ሐምሌ 29 ፣ 2014

'ክላስተር' እና አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ የክልልነት ውሳኔዎች

City: Hawassaፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት እስካሁን በአዲሱ አደረጃጀት ዙሪያ አልተወያየም፤ በቀጣይም በጉዳዩ ላይ መቼ ውይይት እንደሚያደርግ አልታወቀም።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

'ክላስተር' እና አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ የክልልነት ውሳኔዎች
Camera Icon

ፎቶ፡ ከኢትዮጵያ ኢንሳይደር

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 47 ተራ ቁጥር 2 ላይ የሚከተለው ሃሳብ ስፍሯል፤ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከቱት ክልሎች ውስጥ (በዘጠኙ ክልሎች) የተካተቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው፡፡ 

ይህን ሃሳብ ይዘን ወደ ደቡብ ክልል ብንመለከት በክልሉ ውስጥ 56 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ይኖራሉ። ታዲያ የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል ስንት ክልል ይወጣዋል? ነባሩ ክልል እስካሁን (እስከ ነሐሴ 2014 ዓ.ም) ድረስ ከአንድ ወደ ሶስት ክልልነት ተከፋፍሏል። በቀጣይ ክልል የሚሆነው የትኛው ዞን ይሆን? 

በ 1983 ዓ.ም በወርሃ ሰኔ ላይ በወጣዉ የሽግግር ዘመን ቻርተር ሀገሪቷ አዲስ አበባን ጨምሮ በአጠቃላይ 14 ክልሎች የነበሯት። ከነዚህም ውስጥ ከክልል 7 እስከ ክልል 11 ድረስ የሚገኙ ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች መሆናቸዉን መረጃዎች ይጠቁማሉ ።  

በወቅቱ ከክልል ሰባት እስከ አስራአንድ የነበሩት:- 

ክልል 7 (ጉራጌ፣ ከምባታ፣ ሃዲያ፣ የም፣ ሐላባና ስልጤን)

ክልል 8 (ሲዳማ፣ ጌዲኦ፣ አማሮ እና ቡርጂ) 

ክልል 9 (ወላይታ፣ ጋሞ ጎፋ፣ ዳውሮ ፣ ኮንሶ ፣ ደራሼና ሰሜን ኦሞ) 

ክልል 10 ( በደቡብ ኦሞ ውስጥ ያሉ ዞኖች) 

ክልል 11 ደግሞ (ከፋ፣ ቤንቺ፣ ማጂና ሸካ) በአንድ ላይ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ተብለዉ ከዉሳኔ ሊደረስ መቻሉን የክልል አደረጃጀት ጥያቄዎች መንስኤና የመፍትሔ አቅጣጫዎች በሚል ህዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም ደኢህዴን ባስጠናዉ ጥናት ተመልክተናል ።

ከአራት ዓመታት በኋላ አዲስ አበባን ጨምሮ አስራ አራት የነበሩት ክልሎች የብሔር ስያሜን በመያዝ ወደ ዘጠኝ ክልል ተዋቀሩ። አዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች ደግሞ በየራሳቸው የከተማ አስተዳደር ስር ተዋቀሩ። በዚህ ጊዜ ነበር በአምስት ክልሎች ተደራጅቶ የነበረው፤ 56 ብሔር ብሔረሰቦችን የያዘው የሀገሪቱ ክፍል 'የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት' ተብሎ በአንድ ክልል ስር የተደራጀው።  

በዚህም አብዛኞቹን በዞን ደረጃ የተቀሩትን ደግሞ በወረዳና በልዩ ወረዳነት ሲያደራጅ፤ በባህልና በቋንቋ የሚቀራረቡ ብሔር ብሔረሰቦችን በጋራ ለማደራጀት ተሞክሯል። ይሁንና ከጊዜያት ሂደት በኋላ በክልሉ የሚገኙ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ቋንቋቸዉ እንዲሁም ባህላቸዉ ሊመሳሰል ከማይችሉ ብሔሮች ጋር አንድ ላይ መሆንን መቃወም ጀመሩ።

