የካቲት 2 ፣ 2014

“ወደ ከሰል ማምረት ሥራ የገባሁት ችግር አስገድዶኝ ነው” የሐዋሳዋ የቀድሞ ሞዴል

City: Hawassaምጣኔ ሃብትአካባቢ

ከምትኖርበት ሐዋሳ ወደ አዲስ አበባ ተጉዛ በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ ለ3 ዓመታት እንቅስቃሴ ብታደርግም የጠበቀችውን ለውጥ ሊያስገኝላት አልቻለም።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

 “ወደ ከሰል ማምረት ሥራ የገባሁት ችግር አስገድዶኝ ነው” የሐዋሳዋ የቀድሞ ሞዴል
Camera Icon

ፎቶ፡ እያሱ ዘካሪያስ

ሞዴል አብነት ኃይሉ በ1998 ዓ.ም. የሚስ ሐዋሳ የቁንጅና ውድድር ተሳታፊ ነበረች። በወቅቱ ለውድድር ከቀረቡት ከ300 በላይ ቆነጃጅት መካከል ተወዳድራ ምርጥ 10 ውስጥ መግባት ችላለች። የምትኖረው በሐዋሳ ከተማ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ውስጥ ነው። በአሁን ሰዓት ራሷን ጨምሮ ሦስት ልጆቿን የምታስተዳድረው ከሰል በማምረት ነው። ከአገልግሎት በኋላ “አይጠቅምም” ተብሎ የተጣለን ቆሻሻ ሰብስባ ከሰል ማምረት ከመጀመሯ በፊት ስለሞከረቻቸው የሥራ መስኮች ስትናገር ፊቷ ላይ ሐዘን ይነበባል። “ብዙ ነገር ነበረኝ” በማለት በራሷ ጥረት አቋቁማቸው ከአቅሟ በላይ በሆነ ምክንያት ስለተቋረጡት የንግድና የአገልግሎት ዘርፎች ታስረዳለች።

“የባህል ምሽት ቤት፣ የሴቶች የውበት ሳሎን፣ የመኪና ኪራይ፣ ከ6ወራት በታች ለሚገኙ ህጻናት የምግብ ማቀነባበሪያ ድርጅት ያልሞከርኩት ነገር የለም” የምትለው የ36 ዓመቷ ወጣት የቢዝነሱን ዓለም የተቀላቀለችው በፋሽን ኢንዱስትሪው እንደነበር ታስቃውሳለች።

ከምትኖርበት ሐዋሳ ወደ አዲስ አበባ ተጉዛ በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ ለ3 ዓመታት እንቅስቃሴ ብታደርግም የጠበቀችውን ለውጥ ሊያስገኝላት አልቻለም። “የአዲስ አበባ ኑሮ እንደ ሐዋሳው አልሆነልኝም። ሲከብደኝ ወደ ሐዋሳ ተመለስኩ” ትላለች። የሴቶች የውበት ሳሎን እና የመኪና ማከራያ ከፍታ ለ4 ዓመታት ከሰራች በኋላ የተሻለ ገቢ ለማግኘት በማሰብ “አብነት” የሚል መጠሪያ ያለው ባህላዊ የምሽት ክበብ ከፈተች። “ክበቡ ታዋቂ ሆኖ ነበር። ከአዲስ አበባ ታደሰ መከተ፣ አስኔ አባተ፣ ኮሚዲያን በረከት (ፍልፍሉ) ሰብለ መዝሙርን የመሰሉ ታዋቂ ድምጻውያንና የመድረክ ሰዎች እየተጋበዙ ስራቸውን አቅርበውበታል” ስትል የወቅቱን ሁኔታ የምታስታውሰው ሞዴል አብነት ሶስት ዓመታት የሰራችበትን ባህላዊ የምሽት ክበብ ዘግታ ከ6ወራት በታች ለሚገኙ ህጻናት የምግብ ማቀነባበሪያ ድርጅት ለመክፈት በቅታለች። 

