የግዙፉ ሐውልት ባለታሪክ

Avatar: Muluneh Kassa
ሙሉነህ ካሳነሐሴ 20 ፣ 2013
City: Hawassaታሪክ
የግዙፉ ሐውልት ባለታሪክ

በታቦር ተራራና በሐዋሳ ሐይቅ መካከል የምትገኘው የደቡብ ኢትዮጵያዋ ፈርጥ ሐዋሳ ከመዲናይቱ አዲስ አበባ በ275 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ በውስጧ ያሉት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መስህቦቿ ለቱሪስት መዳረሻነት ተመራጭ አድርገዋታል፡፡ ተስማሚው የአየር ንብረቷ እና እንግዳ ተቀባይ ነዋሪዎቿ የድምቀቷ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ዓይነ-ገብ ከሆኑት የጉያዋ ትሩፋቶች መካከል በየአደባባዮቿና በሲዳማ ባህል አዳራሽ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙት ሀውልቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ጀግኖችን አስታዋሽ፣ ታሪክና ባህልን ዘካሪ የሆኑት ሐውልቶች የከተማዋ ድምቀት ከመሆን ባሻገር የማኅበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ለእንግዶች ያስተዋውቃሉ፡፡ 

“ሱሙዳ”፣ “የአሊቶ ሄዋኖ”፣ "የላንቃሞ ናሬ"፣ "የመንግሥቱ ሀሜሶ" እና የ”ወልደ ዓማኑኤል ዱባለ ሀንከርሶ (ዱጉናው) መታሰቢያ ሀውልቶች ታሪክና ባህልን አስታዋሽ ከሆኑት የአደባባይ አድማቂዎቿ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በከተማዋ ዳርቻ ለተንጣለለው የሐዋሳ ሀይቅ ደረቱን ሰጥቶ የቆመውን የወልደ ዓማኑኤል ዱባለ መታሰቢያ ሐውልት ከነዚህ መካከል ተጠቃሽ ነው። በ2003 ዓ.ም. የደቡብ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና የመንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ አማካኝነት አምስት የጥናትና ምርምር ባለሙያዎችን በማቀናጀት ተዘጋጅቶ ለንባብ የበቃውን “የሲዳማ ብሄር ባህልና ታሪክ” የተሰኘውን መጽሐፍ፣ የስነ- ሀውልት ባለሙያዎችን፣ የሚመለከታቸው አካላት፣ የብሔሩ ተወላጅ የሆኑ የእድሜ ባለጸጎችን ሃሳቦች በማጠናቀር ቃለ መጠይቅ፣ ከሐውልቱ ግርጌ የተጻፈውን ማስታወሻ እና ሌሎች ድርሳናትን አገላብጦ እንዲህ አሰናድቶታል፡፡

“ዱጉናው” በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት የወልደ ዓማኑኤል ዱባለ ሀንከርሶ ሐውልት የተገነባው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ዱጉናው ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚጠሩበት ሁለተኛ ስማቸው ነው፡፡ ሐውልቱ የቅዱስ ገብርኤል (ሐዋሳ ገብርኤል) ቤተክርስቲያንን ተጎራብቶ “ከአቶቴ” ወደ “አላቲዮን” በሚወስደው አውራ ጎዳና በከተማ አስተዳደሩ ሕንጻ ፊትለፈት በሚገኝ አደባባይ ላይ በግርማ ሞገስ ቆሟል።

የግዙፉ ሐውልት በከተማዋ መቆም ምክንያቶች ታሪክን መሰነድ፣ ጀግኖችን ማወደስ፣ ባለታሪኮችን ከፍ ማድረግ እንዲሁም ለነገ ባለታሪኮች መነሳሳትን መፍጠር ናቸው።

ወልደ ዓማኑኤል በቀደምትነት ከሚጠቀሱት የሲዳማ ታጋዮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ የብሔረሰቡ ታሪክ አዋቂዎች እንደሚሉት ለፓርላማ ከተመረጡ ቀደምት የሲዳማ ሕዝብ ተወካዮች ውስጥ አንዱ ሲሆኑ ለአርሶ አደሩ መብት በመሟገት ይታወቃሉ፡፡ በትግል ወቅት ከቆሙላቸው ዓላማዎች ውስጥም “መሬት በጭቁን አርሶ አደሮች ይዞታ ስር ይሁን” የሚለው ይጠቀስላቸዋል። በማኅበረሰቡ ዘንድ ይህን ያህል ከበሬታ ይሰጣቸው እንጂ ተቃዋሚዎች እና ተቺዎችም ነበሯቸው፡፡

