መጋቢት 27 ፣ 2014

ፍቅርን ፍለጋ ከኢንተርኔት መንደር

የአኗኗር ዘይቤማህበራዊ ጉዳዮች

ምንም እንኳን በፍቅር አጋር አፋላጊ መተግበሪያዎች ጥቂት የማይባሉ ግንኙነቶች ባይሰምሩም አያሌ ትውውቆች ደግሞ ቁምነገር ላይ ደርሰዋል

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

ፍቅርን ፍለጋ ከኢንተርኔት መንደር

የፍቅር/ የትዳር አጋር መፈለጊያ የኢንተርኔት ድረ-ገፆች ወይም መተግበሪያዎችን (Dating apps/ sites) መጠቀም በሌላው ዓለም እጅግ የተለመደ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ግን በብዛት ሲጠቀሙበት አይስተዋልም ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እየተለመደ የመጣ ይመስላል። ለዚህም አንዱ ማሳያ ለኢትዮጵያውያን ታልመው የተዘጋጁ መተግበርያዎች ብቅ ብቅ ማለት መጀመራቸው ነው።

ሁነኛ የፍቅር አጋር አግኝቶ ትዳር መመስረት የብዙዎች ግብ መሆኑ ይታወቃል። ትዳር ከፍተኛ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ትርጉም በሚሰጠበት በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ደግሞ መሟላት ያለባቸው አያሌ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ፍላጎቱ እንዳለ ሆኖ ከዘመን ጋር እየተለወጠ የሚሄደው የአኗኗር ዘይቤያችን ብዙ የህይወት መልኮችን እንደቀየረው ሁሉ ትዳር ምስረታ ላይም የራሱን ተፅዕኖ አሳርፏል።

ታዲያ በነዚህ እና መሰል ምክንያቶች በተለይ ግለኝነት በሚበዛበት የውጭ ሀገር የስደት ኑሮ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለመደው ማህበራዊ ሂደት ውሃ አቅጣጫቸውን ለማግኘት ይበልጥ እንደሚቸገሩ ይናገራሉ።

ድንቅነሽ ንዳ የተባለች በአሜሪካ የሲልቨር ስፕሪንግ ነዋሪ ወጣት ከዚህ ጋር በተያያዘ ያላትን ገጠመኝ ስትናገር፣ “አሜሪካን ሀገር የፍቅር ግንኙነትን መመስረት ትንሽ ከበድ የሚል ይመስለኛል፤ ለምሳሌ ያህል የስራ ሁኔታዎች መጣበብ እና የፕሮግራሞች አለመገናኘትን እንደ ምክንያት መጥቀስ ይቻላል፣ አንድ ሰው አንድ ስራ ብቻ ላይሆን ይችላል የሚሰራው ያ ሲደማመር ከባድ ያደርገዋል” ስትል ያሉትን ማህበራዊ ተግዳሮቶች ትገልፃለች።

የፍቅር አጋር አፋላጊ የኢንተርኔት ድረ-ገፆችና መተግበሪያዎች በሌላው ዓለም በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉ ተመራጭ ቴክኖሎጂዎች ናቸው። ዘመናዊ የስራ ሁኔታዎች እና አኗኗር ዘይቤዎች ለማህበራዊ ህይወት በቂ ጊዜ እንዳይኖር ባደረጉበት በዚህ ዘመን ደግሞ ይህንን አገልግሎት የሚፈልጉ ተጠቃሚዎች ቁጥር እንዲያሻቅብ አድርጓል። አገልግሎቱን የሚያቀርቡ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችም የተለያዩ አማራጮችን በመጨመር የተጠቃሚውን ትኩረት ለማግኘት ርብርብ እያደረጉ ነው። 

ለኢትዮጵያውያን ተብሎ ከተቋቋሙ መሰል የፍቅር አጋር አፋላጊ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች መካከል ቁምነገር በመባል የሚታወቀው መተግበርያ አንዱ ነው። ከመስራቾቹ አንዷ የሆነችው ብርሃን ታደሰ ስለመተግበርያው ስትናገር፣ “ቁምነገር በተከፈተ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከስድስት ሺህ በላይ ተጠቃሚዎች ተመዝግበውበታል፣ በዚህም ምቹ ሁኔታ ያለመፈጠሩ ጉዳይ ነው እንጂ ብዙ የዚህ አገልግሎት ፈላጊዎች መኖራቸውን ለማወቅ ችለናል” ትላለች።