"አስካ ተብሎ የሚጠራውን ፋብሪካ ለመክፈት በወቅቱ የከተማ አስተዳደሩም በተወሰነ ደረጃ ትብብር ስላለበት መነሻዬ ይሄን ያህል ብር ነው ብዬ መናገር አልችልም" የምትለዋ ሞዴል አብነት ለአራት ዓመታት ፋብሪካውን አንቀሳቅሳለች።

ከሞዴሊንግ ስራዋ አስከትላ ወደ ትዳር የገባቸዉ አብነት የአምስት ልጆች እናት ናት። ከልጆቿ አባት ጋር የነበራት የትዳር ህይወት ከዓመታት በኋላ (ስንት ዓመት እንደሆነ ለመናገር አልፈቀደችም) በፍቺ ሲደመደም “አሁንም ጥሩ ግንኙነት አለን” ትላለች። ሦስቱ ልጆቿ እሷ ጋር ሁለቱ ደግሞ አባታቸዉ ጋር እንደሚኖሩ ነዉ የነገረችን።

የህይወት ውጣ ውረድ በራሷ ስህተትና በሁኔታዎች አለመመቻቸት አሁን የምትገኝበት አኗኗር ላይ ቢጥላትም በልበ ሙሉነት “ተስፋ አልቆርጥም። አሁን ያለሁበትን ዝቅታ አሸንፌ ነገ ከፍ ያለ ቦታ እገኛለሁ” ትላለች። በተከራየቻት አነስተኛ ክፍል ውስጥ ማምረት የጀመረችውን ከሰል ወደ ፋብሪካ የማሳደግ ህልም አላት።

ከሰል ማምረት የጀመረችበትን ምክንያት ስታስረዳ “ወደ ከሰል ማምረት ሥራ የገባሁት ችግር አስገድዶኝ ነው” ትላለች። የሰው ፊት ከማየት ይሻለኛል ብላ የገባችበት የሥራ መስክ ችግሯ የወለደው ብልሃት ቢሆንም የእለት ጉርስ እንዳላሳጣት ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራለች።

“አንድ ቀን ምግብ ለማብሰል ከሰል አስፈለገኝ። የምገዛበት ብር ስላልነበረኝ ተስፋ ቆርጩ ቁጭ ባልኩበት አንድ ሐሳብ መጣልኝ። ከተጣለው ቆሻሻ ከሰል ለማምረት ወሰንኩ። በቀድሞ መኖሪያዬ በተወሰነ መልኩ የከሰል ምርት ሂደትን ዐይቼ ስለማውቅ ብዙም አልከበደኝም። ሳላመነታ ገባሁበት። አሁን ከግል መጠቀሚያ አልፌ ለገበያ እያቀረብኩት ነው” በማለት ታስረዳለች። “ከሰል የማመርትበትን ግብአት የማገኘው ከቆሻሻ መጣያዎች ነው። እንደ ፌስታልና የፕላስቲክ ጠርሙስ ካለ የማይበሰብስና የሚቀልጥ ቆሻሻ በስተቀር ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ የተጣሉ ማናቸውም ተረፈ ምርቶች ሰብስቤ ከሰል አመርታለሁ።”   

ከሰል የማምረቻ ግብአት የሚሆነውን ቆሻሻ የምታገኘው ከምትኖርበት አካባቢ ነው። የከብቶች አዛባ፣ ደረቅ ሳር፣ ገለባ፣ የእንጨት ቤት ተረፈ ምርት (ሰጋቱራ)፣ የፍራፍሬ እና የአትክልት ልጣጭ ከግብአቶቹ መካከል ይገኛሉ። የተጠቀሰውን የሚጣል ቆሻሻ ለማግኘት በሆቴሎች እየዞረች ትሰበስባለች። “በተጨማሪም” ትላለች አብነት “በተጨማሪም ሥራዬን የሚያውቁ የአካባቢዬ ሰዎች ሊጥሉት ያዘጋጁትን ቆሻሻ ያመጡልኛል።”   

