ጳጉሜ 4 ፣ 2014

የበአል ባዛር ገበያዎች እውነት የዋጋ ቅናሽ አላቸው?

የአኗኗር ዘይቤኢኮኖሚወቅታዊ ጉዳዮች

በዓላትን ተከትሎ በትልልቅ ከተሞች ኤግዝቢሽንና ባዛሮች የተለመዱ ሲሆን በአነስተኛ ከተሞች ደግሞ ተጓዥ ባዛሮች በስፋት ይታወቃሉ

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

አዲስ ዘይቤ የዲጂታል ዜና ሚዲያ ነው።

የበአል ባዛር ገበያዎች እውነት የዋጋ ቅናሽ አላቸው?
Camera Icon

ፎቶ ክሬዲት ካላዩ ሃጎስ

ኢትዮጵያውያን አሮጌዉን አመት ለመሸኘት እና አዲሱን ለመቀበል ከቤተሰቦቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው እና ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመሰባሰብ በተለይ የአዲስ አመቱን የመጀመርያ ቀን (እንቁጣጣሽን) በደመቀ ሁኔታ ለማሳለፍ እንደየ አቅማቸው ሽር ጉድ ይላሉ።   

ይህንም ለማድረግ ወደተለያዩ የገበያ ማዕከላት በማቅናት ለበዓሉ የሚያስፈልጓቸው የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦች ይሸምታሉ። በየዓመቱ ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር ለመግዛት ከሚያዘወትሯቸው የገበያ ማዕከላትና ዝግጅቶች ከቅርብ አመታት ወዲህ ተመራጭ የሆኑት ባዛሮች ይገኙበታል።    

አዲስ ዘይቤም አዲስ አመትን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ከተሞች ወደተዘጋጁት የባዛር ገበያዎች በማቅናት ቅኝት አድርጋለች።

አዲስ አበባ የሚገኘው የኤግዚቢሽን ማዕከል ባዛር የመግቢያ ትኬት 50 ብር ሲሆን፣ ሰዎች በሁለት ቦታ ጥብቅ ፍተሻ ከተደረገላቸው በኋላ ወደ ማዕከሉ በመግባት የሚፈልጉትን ነገር ማየትና መግዛት ይጀምራሉ። 

አቶ ሌሊሳ ጥበቡ የኤግዚቢሽን ማዕከል አስተባባሪ ሲሆኑ ባዛሩ ከተጀመረ ማለትም ከነሃሴ 14 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በአማካኝ በቀን ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ ሸማቾች ወደ ኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚገቡ በመግለጽ እንደየእቃው አይነት ቢለያይም ውጪ ከሚሸጥበት ቅናሽ እንዳለው አስረድተውናል።

በተለይ በፋብሪካ እቃዎችና ልብስ ላይ በጣም የዋጋ ቅናሽ እንዳለ የሚናገሩት አቶ ሌሊሳ “በትላንትናው ቀን ማለትም ጳጉሜ 3 ቀን 2014 ዓ.ም ብቻ ኤግዚቢሽኑን የጎበኙ ሰዎች ቁጥር ባልተለመደ ሁኔታ ወደ 18 ሺህ ከፍ ብሎ ነበር” ብለውናል።   

ከባዛሩ የገበያ እንቅስቃሴ ሰዉ የአዲስ አመት በአልን ለማክበር ምን ያህል ጉጉትና ተስፋ እንዳለው በሰዉ ብዛት እና በገበያው መጨናነቅ ለመረዳት አዳጋች አይደለም። 

በዚህ የባዛር ገበያ ሃረር እና ዋልያ ቢራን ጨምሮ የተለያዩ መጠጦች፣ የተለያዩ ብራንድ እቃዎች፣ የህፃናት መጫዎቻዎች፣ ለበዓሉ የሚሆኑ የባህል አልባሳት፣ ቅመማ ቅመሞች፣ ስጋ እንዲሁም ሌሎች ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ የሸቀጣሸቀጦች አቅርቦት በተለያዩ ዳሶችና አዳራሾች አካተው ይዘዋል። በአጭሩ በኤግዚቢሽን ማዕከል የባዛር ገበያ ላይ የማይገኝ የእቃ ዓይነት የለም። 

