ግንቦት 15 ፣ 2014

በማዳበሪያ ዋጋ ንረት ምክንያት ከ380 በላይ የሻይ ቅጠል አልሚ አርሶ አደሮች ስራ አቆሙ

City: Hawassaምጣኔ ሃብትወቅታዊ ጉዳዮች

ዉሽዉሽ ሻይ ልማት ድርጅት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል አረንጓዴ ሻይ ቅጠል በኪ.ግ በ4.92 ብር እንዲሁም ለውጭ ገበያ ደግሞ በ7.38 ብር ከአርሶ አደሮቹ ላይ ይረከባል።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በማዳበሪያ ዋጋ ንረት ምክንያት ከ380 በላይ የሻይ ቅጠል አልሚ አርሶ አደሮች ስራ አቆሙ
Camera Icon

ፎቶ : ጊምቦ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ቢሮ

በከፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ወስጥ የሚገኙ ስድስት የሻይ አልሚ ማህበራት ምርታቸዉን ከዚህ ቀደም ሲረከባቸዉ ከነበረዉ ዉሽዉሽ የሻይ ልማት ድርጅት ጋር የገቡትን የዉል ስምምነት ከመጋቢት 27 ጀምሮ ማቋረጣቸዉ እና ሙሉ በሙሉ ስራ ማቆማቸዉ ታውቋል። 

በወረዳዉ ዉስጥ የሚገኙ በስድስት ማህበራት ዉስጥ የታቀፉ ከ380 በላይ አርሶአደሮች ከ1997 ዓ.ም ወዲህ የሻይ ቅጠል ምርታቸዉን ለዉሽዉሽ የሻይ ልማት ድርጅት እያቀረቡ የቆዩ ቢሆንም ከአንድ ወር ወዲህ ግን በመሃከላቸዉ ያለዉ ስምምነት መቋረጡን ለአዲስ ዘይቤ የደረሰዉ መረጃ ያሳያል ። 

ለዉሽዉሽ ሻይ ልማት ድርጅት የሻይ ቅጠል ምርታቸዉን ከሚያቀርቡት በጊምቦ ወረዳ ስር ከሚገኙ ስድስት ማህበራት መካከል ሚቺቲ፣ ተጋ፣ ጨረሳ፣ ፊጦ የሻይ ልማት ማህበራት ተጠቃሽ ሲሆኑ ከ400 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ያረፈ ተክል አላቸዉ ።  

አቶ አሸብር ኃይሌ የሚቺቲ የሻይ ልማት ማህበር ሰብሳቢ ሲሆኑ የማዳበሪያ መወደድና ለጉልበት ሰራተኛ የሚከፈለዉ ወጪ ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱ ለተፈጠረዉ የዋጋ አለመስማማት መንስኤዎች እንደሆኑ ያስረዳሉ። "ከዚህ ቀደም በ1 ሺህ 700 ብር የምንገዛዉ ማዳበሪያ አሁን ላይ 5 ሺህ ብር ሆኗል ፤ የእኛም ጥያቄ ተመጣጣኝ እና ተገቢ ክፍያ ይከፈለን የሚል ነዉ" ይላሉ።

ምርታቸው ሳይለቀም ከአንድ ወር በላይ ማስቆጠሩንና በዚህ ምክንያት ደግሞ ለኪሳራ መዳረጋቸውን የገለጹልን ደግሞ የሻይ አልሚ አርሶአደር የሆኑት አቶ አይረዲን ኢብራሂም ናቸዉ።  "ከዚህ ቀደም በየሳምንቱ፣ ካልሆነ ደግሞ በአስራ አምስት ቀን አንዴ ምርታችን ይሰበሰብ ነበር" ሲሉ ተናግረዋል። 

እንደ አቶ አይረዲን ኢብራሂም ገለፃ "መተዳደሪያችን የሻይ ቅጠል ምርታችን ነዉ፣ እሱ ከሌለ ባዶ እጃችንን ነዉ የምንቀመጠዉ፤ ከድርጅቱ የሚከፈለን ክፍያ እኛ ከምናቀርበዉ አቅርቦት ጋር አይገናኝም" ብለዋል።

