የዘራፊዎች ምሽግ በመሆን ላይ ያሉት የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች

Avatar: Muluneh Kassa
ሙሉነህ ካሳነሐሴ 5 ፣ 2013
City: Hawassaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች
የዘራፊዎች ምሽግ በመሆን ላይ ያሉት የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች

በሀዋሳ ከተማ መንገዶች የንጥቂያ ተግባራትን ማስተናገድ የእለት-ተእለት ተግባራቸው እየሆነ መጥቷል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ መንገደኞች የያዙትን ንብረት፣ ጌጣጌጣቸውን፣ ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን ነጥቀው የሚሮጡና የጎርፍ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ የሚገቡ ነጣቂዎች በርክተዋል። 

ከአስፖልት ዳር የተገነቡ የፍሳሽ እና የጎርፍ ማስወገጃ ቱቦዎች ስር ተወሽቀው አሳቻ ሰዓት በመጠበቅ በቱቦው አጠገብ የሚያልፉ ሰዎችን ንብረት ነጥቆ ወደ ቱቦ ውስጥ ዘሎ በመግባት የሚያመልጡ ዘራፊዎች ቁጥር ከቀን ወደቀን እየጨመረ መምጣት የከተማዋን ሕብረተሰብ ስጋት ውስጥ ከቷል። 

ለአብነት ያህል በተለምዶ ፒያሳ፣ አቶቴ፣ ንግሥት ፉራ (ሰሊሆም ክሊኒክ አከባቢ)፣ አሮጌው ገበያ፣ ሞቢል ታክሲ ተራ፣ አላሙራ ትምህርት ቤት፣ አዲሱ ገበያ እና ሌሎችም አሳቻ ለንጥቂያ እና ለዘረፋ ምቹ የሆኑ ቦታዎች፣ ማምለጫ የጎርፍ ማስወገጃ ቱቦዎች በሚገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ ዝርፊያ ይከወናል። አሁን አሁን ነጣቂዎቹ የሰውን ስልክ እና ቦርሳ ነጥቀው ዘለው የጎርፍ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ ከገቡ በኋላ ሰዎች ተሰብስበው ወደቱቦው ሲያማትሩ መመልከት ለአላፊ አግዳሚው የተለመደ ሆኗል። ዘራፊዎቹም ከማለዳ እስከ ጀምበር መጥለቂያ ድረስ ባለው የሥራ እና የእንቅስቃሴ ሰዓት የአላፊ አግዳሚውን ንብረት ነጥቀው በማምለጥ የኅብረተሰቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደፈረሱት ይገኛል። ድርጊቱ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ይበልጥ እየተስፋፋ እንደሚገኝ ነዋሪዎች ያስረዳሉ።  

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ በረከት ዳንኤል በከተማው ውስጥ በሚስተዋለው ንጥቂያ እና ዝርፊያ ላይ የጎዳና ልጆች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ የሚል ሐሳብ አላቸው፡፡ ቀደም ሲል በኮቪድ ምክንያት ከማረሚያ ቤት ምህረት ተደርጎላቸው የተፈቱ እስረኞች ወደ ማኅበረሰቡ ከተቀላቀሉ ወዲህ ሁኔታው ይበልጥ መስፋፋቱን መታዘባቸውን ይናገራሉ። በሐዋሳ ከተማ የታቦር ክ/ከተማ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር መለሰ ቡክራ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ ከማረሚያ ቤት የተለቀቁ ግለሰቦች ዳግም በንጥቂያ ምክንያት ተይዘው ወደ ጣቢያ እንደመጡ አስታውሰው በከተማዋ የተስፋፋውን ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙት ከእስርቤት የወጡ ብቻ ናቸው ብሎ መደምደም አይቻልም ባይ ናቸው፡፡ 

ሌላዋ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ ወይዘሪት መብራት ባዩ በበኩሏ ምሽት ላይ የሚካሄደው የፓትሮሎች ስምሪት በጥሩነት እንደሚነሳ ትናገራለች፡፡ ቅኝቱ እና ቁጥጥሩ ጥሩ ቢሆንም ዝርፊያውን ከመባባስ እያዳነው ስላልሆነ ይበልጥ መጠናከር አለበት ባይ ናት፡፡ “በቂ ክትትል ቢደረግና የተጀመረው የፓትሮል ቁጥጥር ቢጠናከር ጉዳዩ የየዕለት ገጠመኝ አይሆንም ነበር” ትላለች፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ብሩክ ኃይሉ የሞባይል ንጥቂያ በብዛት የሚዘወተርበት አካባቢ ከቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ጀርባ ያለው የእግረኛ መንገድ እንደሆነ አንስቷል። ዘራፊዎቹም በስፍራው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ተንቀሳቃሽ ስልክ እና ጌጣጌጥ ወይም ቦርሳ ነጥቀው ወደ መቃብር ግቢ ዘለው እንደሚገቡ ያብራራል። አያይዞም ከአቶቴ ወደ ንግሥተ ፉራ መንገድ ሰሊሆም ክሊኒክ እና የቦሌ ትራፊክ ላይት አከባቢ የእናቶች፣ የሴቶችን እና በእድሜ ጠና ያሉ ሰዎችን ስልክ፣ ቦርሳ ነጥቀው ወደ ቱቦ ውስጥ ዘለው እንደሚገቡ ተናግሯል።