በዚሁ ገበያ ያሉት ሻጮችና ሸማቾች ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የተለያዩ ነጋዴዎችም ጭምር ይገኙበታል። ለምሳሌ ከዓረብ ሀገራት መጥተው በጨርቅ ንግድ የተሰማሩ ያሉ ሲሆን፣ ከህንድ እንዲሁም ከሌሎች ሀገራት የመጡ ነጋዴዎች የተለያዩ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ እቃዎችን በመሸጥ ላይ ተሰማርተዋል። 

አንዳንድ ሰዎች የእቃዎች ዋጋ በባዛር ገበያ እንደሚቀንስ ሲናገሩ፣ ሌሎቹም ደግሞ ውጭ ከሚሸጠው ምንም ዓይነት የዋጋ ልዩነት እንደሌለው ሲናገሩ ይደመጣሉ። 

ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉ አንድ ሸማች (ስማቸውን መናገር ያልፈለጉ) “እቃዎቹ ላይ ይህ የሚባል የዋጋ ቅናሽ የለም፤ ሆኖም አንዳንድ እቃዎች ስትገዛ ቦነስ ታገኛለህ፣ ጥቅሙ እሱ ነው” በማለት የባዛር እቃዎች እንደሚወራው የዋጋ ቅናሽ እንደሌላቸው ያስረዳሉ። 

ሆኖም አንዳንድ እቃዎች ላይ ለምሳሌ የልብስ ዋጋ እስከ 20% ቅናሽ አድርገው የሚሸጡ ያሉ ሲሆን ምንም የዋጋ ቅናሽ የሌላቸው እቃዎችም እንዳሉ አዲስ ዘይቤ ታዝባለች።

የዋጋ ቅናሽ ባይኖርም የተለያዩ እቃዎችን ከባዛር ገበያ ለመሸመት ወደ ኤግዚቢሽን ማዕከል የሚመጣ የሰው ቁጥር ግን ቀላል የሚባል አይደለም። 

ሐዋሳ

በሐዋሳ ከተማ የአዲስ አመት ንግድና ባዛር ኤግዚቢሽን የተከፈተው ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በ መስቀል አደባባይ ነው። የአዲስ ዓመት ዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተከፈተዉ ባዛር የተዘጋጀው ለተጠቃሚው የተለያዩ ቁሶችን በቅናሽ ማቅረብ በሚል ነዉ። 

የአዲስ ዘይቤ የሐዋሳ ሪፖርተር በንግድና ባዛር ኤግዚቢሽኑ ተገኝቶ ቅኝት ያደረገ ሲሆን ነጋዴዎችን እና ገዢዎችንም አነጋግሯል። ያነጋገርናቸው ሸማቾች ባዛሩ መኖሩ እቃዎችን በአንድ ቦታ ለማግኘት እንደሚያስችል ሁሉም ይስማሙበታል። 

ነገር ግን አንዳንድ ሸማቾች እንደሚሉት በባዛሩ ላይ የእቃዎች ዋጋ ቅናሽ ብዙም አይስተዋልም። እየተዘዋወሩ የባህል አልባሳትን እየተመለከቱ ከሚገኙት ገዢዎች መካከል ብሌን እና አዜብ የተባሉ ወጣቶች እንደሚሉት የአልባሳቶቹ ዋጋ ተመጣጣኝ አይደለም። “በመደበኛ ሱቅ 1000 ብር የሚገዛው የባህል ቀሚስ በባዛሩ ላይ 1200 በመሸጥ ላይ ነዉ” ብለዋል።     

ሌላኛዋ ሸማች ደግሞ ከቤቷ ይበቃኛል በሚል ይዛ የወጣችው የገንዘብ መጠን እሷ ከምትፈልገዉ እቃ ጋር ባለመገናኘቱ የምትፈልገውን ያህል ሳትገበይ መመለሷን ተናግራለች። 

በባዛሩ ላይ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ የልጅና የአዋቂ አልባሳት፣ የቤት ዉስጥ እቃዎች እና በአጠቃላይ ከቁም እንስሳት ዉጪ ሁሉም በአንድ ላይ ይገኛሉ። 

ካለፈዉ የፋሲካ በዓል አንፃር የዘንድሮዉ ከዋጋ አንፃር መወደዱን በማንሳት ነገር ግን የአቅርቦት ችግር እንደሌለ የሚናገረው ደግሞ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን እየሸጠ ያገኘነው በረከት ነዉ። 