የምታመርተው ከሰል ከተለመደውና በስፋት አገልግሎት ከሚሰጠው የእንጨት ከሰል ጋር ሲነጻጸር የተሻለ የቆይታ ጊዜ እንዳለው የተጠቃሚዎችን ምስክርነት ጠቅሳ ስትናገር “ደንበኞቼ ሦስት ሰዓት ይቆያል ብለውኛል። እኔም ሞክሬ አረጋግጫለሁ” ትላለች። ሥራዋ የአካባቢን ንጽህና ከመጠበቅ አንጻር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንዳለውም ታምናለች። ደን ተጨፍጭፎ ከሚዘጋጀው ከሰል ይልቅ አካባቢን ሊበክል የሚችለው ቆሻሻ ለተጨማሪ ጥቅም እንዲውል ማድረጉ ከአንድ በላይ ጥቅሞች እንዳሉት ታስረዳለች።

በከሰል ምርቱ የእለት ጉርሷን ከመሸፈን ያለፈ ጥቅም አለማግኘቷ የመንቀሳቀሻ ገንዘብ እጥረት ስለመሆኑ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራለች። የምርቱን ሂደት በተመለከተ በሰጠችው ማብራሪያ “የተሰበሰበው ቆሻሻ ደረቅ ወይም እርጥብ ሊሆን ይችላል። የመጀመሪያው ሥራ እርጥቡን ከደረቁ መለየት ነው። ለብቻ የተለየው እርጥብ ቆሻሻ በጭስ እንዲደርቅ ይደረጋል። ጭሱ ቆሻሻውን ወደ ካርበን ይቀይረዋል። ቀጥሎ ሁሉንም በአንድ ላይ ተቀላቅሎ ይወቀጣል። ደርቆ ተወቅጦ የደቀቀው ቆሻሻ በጣም ሳይቀጥን በጣም ሳይወፍር ይቦካል። በማስከተል ለእርሱ በተዘጋጀው ትቦ ሲያልፍ ቅርጽ ይይዛል። ቅርጽ የያዘው እርጥብ ከሰል በእሳት ሲደርቅ ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ከሰል ይሆናል” ምርቱ በከሰል ለሚሰሩ ማናቸውም የቤት ውስጥ አገልግሎቶች ማለትም ቡና ለማፍላት፣ ምግብ ለማብሰል እንዲሁም በቆሎ ለመጥበስ አስተማማኝ እንደሆነም አክላለች።

ለባለሱቆች ሩብ ኪሎ በ3 ብር ከ50 የምታስረክበውን እነርሱ ለተጠቃሚዎች አምስት ብር ይሸጡታል። የከሰል ምርቱ ገበያ ላይ ከዋለ ከሦስት ወራት በላይ ቢያስቆጥርም ማስተዋወቅ ላይ ደካማ እንደነበር ታስባለች። ለዚህም የሚረዳት ወይም አብሯት የሚሰራ ትፈልጋለች።

ውሎዋም አዳሯም የስራ ቦታዋ ላይ የሆነውን የሥራ ፈጣሪ የቀድሞዋን ሞዴል አብነትን ብቸኝነት ተመልክቶ ወጣት መኮንን ለሽያጭ የተዘጋጀውን ከሰል በነጻ ወደ ሱቆች ያደርስላታል። "አብነት የምትሰራው ስራ ለእሷ የምትኖርበትን ገንዘብ ያስገኛል። ከተማዋንም ያጸዳል። ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑን በመመልከት ነው ላግዛት የወሰንኩት” ያለ ሲሆን የሚደግፋት የግልም ሆነ የመንግሥት አካል ቢኖር ለሐዋሳ ብቻ ሳይሆን ለሐገረቱ የሚጠቅም መንገድ ላይ መሆኗን እንደሚያምን አጫውቶናል።

"ከየቤቱ አውጥቶ የሚደፋውን ቆሻሻ እንዲሁም በሆቴሎችም የሚጣል ቆሻሻ በመሰብሰብ መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ሥራዬን እቀጥልበታለሁ። በዚህም የሚጣለው ቆሻሻ ጤና ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት መቀነስ እና የከተማዋን ውበት መመለስ እችላለሁ” የምትለው ወጣት አብነት ከቆሻሻ የሚመረተውን ከሰል በቅናሽ ዋጋ የሚያከፋፍል ፋብሪካ የማምረት ህልም እንዳላት ትናጋራለች።

አስተያየት