ብርሃን ከባልደረቦቿ ጋር ይህን መተግበርያ ለማቅረብ ሲወስኑ የዳሰሳ ጥናት ማካሄዳቸውንና ስለገጠማቸው ችግር ስትገልፅ ማህበረሰቡ እንደዚህ አይነት አፕሊኬሽን ላይ መታየቱን እንደማይፈልገውና ይህም የማህበረሰቡ አኗኗር ዘይቤ ያመጣው ተፅዕኖ ይመስለኛል ትላለች። ሆኖም ያሉት ተግዳሮቶች ሳይገድባቸው 'ቁምነገር' የፍቅር አጋር አፋላጊ መተግበሪያን በስራ ላይ ማዋል ችለዋል።  

መጀመርያ በውጭ አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መመዝገባቸውን እና እየዋለ እያደርም በሀገር ውስጥ ያሉ ተጠቃሚዎችም እየለመዱት እንደመጡ መስራቿ ትናገራለች።

ሁሉም የቁም ነገር ተመዝጋቢ በየዕለቱ በመተግበሪያው ላይ ከሚያሳየው ፍላጎት በመነሳት ሶስት ከፍላጎቱ ጋር ይስማማሉ ተብለው የሚታሰቡ አቻዎች ተመርጠው ይቀርቡለታል። ትውውቅ መጀመሩ እና አለመጀመሩ በተጠቃሚዎች ነፃ ፍቃድ ላይ የሚወሰን ሲሆን አቻ የማጣመሩ ስራ በኮምፒውተር የፕሮግራም ቀመር (artificial algorithm) የታገዘ ነው። ፕሮግራሙም የተጠቃሚዎችን ፍላጎት በመረዳት ተመሳሳይ ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ጋር የሚያጣምር ምርጫዎችን ያቀርባል።

በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖሩና የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችን የሚያገለግሉት እነዚህ የተለያዩ መተግበርያዎች በአይነትም እየበዙ ከመሄዳቸው አኳያ ዘርፉ በፍጥነት እያደገ መሄዱን ያሳያሉ። እነዚህ መተግበሪያዎች አንዳንዶቹ በክፍያ የሚሰሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ነፃ ናቸው።

ለምሳሌ ቁም ነገር መተግበሪያ ላይ ከመመዝገብ ጀምሮ ተጣማሪ አቻን እስከመፈለግ ድረስ ያለው ሂደት ነፃ ሲሆን መተዋወቅ የፈለጉ ጥንዶች መልዕክት መለዋወጥ ሲጀምሩ ግን እንዲከፍሉ ይደረጋል።

ሌላኛው የመተግበርያ ምሳሌያችን ደግሞ ሎሚ የፍቅረኞች መገናኛ ሲሆን፣ የመተግበርያው ስራ አስኪያጅ ሜሮን ስለሺ ሎሚ ሀሳቡ የተጠነሰሰው ከአራት አመት በፊት እንደሆነና ከሁለት አመት በፊት ተግባራዊ መደረጉን ነግራናለች። 

“በአፕሊኬሽኑ ከ18 እስከ 65 ዓመት የሆናቸው ኢትዮጵያውያን የፍቅር ጓደኛ ፈላጊዎች መሰረታዊ የግል መረጃቸውንና ፎቶግራፋቸውን ካስገቡ በኋላ ለሚፈልጓቸው ሰዎች ሎሚ በመወርወር መተዋወቅ ይችላሉ” በማለት ሜሮን መሰረታዊ አሰራሩን ታስረዳለች።

በአሁን ሰዓት ይህን መሰል አገልግሎቶችን የሚጠቀሙ ተገልጋዮች ቁጥር በአፍሪካ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ መሄዱን ጥናቶች ያሳያሉ። ለዚህም የወጣቶች በቴክኖሎጂ አጠቃቀም መዳበር፣ የዘመናዊ ስልኮች መስፋፋት እና የኢንተርኔት አገልግሎት ምቹ እየሆነ መሄዳቸው እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እና በቁምነገር አማካኝነት ግንኙነት መጀመራቸውን የሚናገሩት ጥንዶች፣ “ሁለታችንም በየግላችን ይህን አፕሊኬሽን ለመጠቀም ስናስብ ላይሳካ ይችላል የሚለው ግምታችን ከፍተኛውን ቦታ ይወስድ ነበር። ነገር ግን ከሚገመተው በላይ ሚስጥራዊነቱ የተጠበቀ፣ ምርጫን ያከበረ እና የፍላጎትን ግብ የሚመታ አጣማሪ ሆኖ አግኝተነው ለዚህ በቅተናል” ይላሉ።

በዓለም ላይ በዚህ ዘርፍ እያገለገሉ ከሚገኙ አለም አቀፍ አገልግሎቶች መካከል Tinder እና Bumble የተሰኙት ግንባር ቀደም ሲሆኑ፣ ሁለቱም በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች እንዳሏቸው ይነገራል። የተጠቃሚዎች የፆታ ስብጥርም ሲታይ በአንፃራዊነት ሚዛናዊ ነው ይባላል።

