የካቲት 15 ፣ 2015

አፄ ምኒሊክ ለፕሬዝዳንት ሩዝቬልት የላኳቸው ታሪካዊ የሰጎን ስጦታዎች

ታሪክ

ሩዝቬልትና አፄ ምኒሊክ ስጦታ ለመለዋወጥ አዲስ አልነበሩም። ሩዝቬልት ቀደም ብለው ስለላኩላቸው የሁለት ሽጉጦች እና የፅህፈት መኪና ስጦታዎች ምስጋና ለማቅረብ አፄ ምኒሊክ እ.አ.አ በ1903 ለሩዝቬልት ደብዳቤ ፅፈው ነበር

Avatar: Abiy Solomon
አብይ ሰለሞን

አብይ የአዲስ ዘይቤ ዋና አዘጋጅ ሲሆን በጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ዘርፎች ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ጋዜጠኛ ነው። አብይ በዴይሊ ሞኒተር፣ ሪፖርተር፣ ፎርቹን፣ ቢቢሲ ሚድያ አክሽን በተለያዩ የኤዲቶርያል የስራ መደቦች አገልግሏል።

አፄ ምኒሊክ ለፕሬዝዳንት ሩዝቬልት የላኳቸው ታሪካዊ የሰጎን ስጦታዎች
Camera Icon

ፎቶ፡ የኢንተርኔት ምንጮች እና ስሚዝሶንያን ሙዝየም

ጊዜው እ.አ.አ ኖቬምበር 7፣ 1907 ነበር። አትላንቲክን የምትቀዝፈው ሚኒያፖሊስ መርከብ ኒውዮርክ ወደብ ላይ ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎላት ደርሳለች። ከያዘችው ጭነት ውስጥ ሁለት ጦጣዎች፣ አንድ የሜዳ አህያ፣ ሁለት የአንበሳ ደቦሎች (አንዷ በመንገድ ላይ ሞታለች) እና ሁለት መለሎ ሰጎኖችን ያካተተ ለፕሬዝዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት የተላኩ የእንሰሳት ስጦታዎች ይገኝበታል። እንሰሳቱ ከመርከብ በሚወርዱበት ጊዜም በተለይ ሁለቱ ሰጎኖች ልዩ እይታ ፈጥረው ነበር።

እነዚህ ከምስራቅ አፍሪካ ባህር አቋርጠው ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት የመጡት ስጦታዎች የተላኩት ከኢትዮጵያው ንጉስ አፄ ምኒሊክ ነበር። አፄ ምኒሊክ ስጦታዎቹን የላኳቸው ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት እ.አ.አ በ1904 ለሁለተኛ የስራ ዘመን በሚያደርጉት የምርጫ ወቅት ነበር።  

ስለእነዚህ ከ 119 አመት በፊት ከአንድ አፍሪካዊ ንጉስ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ስለተላኩት የእንሰሳት ስጦታዎች የአሜሪካው ስሚዝሶኒያን ሙዝየም የዘንድሮውን የፕሬዝዳንቶች ቀን በማስመልከት ልዩ ዳሰሳ አቅርቧል። 

ስጦታዎቹ በተላኩበት ቀን ማግስት የአሜሪካው ስመ ጥር ጋዜጣ ኒውዮርክ ታይምስ ያወጣው ዘገባ ርዕስ “የምኒሊክ ስጦታዎች ደርሰዋል” የሚል ነበር። ጋዜጣው በዘገባው “የአቢሲኒያው ንጉስ ሩዝቬልት ስጦታዎቹን ዛሬ እንዲያገኛቸው ፈልገዋል፤ ምክንያቱም ሩዝቬልት በዚህ ቀን ፕሬዝዳንት ሆኖ እንደሚመረጡ ንጉሱ ተስፋ ስላደረጉ ነው” በማለት ፅፏል። ፕሬዝዳንት ሩዝቬልትም በጊዜው በሰፊ ልዩነት የአሜሪካ ፕሬዝዳንትነትን መንበር መቆጣጠር ችለዋል። 

ሩዝቬልትና አፄ ምኒሊክ ስጦታ ለመለዋወጥ አዲስ አልነበሩም። ሩዝቬልት ቀደም ብለው ስለላኩላቸው የሁለት ሽጉጦች እና የፅህፈት መኪና ስጦታ ምስጋና ለማቅረብ አፄ ምኒሊክ እ.አ.አ በ1903 ለሩዝቬልት ደብዳቤ ፅፈው ነበር። ንጉሱ በደብዳቤው እንደገለፁት ለተላከላቸው ስጦታ ምስጋና ለማቅረብና በሩዝቬልት አገዛዝ ዘመን የደረጀውን የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት እንደሚያጠናክር በማመን እርሳቸውም በምላሹ ሁለት አናብስትና የዝሆን ቀንድ ስብስቦች እንደሚልኩ ቃል ገቡ። 