በ2003 ዓ.ም የታተመው “የሲዳማ ብሄር ባህልና ታሪክ” የሚለው መጽሐፍ ላይም በትግል አላማቸው የተበሳጩት ቀኝ አዝማች ደምሴ ይርዳው የሲዳማ ተወላጆች ለፓርላማ እንዳይመረጡ እስከማከላከል ደርሰው እንደነበር ይነገራል፡፡ የሲዳማ ብሄር በንጉሡ ላይ አምጿል በሚል በተጠራው ጉባኤ ላይ በድንገት የተገኙት ወልደ ዓማኑኤል የህዝቡን አመጽ አብርደው፣ ሰልፈኞችን መክረው መመለሳቸው ከሚጠቀሱ የሰላማዊ ትግል ገድሎቻቸው መካከል አንዱ ነው፡፡

አቶ ወልደ አማኑኤል ዱባለ በ1923 ዓ.ም. በቀድሞው ዞን ወንሾ ወረዳ ገጃባ ቀበሌ "አቱካ" በተባለች መንደር እንደተወለዱ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ አባታቸው በአከባቢው ታዋቂ የነበሩት ባላምባራስ ዱባለ ሀንካርሶ ሲሆኑ፤ እናታቸው ወ/ሮ ሻቃጣ ጋዳዮና ይባላሉ፡፡ የባላባት ልጅ በመሆናቸው በወቅቱ የትምህርት እድል ካገኙት ጥቂቶች መካከል ናቸው። የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በይርጋዓለም ራስ ደስታ ተከታትለዋል። እንዳጠናቀቁ በአባታቸው ስም በሚመራው አጥቢያ ችሎት በጸሐፊነትና በረዳትነት ያገለግሉ ነበር።

በወቅቱ ባገኙት ውስን ዕውቀትና ትምህርት አማካኝነት በሲዳማ ብሄር ላይ ተጭኗል ብለው ያመኑትን ጭቆናና ብዝበዛ ለመዋጋት ወደ እንቅስቃሴ ገብተዋል። በዚያ የልጅነት እድሜአቸው በሚያገኟቸው አጋጣሚዎችም የስርዓቱን አስከፊነትና ኢሰብዓዊነት በይፋ መቃወምና ከተጎጂዎች ጎን መሰለፍ ጀመሩ። በተጨማሪም በወቅቱ ዕውቀት እና አቅም ለሌላቸው ጥብቅና እስከ መቆም እንደደረሱ ይነገርላቸዋል። 

ከ1940ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ የወቅቱን አገዛዝ በመቃወም ታግለዋል፤ የትግል ስልቶችን በመንደፍም የስርዓቱን አስከፊነት ብዝበዛና ጭቆና በመታገልና፣ ማኅበረሰቡን በማንቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። 

ከበንሳ፣ አሮሬሳ፣ ለኩ፣ ሸበዲኖ እንዲሁም ከተለያዩ የሲዳማ ክፍለ-ሀገራት ከ50 ኪ.ሜ. በላይ ተጉዘው ይርጋለም ከተማ አቤቱታቸውን የሚያሰሙ ገባሮችን እና ጭሰኞችን በመደገፋቸው፣ ጥብቅና ቆመው ለመብታቸው በመሟገታቸው እውቅናና ክብር አግኝተዋል።

በ1954 ዓ.ም. ለንጉሡ ፓርላማ ተወዳድረው ያሸነፉ የብሄሩ ቀደምት ታጋይ ናቸው። ከ1954-1965 ዓ.ም. ድረስ ለተከታታይ ሦስት ዙሮች ፓርላማ ተመርጠው የህዝብ እንደራሴ በመሆን ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። በወቅቱ የብሄሩን ድርብ ጭቆና ለማስወገድ በመታገል ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላ ወደ ሀረር ተልከው በሀረርጌ እና በኢሊባቡር በዳኝነት በማገልገል ላይ እያሉ አብዮቱ ፈነዳ፡፡ ከ1966ቱ አብዮት በኋላ የሲዳማ አውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በ1970 ዓ.ም. የሲዳማ ወጣቶች ለወታደራዊ ስልጠና እንዲነሳሱ አስተባባሪም ነበሩ። በዚያው ዓመት የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲዓን) ፓርቲን መስርተው ህይወታቸው እስካለፈበት 2000 ዓ.ም. ድረስ በፓርቲው መሪነት አገልግለዋል። 

በወቅቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የደርግ ተቃዋሚ በነበረው “መኢሶን” ውስጥ በነበራቸው የፖለቲካ ተሳትፎ ከደርግ ጋር ቅራኔ ውስጥ በመግባታቸው የደርግ መንግስት ሲፈልጋቸውና ሲያሳድዳቸው ወደ እንግሊዝ ሀገር ተሰደዱ። ትግሉን እዚያው እንግሊዝ ሀገር ሆነው ደርግ እስከወደቀበት 1983 ዓ.ም. ድረስ ለሲዳማ ህዝብ ነፃነት ሲታገሉ ቆይተዋል። በ1983 ዓ.ም. የኢህአዴግ የሽግግር መንግስት ለውጥን ተከትሎ ከስደት ወደ ሀገራቸው በመመለስ በሰላማዊ መንገድ ትግሉን በሀገር ውስጥ ሆነው ስለመምራታቸው የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

