መጋቢት 29 ፣ 2015

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ነገ በድጋሜ ወደ ጉራጌ ዞን ያመራሉ

City: Hawassaፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮችምጣኔ ሀብት

ነገ ቅዳሜ በድጋሚ ወደ ዞኑ የሚያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋናነት የጢያ ተክል ድንጋይ ፕሮጀክትን ለማስጀመር መሆኑ ተነግሯል

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ነገ በድጋሜ ወደ ጉራጌ ዞን ያመራሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በወርሃ መጋቢት ለ2ኛ ጊዜ ከፌደራል እና ከክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ወደ ደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ነገ ቅዳሜ መጋቢት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሚሄዱ ምንጮች ለአዲስ ዘይቤ ገለፁ። 

ነገ በድጋሚ ወደ ዞኑ የሚያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋናነት የጢያ ተክል ድንጋይ ፕሮጀክትን ለማስጀመር መሆኑም ተነግሯል። 

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በ1972 ዓ.ም. በዓለም መካነ ቅርስነት የተመዘገበው የጢያ ትክል ድንጋይን ለማደስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርብ ካሳተሙት "የመደመር ትዉልድ” መፅሐፋቸዉ በደቡብ ክልል ብቻ የሚሸጠዉን ገቢ ለፕሮጀክቱ እንዲዉል ማለታቸዉ ይታወሳል። 

ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሶዶ ወረዳ ነዋሪ እና በወረዳዉ በመንግስት ኮሙኒኬሽን ዉስጥ የሚሰሩ የአዲስ ዘይቤ ምንጮች እንደተናገሩት በግልፅ ስለ "የጠቅላይ ሚኒስትሩ መምጣት የተባለ ነገር ባይኖርም" በእርግጠኝነት እንደሚመጡ እና ከገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በኋላ "ከማህበረሰቡ ጋር ዉይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል" ብለዋል። 

"የሶዶ ክስታኔ ማህበረሰብን በክላስተሩ ጉዳይ ለማዉራት እንዳቀዱ እየተነገረ ይገኛል" የሚሉት የአካባቢው ተወላጆች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክቶች ያሉባቸዉ ፅሁፎች በከተማዋ እየተሰቀሉ ሲሆን ድንኳኖች መዘርጋት፣ ተማሪዎችና የአካባቢው ሰዎች በፅዳት ስራ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።

የሶዶ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ከሰዓታት በፊት በማህበራዊ ትስስር ገፁ እንዳሰፈረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የመደመር ትዉልድ መፅሐፍ የሽያጭ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ነገ በጢያ ተክል ድንጋይ እንደሚካሄድ ገልፆ ከፌዴራል፣ የአዲስ አበባ ፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ይገኛሉ ቢልም የጠቅላይ ሚኒስትሩን መምጣት ግን ግልፅ አለማድረጉ ተመላክቷል።

ባለፈው መጋቢት 16  በወልቂጤ ከተማ ተገኝተዉ ከማህበረሰቡ ከተወጣጡ ተወካዮች እና የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ጋር ሲወያዩ ከማህበረሰቡ ተወካዮች ቀርቦ የነበረዉን በክልል መደራጀት ጥያቄን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ "መከፋፈል ጥሩ አይደለም  ለልማት በጋራ ለመበልጸግ እና ለማደግ በአንድ ላይ መሆኑ ጥሩ ነዉ" ማለታቸው ይታወሳል። 

አስተያየት