የካቲት 11 ፣ 2015

የዩኒቨርስቲ መምህራን መንግስት በቤት አበል ላይ ያደረገውን ጭማሪ አንቀበለውም አሉ

City: Hawassaዜናወቅታዊ ጉዳዮች

በተደረገው ጥናት መሰረት ዝቅተኛው የቤት ኪራይ አበል 3 ሺህ ብር የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ ይደረጋል በተባለው ስሌት ግን 1 ሺህ ብር ዝቅተኛው መሆኑን የጥናት ቡድኑ አባል ገልፀዋል

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የዩኒቨርስቲ መምህራን መንግስት በቤት አበል ላይ ያደረገውን ጭማሪ አንቀበለውም አሉ

የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ለዩኒቨርስቲ አመራሮች፣ መምህራን እና ቴክኒካል ረዳቶች ከየካቲት ወር ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የመኖሪያ ቤትና የኃላፊነት አበል ጭማሪ ማድረጉን አስታውቋል። ይህ አንገብጋቢ የመምህራን ጥያቄ ቢሆንም ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉ መምህራን ጭማሪዉ በጥናት ላይ ያልተመሰረተ በመሆኑ ተቀባይነት የለዉም ብለዋል።

ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ተደርጓል በተባለዉ የመኖሪያ ቤት አበል ከዚህ ቀደም 800 ብር የነበረው አሁን ወደ 1 ሺህ 800 ብር ተደርጓል፣ ለዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት 2 ሺህ 500 ብር የነበረዉ የመኖሪያ ቤት አበል ደግሞ ወደ 12 ሺህ ብር ከፍ ማለቱን ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መረጃ ተመልክተናል። 

ኮሚሽኑ በዚህ ሳምንት የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መምህራን እና አመራሮች የመኖሪያ ቤትና የኃላፊነት አበል ጭማሪ መደረጉን ባሳወቀበት ደብዳቤ ላይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን እና በሚመለከታቸው ተቋማት የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ በተደረገ ጥናት መሰረት ተግባራዊ መደረጉን ገልጿል።

ከየካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል በተባለዉ የመኖሪያ ቤት አበል ጭማሪ ላይ የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በሚመለከተዉ አካል ጥናት ተደርጎበታል ያለ ቢሆንም ለአዲስ ዘይቤ ቅሬታቸዉን ያቀረቡ መምህራን ግን በተደጋጋሚ እያነሱ የሚገኙትን ጥያቄዎች ያላማከለ በመሆኑ “አንቀበለዉም” ብለዋል።

ከህዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለተወሰኑ ቀናት የዩኒቨርስቲ መምህራን የደመወዝ ጭማሪ በስራ ክብደት ምዘና (JEG)፣ የመኖሪያ ቤት አበል እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ይለቀቅልን በማለት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራንና ቴክኒካል ረዳቶች ማህበር አስተባብሮታል የተባለ የስራ ማቆም አድማ ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጂ በህጋዊነት በተቋቋመዉ የዩኒቨርስቲዎች መምህራን ማህበር ለአድማው እዉቅና ሳይሰጠው መቅረቱ ይታወሳል።

መምህራኑን እያስተባበሩ የሚገኙ እና በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጥናት ላይ ነበርኩኝ ያሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ መምህር "የፌደራል መንግስቱ በጥናት ላይ ተመስርቶ ያደረገዉ የመኖሪያ ቤት አበል ጭማሪ አሁን ላይ ያለዉን የሀገሪቱን የኑሮ ሁኔታ ያገናዘበ አይደለም” ብለዋል።

ከዩኒቨርስቲ መምህራን ማህበር፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለሞያዎች እና ከገንዘብ ሚኒስትር በተዋቀረ የጥናት ቡድን ስራዎች መሰራታቸውን የሚገልፁት መምህሩ ጥናቱ ፀድቆ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም ተመልክቶት ካመነበት በኋላ በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. ዉሳኔ እንዲሰጥበት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤዉ ገብቷል ሲሉ ገልፀዋል። ይሁን እንጂ እንደመምህሩ ገለፃ “ከወር በኋላ እንደሚለቀቅ የተነገረ ቢሆንም ይህ ሳይሆን ቀርቶ በጉዳዩ ላይ ዝምታ ተመርጧል"።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጥኚዎች ቡድን የገባዉ ጥናት “የተሻሻለ የመኖሪያ ቤት አበል፣ የደረጃ እድገት፣ የትርፍ ጊዜ ክፍያ እና የስራ ምዘና ክብደት” የሚገኝበት ቢሆንም “አሁን ተግባራዊ የተደረገዉ አንዱ ብቻ ተለይቶ ከመሆኑም በላይ በወቅቱ ጥናት የተደረገበት አይደለም" ሲሉ የአዲስ ዘይቤ ምንጮች አስረድተዋል።

