ነሐሴ 13 ፣ 2013

“ወማ” ባህላዊ የሹመት ስርዓት

City: Hawassaባህል

ከማህበረሰቡ የአኗኗር ልማዶች በትውልዶች ቅብብሎሽ ዘመናትን ተሻግረው ከዛሬ ደጃፍ ከደረሱት አምስቱ የሲዳማ ብሔር ባህላዊ የአስተዳደር እርከኖች እና የዳኝነት መዋቅሮች መካከል የወማ የአሿሿም እና የኃላፊነት ድርሻ በዚህ ጽሑፍ ተዘግቧል።

Avatar: Muluneh Kassa
ሙሉነህ ካሳ

በፎክሎር (በባህል ጥናት) እና በሽያጭና በገበያ ጥናት ዲግሪ አለኝ፡፡ በአዲስ ዘይቤ ዲጅታል መጽሔት ላይ በሪፖርተርነት እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡

“ወማ” ባህላዊ የሹመት ስርዓት

የሲዳማ ህዝብ በጥንታዊ ባህልና ትውፊታዊው የአኗኗር ልማዱ የራሱ የሆነ የአስተዳደር እና የዳኝነት መዋቅሮች አሉት፡፡ ነባሩ አስተዳደራዊ ስርአት ለአድልዎ ያልተመቸ እኩልነትን ማዕከል ያደረገ ነው። በብሔሩ ጎሳዎች የተለያዩ የአስተዳደራዊ ሥልጣን እርከኖች እና ኃላፊነቶች አሉ፡፡ የሥልጣን እርከኑ መጨረሻ "ሞቴ" ወይም ጎሳን መምራት ነው፡፡ የባህላዊ አስተዳደር እና ዳኝነት ስርዓት የሆነው “ሶንጎ” ከግለሰቦች ይልቅ ለማኅበረሰባዊ ደህንነት ቅድሚያ ይሰጣል። በሲዳማ ባህል ሐገር በቀል እውቀት መሰረት 5 የአስተዳደር እርከኖች አሉ፡፡ እነዚህም ሞቴ፣ ወማ፣ ጋዳና፣ ጭሜሳ፣ ናፋር ጌርቾ ይባላሉ፡፡ "ሞቴ" የጎሳ መሪ፣ "ወማ" የጎሳ መሪው ልዩ የቅርብ ረዳት፣ “ጋዳና” የጋዳ አባት (ሰላም አምጪ፣ የሰላም አባት) ወይም የሉዋ (በትውልድ እርከን መሠረት የሚደራጅ ማኅበራዊ ተቋም) ስርዓት አስፈፃሚ፣ "ጭሜሳ" የሀገር ሽማግሌ እና "ናፋር ጌርቾ" የቀዬ ወይም የጎረቤት ሽማግሌ እንደ ማለት ናቸው። 

በዚህ ጽሑፍ በትውልዶች ቅብብሎሽ ዘመናትን ተሻግረው ከዛሬ ደጃፍ ከደረሱት አምስቱ የሲዳማ ብሔር ባህላዊ የአስተዳደር እርከኖች መካከል የወማን የአሿሿም እና የኃላፊነት ድርሻ እንመለከታለን፡፡

“ወማ” ከጎሳ መሪው “ሞቴ” ቀጥሎ ፪ኛ ደረጃ የሚሰጠው ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ነው፡፡ ለጎሳ መሪው እንደ ቅርብ አማካሪ (ምሰሶ) ይታያል፡፡ ዋነኛ ኃላፊነቱ የጎሳ መሪውን መዋቅር መደገፍ ነው፡፡ የ‹‹ሞቴ›› የቅርብ ሰው የሆነው ‹‹ወማ›› መንፈሳዊ ስርአቶችን ያስፈጽማል፤ ማኅበራዊ ጉዳዮችንም ይደግፋል፡፡ በአስተዳደራዊ ምክክሮችና የግጭት ማስወገጃ ጉባኤዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የጎሳ መሪውን ያግዛል። አልፎ አልፎ የጎሳ መሪው "ሞቴ" ኃላፊነቱን በሚገባ ባልተወጣበትና በተለያዩ ግድፈቶች የተነሳ ተቀባይነቱ ሲሸረሸር ወማ የመሪነቱን ሚና ወስዶ የጎሳውን ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች እንዲያስተባብር ይፈቀድለታል። 

