የካቲት 13 ፣ 2015

በጦርነት ሳቢያ ከሁለት ዓመታት በኋላ በአደባባይ የተከበረው የህወሓት የምስረታ በዓል

City: Mekelleዜናወቅታዊ ጉዳዮች

“በቅርቡ በተደረገው የምከታ ትግልም የትግራይ ህዝብን ለማጥፋት የከፈቱትን ወረራ መክቶ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ አሸጋግረውናል”- ደብረፅዮን ገብረሚካኤል

Avatar: Meseret Tsegay
መሰረት ፀጋይ

መሰረት ፀጋይ በጋዜጠኝነት ስራ ልምድ ያላት ሲሆን የአዲስ ዘይቤ የመቀሌ ከተማ ዘጋቢ ናት።

በጦርነት ሳቢያ ከሁለት ዓመታት በኋላ በአደባባይ የተከበረው የህወሓት የምስረታ በዓል
Camera Icon

(የፎቶ ምንጭ፡ ትግራይ ቴሌቭዥን- የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የአበባ ጉንጉን ሲያስቀምጡ)

ለሁለት ዓመታት በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ሳቢያ በአደባባይ ሳይከበር የቆየው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የምስረታ በዓል፤ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በመቀሌ ከተማ ተከብሯል።

48ኛው የህወሓት የምስረታ በዓል ባሳለፍነው ቅዳሜ የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በመቀሌ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል። የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የህወሓት ሊቀ መንበር እና የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት የሆኑት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በሰማዕታት ሐውልት ቅጥር ግቢ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።

ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት “ያለፉት 48 ዓመታት በርካታ ውጣ ውረዶች የታለፉበት፣ ከባድ ፈተናዎችን መሻገር የተቻለበትና በርካታ ድሎችን ማስመዝገብ የተቻለበት ዓመታት ናቸው” ብለዋል። የክልሉ ፕሬዝዳንት አክለውም ከትጥቅ ትግሉ በኋላ በርካታ የልማት ጊዜያት ቢያልፉም በድጋሜ ሌላ ትግል ውስጥ ተገብቶ የታለፈበት ወቅት በመሆኑ ሰማዕታትን ማስታወስ ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል።

“በቅርቡ በተደረገው የምከታ ትግልም የትግራይ ህዝብን ለማጥፋት የከፈቱትን ወረራ መክቶ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ ያሸጋገሩንን ሰማዕታት ዓላማ ማስጠበቅ ይገባል” ሲሉም ከጦርነቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከበረው የካቲት 11 በዓል ላይ የህወሓት ሊቀ መንበር ተናግረዋል።

የትግራይ ህዝብ ያለፉት 17 የትግል አመታት ብቻ ሳይሆን፣ የህዝቡን ህልውና ለማረጋገጥ የትግራይ አዲሱ ትውልድ ባደረገው ተጋድሎ ደማቅ ታሪክ ፅፏል” ብለዋል። የትግራይ ህዝብ ትጥቅ ትግል የጀመረበት የካቲት 11 በዓል በጦርነቱ ሳቢያ በሰማዕታት መታሰቢያ ለሁለት ዓመታት ሳይከበር ቢቆይም ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በተለያዩ ሁኔታዎች ሲያከብሩት ቆይቷል።

በዓሉን ለማክበር በሰማዕታት ሐውልት ታድመው ያገኘናቸውና ሀሳባቸውን ለአዲስ ዘይቤ ያካፈሉ ነዋሪዎች “የካቲት 11ን ከሁለት ዓመታት በኋላ በአደባባይ በማክበራችን ደስታ ተሰምቶናል” ያሉ ሲሆን አሁን ያለው የሰላም ተስፋ ዘላቂ እንዲሆን እንፈልጋለን ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ ባለፈው 17 ዓመታት ባካሄደው የትጥቅ ትግል ብቻ ሳይሆን “በታወጀበት የጄኖሳይድ ጦርነትን ለመመከት ያሳየው ፅናት እና ተጋድሎ በታሪክ በወርቅ ቀለም የተከተበ ነው” ሲሉም የህወሓት ሊቀ መንበር ተናግረዋል። የትግራይ ህዝብ እሴቶች ትውልዶች ሊማሩበት የሚገባ በመሆኑ ይህ ታሪካዊ ፅናት እና ጀግንነት በጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል የወደሙና የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን ዳግም ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ ሊደገም እንደሚገባ አፅንዖት ተሰጥቷል።

አሁን የተገኘውን ሰላምና ልማት በማክበር ወደ ተሻለ ለውጥ ለማምጣት ተጋግዘው አንድነታቸውን አጠናክረው መስራት እንደሚገባቸው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ደብረፅዮን (ዶ/ር) ገልፀዋል። በበዓሉ ላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግስት ኮሚቴ ሰብሳቢ ጀነራል ታደሰ ወረደን ጨምሮ የክልሉ አመራሮች ተገኝተዋል።

አስተያየት