የፍጆታና የሸቀጥ እቃዎች ዋጋ መናር በሀዋሳ

Avatar: Muluneh Kassa
ሙሉነህ ካሳነሐሴ 20 ፣ 2013
City: Hawassaኢኮኖሚወቅታዊ ጉዳዮች
የፍጆታና የሸቀጥ እቃዎች ዋጋ መናር በሀዋሳ

በሹፍርና ስራ በሃዋሳ ከተማ የሚተዳደሩት አቶ ታምራት ዮሀንስ በሚያገኙት ገቢ ሦስት ቤተሰብ ያስተዳድራሉ። ለባለቤታቸው ለቤት አስቤዛነት የሚሰጡት ገንዘብ ከወር እስከወር እያደረሰን አይደለም ሲሉ ምሬታቸውን ለአዲስ ዘይቤ አጋርተዋል። አቶ ታምራት ለልጆቻቸው አልፎ አልፎ ከስራ ሲመለሱ ፍራፍሬ ይዘው እንደሚገቡና ይህም ከዚህ በፊት በኪሎ ከ50-60 ብር ድረስ ይገዙ እንደነበር ነው የነገሩን። አሁን ላይ ግን አንድ ኪሎ ብርቱካን ሊገዙ በሄዱበት 80 ብር ሲሏቸው ሳይገዙ ትተው እንደተመለሱ ነው ያጫወቱን።

በሀዋሳ ከተማ ከእለት ወደ እለት የፍጆታና የሸቀጥ እቃዎች ዋጋ እየናረ መምጣት ህዝቡን ስጋት ውስጥ ከቶታል። በአከባቢው የሚመረቱ እንዲሁም ከሌላ አከባቢ ተመርተው ወደከተማዋ የሚገቡ የፍጆታ እና የሸቀጥ እቃዎች ላይ ከቀን ወደ ቀን እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት ለመዳሰስ ተችሏል። አዲስ ዘይቤ በከተማው ተዟዙራ ሸማቹንና በንግዱ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙትን፣ ግብይቱን፣ የባለሙያዎችን ትንታኔ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ቀርባ የሚመለከታቸው አካላትን ሀሳብ አካታ ለማቅረብ ሞክራለች። 

አዲስ ዘይቤ በጉዳዩ ዙሪያ በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት ዲን እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው በመምህርነት ሙያ ስምንት አመታትን ያገለገሉትን አቶ ዘመዴ ጫሚሶን አነጋግራለች። የሁለተኛ ድግሪ ትምህርታቸውንም ያጠናቀቁት በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ነው። በ በ"micro economy" ደረጃ ለምሳሌ በግብርና እና በተለያዩ አከባብያዊ (urban poverty) ጥናቶች ላይ ተሳትፈዋል። 

ባለሙያው የዋጋ ንረት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።  የዋጋ ንረቱን አንዳንዶች የዋጋ ግሽበት ነው የሚሉት ነገር ግን በአቻነት የዋጋ ንረት ተብሎ የሚጠራው የምጣኔ ሃብት ጽንሰ ሃሳብ  በአማካይ ከወር እስከወር፤ ከአመት እስከአመት የገንዘብ የመግዛት አቅምን የሚያትት ነው። በዚህ ውስጥም የኑሮ ውድነቱን ማሳየት ይቻላል። ሳይንሱ የዋጋ ንረቱን (imbalanced demand and supply) ይለዋል። ይህም የሸማቹ መብዛት እና በአቅርቦት እጥረት ምክንያት የሚከሰት "ሚዛናዊ ያልሆነ" እንደማለት ነው። 

ጽንሰ ሃሳቡን  ወደ መሬት ሲወርድ የቁሶች ዋጋ ከአምና እና ከካቻምና ይሽጥ ከነበረው ዋጋ አንፃር ከ20 በመቶ በላይ መጨመሩን መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም የሀገሪቱ "import" ላይ ጥገኛ መሆን ለዋጋ ንረቱ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ምክንያት እንደሆነ ይጠቀሳል። ምክንያቱም "import" ለማድረግ ሃገሪቱ የምትጠቀመው የውጭ ምንዛሬ የምታገኘው "export" ከምታደርገው ምርት ላይ ነው። የውጪ ንግድ በሚጠበቀው መጠን አለማደግ እና በአሁን ሰአት መንግስት ፊቱን ሙሉ በሙሉ ወደፖለቲካው ጉዳይ ማዞሩ ዓብይ ምክንያቶች ናቸው ሲል ባለሞያው ገልጿል። 