የወማ የአሿሿም ስርዓት በተለያዩ አከባቢዎች እና ጎሳዎች ዘንድ መለስተኛ ልዩነት ቢኖረውም በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው። ለወማ ሹመት በእጩነት የሚቀርበው ግለሰብ የአስተዳደር ስርአቱ በሚከውኑ “ሶንጎ”ዎች (የአስተዳደር እና የሽምግልና ስርዓት አስፈፃሚዎች) ይመከርበታል፡፡ ግላዊ ባህሪው እና የብሔረሰቡ ባሕላዊ እሴቶች ላይ ያለው አቋም ይተቻል፣ ይፈተሻል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አልፎ ለህዝብ ሰላም እና ለሀገር ደህንነት ይበጃል፣ ለበረከት እና ለጥጋብ ገዳም ነው፣ በባህሪው እና በባህላዊ ዕሴቶች ላይ ያለው አቋም ትክክለኛ ነው ተብሎ በሽማግሌዎች የተመረጠው ግለሰብ ለበዓለ ሲመቱ እንዲዘጋጅ ይታዘዛል፡፡ ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ለሽማግሌዎች ባሳወቀ ጊዜ ታዋቂ ጭሜዬዎች (የሀገር ሽማግሌዎች) እንዲሰበሰቡ ጥሪ ተደርጎ በዓለ ሲመቱ ይከናወናል።

የሹመት ሥርዓቱ ሲጀመር በቅድሚያ የሚታረደው ከብት (የመስዋዕት እርድ "kakkalo" ተብሎ ይታወቃል) ደሙን እጩ ተሿሚው "garambicho" በመባል የሚታወቀውን ለመፍለጫና ለዘነዘና መስሪያነት የሚውል ጠንካራ የዛፍ ቅጠል ተቆርጦ በታዳሚዎች ግምባር ላይ እየባረከ እንዲረጭ ይደረጋል። ለበዓሉ ማድመቂያም በከፍተኛ ዝግጅት በጥንቃቄ ለዚህ በዓል ተብሎ የተዘጋጀ "ichate malawo" የሚሰኝ ጥራቱን የጠበቀ ጠጅ ይቀርባል፡፡ በሲዳማ ባህል እንደዚህ ባሉ ታላላቅ በዓላት ከሚቀርቡ የምግብ የመጠጥ ዓይነቶች ውስጥ ሻፌታ (የቆጮ ማዕድ) እና ማላዎ (ማር) በዋናነት ይጠቀሳሉ። የከብት እርድም ይኖራል፡፡

ለጎሳ መሪዎች የሹመት ስርአት የሚከናወንበት ስፍራ "yaakule" በመባል ይጠራል። በጥሬ የአማርኛ ትርጓሜው (ሜዳማ ቦታ ላይ በሚገኝ የዋርካ ጥላ ስር ወይም የታዋቂ ሰው ደጃፍ ላይ) ማለት ነው፡፡ ስርአቱን ለመካፈል በስፍራው የተገኙ ታዳሚዎች ተሿሚው ከዚህ ቀደም የከወነውን መልካም ተግባር እያነሱ፣ ብቃቱን እያደነቁ፣ ችሎታውን እያስታወሱ የሙገሳ ዜማ ያሰማሉ።

በወቅቱ እንደየአካባቢዎቹ የሚለያዩ ስርአቶች ይፈጸማሉ። በአንዳንድ አከባቢዎች ሹመቱ በ"ቄጣላ" (የአባቶች ጭፈራ) ይገለፅና በምርቃት ተደምድሞ የበዓሉ ፍጻሜ ይሆናል። ለምሳሌ በ“ሳዎላ” ጎሳ “ወማ” በሚሾምበት ወቅት ተሿሚው ወማ በሁለት የቅርብ ረዳቶቹ አማካኝነት ሰውነቱን ታጥቦ ቅቤ ተቀብቶ እንደ አስክሬን ተገንዞ የሙገሳ ዜማ እየተዜመለት በሸክም ለበዓሉ ወደተዘጋጀለት ዳስ ተወስዶ በተዘጋጀለት አልጋ ላይ እንዲቀመጥ ይደረጋል። ከዚያም መሾሙ ይበሰርና ታዳሚዎች እየተጫወቱ ግብዣውን ይታደማሉ። 

በሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ኮምሽን ቢሮ የፎክሎር ጥናት እና ልማት ባለሙያ የሆነው አቶ ጥበቡ ላሊሞ እንደገለፀው ስርዓቱ አሁንም እየተከወነ ይገኛል። ስርዓቱ በስፋት የሚከወንባቸውን የመልጋና የወንሾ ወረዳዎችን ለአብነት ያህል መጥቀስ ይቻላል። ወማ ሲሾም በባህሉ መሰረት አካለ ጎዶሎ አይኑ የጠፋ መሆን የለበትም፤ ቁመናው ወዘተ . . የሚሉ ነገሮች ታይተው ነው የሚመረጠው። አንድ ወማ ሲሾም ከጎሳው ውጪ ሌላ ሰው አይሾምም። ይህም እዛው ጎሳው ውስጥ ካለ ሰው ተመርጦ ነው የሚሾመው እንደማለት ነው። በሲዳማ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ባህላዊውን የአስተዳደር ስርአት እና የግጭት አፈታት ዘዴ በዩኔስኮ ደረጃ ለማስመዝገብ ጥናት እና የተለያዩ ዝግጅቶ እየተደረገ እንዳለም አክሎ ገልጿል።

አስተያየት