታይ ነገር የለም፡፡ ጫት የሚቅመው በረንዳ ላይ ወጥቶ ይቅማል፤ ቪድዮ ለማየት የሚኳትነውም ይኳትናል፡፡ ይህ ቀበሌ ለብዙ ወጣቶች መደበርያ ሊሆናቸው የሚያስችል ቪድዮ ቤቶችን የያዘ ነው፡፡ አብዘሀኛው የቂርቆስ ወጣት ሱስ ሀሁ የጀመረው እንደ አሸን በፈሉት የአስራ ሶስት ቀበሌ ቪድዮ ቤቶች ውስጥ ተደብቆ ነው"(ገጽ-37) ፡፡

ደራሲ መሀመድ ሰልማን በበኩሉ የዶሮ ማነቂያ ቪድዮ ቤቶች እንዴት የራሳቸውን ቋንቋ ፈጠረው የወሲብ ፊልም እንደሚያስኮመኩሙ በ'ፒያሳ ሙሀመድ ጋ ጠብቂኝ' መጸሀፉ ይገልጻል  (በርግጥ እርሱ ይህን ክስተት ከአራዳነት ጋር አያይዞታል ሆኖም እኔ አልስማማበትም)፡፡

እነዚህ ሁለት ምሳሌዎች ፊልም ቤቶች እንዴት ከፍ እንዳሉና  የአገልግሎት አድማሳቸውም እያሰፋ መምጣታቸውን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ጆንአቢንክ Being young in Africa: The politics of despair and renewal የተሰኘመጣጣፍአለው፡፡

በጽሁፌ አጋማሽየ ድህረነጻነት ትውልድ(Post independence generation) የሚባለው አፍሪካዊ እንዴት ተስፈኛ፣ለለውጥ የቆረጠ እና ለራሱ የነበረው ግምት ከፍተኛ እንደነበር ያብራራል፡፡

በኢትዮጵያም በተለይ የ1960ዎቹ ትውልድ ለዓላማው ባለው ቁርጠኝንት (ትክክልም ይሁን ስህተት) ፤ ለሀገር ባለው ፍቅር (እውነትም ይሁን ውሸት) ፤ለስነምግባር ባለው ግምት (የራሱ ይሁን የተኮረጀ) በጉልህ ይጠቀሳል፡፡እውቁ የፍልስፍና መምህር መሳይ ከበደ በበኩሉ የ‹ያትውልድ› መለያው ዘመናዊ ትምህርት፣ ሥልጣኔው ምዕራባዊነቱ፣ ዕውቀቱ ዲፕሎማው ነበር።በጥድፊያ ወጥኖ፣በአቆራራጭ ለመቋጨት የሚባትል የዋህ ነበር። ሥርነቀላዊነት መቆላመጫው፣ ተልዕኮው ጻድቅና ሐዋሪያዊ፣ መርሁም የማይበረዝ የማይከለስ በመሆኑ፣ ለመግባባት፣ ለኅብር፣ ለተቻቻይነት፣ ለጥገና፣ በአጠቃላይ ለሰብኣዊነት ጊዜ አልነበረውም ይላል። ይህን ባተሌነት የታዘቡት የ'ምርኮኛ' መጸሀፍ ደራሲ ቆንጅት ብረሀን "እረፍት አልባው ትውልድ" ሲሉ ይገልጹታል፡፡

ይሁን እንጂ ረጅም ርቀት ያደርሳሉ የተባሉት የነጻነት መሪዎች የህዝባቸውን ማህበረ- ኢኮኖሚ ህይወት ማሻሻል ተስኗቸው በቀደመ ስኬታቸው ተጠልፈው ወድቀዋል፡፡እናም የእነዚህ እብዮተኛ ልጆችም ባዶነት እንዲሰማቸው፣ በፍረሀት እንዲከበቡና የቀቢሰ-ተስፋ እስረኛ እንዲሆኑ አስገድዷል፡፡ ከታሪኩና ከወላጆቹ የተነጠለ ታዳጊ የማንነት ክፍተት ያጋጥመዋል፡፡ ሙዱ ተደክሎ ድብርት ጎጆ ይሰራበታል፡፡ ይህን ቀዳዳ ለመድፈን ፊልምና ጫት ቤቶች እንደ መፍትሄ ይወሰዳሉ፡፡ እነርሱ ደግሞ ማስረሻ/ማደንዘዣ ይሆናሉ እንጂ ዋናውን መደኃኒት አይተኩም፡፡

Photo: FAO/Petterik Wiggers

ምናባዊ ልጆች

ጃኪ ቻን ሀይሌ ሪዞርት ተከስቷል፡፡ እንደጠበኩት አላገኘሁትም፤ አርጅቷል፡፡ ሳቁ እንዳለች ናት፤ ቅልጥፍናው ዛሬም አብራው ነች፡፡ የሆነ የቅርብ ቤተሰቤን ያገኘሁ ያክል ተሰምቶኛል፡፡ ለነገሩ እኔ ብቻ አይደለሁም ብዙ ወጣቶች እሱን ለማቀፍና አብረውት ፎቶ ለመነሳት ሲጓጉ ታዝቤያለሁ፡፡ ለእርዳታ ነበር የመጣው፤ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና እርሻ ልማት ድርጅት(FAO) ፕሮጀክቶችን ለመጎብኘት፡፡"ባህላችሁ እና ሀገራችሁ ውብ ነው፤ ለሌሎች አስተዋውቁ፤ ጠብቁትም" ሲል ሰማሁት፡፡ ከተሰረቅን በኃላ፤ ልባችን ከሀገር ከወጣ በኃላ! 

በራምቦ፣ በቡርስሊና መሰል የፊልም አክተሮች ያደግን የመንፈስ ልጆች ዛሬ ሌላ ዓለም ገብተናል፡፡ ከሚታየውም ሆነ ከማይታየው ዓለም በጣም ርቀናል፡፡ ይህን ቀዳዳ ይሞላልናል ያልነው ፊልምም ቅዠት ሆኖ ሜዳ ላይ በትኖናል፡፡  የዘመኔ መንፈስ እንዲህ ሆኗል! ዘመናዊነትን ከነአሰስገሰሱ የወረሰ፤ ከራሱ ባህል የተገነጠለ፤ ከነባራዊው እሴት ያፈነገጠ፣ ያለበትን ኅብረተሰብ ከምዕራቡ ጋር እያነፃፀረ የሚብከነከን፣ ራሱን በለውጥ ሐዋርያነት የሚፈርጅ ትውልድ አየሩን ሞልቶታል፡፡ የኔ ትውልድ ሰምና ወርቅ ይህን መስሏል፡፡ መሳይ ከበደ "ይኽ ተቀጣጣይ ዝንባሌ በፅኑ ማኅበራዊ ቀውስ ወይም በሌሎች ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች በመባባስ፣ ወጣቱን ወደአብዮታዊና ፅንፈኛ ርዕዮቶች ይገፋፋዋል፣ ትውልዳዊ ግጭቱንም አስከፊ ያደርገዋል" ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር  (ገጽ71፤ትርጉም ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም)። አሁን  በሀገራችን የምናየው ይሄን ይሆን? የጃኪ ቻን የመንፈስ ልጆች አደባባዩ ጋ ደርሰን ይሆን እንዴ?

አስተያየት