"አፊኒ" የሲዳማ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሂደት

Avatar: Muluneh Kassa
ሙሉነህ ካሳሐምሌ 30 ፣ 2013
City: Hawassaባህል
"አፊኒ" የሲዳማ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሂደት

ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለዘመነው ማኅበረሰብ ምሰሶዎች ናቸው። ከነዚህም ውስጥ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሂደቶች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። ይህም በባህል ዘውግ መሰረት ሰዎች ባልተስማሙባቸው አውዶች ላይ እርቅን ለመፍጠር የሚፈፀሙ ሸንጎዎችና ባህላዊ የግጭት አፈታት ስነ-ስርዓቶች ሀገር በቀል ዕውቀት በመሆናቸው ከዘመናዊው የፍርድ ቤት የዳኝነት ስርዓት የተለዩ ናቸው። የሲዳማ ህዝብ እንደማኅበረሰብና እንደ ትውልድ ለዘመናት ጠብቆና ተንከባክቦ ያቆየው የራሱ የሆነ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ አለው። በዚህ የግጭት አፈታት አውድ ውስጥ "አፊኒ" (በግጭት አፈታት ስነስርዓት ውስጥ ሀሳብን የማንሸራሸር ስልት) ዋነኛው ነው። ይህም ቀጥተኛ የአማርኛ ትርጉሙ "ሰማችሁ ወይ" እንደማለት ነው። 

አፊኒ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ግለሰቦች ወይም አካሎች በሸንጎ ውስጥ በውይይት ወይም በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት እንዲሳተፉ ዕድል የሚሰጥ መንገድ ነው። ሀሳብን ለማንሸራሸርና ለማሰባሰብ ጊዜ ለማግኘት ጭምር የሚረዳ የንግግር መሳሪያም ነው ማለት ይቻላል።

አፊኒ የሚቀርበው፤ የቀረበውን ሀሳብ አቅጣጫ ተረድቶ እየተከታተለ ያለው ወገን እንዲረዳውና ሀሳቡን ለተሰብሳቢው ያደረሰው ወገን ጊዜ ወስዶ በማጤን እውነትን በመግለጥ ሙግቱን ለመርታት ወሳኝ የሆኑ ቁልፍ መከራከሪያ ምክንያቶችን ለማሰባሰቢያ ነው። እንዲሁም የሀሳቡ ደጋፊዎች ጉዳዩን በአፅንኦት እንዲከታተሉ እና ደጋፊ ሀሳብ እንዲያመነጩ ለማጠናከር ጭምር ነው። ይህም ለመጨረሻ ውሳኔ አቅጣጫ ደጋፊዎቹን ለማስማማት ያለመ ነው። የሚቃወም ካለም "እዚህ ጋር የተለየ ሀሳብ አለኝ" ብሎ የመቃወሚያ ሀሳቡን እንዲያቀርብ  የአፊኒ ስርዓት ዕድሉን ያሰጣል። 

በሲዳማ ባህል ሰዎች ሲናገሩ "አፊኒ" ሳይባል ጣልቃ አይገባም። በሌላ መልኩ አንድ የተበደለ ሰው ማንኛውም አይነት እርምጃ ከመወሰዱ በፊት በአጠገቡ ላሉት ወይም ለታላላቆቹ "አፊኒ" በማለት ማሳወቅ ባህላዊ ግዴታው ነው። ይህንን ሳያደርግ በግብታዊነት እርምጃ የወሰደ እንደሆነ ቅጣት ይጣልበታል። አጥፊው ቅጣቱ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እንዲያጣ ስለሚያደርገው ከባድ ይሆንበታል፡፡ ከቅጣቶቹ ውስጥ እድር፣ እቁብ ወይም ሌሎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያለውን ሥልጣንና ተሳትፎ እንዲያጣ፣ እንዳይሸጥ እና እንዳይገበይ፣ ልጆቹን እንዳይድር የሚከለክሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አፊኒ እውነትን ከማፈላለግና ከፍትሕ አሰጣጥ ጋር በእጅጉ ይተሳሰራል። እውነትን በማጣራትና በማረጋገጥ ወደሚቀጥለው እርምጃ ለመራመድ አፊኒ ወሳኝ መንገድ ነው። ይህም የሚሆነው አፊኒ በጉዳዩ ላይ እውቀት ያለው ማንኛውም ሰው መረጃ እንዲሰጥ ሰፊ እድል ስለሚሰጥ ነው። 