በ2014 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በገባዉ ጥናት መሰረት “ዝቅተኛዉ የመኖሪያ ቤት አበል 3 ሺህ ብር ሲሆን ከፍተኛዉ ደግሞ 18 ሺህ ብር ነበር” የሚሉት የጥናት ቡድኑ አባል የሆኑ መምህር በተደረገዉ ጥናት ላይ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች የተካተቱበት አልነበረም ብለዋል። 

በዚህም መሰረት የመኖሪያ ቤት አበል ጭማሪው ለቴክኒካል ረዳቶች 3 ሺህ ብር፣ ለረዳት መምህራን 8 ሺህ ብር፣ ለመምህራን 13 ሺህ ብር እንዲሁም በፕሮፌሰር ማዕረግ ለሚገኙ መምህራን 18 ሺህ ብር መሆን የነበረበት በመሆኑ አሁን ከተደረገው ጭማሪ ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ ሰፊ ነው። 

ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የካቲት 03 ቀን 2015 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ተፅፏል ባለዉ ደብዳቤው ላይ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመኖሪያ ቤት አበል እና የኃላፊነት አበል ተጠንቶ የቀረበዉ ተፈፃሚ መሆኑን አስታዉቋል። ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት አበል ጭማሪ የተደረገዉ ለዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ሲሆን ከዚህ ቀደም 2 ሺህ 500 ብር የነበረው ወደ 12 ሺህ 000 ብር ከፍ ሲል ለምክትል ፕሬዝዳንት 2 ሺህ 200 ብር የነበረው ወደ 10 ሺህ ብር እንዲሁም ለመምህራን ደግሞ 800 ብር የነበረው ወደ 1 ሺህ 800 ብር ጭማሪ ተደርጎበታል። 

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በጥር ወር ላይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ጋር ባደረጉት ዉይይት ላይ በዋናነት ከተሳታፊዎች የተነሳዉ ጥያቄ የደመወዝና ሌሎች የጥቅማ ጥቅሞች ጭማሪ ነበር። አዲስ ዘይቤ ያናገረቻቸዉ የሐዋሳ፣ የአርባ ምንጭ እና የዲላ ዩኒቨርስቲ መምህራን የተደረገዉ ጭማሪ ኢ-ፍትሃዊ ነዉ ብለዋል። 

“ለዓመታት ስንጠይቅ የነበረዉ የመኖሪያ ቤት አበል ጭማሪ ብቻ ሳይሆን የደረጃ እድገት፣ የቤት መስሪያ ቦታ እና የደመወዝ ጭማሪ ይገኙበታል” ያሉት መምህራን አሁን የተሰጠው መፍትሄ “ወቅቱን የማይመጥን ነዉ” ሲሉ አክለዋል። 

እንደ መምህራኖቹ ቅሬታ ተደርጓል የተባለዉ ጭማሪ ተደረገም አልተደረገም፤ አሁንም ጥያቄዎቻቸውን በወከሏቸው መምህራን በኩል ማቅረባችንን እንቀጥላለን ካሉ በኋላ “ይህ የማይሆን ከሆነ በድጋሚ የስራ ማቆም አድማ ከማድረግ ጀምሮ የመጨረሻ ያሉትን ሂደት እንከተላለን” ብለዋል።

ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከየካቲት 1 ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለዉን ጭማሪ እንደማይቀበሉት የሚገለፅ ደብዳቤ በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ገልፅው “አፋጣኝ ምላሽ ካላገኘን ለቀጣይ እርምጃዎች ተዘጋጅተናል” በማለት ቅሬታቸውን ገልፀዋል። 

አስተያየት