ይህን አስመልክቶ የባዛሩን አዘጋጆችን ለማግኘት ያደረግነዉ ጥረት ባይሳካም የሐዋሳ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ከሆኑት ወ/ሪት በላይነሽ ገዳ ጋር ቆይታ አድርገናል። 

ኃላፊዋ እንደሚሉት የባዛሩ መከፈት ዋናዉ አላማ ለህብረተሰቡ ከመደበኛ ዋጋ አንፃር በቅናሽ ማቅረብ ነዉ። በባዛሩ ላይ በማህበር እና በግል እቃዎችን እያቀረቡ የሚገኙ ነጋዴዎች መኖራቸዉን የጠቆሙት ኃላፊዋ "ከዉጪ ገበያ 1000 ብር የሚሸጡ እቃዎች በባዛሩ ላይ ግን እስከ 900 ብር እየተሸጡ እንደሚገኙ አረጋግጠናል” ብለዋል።  

በሐዋሳው ባዛር በመደበኛ የአልባሳት እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ አቃዎች መሸጫ ሱቆች እና በባዛሩ ላይ የሚገኙትን አቅርቦቶች በተመለከተ በአብላጫው በባዛሩ ላይ የሚገኙ እቃዎች የ100 እና 200 ብር ጭማሪ እንዳላቸዉ ታዝበናል። በሁሉም እቃዎች ላይ ለማለት በሚያስችል መልኩ ካለፈዉ በዓል አንፃር ዋጋቸዉ መጨመሩንም ተመልክተናል። 

ባህር ዳር

ዘንድሮ በባህር ዳር ከተማ የተዘጋጀው እንቁጣጣሽ የንግድ ትርኢት እና ባዛር ሳምንት አስቆጥሯል። የዘንድሮውን እንቁጣጣሽ ባዛር የአማራ ክልል የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አዘጋጅቶታል።

የክልሉ የዘርፍ ማህበራት ስራ አስኪያጅ አቶ ገብሬ ደርበው እንዳሉት ባዛሩ 130 አምራቾች እና አገልግሎት ሰጪዎች እና ሁለት የውጭ ሀገር አምራቾች ተሳትፈውበታል። እንደ ስራ አስኪያጁ ማብራሪያ የውጭ ሀገር ተሳታፊዎች ቁጥር ከዓምናው ጋር ሲነፃፀር ቁጥሩ ቀንሷል። ባዛሩ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም የጀመረ ሲሆን እስከ ጳጉሜ 5/2014 ዓ.ም ድረስ ይዘልቃል። እንደ አማራ ክልል የዘርፍና ንግድ ማህበራት መረጃ የዘንድሮውን ባዛር በቀን በአማካኝ ሶስት ሺህ ሰዎች እየጎበኙት ይገኛል። ይህ ቁጥር ከአለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ቁጥሩ መቀነሱን ያሳያል። 

ከሸማቾች መካከል ወ/ሮ ደስታ የቆየ ከልጃቸው ጋር በባዛሩ አግኝተናቸዋል። ወ/ሮ ደስታ እንደሚሉት ባዛሮች ምንም እንኳን ከበዓላት ጋር ተያያዞ ቢዘጋጁም ለበዓል የሚያስፈልጉ ነገሮች አይገኙባቸውም። “ከዚያ ባለፈ ባዛሩ ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ዕቃዎች ዋጋ ገበያ ውስጥ ካለው ጋር ብዙም ልዩነት የለውም” ብለውናል። 

ሰብለ ጌታሁን ሌላዋ ባዛሩን ስትጎበኝ ያገኘናት ሸማች ነች። “በባዛሩ በአብዛኛው የመዋቢያ ዕቃዎች አግኝቻለሁ፤ ዋጋቸውም ገበያ ውስጥ ካለው የተሻለ ሆኖ ነው ያገኘሁት” በማለት ባዛሩን መጎብኘቷ እንደጠቀማት አጫውታናለች። 

በባዛሩ የተዘጋጁ የወንዶች ልብሶች ስትሸጥ ያገኛናት ወ/ሮ ትግስት ይርጋ በተከታታይ ለአራት ዓመታት በተዘጋጁ ባዛሮች ተሳትፋለች። “የዘንድሮው ባዛር ቀዝቃዛ ነው፤ ብዙም ሸማቾች የሉበትም። ለዚህም በሀገራችን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እና የሸቀጦች ዋጋ መናር ይመስለኛል” በማለት የግል አስተያቷን ሰጥታናለች።

