ኅዳር 20 ፣ 2015

በዳዉሮ ዞን ደመወዝ በወቅቱ ባለመክፈሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ተባለ

City: Hawassaወቅታዊ ጉዳዮች

አዲስ ዘይቤ በጉዳዮ ዙሪያ ምላሽ ለማግኘት ብትሞክርም ከላይ በመጣ ትዕዛዝ ነዉ በማለት መረጃ እንዳትሰጡ መባላቸዉን ከወረዳዉ የመንግስት መስሪያ ቤት ዉስጥ ከሚሰሩ ባለሞያዎች ሰምተናል

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በዳዉሮ ዞን ደመወዝ በወቅቱ ባለመክፈሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ተባለ
Camera Icon

የክልሉ መምህራን ማህበር የፃፈዉ ደብዳቤ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በዳዉሮ ዞን የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ከመስከረም ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው ገለፁ። በዚህም ምክንያት በዞኑ ያሉ የመንግስት መሰሪያ ቤቶች አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ታውቋል።

በዳዉሮ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ ዛባ ጋዞ ወረዳ፣ ታርጫ ዙርያ ወረዳ እና ዲሳ ወረዳ ይጠቀሳሉ። ለአዲስ ዘይቤ በደረሰዉ መረጃ ዲሳ ወረዳ ላይ የትምህርት ተቋማት፣ ፍርድ ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና ሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከደመወዝ ክፍያ ጋር ተያይዞ እስካሁን አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን ሰራተኞቹ ቅሬታቸዉን አሰምተዋል።

በዲሳ ወረዳ 39 የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ የመንግስት የትምህርት ተቋማት ሲኖሩ 675 መምህራን ይገኛሉ። ይህ መረጃ እስከ ተጠናቀረበት ህዳር 20 ቀን 2015 ዓ.ም. መደበኛ የመማር ማስተማር ስራ እንዳልጀመረ እና ለዚህ ምክንያት ደግሞ ደመወዝ ሳይከፈል ከሁለት ወር በላይ በማስቆጠሩ ነዉ ተብሏል።

ለአዲስ ዘይቤ ቅሬታቸዉን ያቀረቡ እና በወረዳዉ ዲሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ አብድልከሪም ያሲን እንደሚሉት ከዚህ ቀደም ወሩ አልፎ ባሉት አምስት ቀናት ዉስጥ ይከፈል የነበረዉ ደመወዝ አሁን ግን ከ65 ቀናት በላይ ሆኖታል በዚህም በችግር ዉስጥ እንገኛለን ብለዋል።

"በ2014 ዓ.ም. ከደመወዝ ጋር ተያይዞ ትምህርቱ ያለቀዉ ሁለት እና ሶስት ሳምንት እየቆየ ነዉ፤ የነሐሴ ወር ደመወዝ መስከረም 10 ነበር የተከፈለው፤ አሁን ግን ከሁለት ወራት በላይ ተቆጥረዋል አቤት የምንልበት ሁሉ ምላሻቸዉ አሳዛኝ ነዉ" በማለት ተናግረዋል ።

ሌላኛዉ መምህር ታደለ ነጋሽ የመጀመሪያ ደረጃ መምህር ሲሆኑ ከሌሎች አጎራባች ክልሎች እና አከባቢዎች የመጡ መምህራን ለችግር እና ለርሃብ እየተጋለጡ በመሆኑ ወደ ቤተሰቦቻቸው ጋር እየተመለሱ ነዉ ሲል አሁን ያሉበትን ሁኔታ ያስረዳሉ።

"ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ በተወካዮች አማካኝነት በደብዳቤ እንዲሁም በአካል መፍትሔ እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ምላሻቸው ገንዘብ የለንም ነዉ" የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች “በዚህ ምክንያት ሰራተኞች ብንሆንም የሰዉ እጅ እንድንጠብቅ ሆነናል" ብለዋል።

እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገለፃ የ65 ቀን ደመወዝ ተሰልቶ 50 ፐርሰንት እንዲከፈላቸው ትዕዛዝ ቢመጣም ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ነዉ የተናገሩት። 39 የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤቶች ማለትም ዲሳ፣ ዬሊ ጫዉላ፣ ሾታ 2ተኛ ደረጃ  ትምህርት ቤት እንዲሁም  ማሹንቻ፣ አንኮ፣ ቃዕ፣ ጣሎ፣ አርጋ፣ ጋቶ እና ሃላ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቤቶች አሁን ላይ ዝግ በመሆናቸው በመደበኛ የትምህርት ስርዓቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማምጣቱ በላይ ተማሪዎቹ ከሌሎች ጋር እኩል መሄድ እንዳልቻሉ ገልፀዋል ።

አቶ እስራኤል መስፍን በዲሳ ወረዳ የፍትህ ጽ/ቤት ዐቃቤ ህግ ሲሆኑ "በወቅቱ ደመወዝ ባለመከፈሉ ምክንያት በስራዉ ላይ ተፅዕኖ እንዳለዉ" በመጥቀስ "ስራ ይሰራል ለማለት ወደ ቢሮ ተገብቶ ፊርማ መፈረም እንጂ ደስተኛ በመሆን እየሰራን አይደለንም" ከ65 ቀን በላይ ተሰርቶ የ15 ቀን ክፍያ እንፈፅማለን ብንባልም አልተቀበልንም" ብለዋል።

የጤና ተቋማት የመድኃኒት እጥረት በመኖሩ ህብረተሰቡ ተቸግሯል፣ የቤት ኪራይ እንዲሁም ቤተሰብን ለማስተዳደር የኑሮ ሁኔታዉ አስቸጋሪ በመሆኑ ለመኖር ከብዶናል በማለት የሚናገሩት ሰራተኞቹ ለሚመለከተው አካል አቤቱታቸውን አቅርበዋል።

አዲስ ዘይቤ በጉዳዮ ዙሪያ ምላሽ ለማግኘት ወደ ወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት እንዲሁም የወረዳው አስተዳዳሪ ጋር ሙከራ ብታደርግም ሊሳካ አልቻለም። ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ጉዳይ ላይ ከላይ በመጣ ትዕዛዝ ነዉ በማለት መረጃ እንዳትሰጡ መባላቸዉን ከወረዳዉ የመንግስት መስሪያ ቤት ዉስጥ ከሚሰሩ ባለሞያዎች ሰምተናል። 

በ2014 ዓመት ሰኔ ወር ላይ በተመሳሳይ በዳውሮ ዞን የመንግስት ትምህርት ቤቶች መምህራን ደመወዝ በወቅቱ ባለመከፈሉ ምክንያት ትምህርት ተቋርጦ እንደነበረ ቅሬታቸውን ለአዲስ ዘይቤ የገለፁ ተማሪዎችና መምህራንን አነጋግረን መዘገባችን ይታወሳል።

አስተያየት