አዲስ ዘይቤ በ "inflation" (የዋጋ ንረት) ዙሪያ በዩኒቨርስቲው የተሰሩ ጥናቶች አሉ? ስትል ላነሳችላቸው ጥያቄ "ብዙውን ጊዜ ዩኒቨርሲቲዎች "macro economy issues" (ገዝፈው በሀገር ደረጃ የሚነሱ ጉዳዮች) ላይ ብዙም ለጥናት እና ሪሰርች ፈንድ አይለቁም። ወጪያቸው ትንሽ ለሆኑ "micro economy issues" ወይም (በጣም ጥቃቅን ለሆኑ አከባቢያዊ ጉዳዮች) ላይ ነው ትኩረት እየተደረገ ያለው። ጉዳዩ እንደግዝፈቱ ፈንድ ተይዞለት በ"macro level" ጥናት ቢደረግ ችግሩን እና የመፍትሔ ሀሳቦችን ለይቶ ማውጣት ይቻላል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። 

አቶ ኤልያስ ጎአ በሀዋሳ ከተማ ሰፈረ ሰላም አላሙራ አካባቢ በጥራጥሬ እና ሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ ነጋዴ ነው፡፡ “እውነት ለመናገር መግዛት እየፈለጉ የመግዛት አቅሙ አጥሯቸው ብዙ የተቸገሩ ሰዎች አሉ። ከዚህ በፊት ለአስቤዛ ምስር እስከ አምስት ኪሎ ድረስ ይወስዱ የነበሩ አሁን ላይ ሁለት እና ሦስት ኪሎ ነው የሚገዙኝ። እኔ ዋጋ የጨመርኩባቸው የሚመስላቸው ደምበኞችም አሉኝ። ጅምላ አከፋፋዮች ለኛ ጨምረው ስለሚያስረክቡን ነው እኛም የዋጋ ጭማሪ አድርገን የምንሸጠው” ብሏል። 

ሌላኛዋ ወይዘሮ ቤተልሄም ተስፋዬ በሀዋሳ ከተማ ታቦር ክፍለ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ከእሩቅ ቦታ ሳይመጡ ከሎቄ፣ ከቱላ እና መሰል  በሀዋሳ ከተማ ስር ያሉ ገጠራማ አከባቢዎች ላይ የሚመረተው ሽንኩርት፣ ድንች እና ጥቅል ጎመን እራሱ ዋጋቸው እንደጨመረ ትዝብቷን ታጋራለች። ለምሳሌ ጥቅል ጎመን ከ10 እስከ 12 ብር ድረስ ይሸጥ የነበረው አሁን ላይ እስከ 20 ብር ድረስ ነው የምንገዛው። ራቅ ካለ አከባቢ የትራንስፖርት ወጪ ተደርጎባቸው የመጡ ቢሆኑ ጭማሪው ምክንያታዊ ነው ብለህ ትቀበላለህ። ነገር ግን ይሄ የነጋዴው ህዝቡን የመዝረፍ ስራ እና የሚቆጣጠሩ አካላትን ድክመት ነው የሚያሳየው ስተል ሃሳቧን ታጠቃልላች። 

ወይዘሪት ሜሮን ይታየው ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፋት የሚገኝ የሜሮን ሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ባለቤት ስትሆን ምስር ከዚህ ቀደም 65 ብር የነበረው አሁን ላይ 100 ብር እየሸጡ እንደሆነ ትገልፃለች፣ ቀይ ሽንኩርት 10 ብር የነበረው አሁን ላይ 25 ብር፣ ፖስታ 27 ብር የነበረው አሁን ላይ 33 ብር እየሸጥን እንገኛለን ብላለች። ነጋዴዋ አያይዛም እቃዎቹ የሚጫኑበት የትራንስፖርት ዋጋ መጨመርና እቃ አከማችተው የሚደብቁ ግለሰቦችን ለዋጋ መናሩ እንደምክንያት አስቀምጣቸዋለች። 

አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ የሸማቾች ትምህርትና ስልጠና የስራ ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት አቶ አየለ ሀብሳ ለዋጋ ንረቱ ሦስት ምክንያቶችን እንደምክንያት አስቀምጠዋል። አነሱም የአቅርቦት እጥረት፣ የሀገር አለመረጋጋት እና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን እንደምክንያት አንስተዋል። እንዲሁም ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ምርት በማከማቸት በአቋራጭ ለመክበር የሚፈልጉ ግለሰቦች እንዳሉም አክለዋል። 