በደርግ ዘመን ወልደ አማኑኤል ዱባለ የቆሙላቸውን አላማዎች የተቃወሙት ፊትአውራሪ አበበ አባፈርዳ በቀዌና እና ጋጣ አከባቢዎች ገዢም ነበሩ። ጣልያን እንደወጣ በቀዌናና አሺሾ አከባቢ የተፈፀሙ የጅምላ ግድያዎችን ያስተባበረና የመራ ግለሰብ ነው። ብሄሩ በንጉሱ ላይ አምጿል በሚል በተጠራው ስብሰባ ላይ ወልደአማኑኤል ተገኝተው:- 

"የጠነሰሰው ሴራ ዘገየ፣ ፊታውራሪ አበበ አባፈርዳም አረጀ፣ ሴራውን የቆዳ ለባሽዋ ልጅ አፈረሰው ስለዚህ አሁን እኛ ዛብያ ገዝተን አጎንብሰን እርሻችንን መስራት አለብን።" ሲሉ መልዕክት አዘል በሆነ ስነ-ቃል (weeddo) ህዝቡን መክረው ጉባኤው እንዲበተን ማድረጋቸውን የ2003 ዓ.ም. እትም የሆነው "የሲዳማ ብሄር ባህልና ታሪክ" መጽሐፍ ያትታል።

ከሚኖሩበት እንግሊዝ ሀገር በ1983 ዓ.ም. ለሰላማዊ ትግሉ ወደ ሀገር ቤት ከገቡ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ በ1990 ዓ.ም. በገጠማቸው የጤና እክል ምክንያት ለህክምና ተመልሰው ወደ እንግሊዝ ሄደዋል። እንግሊዝ ሀገር በህክምና ሲረዱ ቆይተው ህዳር 10 ቀን 2000 ዓ.ም. ህይወታቸው አልፏል፡፡ የቀብር ስነ-ስርአታቸው በትውልድ ቀያቸው አቱካ ህዳር 17 ቀን 2000 ዓ.ም. ተፈፅሟል።

ህልፈታቸውን ተከትሎ በሀዋሳ ከተማ የቆመው ሀውልት መታሰቢያቸው ይሆን ዘንድ እንዲሁም ዕድሜአቸውን ሙሉ የታገሉለት ሕዝብ ውለታቸውን እንዲወሳ ተገነባ። 

የብሄሩ ተወላጅ የሆኑት የ69 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ አቶ ዓለማየሁ ሀሜሶ “ወልደ አማኑኤል በሦስቱም መንግሥታት ህዝብን ወግነው፣ ከህዝብ ጎን ቆመው የታገሉ ጀግና የሲዳማ ታጋይ ናቸው” ሲሉ ይገልጿቸዋል፡፡ “ለዚህ ጀግንነታቸው እና የሕይወት ዘመን አገልግሎታቸው የአደባባይ ስያሜ እና ሐውልት መሰየሙ ገድላቸው ትውልድን እንዲሻገር ያደርጋል” ብለዋል፡፡

የወልደ አማኑኤል ዱባለን በሀዋሳ ከተማ የቆመላቸውን መታሰቢያና በመኖርያ ቤታቸው ደጃፍ ላይ የተሰራውን የመቃብር ሀውልት የቀረጸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ጥበብ ትምህርት ቤት የ"monumental sculpture" (አደባባይ ላይ የሚቆም የሀውልት ቅርፅ ስራ) መምህር አርቲስት ግርማ ወልደሰማያት ነው።  አስር ወራት የወሰደው የሃውልቱ ግንባታ 2.5 ሚሉዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል። 

“መታሰቢያ ሀውልቱን ከመስራታችን በፊት የሳቸውን ሙሉ ታሪክ ቀድመን አንብበን ነው ወደስራው የገባነው” ሲል ይገልፃል ግርማ። 

በሃውልቱ ላይ ወልደአማኑኤል በቀኝ እጃቸው የተደገፉት በትረ ስልጣናቸውን ይወክላል። በግራ እጃቸው ደግሞ  መፅሀፍ ይዘዋል። መሉ ቁመቱ ወደላይ 14 ሜትር ሲሆን ከወገብ በላይ የሚያሳየው የቀረፃ ስራ ብቻ 5 ሜትር ነው፣ ከታች ያለው በሴራሚክ የተለበጠው የኮንክሪት ስራ ደግሞ ቀሪውን 9 ሜትር ይሸፍናል። ሙሉ ሀውልቱ  4.50 ሜትር የጎን ስፋት ይዞ ነው ያረፈው።

