መጋቢት 16 ፣ 2014

በሐዋሳ ከተማ ከሕገ-ወጥ የነዳጅ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ሦስት ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተሰማ

City: Hawassaዜና

በቅርቡ ከሕገ-ወጥ ነዳጅ ሽያጭ ጋር በተያያዘ በተወሰደ እርምጃ አራት የማደያ ሰራተኞች እና ከ30 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን በቁጥጥር ስር ዋሉ

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በሐዋሳ ከተማ ከሕገ-ወጥ የነዳጅ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ሦስት ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተሰማ
Camera Icon

ፎቶ፡ እያሱ ዘካሪያስ

በሐዋሳ ከተማ ከሕገ-ወጥ የነዳጅ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ሦስት ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተሰማ። ከነዳጅ ማደያ ጣቢያ ሰራተኞች ጋር በመመሳጠር በቀላሉ ሊጠረጠሩ በማይችሉ ታዳጊዎች በሊትር እስከ 100 ብር ሲሸጡ የተገኙ ከ26 በላይ ታዳጊዎች እና ያሰማሯቸው 2 ደላሎችም በቁጥጥር ስር ውለው ውሳኔ በመጠቅ ላይ ናቸው። በተጨማሪም ባልተገባ መልኩ ነዳጅ በጀሪካን ቀድተው በመኖርያ ቤታቸው የደበቁ ሦስት ግለሰቦች እርምጃ ተወስዶባቸዋል።

በቅርቡ ከሕገ-ወጥ ነዳጅ ሽያጭ ጋር በተያያዘ በተወሰደ እርምጃ አራት የማደያ ሰራተኞች እና ከ30 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን በቁጥጥር ስር መዋሉን የሐዋሳ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የኢንስፔክሽን እና ሬጉላቶሪ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መሰለ ከበደ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

ከ25 በላይ አነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖች እና 19 ሞተር ሳይክሎች ደግሞ በቀን ከተፈቀደው በላይ ነዳጅ ሲቀዱ መያዛቸውን ሰምተናል። “የነዳጅ እጥረት የለም!” የሚሉት አቶ መለሰ የተጋነነውን ሰልፍ የፈጠረው ላልተገባ ጥቅም የሚሯሯጡ ሕገ-ወጦች ድርጊት ስለመሆኑ ይናገራሉ።

አስቻለው ዓለሙ ለባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ነዳጅ ለመቅዳት ለሁለት ቀናት እንደተሰለፈ ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል። “ከጸሐይ እና ከብርዱ በተጨማሪ የሥራ ሰዓቴን ከማቃጥል ብዬ አንድ ሊትር በ62 ብር ገዝቻለሁ” ብሎናል። ቤንዚሉን የቀዳው በጀሪካን ቀድተው በትርፍ ከሚሸጡ ሰዎች መሆኑንም ነግሮናል። ከሕግ አስከባሪዎች ተሸሽገው ሌሊት የሚቀዱትን ነዳጅ በ31.97 የሚገዙት አትራፊዎቹ ከማደያው ውጭ ከ60 እስከ 100 ብር እንደሚሸጡት ሰምተናል።

የሲዳማ ፖሊስ ኮሚሽን ጨለማን ተገን አድርገው 42 ሺህ ሊትር ቤንዚን የጫኑ ተሽከርካሪዎችን በደረሰው ጥቆማ መሰረት መያዙን አሳውቋል።

የሕገ-ወጥ የነዳጅ ስርቆትን ለመከላከል የተወሰደውን እርምጃ በተመለከተ አስተባባሪው አቶ መሰለ የከተማዋ በከተማዋ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ በኩል የተዘጋጀ ኩፖን ለሁሉም አሽከርካሪዎች እንደተሰጣቸው ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

በሐዋሳ ከተማ  16  የነጃጅ ማደያ ጣቢያዎች ቢኖሩም በአሁን ሰዓት አገልግሎት እየጡ የሚገኙት 6 ያህሉ ብቻ መሆናቸውን የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ታዝቧል። በአሁን ሰዓት በከተማዋ የነዳጅ አገልግሎት እየሰጠሱ የሚገኙት ሼል አካባቢ የሚገኘው ኖክ ማደያ፣ አሮጌው መናኸሪያ አጠገብ የሚገኘው ቶታል እና  ጎመጁ ይገኙበታል።

አስተያየት