በመሬት፣ በድንበር፣ በትዳር፣ ነፍስ በማጥፋት፣ በጠለፋ፣ የሰው ሀቅ በመብላት፣… ስሞታ የቀረበባቸው ጉዳዮችት ወደ ሕግ ከማምራታቸው በፊት በሲዳማ ባህል በአፊኒ ስርዓት ይዳኛሉ። በማኅበረሰቡ ዘንድ ግጭቶች በአፊኒ የመፈታት እድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡

አፊኒ በአንድ እና በሁለት ሰዎች መካከል ውሳኔ አይሰጥም። አራት እና አምስት ከዚያም በላይ በሆኑ ሰዎች አማካኝነት ይከወናል። አፊኒ በጉዱማሌ (ጉዱማሌ ቀጥተኛ የአማርኛ ትርጉሙ “አደባባይ” ማለት ሲሆን የፍቼ ጫምባላላንና የዳኝነት ስነ-ስርአትን ጨምሮ ሌሎችም ማኅበራዊ ጉዳዮች ይከናወኑበታል፡፡) እና መሰል ትልቅ የዋርካ ጥላ የሚገኝባቸው የሸንጎ አውዶች ላይ ይከወን እንጂ በዕለት-ተእለት መስተጋብር ውስጥ ሰዎች ሲጋጩ እዚያው በተጋጩበት ቦታ ላይ አስታራቂዎች ደርሰው ቦታ ሳይመርጡ በአፊኒ ስርዓት መሰረት ግጭቱን ሊፈቱ ይችላሉ። 

በአፊኒ ስርዓት መሠረት ሽማግሌዎች ቁጭ ብለው "halaale" (እውነትን የማውጣት) ስራ ይሰራሉ። 

አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የብሄሩ ተወላጅ አባት አዛውንት የሆኑት አቶ መብራቱ ማቲዎስ አፊኒን ሲገልፁት የእርቅ ማጣፈጫ ቅመም ነው ይላሉ። ይህም በግጭት፣ በሸንጎ፣ በጉርብትና መሀል ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሔ ያበጃል። ነገር ግን ድንገት ከሸንጎ አፈንግጦ ቢፋፋም እንኳ አፊኒ መልሶ ያረግበዋል ሲሉ ይገልፃሉ። 

በሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ኮምሽን ቢሮ የፎክሎር ጥናት እና ልማት ባለሙያ የሆነው አቶ ጥበቡ ላሊሞ እንደገለፀው አፊኒ የሲዳማ ህዝብ ባህላዊ እሴቱ ነው። ህዝቡ ለዘመናት ሲገለገልበት የቆየ ስርዓት ሲሆን እድሜ፣ ፆታ፣ ማኅበራዊ ደረጃ እንዲሁም አውድን አይመርጥም ሲል ገልፆታል። በግለሰቦች ወይም በቡድኖች መካከል ግጭት ቢፈጠር፤ ተጎጂው አካል አጠገቡ ላሉ ሰዎች አፊኒ (ሰማችሁ ወይ) መበደሌን ብሎ ስሞታውን ያሰማል። አፊኒ ከተባለ በኋላ ግጭት ይረግባል። ወቃሽ እና ተወቃሽን የመለየት እንዲሁም ችግሮችን የመፍታት ስራ ነው የሚሰራው።

በየፍርድ ቤቱ ያሉ መጉላቶችን፣ ጊዜ እና ወጪን ይቆጥባል፣ ማኅበራዊ ትስስርን ያጎለብታል ይላሉ ባለሙያው ስለ አፊኒ ፋይዳ ሲያብረሩ። አያይዘውም ትልልቅ ግጭቶች በሚኖሩበት ጊዜ በአፊኒ ውስጥ "ቆሬ" ስለሚባለውም ስርዓት አንስተዋል።  "ቆሬ" ነገርን ለነገ ማሳደር ወይም ጉዳዩ ጀርባው ይጠና እንደማለት ነው። በዚህም ተበዳይን ሄደህ ከልጆችህ ከቤተዘመዶችህ መረጃ አሰባስበህ ቅረብ ይሉታል ሲል ገልጿል።

Author: undefined undefined
ጦማሪሙሉነህ ካሳ

በፎክሎር (በባህል ጥናት) እና በሽያጭና በገበያ ጥናት ዲግሪ አለኝ፡፡ በአዲስ ዘይቤ ዲጅታል መጽሔት ላይ በሪፖርተርነት እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