“የአደባባይ ሀውልት በሳይንሱ መሠረት ከእሩቅ ሆነህ ስታየው ሰው የሚመስል ነገር ግን ስትቀርበው ገዝፎ የሚታይ መሆን አለበት።” የሚለው ባለሙያው የወልደአማኑኤል መታሰቢያ ሀውልት የ"sculpture science" (የስነ-ሀውልት ቀረፃ ሳይንስ) የሚለውን ያሟላ ነው ሲል ይገልፀዋል። 

“ሳይንሱ እደ ጥበቡን በሰባት ከፍሎ ያጠናዋል። እነሱም የእንጨት፣ የብረት፣ የመስታወት፣ የሴራሚክ፣ የፕላስቲክ፣ የቆዳና የጨርቃጨርቅ ዘርፎች ናቸው። የወልደአማኑኤል ሀውልትን የመቅረፅ ስራ ሲሰራ መጀመሪያ በሲሚንቶ ቅርፁ መሰረቱን እንዲይዝ ይደረጋል። ከዛ በኋዋላ የሳቸውን የሚፈለገውን ገፅታ ለማምጣት የጠረባ ስራው ተሰራ። የሀውልቱ ገፅታ የሳቸውን ሁለት አይነት ገፀ ባህሪ የተላበሰ ነው። አንደኛው ኮስተር ያለውና ሌላኛው ደግሞ የደግነት ባህሪያቸው ነው። እንደተመልካቹ ዕይታ ገፅታቸውን መረዳት ይቻላል። የሀውልቱ ከለር "ቡሽመር" ይባላል (የተጠረበ ድንጋይ) የሚመስል እንደማለት ነው። ብዙ ሀውልቶች የቡሽመር ከለር ነው ያላቸው። ይህም ዓለም አቀፍ ሕግ ነው” ሲል ገልጿል። 

ሀውልቱ ፊት ለፊቱን ለሀይቁ፤ ጀርባውን ደግሞ ለፀሀይ የሰጠበት ምክንያት "light size" (የሀውልቱንና የተመልካቹ ዕእይታ የብርሀን መጠን) ለማግኘት ሲባል የተደረገ ነው። ይህ የብርሀን መጠን በሳይንሱ መሰረት የሚገኘው ከ14 ሜትር ርቀት ላይ ነው። ወይም ተመልካቹ በ14 ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ በዓይኑ ቀጥታ ሀውልቱን ሲመለከት ከሀውልቱ ግርጌ እስከ አናቱ ድረስ ያለው በ27 ድግሪ ዕይታ ውስጥ መምጣት አለበት። ይህም ከእሩቅ ሆኖ ሲታይ ሰው የሚመስል ነገር ግን ቀረብ ሲባል ገዝፎ እንዲታይ ያደርጋል። እነዚህን ዕይታዎች እንዲያሟላ በሚል ነው ሀውልቱ ፊትለፊቱን ወደሀይቁ በሚወስደው የአቶቴ መንገድ ትይዩ እንዲሆን የተደረገው። ሌላኛው ከሀውልቱ ጀርባ ያለው አካባቢ እንደ አሁኑ ከማደጉ በፊት በሰዓቱ ሜዳማ በመሆኑ ነው የሀውልቱ ጀርባ እንዲሆን የተደረገው። 

ቀራፂው አያይዞም እነዚህ የ"sculpture" (የስነ-ሀውልት ቀረፃ ስራዎች) በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አማካኝነት በእንጨት እና በብረት 40 እና 50 ሳ.ሜ. በሚሆን ቁመት ተሰርተው ወደ ከተማዋ ለሚመጡ ጎብኚዎች ቢሰጥ ወይም በሽያጭ መልክ ቢቀርብ ጥሩ ነው። ለምሳሌ ብራዚልን የሚጎበኝ ቱሪስት የእየሱስ ክርስቶስን እጁን ዘርግቶ የሚያሳየውን ሀውልት አውሮፕላን ውስጥ ለመያዝ በሚያመች መልኩ በተለያየ ትንንሽ መጠን ስለሚዘጋጅ ሲመለሱ ለማስታወሻነት ይሸምቱታል። አንድም በእንግዳው ላይ ትውስታን በመፍጠር ሀውልቱን ከነገድሉ ማስተዋወቅ ነው። ሌላም የ"sculpture" ሙያውን ያሳድገዋል። ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

Author: undefined undefined
ጦማሪሙሉነህ ካሳ

በፎክሎር (በባህል ጥናት) እና በሽያጭና በገበያ ጥናት ዲግሪ አለኝ፡፡ በአዲስ ዘይቤ ዲጅታል መጽሔት ላይ በሪፖርተርነት እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