በምብል የሚሰኘው መተግበርያ ከቲንደር የሚለየው ለሴቶች ምርጫ ቅድሚያ በመስጠቱ ሲሆን፣ በመተግበርያው ደንብ ሴቶች ብቻ ናቸው ቀድመው መውደዳቸውን መግለፅ የሚችሉት።

ኑሮውን በአሜሪካ ሜሪላንድ ያደረገ ናሁሰናይ አሰፋ የተባለ ወጣት በበኩሉ 'ጀበና' ተብሎ የተሰየመውን እና ትኩረቱን በዳያስፖራ ሀበሾች ላይ ያደረገውን መተግበርያ እንደሚጠቀም ሲነግረን፣ "እዚህ ሀገር ከሀገራችን ሴቶች ጋር ለመተዋወቅ ወይ የሆነ የጋራ ፕሮግራም ላይ መገኘት ግዴታ ነው፣ አለበለዚያ ህይወት እዚህ ሩጫ ብቻ ነው፤ በየት በኩል እንገናኛለን?” ይላል። ታዲያ ናሁሰናይ በዚህ መተግበርያ በመጠቀም ሲትራ ከተባለች ወጣት ጋር ፍቅር ጀምሮ መተጫጨታቸውን አጫውቶናል።

ታዲያ በነዚህ መተግበሪያዎች ተዋውቆ ከመጣመር ባለፈ እጅግ ለየት ያሉ ገጠመኞች መኖራቸውንም ሰምተናል። ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ስሙ የተቀየረ ሳምሶን የተባለ ወጣት አለምአቀፍ የሆነውን 'ሚንግል' የተሰኘ አጣማሪ መተግበርያ በመጠቀም የፍቅር ግንኙነት ከመመስረት ጀምሮ ብዙ ለየት ያሉ ሰዎች እና ባህሪዎች ሊያጋጥሙት እንደቻሉ አጫውቶናል።

“የመጀመርያው ትውውቄ በኢትዮጵያ በአንድ አለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ ከምትሰራ ኡጋንዳዊት ወጣት ጋር ነበር፣ ግንኙነት ከጀመርን በኃላ ለስድስት ወር ገደማ የዘለቅን ቢሆንም መጀመርያ ላይ ግን ትክክለኛ የፍቅር ግንኙነት የምፈልግ ሰው መሆኔን ለማመን ስትቸገር እንደነበር አስተውያለሁ” በማለት ኢትዮጵያውያን ወንዶች ሊታመኑ የማይችሉ ሰዎች እንደሆኑ ተደርጎ በአዕምሮዋ እንዲሳል መደረጉንና እሷን መሰል ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ የሌላ ሀገራት ዜጋ ሴቶች ኢትዮጵያዊ ወንዶችን ለመቅረብ እንደሚቸገሩ ነግሮናል።

“ነገር ግን በመቀራረብ እና በመነጋገራችን ውስጥ የሰማችው አሉባልታ ውሃ የማያነሳ መሆኑን ተረድታ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ መግባት ችለናል፣ ሆኖም በመሃል ወደ ሀገሯ በምትሄድበት እና በምትመጣበት ወቅት በሚፈጠሩ የርቀት ክፍተቶች ሳቢያ ግንኙነቱ ከስድስት ወር ማለፍ አልቻለም” ይላል።

ሳምሶን በመተግበርያው አማካኝነት በድጋሚ የፍቅር ግንኙነት ከአንዲት ኢትዮጵያዊ ጋር ቢጀምርም ወጣቷ ትዳር እና የተለያዩ ሃላፊነት የተሞላባቸው ህይወቶችን ግብ በማድረጓ እና እሱ ግን ለዚያ ዝግጁ ስላልነበረ ግንኙነቱን በጊዜ ማቆሙን ነግሮናል።

ስለመተግበሪያው ክፉ ጎኖችም ሳምሶን ያወጋን ሲሆን፣ “አንዳንድ ሰዎች ትክክለኛ ማንነታቸውን በመደበቅ እና የውሸት ማንነት በመላበስ ተቃራኒ ፆታዎችን በማውራት እና በማሳመን ገንዘብ ከማስላክ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች ያጭበረብራሉ” ሲል ያስረዳል።

