መጋቢት 22 ፣ 2013

የአዋሽ 2 እና 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሠራተኞች መኖሪያ ላይ የእሳት ቃጠሎ ተከሰተ

ዘገባ

በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ የሚገኘዉ የአዋሽ ሁለት እና ሦስት የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሰራተኞች መኖሪያ ላይ በአንደኛዉ ብሎክ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ አደጋ የ19 አባወራ መኖሪያ ቤት ወደመ።

የአዋሽ 2 እና 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሠራተኞች መኖሪያ ላይ የእሳት ቃጠሎ ተከሰተ

ከአዲስ አበባ 117ኪ.ሜ ርቀት አርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ የሚገኘዉ የአዋሽ ሁለት እና ሦስት የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሰራተኞች መኖሪያ ላይ በአንደኛዉ ብሎክ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ አደጋ የ19 አባወራ መኖሪያ ቤት መውደሙ ተነግሯል። ከወደሙት 19 ቤቶች ውስጥ 3ቱ ሰው ያልገባባቸው እንደነበሩ ተነግሯል።

 

ሁለት ሰዎችን ለሞት ዳርጎ በአንድ ሰው ላይ ደግሞ መጠነኛ የአካል ጉዳት ያስከተለው ይህ የእሳት አደጋ ከ3.9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የንብረት ጉዳት እንዳደረሰ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።

 

አቶ ደቀቦ ባልቻ የአዋሽ ሁለት እና ሦሰት የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የጥበቃ አባል እና የሦስት ልጆች አባት ሲሆኑ በቃጠሎው ምክንያት በቤተሰባቸው እና በንብረታቸው ላይ ከፍተኛዉን ጉዳት አስተናግደዋል። ስለሁኔታዉ ሲያስረዱ “ከቀን 7 ሰዓት ጀምሮ መብራት ባለመኖሩ ምክንያት ማታ ላይ ከ8 ወር አራስ ባለቤታቸው ጋር ሻማ ለኩሰዉ አብረዉ እንዳመሹ” ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

 

ባሳለፍነዉ ጥቅምት ወር በኮሮና ቫይረስ ተይዘዉ በቅዱስ ጴጥሮስ ሆሰፒታል ለ15 ቀን በከፍተኛ ክትትል እንዳገገሙ የነገሩን አቶ ደቀቦ የሳንባ ቁስለት በሽታ ጭምር ስላለባቸው ለልጆቻቸው ደህንነት ሲሉ አንድ ልጃቸዉን ብቻ በመያዝ ሌላ ክፍል እንደሚተኙ ያስረዳሉ።

 

ባለቤታቸው ወ/ሮ አያሉ ቦሌ የ8 ወር ልጃቸውን እያጠቡ እንቅልፍ ሳይወስዳቸው እንዳልቀረና የተለኮሰው ሻማ አልቆ እሳቱ እንደተነሳ ግምታቸውን የሚያስቀምጡት አቶ ደቀቦ በዚህም ሟች ወ/ሮ አያሉ ትልቁ ልጃቸዉን ቀስቅሰዉ ከቤት ካስወጡ በኋላ ወደ ህፃን ልጃቸዉ ሲመለሱ ጭሱ አፍኗቸዉ ከነህጻን ልጃቸዉ ተቃጥለዉ እንደሞቱ፤ ትልቁ ልጃቸዉ ግን መጠነኛ ጉዳት ቢደርስበትም በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ነግረውናል።

 

የአዋሽ ሁለት እና ሦስት የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸዉ አበበ የእሳት ቃጠሎዉ በኃይል ማመንጫ ጣቢያው ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልፈጠረና በሠራተኞቹ መኖሪያ ላይ የደረሰዉ አደጋ በአካባቢዉ ነዋሪ ትብብር ከአንድ የመኖሪያ ጣቢያ ወደ ሌላ ጣቢያ እንዳይተላለፍ ማድረግ መቻሉን እና ጉዳት ለደረሰባቸው የድርጅቱ ሰራተኞች የተለያዩ የምግብ፣ የመኝታ እና የአልባሳት ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

 

በአዋሽ ተፋሰስ ላይ የተገነቡት የአዋሽ 1፣ 2 እና 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በአጠቃላይ 107 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫሉ።

አስተያየት