ለአዲስ ዘይቤ ቅሬታቸዉን ያቀረቡት አርሶ አደሮቹ እንደሚሉት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል አረንጓዴ ሻይ 1 ኪ.ግ  በ4 ብር እንዲሁም ለውጭ ሀገር ገበያ የሚውል አረንጓዴ ሻይ በ6 ብር የውሽውሽ ሻይ ልማት ድርጅት እንደሚረከባቸው ገልፀዋል። ይህ የዋጋ ምጣኔ አርሶ አደሮቹ ለሻይ ቅጠል ልማቱ የሚያወጡትን የግብዓትና መሰል ወጪዎች እንኳን መሸፈን እንደማይችልና በድርጅቱ በኩል ተመጣጣኝ የሆነ የዋጋ ማስተካከያ የማይደረግ ከሆነ የሻይ ተክሉን ከማሳቸው እስከ መንቀል ድረስ እንደሚደርሱ ተናግረዋል።

የዉሽዉሽ ሻይ ልማት ድርጅት ዋና መቀመጫዉን በአዲስ አበባ ያደረገ ሲሆን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በከፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ እና በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ኢሉ-አባቦራ ዞን ጉመሮ አካባቢ ሰፋፊ እርሻዎች አሉት። በእነዚህ እርሻዎች ላይ በሻይ ቅጠል ማምረት ስራ ተሰማርተው የሚገኙ አርሶአደሮች ለአገር ዉስጥ ፍጆታና ለዉጪ የሚላክ በሚል የተለያየ የዋጋ ተመን የሻይ ቅጠል ምርት እየተረከበ እንደሚገኝ በጊምቦ ወረዳ የውሽውሽ ሻይ ልማት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ መሠረት አየለ በተለይ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። 

ኃላፊዉ እንደሚሉት የሻይ አልሚ ማህበራቱ የዋጋ ማስተካከያ ይደረግልን የሚል ጥያቄ በደብዳቤ አቅርበዋል። ዉሽዉሽ የሻይ ልማት ድርጅት በስምምነት ነዉ የሚሰራዉ የሚሉት አቶ መሠረት ጥያቄያቸዉን መነሻ በማድረግ "ከዚህ ቀደም በኪ.ግ 4 ብር የነበረው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል አረንጓዴ ሻይ 4.92 ብር እንዲሁም 6 ብር የነበረው ለውጭ ገበያ የሚውል አረንጓዴ ሻይ 7.38 ብር ተደርጓል" ብለዋል ።

አቶ መሠረት እንዳረጋገጡት በተደረገዉ የዋጋ ጭማሪ አርሶአደሮቹ ደስተኛ አይደሉም ፤ ይልቁኑም ሙሉ ለሙሉ ስራ አቁመዋል ።

ድርጅቱ በስሩ ቀጥሮ ለሚያሰራቸው የቀን ሰራተኞች እና ከራሳቸው መሬት የሻይ ቅጠል ምርት ለሚያቀርቡ አርሶአደሮች የሚከፍለዉ የብር መጠን ተመጣጣኝ አለመሆን እንዲሁም ወቅቱን የጠበቀ የዋጋ ማስተካከያ አለመደረጉ አርሶ አደሮቹን አስቆጥቷል። ወደ ኢንዱስትሪ ማደግ እንፈልጋለን የሚሉት የሻይ ቅጠል አልሚዎቹ አርሶአደሮች ጥያቄያቸዉን ለሚመለከተውው አካልም ወስደናል ቢሉም የዉሽዉሽ ሻይ ልማት ድርጅት ስራ አስኪያጅ ግን ሁሉም ነገር በስምምነት እና በድርድር መሆን እንዳለበት በማንሳት የድርጅቱን ጥቅም እስካልነካ ድረስ ለመስማማት ዝግጁ መሆናቸዉን ጨምረዉ ተናግረዋል ።

አስተያየት