ከዚህ ቀደም በባህር ዳር ከተማ ይካሄዱ የነበሩ የንግድ ትርዒትና ባዛሮች የምግብ እና መጠጥ አገልግሎቶች ያሉባቸው ከመሆናቸው በተጨማሪ የተለያዩ የሙዚቃ ድግሶች ያስተናግዱ ስለነበር ደማቅ እንደነበሩ ብዙዎቹ ያስታውሷቸዋል። 

የዘንድሮው ባዛር ላይ የሙዚቃ ድግስ እንዲሁም የምግብ እና መጠጥ አገልግሎት ስሌለው ከዚህ ቀደም ከነበሩት ቀዝቀዝ ያለ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል።

አዳማ

ባዛር ሲባል የበዓል መቃረብን አልያም የተለያዩ አዳዲስ ምርቶችን የማስተዋወቅ ክንውን ኃሳብን በብዙዎች አዕምሮ ያመጣል። በትልልቅ ከተሞች በዓላትን ተከትሎ የሚዘጋጁ ኤግዝቢሽን እና ባዛሮች ተለምደዋል። በአነስተኛ ከተሞች ደግሞ በባዛር አዘጋጆች የሚዘጋጁ ተጓዥ ባዛሮች በስፋት ይታወቃሉ።

በአዳማም በተደጋጋሚ ባዛሮች ይከናወናሉ። በከተማዋ በሚገኘው መስቀል አደባባይ ከሚዘጋጀው ትልቅ ባዛር በተጨማሪ በፖስታ ቤት፣ መብራት ኃይል እና ፍራንኮ አካባቢ ያሉት የመንገድ ላይ አነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ባዛሮች በስፋት ይታወቃሉ።

በአሁኑ ወቅት የ2015 ዓ/ም ዘመን መለወጫ በዓልን ተከትሎ በአዳማ የመስቀል አደባባይ በዓልን ጨምሮ በፖስታ ቤት እና በመብራት ኃይል አካባቢ ባዛሮች ተዘርግተዋል።

በባዛሩ አካባቢ ያገኘናት ወ/ሮ መድሃኒት ጌታቸው የበዓል ወቅት ባዛሩን የመጎብኘት ኃሳብ እንዳላት ላቀረብንላት ጥያቄ “ባዛር ከገባሁ ረጅም ጊዜ ሆኖኛል፤ ምክንያቱም ምንም አዲስ ነገር የለውም፤ ዋጋውም ቅናሽ አይታይበትም” ስትል አስተያየቷን ሰጥታናለች። 

በሞያው አርክቴክት የሆነው አቶ ግርማ ሞገስ ደግሞ በመድሃኒት ሀሳብ አይስማማም። ባዛሩ መዘጋጀቱ ጥሩ እድል እንደፈጠረለትና የተሻለ ዋጋ እንዳገኘም ይናገራል። 

“አንዳንድ አነስተኛ እቃ የሚሸጡ ነጋዴዎች የባዛሩን ወጪያቸውን ለመሸፈን ዋጋ ይጨምራሉ” የሚለው ግርማ ሆኖም ብዙ ከገበያ የተሻሉ ዋጋዎች እንዳገኘም ነግሮናል። 

የጁስ መፍጫ ሲገዛ ያገኘነው አቶ ግርማ “እቃው እጅግ ከፍተኛ ቅናሽ አለው፤ አዳማ ላይ ሱቆች ውስጥ ላገኘው አልቻልኩም ነበር፤ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ መግዛት ችያለሁ” በማለት ይናገራል። 

ዳንኤል ተመስገን የተለያዩ የቤት እና የማዕድ ቤት እቃዎችን ይዞ አዳማ መስቀል አደባባይ የተዘጋጀው ኤግዚቢሽን እና ባዛር የተገኘ ነጋዴ ነው። በዳንኤል መሸጫ ቦታ የተለያዩ የምግብ ማብሰያ የኤሌክትሪክ ማሽኖችን እንዲሁም የልብስ ማጠቢያ እና ሌሎች የቤት ቁሳቁሶችን ተመልክተናል።