በአንድ ክልል በጋራ ለመኖር እንደማይመርጡ እና ህገመንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው እራስን በራስ ማስተዳደር እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ጥያቄ ማንሳት ቀጠሉ። ከእንዚህ ጥያቄዎች መካከል የስልጤ ብሔረሰብ የዞንነት ውሳኔና እሱን ተከትሎ የመጡት የሌሎች ዞኖችና የልዩ ወረዳዎች ጥያቄ በክልሉ አለመረጋጋትን ብሎም ግጭቶን ፈጠረ።  

የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ስር እየተዳደሩ በሚገኙ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች የመዋቅር ጥያቄዎች ምላሽ አላገኙም። ጥያቄያቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ከመጠየቅም ባሻገር አለመረጋጋት ተስተዉሎ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ሲሆን በዚህም ለሰው ሕይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት መንስኤ እስከመሆን ደርሰው ነበር።

በ1994 ዓ.ም የሲዳማ ዞን ያቀረበው የክልልነት ጥያቄ 'አፋጣኝ ውሳኔ አላገኘም' ያሉ የብሔሩ ተወላጆች ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ። ከሃዋሳ ከተማ ሎቄ በተባለ ስፍራ ላይ በተደረገው በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የፀጥታ አካላት ትኩስ ከፍተው ብዙዎች ተገደሉ።   

ለዓመታት ተዳፍኖ የቆየዉ ይህ የክልልነት ህገመንግስታዊ የመብት ጥያቄ በ 2010 ዓ.ም ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣል መምጣትን ተከትሎ በደቡብ ክልል በብዙ ቦታዎች ጥያቄው እንደገና ተነሳ።

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ 10ኛ ክልል የሆነዉ ሲዳማ  እንዲሁም በቅርብ የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የከፋ፣ የዳውሮ፣ የሸካ ዞኖች እና የኮንታ ልዩ ወረዳ በመያዝ 11ኛ ክልል መሆን የቻለዉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ተመሰረተ። ይህ ሁኔታ ለሌሎች ወረዳዎች እና ዞኖች በይበልጥ ለመዋቅራዊ ጥያቄዎች መነሻ ምክንያት እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል ።

ከሰሞኑ ከደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስር በመዉጣት ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች ሆነው  መቀጠል እንዲችሉ የተለያዩ ጥያቄዎች ሲያቀርቡ የነበሩ ዞኖችን እና ልዩ ወረዳዎች፤ ከሌሎች ዞኖች ጋር ለመደራጀት በምክር ቤታቸዉ ባደረጉት ስብሰባ ከዉሳኔ መድረሳቸዉ ተሰምቷል። ይህም ተጎራባችና በአኗኗርና በባህል እንዲሁም በቋንቋ ተቀራራቢ የሆኑ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎችን ሊያቅፍ እንደሚችል ታምኖበታል።

በዚህም መሰረት የወላይታ ዞን ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ ዞን እና የጌዲኦ ዞን እንዲሁም የአማሮ፣ የቡርጂ፣ የባስኬቶ፣ የአሌ እና የደራሼ ልዩ ወረዳዎች አንድ ላይ በመዋሃድ አዲስ ክልል ሆነዉ ለመደራጀት ከዉሳኔ ደርሰዋል። 

በተመሳሳይም በአንድ ክልል ስር ለመሆን የምክረ ሃሳብ ያቀረብት የጉራጌ ዞንን ሳይጨምር የሀዲያ፣ የስልጤ፣ የከምባታ ጠምባሮ፣ የሀላባ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳዎች በምክር ቤቶቻቸው ባካሄዱት ጉባኤ በአዲስ ክልል ለመዋቀር የቀረበዉን የወሳኔ ሀሳብ ተቀብለዋል አፅድቀዋል። ይሁንና ይህ ሪፖርት እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ያወጣው መግለጫ የለም።

አዲስ ዘይቤ ከጉራጌ ዞን አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም። ይሁንና የዞኑ መንግስት የኮሚኒኬሽን እና ሚዲያ ቡድን መሪዉ አቶ ፈቃዱ ዘለቀ ሐምሌ 27 ቀን 204 ዓ.ም. ለብስራት ራዲዮ በሰጡት መረጃ የጉራጌ ዞን እራሱን ችሎ በክልልነት ለመደራጀት ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀረበዉን ጥያቄ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ እና በዚህ ምክንያት ከሌሎች ዞኖች ጋር መዋሃድ እንዳልቻለ ገልጸዋል። 

“የህዝቡ ጥያቄ በክልልነት ለመዋቀር ነው። ይሄንንም ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቅርበን ምላሹን እየጠበቅን ነዉ”ያሉት ኃላፊዉ። “የዞናችን ምክር ቤቱ እስካሁን በአዲሱ አደረጃጀት ዙሪያ አልተወያየም። በቀጣይም በጉዳዩ መቼ ውይይት እንደሚደግ አይታወቅም። በማህበራዊ ሚዲያ 'ዞኑ የክላስተር መዋቅሩን አጽድቋል፤ በሌላ በኩል አላጸደቀም' ተብለው የሚሰራጩ መረጃዎች የተሳሳቱ ናቸው። ይህ በዞኑ አመራሮች ላይ ጫናን ለማሳደር የታሰበ ነው” ሲሉ አሳዉቀዋል። 

አሁን ላይ ከስምምነት የተደረሰዉ የመዋቅር ሀሳብ የበላይ አካላት ዉሳኔ እንጂ የማህበረሰብ ጥቅምን ያልጠበቀ እንደሆነ በሚያነሱ አሉ። በሌላም በኩል ለዚህ ዉሳኔ እዉቅና በመስጠት የድጋፍ ድምፃቸዉን በሚያሰሙ ነዋሪዎች መካከል ልዩነት መፈጠሩን አዲስ ዘይቤ ያሰባሰበችው መረጃ ያሳያል። 

በአኗኗር ዘይቤ የማይገናኙ ልዩ ወረዳዎች እና ዞኖችን በአንድ ላይ መታጨቁ የህዝብን ድምፅ ማፈን እንደሆነ የሚናገሩት በወላይታ እና በጌዲኦ ዞን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል። ማህበረሰብን ያላማከለ እና እንደማንኛዉም ዜጋ የተደረሰዉን ስምምነት በቴሌቪዥን መስኮት መመልከቻቸዉ እንዳሳዘናቸውም ጨምረው ነግረውናል።

ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጌዲኦ ዞን ነዋሪ የሆኑት እናት እንደተናገሩት “በክልል የመደራጀት ጥያቄን እስከ መጨረሻዉ መፍትሔ ለመስጠት ታስቦ ከሆነ ሁሉንም በአንድ ላይ መጨፍለቅ እና የዘመናት ጥያቄን ባዶ ማስቀረት ይሆናል” ሲሎ የሚገልጹት እኚህ እናት በቋንቋ እና በአኗኗር ዘይቤ የማይቀራረብ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች እንደተዋቀሩ ያስረዳሉ። ለአብነትም የወላይታ፣ የአማሮ እና የባስኬቶ ቋንቋ እና ባህል ከጌዲኦ ማህበረሰብ ጋር ሊቀራረብ እንደማይችል አንስተዋል።

በተመሳሳይ በወላይታ ዞን የቦዲቲ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳዊት ስለሺ “ውሳኔው የህዝቦችን አንድነት እና መብት ያላከበረ ነው። ከኢህአዴግ መንግስት አንስቶ እስካአሁን ድረስ የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች በአንድ ላይ እንዲዋሃዱ መደረጉ ምንም አይነት የተለወጠ የመንግስት ስርዓት አለመኖሩ ማሳያ ነዉ” የሚሉት አቶ ዳዊት “ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መልኩ እንዲደራጁ የተረጉት ክልሎች በኃላ ላይ ውሳኔውን ተቋወመ ባሰሙት ድምፅ ሊከፋፈሉ እንደቻለ ሁሉ አሁንም ይህ ክስተት እንደማይደገም ማረጋገጫ የለም”

በጌዲኦ እና በወላይታ ዞን የሚገኙ ነዋሪዎችም ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት የክልልነት ጥያቄ ከደብዳቤ መፃፍ አንስቶ እስከ ሰላማዊ ሰልፍ ድረስ በመዉጣት ምላሽ እንዲያገኝ እና ህገመንግስታዊ መብታቸዉ እንዲከበር መጠየቃቸዉን በማስታወስ በችኮላ የተደረገዉ ዉሳኔ ቁጭ ብሎ ማጤን እንደሚገባዉ ጭምር ይስማሙበታል። 

በሌላ በኩል አስተያየታቸውን የሰጡት የከምባታ እና የሀላባ ዞን ነዋሪዎች ደግሞ የመንግስትን ፈጣን ምላሽ በመደገፍ የሁል ጊዜ ጥያቄያቸዉ እንደተመለሰላቸዉ ይናገራሉ ። በተለይ በሀላባ ዞን በግልፅ ያልወጡ የህዝብ ጥያቄዎችን በይፋ እንዲመለስ በመደረጉ መደሰታቸውን ገልጸውልናል።

“በቀድሞ በደቡብ ክልል ስር የነበሩ ምክር ቤቶች ባካሄዱት በክልል የመደራጀት ጥያቄዎች እና የዉሳኔዉ ሀሳብ ጊዜያዉ ነዉ” በማለት የሚናገሩት በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ደረጀ ኃይሌ ናቸው። የህዝቦችን ጥያቄ በዘላቂነት የማይፈታ ከሆነ በድጋሚ የራስን በራስ ማደራጀት ጥያቄዎች መነሳታቸዉ እንደማይቀር ይገልጻሉ። 

በህገመንግስቱ አንቀፅ 39 ላይ የተቀመጠዉ 'ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው' ከሚለዉ ህገመንግስታዊ መብት በተጨማሪ በአንቀፅ 47 ስር የሰፈረው 'በክልሎች ውስጥ የተካተቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው' የሚሉት ድንጋጌዎች ለዛሬዉ በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለሚነሱ የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች እንደምክንያትነት ሊጠቀሱ እንደሚችሉ ይነገራሉ ዶ/ር ደረጀ ኃይሌ። 

በህገመንግስቱ አንቀፅ 39 ላይ የሰፈሩት የመብት ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ሊጤን እንደሚገባው በየጊዜው ምክረ ሀሳቦች ቢቀርቡም እስካሁን መሬት የወረደ ውሳኔ አልታየም። 

ዶ/ር ደረጃ ሀይሌ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት “በተለይ በደቡብ ክልል በዋናነት እየተነሱ የሚገኙ የክልልነት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተደረሰዉ የዉሳኔ ሀሳብ በጥሩ ጎኑ ብመለከተዉም፤ በድጋሚ የመዋቅራዊ ጉዳዮች ሊነሱ እንደሚችሉ ግን ግልጽ ነው” ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል። ለዚህ ምክንያት ሲያስቀምጡም “በቋንቋና በባህል የማይገናኙ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በአንድ ላይ መሆናቸዉ ነው” ብለዋል። 

በሌላ በኩል በክልል የመደራጀት ጥያቄዎች በተነሱ ቁጥር 'ሀገሪቷ ትፈርሳለች' የሚል ሀሳብ ውድቅ የሚያደርጉት መምህሩ በአፍሪካ የናይጄሪያን፤ ከእስያ ደግሞ የህንድን ሁኔታ ያነሳሉ። “በናይጄሪያ እና በህንድ የቋንቋ እና የባህል ልዩነቶች መከበር በምሳሌ የሚነሳ ነው። በኢትዮጵያ ስር የሚገኙ ብሔሮች የራሳቸዉ የሆነ ባህልና ስርዓት ስላላቸዉ በህገመንግስቱ መሰረት በክልል ቢደራጁ ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ይበልጣል” ብለዋል።

የአለም አቀፍ ህዝብ ግንኙነት እና በፖለቲካ ጉዳዮች ብዙ ልምድ ያላቸዉ መምህር ዶ/ር ደረጀ ኃይሌ ጨምረው እንዳሉት “በልዩነት ውስጥ አንድነትን ማየት እንደሚቻል እና ፖለቲከኞች ማንኛዉንም ውሳኔ ከመወሰናቸዉ በፊት የህዝብ ጥቅም እና መብት ማስቀደም ይኖርባቸው” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አዲሱን የክልል አደረጃጀት ተቀብለዉ በምክር ቤታቸዉ ከውሳኔ የደረሱት ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በክልል አወቃቀር ለመታቀፍ መስማማታቸውን ተከትሎ ድጋፉን የሰጠዉ እና በአስፈፃሚነት የሚሰራው የደቡብ ክልል መስተዳድር ውሳኔያቸውን 'በሳል' ነዉ ሲል ማሞካሸቱ ይታወሳል።

አስተያየት