“ቱቦው የከተማ ጎርፍ እና ፍሳሽ ማስወገጃ እንደመሆኑ ውስጥ ለውስጥ ሮጠው እንዲያመልጡ ምቹ ምሽግ ሆኗቸዋል፡፡ የከተማው ሰው ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። እንደነዚህ ዓይነት ተግባር የተሰማሩ ወንጀለኞችን ሕብረተሰቡ በመተባበር ለሕግ አካላት ጥቆማ ቢሰጥ ዝርፊያውን መቀነስ ይቻላል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። 

ወይዘሮ ነፃነት ተሰማ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ስትሆን የንጥቂያው ገፈት ተቋዳሽም ነች። ከሦስት ሳምንታት በፊት በተለምዶ አቶቴ ሰሊሆም ክሊኒክ ፊት ለፊት የሚገኘውን የጎርፍ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ በምታቋርጥበት ጊዜ ቦርሳ እና ስልኳን መነጠቋን ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች።

“ባልጠበኩት እና ባልገመትኩት ሁኔታ ነው በቀን በጠራራ ፀሀይ ከእጄ ነጥቆ ቱቦ ውስጥ ዘሎ የገባው። በአከባቢው የነበሩ ሰዎች ደርሰው ልንይዘው ብንሞክርም ውስጥ ለውስጥ ሮጦ ከመቼው እንዳመለጠ ልንደርስበት አልቻልንም” ስትል ብሶቷን አጋርታናለች።

ወይዘሮ ነፃነት አያይዛም ነጣቂዎቹ ዘለው ቱቦ ውስጥ በሚገቡ ጊዜ ሌላ ውስጥ ላይ ሆኖ የሚቀበላቸው ሰው እንዳለ እና ተደራጅተው ቀድመው በመዘጋጀት የሚፈፅሙት ድርጊት እንደሆነም ታስረዳለች። ቆይታም ወደ ሞባይሏ በመደወል ቦርሳዋ ውስጥ የነበሩ አስፈላጊ መረጃዎች እንዲመልሱላት ስትጠይቅ በሐሳቡ ተስማምተው፣ ከራሷ የነጠቁትን ሰነድ ለራሷ ሊሸጡላት በገንዘብ ከተደራደሯት በኋላ ቆይተው ስልኩን እንደዘጉት በመግለጽ ክስተቱን ለአዲስ ዘይቤ አጋርታለች። በመጨረሻም በክፍለ ከተማው ወደሚገኝ ፓሊስ ጣቢያ በማምራት ማመልከቷን ነው ለአዲስ ዘይቤ ያጋራችው።

በሀዋሳ ከተማ ታቦር ክፍለ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር መለሰ ቡኑራ የተጓዦችን ንብረት ነጥቀው የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ውስጥ ስለሚሸሸጉ ነጣቂዎች ፖሊስ መረጃ እንዳለውና እጅ ከፍንጅ የተያዙም ይገኙበታል ያሉ ሲሆን፤ ሪፈራል ሆስፒታል፣ የመምህራን ማሰልጠኛ አከባቢ የሚገኙ ለመሹለክ የሚያመቹ ክፍት የነበሩ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችንም በመድፈን ሰዎች መሹለኪያ ቀዳዳዎች ጠበው ሰው በማያሳልፉበት መጠን ሆነዋል ብለዋል፡፡

ረዳት ኢንስፔክተሩ አክለውም የፅዳት ሰራተኞች ለማጽዳት የሚከፍቷቸውን ቱቦዎች መልሰው መዝጋት እንዳይዘነጉ አሳስበዋል፡፡ ለቁጥጥር እንዲመቸን ማዘጋጃ ቤትና ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ትብብር እንዲያደርጉልን ጠይቀን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ነግረውናል፡፡

በከተማ ፅዳት ሙያ ላይ ተሰማርታ የምትገኘው ወይዘሮ አማረች ታምሬ በበኩሏ ‹‹በአብዛኛው ቱቦዎቹን የምናገኛቸው ክፍት ሆነው ነው፡፡ የጎዳና ልጆች ከአቅም በላይ ሆነዋል። ምሽግ አድርገውታል፣ ዘርፈው ይደበቁበታል፣ ይፀዳዱበታል እንዲሁም እኛን ሲያዩ ውስጥ ለውስጥ ይሸሻሉ›› ብላለች። ፖሊሶች መረጃ በጠየቋቸው ወቅት መረጃ እንደሚሰጡ እና በእነሱ ጥቆማ ምክንያት ወንጀለኞቹ ተይዘው የሚያውቁበት አጋጣሚ ስለመኖሩም ለአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ተናግራለች፡፡

Author: undefined undefined
ጦማሪሙሉነህ ካሳ

በፎክሎር (በባህል ጥናት) እና በሽያጭና በገበያ ጥናት ዲግሪ አለኝ፡፡ በአዲስ ዘይቤ ዲጅታል መጽሔት ላይ በሪፖርተርነት እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