የካቲት 30 ፣ 2015

በየአመቱ የሚቀያየሩት የጎንደር ከተማ ከንቲባዎች ለከተማዋ ምን ፈየዱላት?

City: Gonderፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

በከተማው ነዋሪዎች ለጎንደር በመሰረተ ልማት ወደኋላ መቅረት ተጠያቂ የሚደረጉት በፍጥነት የሚቀያየሩት ከንቲባዎች ናቸው፣ በዚህ ወቅት በይፋ የተሾመ ከንቲባ የላትም

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በየአመቱ የሚቀያየሩት የጎንደር ከተማ ከንቲባዎች ለከተማዋ ምን ፈየዱላት?

ከንቲባ በየዓመቱ በሚባል ደረጃ የሚቀያየርባት ጎንደር ከተማ የስሟን ያክል የገነነች ከተማ መሆኗ ቀርቶ የነበሩት ጥንታዊ ቅርሶቿ እንኳን የመፈራረስ አደጋ እንዳይገጥማቸው ስጋት እንዳለባቸው የከተማው ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።

ለከተማዋ የሚጨነቁ የጎንደር ሰዎች የመሰረተ ልማት እጦት አንገብግቧቸው ቢጮሁም ሰሚ በማጣታቸው ስደት የመረጡ ነዋሪዎች ብዙ እንደሆኑ አዲስ ዘይቤ በከተማዋ እየተዟዟረች ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች ለጎንደር ያላቸውን ፍቅር እንባ እየተናነቃቸው ነግረውናል። 

አዲስ ዘይቤ በአሁኑ ሰዓት ከንቲባ ባልተሾመላት ጎንደር ከተማ የሚኖሩ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አባቶችንና የሀገር ሽማግሌዎችን ባነጋገረችበት ወቅት ጎንደር በመሰረተ ልማት ከሌሎች ከተሞች ወደኋላ እንድትቀር ከሚያደርጓት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው በየጊዜው የከንቲባዎች መቀያየር እና እሱን ተከትሎ የሚፈጠረው ፕሮጀክቶችን ጀምረው ሳያጠናቅቁ ከስልጣን መነሳትን ያስቀምጣሉ። 

ጎንደር ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2015 ዓ.ም ባሉት 17 ዓመታት ውስጥ ብቻ 7 ከንቲባዎች ተፈራርቀውባታል። ከንቲባዎቹ ሙሉ በሙሉ ምንም አላበረከቱም ብሎ መፈረጅ ባይቻልም፣ የትላልቅ ፕሮጀክቶች መሰረተ ድንጋይ ጥሎ ከማለፍ ውጭ ለአገልግሎት ክፍት ያደረገ ከንቲባ እምብዛም እንደሌለ ነዋሪዎች ይገልፃሉ። 

እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ይጠናቀቃል የተባለው የጎንደር አዘዞ አስፓልት መንገድ እስከአሁን ድረስ አለመጠናቀቁ አንዱ የጀመረውን ከመቀጠል ይልቅ ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች ትኩረት መስጠታቸው ከንቲባዎቹ የሚመለከታቸውን አካላት አስተባብሮ መጨረስ እንደማይችሉ ግልፅ ማሳያ እንደሆነ አዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉት ነዋሪዎች ያስረዳሉ። 

አዲስ ዘይቤ ትዝብቶቿን እና የነዋሪዎቹን አስተያየት በመያዝ ወደ ጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በማቅናት የምክር ቤቱን አፈ ጉባኤ አቶ ፀጋው አዘዘን እንዲሁም የጎንደር ከተማ ምክር ቤት የማህበራዊ፣ ሴቶች እና ህፃናት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ ስለሺ መስፍንን አነጋገራለች። 

አቶ ፀጋው አዘዘ ከንