የባህል አልባሳት የተጋነነ ዋጋ

Avatar: Muluneh Kassa
ሙሉነህ ካሳነሐሴ 20 ፣ 2013
City: Hawassaኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች
የባህል አልባሳት የተጋነነ ዋጋ

አብዛኛውን ጊዜ ከበዓል መባቻነት የማይዘሉት ባህላዊ አልባሳት አልፎ አልፎ በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ሲዘወተሩ ይስተዋል እንጂ በዓላት በመጡ ቁጥር በሀገር ጥበብ ልብስ አምሮና ደምቆ ለመታየት ሁነኛ ምርጫዎች ናቸው። አልባሳቶቹ ለአዘቦት ቀን ለመልበስ ካለመመቸት በተጨማሪም ከፍተኛ የዋጋ ንረት የባህል ልብሶቹ በብዙሃን ዘንድ ከበዓላት ባለፈ እንዳይዘወተሩ አድርጎታል። 

አብዛኞቹ የባህል አልባሳት አምራቾች የሚስማሙባቸው የግብዓቶች ዋጋ መናር የባህል ልብሱን የመሸጫ ዋጋ ጨምረን እንድንሸጥ አድርጎናል ይላሉ። በዋጋ ጭማሪው ምክንያት የአልባሳቱ ተፈላጊነት እየተቀዛቀዘ መጥቷል ሲሉም የጋራ ሀሳባቸውን ይሰነዝራሉ። 

በሀዋሳ ከተማ የሀገረሰብ ባህል አልባሳትን በማምረት የሚታወቁ  ባለሙያዎች በስፋት ከሚገኙባቸው አከባቢዎች ፒያሳ፣ ቅዱስ ገብርዔል አትነት ህንፃ፣ አሊያንስ፣ ሰፈረ ሰላም፣ ጎርጓዳ፣ አሮጌው ገበያ እና ሌሎች ቦታዎች ላይም በሽያጭ መደብሮችን ምርቶቻቸውን ያቀርባሉ። 

አዲስ ዘይቤ በሀዋሳ ከተማ የባህል አልባሳትን ግብይት እንዲሁም የገበያውን ሁኔታ በከተማው ተዟዙራ የሸማቹን እና የአምራቹን የግብይት እንቅስቃሴ ለመቃኘት ሞክራለች። 

ሎጊታ ሰፈር ቴዲ የገበያ ማዕከል ውስጥ የሚገኘው የስንታየሁ የባህል አልባሳት ሱቅ ባለቤት የሆነው አቶ  ስንታየሁ አበበ “አሁን ላይ ለዘመን መለወጫ ከመጡልን ትዕዛዞች ይልቅ አብዛኞቹ ለተመራቂ ተማሪዎች የሚሰሩ ትዕዛዞችን ነው እየሰራን ያለነው። ከሚያዙን ደንበኞቻችን መካከል የአብዛኛው አስተያየት ዋጋ ተወዷል የሚል ነው” ሲል ይገልጻል። 

አሁን ላይ ገበያው ላይ ዝቅተኛ የሚባለው የሃበሻ ቀሚስ ከ1,500 ብር አንስቶ እስከ 18ሺ ብር ድረስ ይሸጣል። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ አቅም ያላቸው ሰዎች ወይም አርቲስቶች በራሳቸው ዲዛይን ሲያሰሩ እስከ 30 እና 40ሺ ብር ድረስ ይሸጣል። 

እኛ በአማካይ ዋጋ እስከ 6 እና 7 ሺህ ብር ድረስ ሰርተን እንሸጣለን። እሱም አያዋጣም። ምክንያቱም ከዚህ በፊት ከሸማኔዎች ከአንድ ሺ እስከ ሁለት ሺ ብር ድረስ የምንረከበው ጥለት አሁን ላይ ከ2,700 እስከ 3,500 ብር ደርሷል። ከጥለቱ በተጨማሪ  የገበር ወጪ አለ፣ በጥለቱ ተመሳሳይ የጥልፍ ስራ አለ፣ ጥልፉን የሚሰሩት ጠላፊዎች አንዷን ትንሽዬ መስቀል ደረት ላይ ለመጥለፍ በፊት 150 ነበር አሁን ላይ 300 ብር ነው የሚጠልፉት። የክር ዋጋም እንደዛው ንሯል። መነን እና ፎዴ የሚባሉ ጨርቆች ናቸው ለሀበሻ ቀሚስ መስሪያነት የሚያገለግሉት። ፎዴውን ከመቶ አንድ ፐርሰንት የሚሆኑት እንኳ አይጠቀሙበትም። ምክንያቱም ብዙም ተፈላጊ አይደለም። መነን ጨርቅ ከዚህ በፊት ሜትሩ 15 ብር የነበረው አሁን 40 ደርሷል። ያንተ የእጅ አለ ይህን ይህን ደምረህ አንዱን የሀበሻ ቀሚስ በአማካይ ዋጋ እስከ  ስድስት እና ሰባት ሺ ብር ድረስ መሸጡ አያዋጣም ትርፉ ድካም ነው ሲል  አቶ ስንታየሁ አዲስ ዘይቤን አጫውቷታል። 