አዲስ ዘይቤ በሀዋሳ አከባቢ የሚመረቱት ምርቶች የትኞቹ ናቸው? ዋጋቸውስ በምን ምክንያት ሊንር ቻለ ስትል ጠይቃለች። ሃላፊው አክለውም ጥቅል ጎመን፣ ድንች፣ ቲማቲም፣ ቀይ ሽንኩርት በከተማዋ ገጠራማ አከባቢዎች ላይ እንደሚመረት ጠቁመዋል። አያይዘውም ምርቶቹ ወቅታዊ (sessional) ናቸው። አንድ ጊዜ ገበሬው ያመርትና በሚደርስበት ጊዜ ልክ ገበያውን ያጥለቀልቁታል። ምርቶቹም እያደሩ ሲቆዩ የሚበላሹ ናቸው። እነዚህ ምርቶች ከአየር ሁኔታ ጋር የተያያዙ ናቸው። ለምሳሌ ዝናብ ሲመጣ ይታፈናሉ። እዛው ሰብሉ ላይ እያሉ ይበሰብሳሉ። ይህን የክረምት ወቅትም ለአቅርቦት እጥረቱ የራሱ የሆነ ተፅእኖ እንዳለው ነው ያስረዱት። ሌላኛው ደግሞ ገበሬው ከማሳው ከቆረጠ በሁዋላ ትራንስፖርት ፍራቻ ቀጥታ ወደገበያው የማድረስ ችግር አለ። አክለውም በሀዋሳ አከባቢ የሚመረቱ ምርቶች ጥራታቸው የወረደ ነው። በገበያው ላይ እንደ አማራጭ ናቸው። ለምሳሌ ከአጎራባች አከባቢ ከኦሮሚያ (ከአዋሽ) የሚገባው ቀይ ሽንኩርት በደምብ ይፈለጋል። ይህ ሽንኩርት ወቅቱ ሲያልፍ በአከባቢው ምርት ይተካል። በአከባቢው የሚመረተው ቀይ ሽንኩርት  ከኦሮሚያ (አዋሽ) ከሚመጣው እኩል በተመሳሳይ ዋጋ ለሸማቹ ሲቀርብ ይስተዋላል። ይህ ነው ሌላኛው ለዋጋ ንረቱ መንስኤ የሆነው ሲሉ አክለዋል። 

በሌላ በኩል ስኳር ከዚህ በፊት በየ45 ቀኑ ይመጣ የነበረ ቢሆንም አሁን ከጠፋ ሁለት ወር እንደሆነው አንስተዋል። በሸማቾች ህብረት በኩል በቤተሰብ ደረጃ አራት አራት ኪሎ ይሰጥ እንደነበረም አስታውሰዋል። ስኳሩ ከጠፋ የወሰደው ጊዜ በ45 ቀን እና በሁለት ወር መሀል ያለችው የአስራአምስት ቀን ልዩነት ለአቅርቦት እጥረቱ እንደመንስኤ ትታያለች። ይህም ለዋጋ ንረቱ አጋዥ ምክንያት እንደሆነ ነው የጠቆሙት። 

ሀላፊው እንደቢሮ ሦስት መፍትሄዎችን አስቀምጠው እየተንቀሳቀሰ እንዳለም አሳውቀዋል። አንደኛው አምራቹን እና ሸማቹን ቀጥታ የማገናኘት ስራ፣ ሁለተኛው በአከባቢው የተቋቋሙት የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት የተባሉት ድርጅቶች ፀጥታው ሙሉ በሙሉ ቢረጋጋ ሄዶ ምርቱን ካለበት ቦታ ቀጥታ በማምጣት በተመጣጣኝ ዋጋ አቅርቦቱን ማሻሻል ነው። ሦስተኛው መፍትሄ በአከባቢው የሚገኙ ገበሬዎች ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ሙያዊ ድጋፍ ሰጥቶ ማብቃት እንደሆነና እቅዶቹንም በረጅምና በአጭር ጊዜ ከፋፍለው ለማሳካት እንዳቀዱ ሃላፊው አክለው ይገልጻሉ።

Author: undefined undefined
ጦማሪሙሉነህ ካሳ

በፎክሎር (በባህል ጥናት) እና በሽያጭና በገበያ ጥናት ዲግሪ አለኝ፡፡ በአዲስ ዘይቤ ዲጅታል መጽሔት ላይ በሪፖርተርነት እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