መጋቢት 25 ፣ 2014

ከ7 ዓመት በፊት ግንባታው የተጠናቀቀው “ቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዝየም” አገልግሎት አልጀመረም ተባለ

City: Hawassaዜና

የኢትዮጵያዊያንን ጥንታዊ የቤት አሰራር ስልት ተከትሎ የተገነባው “ቦንጋ ብሄራዊ የቡና ሙዚየም” ከአዲስ አበባ በ457 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ቦንጋ ከተማ ውስጥ ይገኛል።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ከ7 ዓመት በፊት ግንባታው የተጠናቀቀው “ቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዝየም” አገልግሎት አልጀመረም ተባለ

በአገር አቀፍ ደረጃ ቡና ነክ ጥናትና ምርምር እንዲካሄድበት ታስቦ በ2000 ዓ.ም. የመሰረት ድንጋዩ ተጥሎ በ2007 ዓ.ም. ግንባታው የተጠናቀቀው “ቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዚየም” አገልግሎት አለመጀመሩ እንዳሳዘናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ከሦስት ዓመት በፊት በአካባቢው በአካል የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ሙዝየሙን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ከባህል እና ቱሪዝም ሚንስትር ጋር እንነጋገራለን” የሚል ምላሽ ቢሰጡም የተለወጠ ነገር እንደሌለ ነዋሪዎቹ ጨምረው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነው የቡና ምርምር ሙዝየም የመሰረት ድንጋዩ በቀድሞ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዎርጊስ የተቀመጠ ሲሆን፤ የተመረቀው የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት ነው። በአካባቢው ነዋሪዎች ወርሃዊ መዋጮና በዓይነት ድጋፍ የተገነባው ሙዚየሙ ከ35 ሚልዮን ብር በላይ እንደወጣበት ከከፋ ዞን አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ‘ሙዝየሙ ባለቤት አልባ መሆኑ አሳዝኖናል’ ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ ሙዝየሙ አገልግሎት መስጠት ሳይጀምር እድሳት የሚያስፈልገው ሁኔታ ላይ ይገኛል።

የቦንጋ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ መሀመድ ኢድሪስ የሙዚየሙ መቋቋም ዓላማ የቡና እሴቶችን እና ብዝሃ ህይወት የሚያሳዩ ስብስቦችን ለትውለድ ማሻገር እንደነበር ይናገራሉ። “በተጨማሪም” ይላሉ አቶ መሀመድ “በተጨማሪም ‘ቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዝየም’ ከቡና ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጥናትና ምርምሮች እንዲካሄዱ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ታምኖበት ነበር”

ሌላዋ የአካባቢው ነዋሪ ወ/ሮ ብርቱካን አማረ ከ13 ዓመት በፊት የአንድ ወር ደሞዛቸውን በአንድ ዓመት እንዳዋጡ ያስታውሳሉ። “እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም ሰው አዋጥቷል። ሙዝየሙ በአካባቢያችን ተገንብቶ የማየት ጉጉት ስለነበረን በደስታ ነበር ያዋጣነው። ነገር ግን ያ ሁሉ ተስፋ ቅዠት ሆኖ ቀርቷል። አሁን የሌሊት ወፍ ማደሪያ ሆኖ መቅረቱ ያሳዝናል” ብለውናል።

የኢትዮጵያዊያንን ጥንታዊ የቤት አሰራር ስልት ተከትሎ የተገነባው “ቦንጋ ብሄራዊ የቡና ሙዚየም” ከአዲስ አበባ በ457 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ቦንጋ ከተማ ውስጥ ይገኛል።

“ቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዚየም” ሥራ ያልጀመረበትን ምክንያትና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን ይዘን የከፋ ዞንን እና የቦንጋ ከተማን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። 

አስተያየት