በሌላ በኩልም በእነዚህ መተግበሪያዎች አማካኝነት አፈንጋጭ የወሲብ ግንኙነትን ለማግኘት አላማ አድርገው አካውንት የከፈቱ ሰዎች እንዳሉ ከተጠቃሚዎች ልምድ መረዳት የቻልን ሲሆን፣ ግብረሰዶማውያንም በተለያዩ ዘዴዎች ተመሳሳይ ፃታዎችን ለማጥመድ እንደሚጠቀሙት፣ ይህም ወንዶች የሴት አካውንት በመክፈት ወንዶችን እንደሚያጠምዱ እንዲሁም ሴቶች የወንድ አካውንት በመክፈት ሴቶችን እንደሚያጠምዱ እና ወሬው መጠንከር ሲጀምር የተመሳሳይ ፆታ ፍላጎት ሃሳባቸውን ለማሳካት ጥረት አንደሚያደርጉ አንዳንድ ተጠቃሚዎች ከገጠመኞቻቸው አካፍለውናል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የጋብቻ እና የቤተሰብ ስነ-ልቦና አማካሪ የሆኑት ኮኬት ቶላ በጉዳዩ ላይ ያላችውን ሙያዊ ምልከታ አካፍለውናል።

“በአሁን ሰዓት የአብዛኞቻችን የኑሮ ሁኔታ ከስራ ወደ ቤት ያለ ሩጫ ላይ የተመረኮዘ እንደመሆኑ እና ከወዳጆቻችን ጋር እንኳን ለመገናኘት የምንወጣው አልፎ አልፎ ከመሆኑ አኳያ የፍቅር ጓደኝነትን ለመመስረት ኢንተርኔትን መጠቀም አማራጭ መሆኑ አይገርምም። ይሄንን የኢንተርኔት ትውውቅ ታዲያ መጥፎም ነው ጥሩም ነው ብሎ ለመፈረጅ አስቸጋሪ ይሆናል፣ ምክንያቱም መልካም ጎንም አለው መጥፎ ጎንም አለው" የሚሉት የስነልቦና አማካሪዋ መልካም ጎኖቹን ሲጠቅሱ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆኑን እና ተጠቃሚው የፍቅር ምርጫውን በአካል ለማግኘት በቂ ነው ብሎ እስካላመነ ድረስ የትውውቅ ጊዜው በኢንተርኔት ስለሚሆን ከአልተፈለገ አለመግባባት እና ችኩል ውሳኔ ቆም ብሎ ለማሰብ እንደሚረዳ እና በተጣበበው የእለት ተእለት ሁናቴ ውስጥ ተሁኖም ውሃ አጣጭ ለማግኘት ይረዳል ብለዋል።

በሌላ በኩል ስለመጥፎ ጎኑ ሲያነሱ “ጥንቃቄ የተሞላበት ካልሆነ ብዙ አይነት ውሸታሞች እና አጭበርባሪዎች የታጨቁበት አማራጭ መሆኑም መዘንጋት የለበትም፣ ታዲያ በዚህ ምክንያት የተዋሸው እና የተጭበረበረው ሰው የገንዘብ፣ የሞራል፣ እና የስነልቦና ስብራት ሊደርስበት ይችላል” ይላሉ። 

አያይዘውም አንዳንዶች ደግሞ የድብርት መደበቂያ ሲያደርጉት እንደሚስተዋል ገልፀዋል። ይህንንም ሲያብራሩ “አንዳንዶች በህይወታቸው የሚፈልጉትን የፍቅር ግንኙነት ሲያጡ፣ ሲከዱ፣ ፍላጎታቸውን የሚያሟላ ሰው ካላገኙ እና በብዙ ተመሳሳይ ምክንያቶች ሳቢያ ድብርት ውስጥ ይገቡና ያንን ሽሽት ብቻ በእነዚህ ፕላትፎርሞች ተደብቀው ያልፋሉ፣ ይህም መድሃኒት የሆናቸው ይመስላቸዋል እንጂ እጅግ ጎጂ ነው” ይላሉ።

ፍቅርን በደብዳቤ ከመግለፅና ከመተዋወቅ ጀምሮ ጊዜ ጊዜን ሲተካ ከደብዳቤ ጎን ለጎን የመስመር ስልኮች መጥተው አፍቃሪዎች የተፈቃሪውን/ዋን ስልክ ቁጥር ለማግኘት ከሚደረግ ልፋት ጀምሮ በቀጭኑ ሽቦ ፍቅርን መለዋወጥ እስከመቻል ተደርሷል። 

እንዲህ እንዲህ እያለ ዛሬ ደግሞ በኢንተርኔት መረብ አቻዎችን እየመረጡ ማጥመድ ተጀምሯል። ታዲያ ምንም እንኳን በዚህ መንገድ ጥቂት የማይባሉ ግንኙነቶች ባይሰምሩም አያሌ ትውውቆች ደግሞ ቁምነገር ላይ ደርሰዋል።

አስተያየት