በዚህም መሰረት ከነዚህ ስጦታዎች መካከል የመጀመሪያው ዙር እ.አ.አ በማርች 1904 ቦስተን ከተማ ደረሰ። ከነዚህም ውስጥ የዝሆን ቀንዶቹ፣ “ጆ” የተባለ አንድ የአንበሳ ደቦል እንዲሁም “ቢል” የሚል ስም የተሰጠው ጅብ ይገኙበታል። እንሰሳቱ በሚጓጓዙበት ወቅት ታድያ ከመርከቡ ባልደረቦች ጋር በቀላሉ መላመድ አልቻሉም። በኒውዮርክ ታይምስ የፊት ገፅ ላይ እ.አ.አ ማርች 12 ቀን 1904 የወጣው ዜና እንደሚናገረው፣ የአንበሳ ደቦሉ ወደ እርሱ የቀረቡት የመርከቡ ሰራተኞች ላይ የጥርስ ንክሻ መሰንዘሩ አልቀረም። 

ከአፄ ምኒሊክ ለሩዝቬልት የተሰጡት ሁለቱ ሰጎኖች፣ የሜዳ እህያ እና አንበሳ እ.አ.አ ኖቬምበር 24 ቀን 1904 ወደ ብሔራዊ የእንሰሳት ጥበቃ ፓርክ ተላኩ። እንሰሳቶቹም በአሜሪካ ብሔራዊ ፓርክ በጥበቃ ከተቀመጡ ፕሬዝዳንታዊ የእንሰሳት ስጦታዎች ከመጀመሪዎቹ አንዱ መሆን ቻሉ። 

ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት ለመጨረሻ ጊዜ የተመለከታቸው ሰጎኖች ከአፄ ምኒሊክ የተሰጡት ሰጎኖች ብቻ አልነበሩም። ሁለተኛውን የፕሬዝዳንትነት የስራ ዘመኑን እንደጨረሰ እ.አ.አ በ1909 በስሚዝሶኒያን ሙዝየም አስተባባሪነት ከአያሌ ተመራማሪዎች ጋር በመሆን ወደ ምስራቅ አፍሪካ ጉዞ አድርጎ ነበር። የጉዞውም አላማ የአሜሪካ ብሔራዊ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዝየምን ለማደራጀት የተለያዩ የእንሰሳት ዘር ናሙናዎችን መሰብሰብ ነበር። በቀጣዮቹ ሁለት አመታትም ሩዝቬልትን ያካተተው ተጓዥ ልዑክ በሙዝየሙ የአስደናቂ ስብስቦች ክፍል ውስጥ መቀመጥ የቻሉ በሺህ የሚቆጠሩ የእንሰሳት ናሙናዎችን መሰብሰብ ቻለ። 

በአፄ ምኒሊክ ስጦታ መነሻነት ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት የሰጎኖችን ተፈጥሮ ለመርመር ፍላጎት ያደረበት ሲሆን፣ በአፍሪካ ያደረገው ጉዞ ደግሞ ፕሬዝዳንቱን በሰጎኖች ተፈጥሮ ላይ ከፍተኛ እውቀት ያለው ሰው እንዳደረገውና በርዕሰ ጉዳዩም ላይ በዋቢነት የሚጠቀስ የመረጃ ምንጭ መሆን እንደቻለ ስሚዝሶኒያን ሙዝየም ባቀረበው ዳሰሳ ይገልፃል።  

ለፕሬዝዳንት ሩዝቬልት ከአፄ ምኒሊክ ከተላኩት ሰጎኖች አንዱ በእንሰሳት ማቆያ ፓርኩ ሲገባ እድሜው ወደ 35 አመት ይጠጋ ነበር። አስገራሚ ሊባል በሚችል ሁኔታም ሰጎኑ በዋሽንግተን ለቀጣዮቹ 26 አመታት መኖር ችሏል። ከእድሜው አንጋፋነት የተነሳ ይህ ግዙፍ ወፍ ለተወሰኑ አመታት አይነ ስውር ሆኖ ቆይቶ በመጨረሻም እ.አ.አ በ1930 ህይወቱ አልፏል። አብሮት የመጣው ሌላኛው ሰጎን ከእርሱ ቀደም ብሎ እ.አ.አ በ1910 ሊሞት ችሏል። 

በመጨረሻም የሁለቱ ሰጎኖች ቅሪተ አካል (ቆዳና ላባቸውን ጨምሮ) በአግባቡ መለያ ቁጥርና ማብራሪያ ተሰጥቷቸው በአሜሪካ ብሔራዊ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዝየም በግዙፉ የአዕዋፍ ስብስብ ውስጥ ተቀምጠዋል። የሰጎኖቹ ቅሪተ አካሎችም ከወፍ አጥኚዎች እስከ ታሪክ ተመራማሪ ላሉ ባለሙያዎች ክፍት ተደርገዋል። 

አስተያየት