ሐምሌ 6 ፣ 2013

መጽሐፍትን በትረካ የሚያቀርበው መተግበሪያ

ቴክየአኗኗር ዘይቤ

ማንኛውም ግለሰብ የሚፈልገውን መፅሃፍ በትረካ መልክ በድምፅ የሚያገኝበት 'ተራኪ' የተሰኘ መተግበሪያ ባሳለፍነው ሳምንት ኦልራይትስ ቴክኖሎጂስ በተባለ የቴክኖሎጂ ተቋም ይፋ ሆኖ ለተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

መጽሐፍትን በትረካ የሚያቀርበው መተግበሪያ

ማንኛውም ግለሰብ የሚፈልገውን መፅሃፍ በትረካ መልክ በድምፅ የሚያገኝበት 'ተራኪ' የተሰኘ መተግበሪያ ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ ሆኖ ለተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

ኦልራይትስ ቴክኖሎጂስ በተባለ የቴክኖሎጂ ተቋም ናሆም ጸጋዬ እና አቤል ግርማ በተባሉ ባለሙያዎች አማካኝነት በልፅጎ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይህ መተግበሪያ አማርኛ፣ ኦሮምኛን ጨምሮ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የተፃፉ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መፅሃፍትን ተርኮ የሚያቀርብ ሲሆን ጥቂት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፉ መፅሐፍትንም አካቷል።

አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቻቸው የኦልራይትስ ቴክኖሎጂስ ኃላ.የተ.የግ.ማኅበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ናሆም ፀጋዬ ስለመተግበሪያው እንዲህ በማለት ያስረዳሉ: "ተራኪ መተግበርያ በአሁን ሰዓት ሀያ አምስት የሚሆኑ የተለያዩ ይዘቶች ያላቸውን መፅሐፍትን ለተጠቃሚው በትረካ ያቀረበ ሲሆን ከ30 በላይ ደራሲያን ጋር በህጋዊ መልኩ ውል ወስዶ እየሰራ ይገኛል " ብለዋል።

መተግበሪያው ይፋ በሆነ በሳምንቱ ሰፊ ተደራሽነት ማግኘቱንና በቅርቡም ተጨማሪ መፅሐፍትን በድምፅ ትረካ ለማቅረብ በስራ ላይ እንደሚገኙም ስራ አስኪያጁ ነግረውናል።

የተራኪ መተግበርያ  ፖለቲካ፣ የልጆች ተረት፣ ፍልስፍና፣ ልብወለድ፣ የህይወት ታሪክ/ማስታወሻ፣ ሀይማኖት፣ እውነተኛ ታሪክ እና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ የተፃፉ መፅሀፍትን በትረካ አቅርቧል። 

ተጠቃሚዎች ማግኘት ከሚችሏቸው የድምፅ ይዘቶች መካከል በክፍያ ብቻ ተደራሽ የሚሆኑ ሲኖሩ የተቀሩት ግን በነፃ ቀርበዋል፡፡ በክፍያ የሚቀርቡትን ዓለም አቀፍ የክፍያ ካርዶችን በመጠቀም ማግኘት እንደሚቻልና በቅርቡም ከሀገር ውስጥ ዲጂታል ክፍያ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር የማስተሳሰር ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆናቸው የተራኪ መስራቾች ይናገራሉ፡፡ ለአሁኑ ግን ተጠቃሚዎች 100 ያህል የድምፅ ይዘቶችን ከአንድሮይድ መተግበሪያው (በቅርብ በiOS ይቀርባል) ላይ በነፃ አውርደው መጠቀም የሚችሉ ይሆናል፡፡

ከመፅሐፍቱ በተጨማሪ የተለያዮ በድምፅ የቀረቡ ፕሮግራሞች (ፖድካስቶች) በመተግበሪያው የተካተቱ ሲሆን በመዝናኛ፣ ቴክኖሎጂ፣ ቲቪ/ፊልም፣ ማህበረሰብ/ባህል፣ የህይወት ዘይቤ፣ ዜና፣ ኮሌጅ፣ ኮሜዲ፣ የግል ዕድገት፣ ትምህርትና ሌሎች ተጨማሪ 20 ጉዳዩች እንደሚዳሰሱበት ታውቋል።

ስራ አስኪያጁ እንደነገሩን ከሆነ እንደ'ተራኪ' አይነት መተግበርያ በሀገራችን ሲሰራ የመጀመርያ ባይሆንም ከስፋትና ከተደራሽነት አኳያ ግን የመጀመርያ ነው ለማለት ያስደፍራል።  "ለደራሲዎችስ ምን ጥቅም ይሰጣል?" ስንል የጠየቅናቸው ስራ አስኪያጁ "ይህን ስራ ስንሰራ ከደራሲዎቹ ጋር የምንዋዋለው ውል ይሄን ያካትታል በዛም ከሚያገኙት የተለያዩ ጥቅሞች መካከል ከትረካው ከሚገኘው ገቢ በፐርሰንት ትልቁን ድርሻ መውሰዳቸው አንዱ ነው" ሲሉ መልሰዋል።

የተራኪ መተግበርያ 'ሰርቨር' አገልግሎቱን በጥረት አንዲሰጥ ተደርጎ የተሰናዳና ደረጃዉን የጠበቀ እንደሆነም ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። 

ይሄ መተግበርያ በወረቀት መፅሃፍት ሽያጭ ላይ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀውን ተፅዕኖ ለማወቅ አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቻቸው የሜክሲኮ አምደ መፅሃፍት ባለቤት አቶ ኤሊያስ ገብረማርያም "ለደራሲው ሌላ አይነት አማራጭ ነው የወረቀት ህትመት ሽያጭም ሆነ የዲጂታል ህትመት ሽያጭ የሚያገኙት ገቢ ይኖራል። በኛ ገበያ በኩል ደግሞ ሰው በምርጫው ነው የሚጠቀመው ማንበብ የሚመርጥ ያነባል መስማት የሚፈልግ ይሰማል ስለዚህ አማራጭ ከማስፋት ባለፈ የሚያጠበው ነገር አይታየኝም። በዚያ ላይ ማንበብ እየፈለጉ በተለያዩ ምክንያቶች ለማይችሉና ማየት ለተሳናቸው አሪፍ አማራጭ በመሆኑ ሊበረታታ ነው የሚገባው" ሲሉ አስተያየታቸውን ነግረውናል።

በዓለም ላይ አንደ ኦውዲብል፥ ኮቦ ቡክስ፥ እና አማዞን ኪንድልን የመሳሰሉ የድምፅ መፅሐፍትን አገልግሎት በመስጠት የሚታወቁ መተግበርያዎች መኖራቸዉ ይታወቃል፡፡

አስተያየት