ሸማኔዎቹ  ለአልባሳቶቹ ሁለት አይነት ክሮች ሳባ (የጥልፍ ክር) እና የስፌት ክር ይጠቀማሉ። ሳባ የሚባለው የጥልፍ ክር ወርቀ ዘቦ፣ ጥቁር ሳባ፣ ነጭ ሳባ እና የተለያየ ቀለም ያለው ነው። 

አሁን ላይ የሳባ ክር ዋጋ ተወዷል። አንዳንድ ቦታ እንደውም የለንም፣ ጠፍቷል ይላሉ። አሁን ላይ በጠፉ የጥልፍ ክሮች ቦታ የስፌት ክር እየተተካ ይሰራባቸዋል። ለምሳሌ ጥቁሩ ሳባ የጥልፍ ክር ከጠፋ ቆይቷል። ይህን ክር "እስፖኝ" በሚባል ጥቁር የስፌት ክር ተክቶ እየተጠቀመ እንደሚገኝ ስንታየሁ ይናገራል። እስፓኙ የስፌት ክርም በፊት 25 ብር የነበረው አሁን ላይ 50 ብር ገዝቶ እየተጠቀመ እንዳለ ለአዲስ ዘይቤ አጫውቷል። 

ሌላኛዋ ወይዘሪት ትብለጥ እንዳለ ከሸማኔዎች የምትገዛቸው ጥለቶች እንደደረጃቸው ዋጋቸውም የተለያየ መሆኑን ጠቅሳ ከዚህ በፊት ከሸማኔዎች 1000 ብር የምገዛው ጥለት አሁን 1800 እና ሁለት ሺ እንደደረሰ ትናገራለች። የአንድ የባህል ልብስ ዋጋ በአማካኝ 800 ብር ጨምሯል። ለምሳሌ ውድ የሚባለው የንግስተ ሳባ ጥለት በፊት 2000 ብር የነበር ሲሆን አሁን ላይ 3500 እና 4000 ብር ድረስ ነው ሸማኔዎች  የሚሸጡልን ስትል ታብራራለች። የሱቅ ኪራይ ክር እና የተለያዩ ግብአቶች ወጪ፣ የጠላፊ ክፍያ ጨምሮ የሀበሻ ልብስ እንዲወደድ ያደረጉ ምክንያቶች እንደሆኑ ጠቅሳለች። አያይዛም ክር፣ ጨርቅ እና የተለያዩ ግብአቶች ሲሸጡ  መሀል ላይ ባሉ ደላሎች አማካኝነት ከገበያ እንዲጠፋ እና ዋጋቸው እንዲንር ምክንያት እንደሆኑ ነው የጠቆመችው። 

ፒያሳ አትነት ህንፃ ላይ ሄለን የሀበሻ ልብስ ሱቅ ውስጥ ስትሸጥ ያገኘናት መስከረም ዳፋ በማሽን የሚጠለፈውን ጥለት ሰዉ ብዙም አይፈልገውም ትላለች። ምክንያቱም ጫፉ ላይ አንዷ ክር ከለቀቀች ሙሉው ቀስ እያለ እየተተረተረ ይሄዳል። ሸማኔ በእጁ የሸመነው ግን አይለቅም። ለዛ ነው ሸማኔዎች በእጃቸው የሚሰሩት ጥለት የሚፈለገው በማለት ትገልፃለች። ዋጋቸውም እንደዛው ውድ ነው። ከዚህ በፊት 35 ቁጥር ተብሎ የሚመጣው ወርቀ ዘቦ ክር አዲስ በመጣ 36 ቁጥር በሚባል ክር ተተክቷል። ይህም አዲስ የመጣው 36 ቁጥር ክር ጭራሽ የበፊቱን 35 ቁጥር ክር አይተካውም ምክንያቱም አዲሱ ከለሩ ከወርቃማነት ትንሽ ወደ ኦሬንጅነት የሚያደላ ነው። እኛ እስካሁን ከዚህ በፊት ከመርካቶ በገዛነው ወርቀዘቦ ክር ነው እየተጠቀምን ያለነው ስትል ታክላለች። 

እዛው አትነት ህንፃ ላይ ለራሳቸው፣ ለሁለት ልጆቻቸው እና ለባለቤታቸው ለዘመን መለወጫ ሙሉ ተመሳሳይ የባህል ልብስ ለማዘዝ ሲጠይቁ ያገኘናቸው ወይዘሮ ፅጓ ባዩ 17000 ብር እንደተባሉ ነው ያጫወቱን። "ውድ ነው! በአዘቦት ቀን ላይለበስ ይህን ያህል ወጪ ማውጣቱን ለማንም አልመክርም" ብለዋል።

Author: undefined undefined
ጦማሪሙሉነህ ካሳ

በፎክሎር (በባህል ጥናት) እና በሽያጭና በገበያ ጥናት ዲግሪ አለኝ፡፡ በአዲስ ዘይቤ ዲጅታል መጽሔት ላይ በሪፖርተርነት እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