ነሐሴ 3 ፣ 2014

ትውልደ ኢትዮጵያዊው የማሊያ ኦባማ አዲሱ ፍቅረኛ ዳዊት ኤክሉድ ማነው?

የአኗኗር ዘይቤወቅታዊ ጉዳዮች

እንደ ዴይሊ ሜይል ዘገባ የዳዊት አባት በአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለረዥም ጊዜ ያገለገለ ሲሆን እናቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነች

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

ትውልደ ኢትዮጵያዊው የማሊያ ኦባማ አዲሱ ፍቅረኛ ዳዊት ኤክሉድ ማነው?
Camera Icon

ፎቶ፡ ዴይሊ ሜይል (ጥንዶቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ የፍቅር ስሜታቸውን ሲገላለፁ የሚታይበት ፎቶግራፍ የተነሱት ሐምሌ 28 ቀን በሎስ አንጀለስ ከተማ ነበር)

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ልጅ ማሊያ ኦባማ አዲስ የፍቅር ጓደኛ መያዟ በተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ አውታሮች በስፋት የተናፈሰ ዜና ሆኗል። በአንድ ሳምንት ጊዜ ዉስጥ ብቻ ሶስት ጊዜ አብራው የታየችው ሚስጥራዊው ሰው የሙዚቃ ፕሮዲዩሰሩ ዳዊት ኤክሉድ ነው።

ዳዊት ኤክሉድ ማን ነው? ከየትስ ነው?

ይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ላይ የሰፈረው መረጃ ዳዊት የኢትዮጵያ መዲና ከሆነችው ከአዲስ አበባ እንደሆነ ያመለክታል። ሆኖም መጋቢት 1 ቀን 2008 ዓ.ም ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ በወጣው የዳዊት ፕሮፋይል መሰረት ከወላጆቹ ጋር በአሜሪካን ያደገ ቢሆንም በባንግላዴሽ፣ ግብፅ፣ ኬንያ፣ ሱዳንና ሌሎች ሀገራትም ኖሯል። እንደ ዴይሊ ሜይል ዘገባ አባቱ በአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለረዥም ጊዜ ያገለገለ ሲሆን እናቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነች።

ዳዊት ኤክሉድ በየትኛው ኮሌጅ ትምህርቱን ተከታተለ?

የፌስቡክ ፕሮፋይሉ እንደሚያሳየው ዳዊት በዋሽንግተን ዲሲ የግል ኮሌጅ ከሆነው አፍርካ ጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ አለማቀፍ ልማት አጥንቷል። ከዩኒቨርሲቲ ቆይታው በፊትም በአዲስ አበባ ኢንተርናሽናል ኮሚኒቲ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ተከታትሏል።

ዳዊት ኤክሉድ ሥራው ምንድነው?

ዳዊት ከዋሽንግተን ዲሲ ወጣ ብሎ የሚገኘው የግል የሙዚቃ ሪከርድ ኩባንያ የሆነው የ1432R ሪከርድ መስራችና ፕሮዲውሰር ነው። ዋሽንግተን ፖስት በፕሮፋይሉ እንደገለፀው ዋሽንግተን ከሚገኙ የዳንስ ሙዚቃ ፕሮዲውሰሮች ዳዊት ተጠቃሽ ባለሙያ መሆን የቻለ ሲሆን በጋዜጣው የሰፈረው አስተያየት “ይህም ሊሆን የቻለው የተለያዩ አለም አቀፍ ዘይቤዎችን በስራው በማካተቱ ብቻ ሳይሆን ከልጅነቱ ጀምሮ ከተለያዩ የአለም ሃገራት ዜጎች ጋር የመግባባት ክህሎትን ስላዳበረ ነው” በማለት ገልጾታል።

ዳዊት ኤክሉድ እና ማሊያ ኦባማ የፍቅር ጓደኘነት ከጀመሩ ምን ያህል ጊዜ ሆናቸው?

ጥንዶቹ በይፋ ፍቅረኛ የሆኑበት ጊዜ መቼ እንደሆነ በግልፅ ባይታወቅም ማሊያ ሰኔ 24 ቀን ከዳዊት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ፎቶ ተነስታለች። በቀጣይ ሐምሌ 26 ቀን ላይ ያዘዙትን ምሳ ይዘው አብረው ሲሄዱና ሲሳሳቁ ፎቶ ተነስተዋል። ጥንዶቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ የፍቅር ስሜታቸውን ሲገላለፁ የሚታይበት ፎቶግራፍ የተነሱት ሐምሌ 28 ቀን የሎስ አንጀለስ ከተማ የስነ ጥበብ ሙዝየምን በጎበኙበት ጊዜ ነበር። በዚህ ቀን እጆቻቸውን አጠላልፈው ከፍተኛ መቀራረብ የሚታይበት ሁኔታ ሲያሳዩ ነበር። 

ሚሼል ኦባማ ልጃቸው ማሊያ የወንድ ጓደኛ እንዳላት ይፋ አድርገዋል?

ሚሼል ኦባማ በቅርብ ኤለን ዴጌኔርስ ሾው ላይ በቀረቡበት ወቅት ሴት ልጆቻቸው ማሊያና ሳሻ ኦባማ የወንድ ጓደኞች እንዳሏቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ አድርገዋል። “በፊት በልጅነታቸው ታዋቂ ድምፃውያንን ይወዱ ነበር። አሁን ግን ይህ ፍላጎታቸው እውነታ ሆኖ ጎረምሶች ይዘው እየመጡ ነው” በማለት ቀልድ አዘል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

ማሊያ ኦባማ እና ዳዊት ኤክሉድ ሰፊ የዕድሜ ልዩነት አላቸው?

ፕሮዲዩሰሩ ዳዊት 33 ዓመቱ ሲሆን ማሊያ ኦባማ ግን ባለፈው ወር 24 ዓመት ሞልቷታል፤ ስለዚህም በማሊያ እና ዳዊት መካከል የዘጠኝ ዓመት የዕድሜ ልዩነት አለ ማለት ነው።

ማሊያ ኦባማ ከዚህ ቀደም ጠንካራ የፍቅር ግንኙነት ነበራት?

ማሊያ በሃርቫርድ ዪኒቨርሲቲ ትምህርቷን በምትከታተልበት ወቅት የኮሌጅ ፍቅረኛ ነበራት። ከዚህ ሮሪ ፋርኩሃሰን ከተባለው ፍቅረኛዋ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሳሳሙ ፎቶ የተነሱት በ2017 እ.ኤ.አ የሃርቫርድ እና ዬል ዩኒቨርሲቲዎች የእግር ኳስ ውድድር በተደረገበት ወቅት ነበር። ይህ እንግሊዛዊው የቀድሞው የማሊያ ፍቅረኛ በ ኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት በነበረው ሃገራዊ በቤት ውስት ተለይቶ መቀመጥ ውሳኔ ከኦባማ ቤተሰብ ጋር የተወሰነ ጊዜ እንዳሳለፈ ባራክ ኦባማ በታህሳስ 2013 ዓ.ም ሲመንስ ፖድካስት በተባለው ዝግጅት ላይ ተናግረዋል። 

አስተያየት