“ተሳታፊው ብዙ ነው የገዢው ቁጥር ግን ትንሽ ነው” የሚለው ዳንኤል ገበያው ከባለፈው የፋሲካ ባዛር አንጻር ቀዝቃዛ እንደሆነ ይናገራል።

ፖስታ ቤት በአዳማ እንደ አማካኝ የትራንስፖርት ማዕከል የሚወሰድ ቦታ ነው። እዚህ አካባቢ የሚዘጋጁ የጎዳና ሽያጮች የበዓል ድባቡን የሚያንጸባርቁ ገፅታዎች ናቸው።

መላኩ ወልዴ የቢሊሱማ የጫማ አምራቾች ማህበር አባል ነው። በማህበሩ ጫማን ጨምሮ የተለያዩ የቆዳ ውጤቶች ይመረታሉ። ሚግራ ተብሎ የሚጠራ አካባቢ የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ ሲኖራቸው አዳማ አመዴ ገበያ አካባቢ ደግሞ የመሸጫ ሱቅ አላቸው።

የባዛር ሽያጭ መዘጋጀቱ ትርፉ ለሻጭም ለሸማችም ነው የሚለው መላኩ “እያስተዋወቅን እየሸጥን ነው፤ እዚህ በመጣንባቸው ጊዜዎች ሽያጭ ላይ ተጨባጭ ለውጥ አይተንበታል” ይላል።

በባዛሮች ላይ የዋጋ ቅናሽ አይደረግም ወይ የሚለውን ጥያቄ ያነሳንለት መላኩ “ሱቅ ላይ በ1000 ብር የማይገኝ ጫማ እኛ ጋር 800 ብር ድረስ ይገኛል" ሲል የዋጋ ቅናሻቸውን ገልጾልናል።

ከባዛር እቃዎች ዋጋ ጋር በተያያዘ ያነጋገርነው የባዛሩ ተሳታፊ አቶ ኪያ አለማየሁ የተጓዥ ባዛር ነጋዴ ነው። በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ ተዘዋውሮ ሰርቷል።

አሁን አሁን ባዛሮች ላይ ስለሚነሳው ቅሬታ አስተያየቱን ሲሰጥ “የባዛር ነጋዴ ስቶክ ስለሌለው በየቀኑ ከመርካቶ ነው የሚያስመጣው፤ በወቅቱ ገበያ ነው የሚሰራው። የጭማሪው መንስዔ የሆነው ይኼ ነው” ይላል። 

ሰለዋጋ ልዩነቱ በተጨማሪ ሲያስረዳም “ሱቆች ለወራት የተቀመጠ ምርት ሊኖራቸው ይችላል፤ በዚህም ምክንያት የዋጋ ልዩነት ይኖራል” ብሎናል። በተጨማሪም የባዛር ቦታ ኪራይ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑንም ያስረዳል።

በአንጻራዊነት ነጋዴዎች ገዢን ለመሳብ የዋጋ ቅናሽ ቢያደርጉም የታሰበውን ያክል አለመስራታቸውን ይናገራሉ። በብዙ ነጋዴዎች እንደተነሳው እንዲሁም እኛም እንደታዘብነው በአዳማ የባዛር እንቅስቃሴው ከዚህ ቀደሙ ጋር ሲነጻጸር እጅግ የቀነሰ ፍላጎት የተስተዋለበት ነው።

በበዓል ወቅቶች በከተሞች የሚዘጋጁት የባዛር ገበያዎች ዋና አላማ በርካታና የተለያዩ እቃዎችንና ሸቀጦችን በቅናሽ ዋጋ በአንድ ስፍራ ለሸማቹ ማቅረብ እንደሆነ ይታሰባል። ነገር ግን በዘንድሮዎቹ ባዛሮች የዋጋ ቅናሽ አለ በሚለው ላይ ሁሉም ሸማቾች አይስማሙም። በተለያዩ ከተሞች ያሉትን ባዛሮች የሚጎበኙት ሰዎች ቁጥርም እንዳለፉት አመታት እንዳልሆነ ታዝበናል። ለዚህም የዋጋ ግሽበቱ የደረሰበት ደረጃ እና ሃገሪቷ ያለችበት የፀጥታ ሁኔታ እንደ ምክንያት ይነሳሉ።   

አስተያየት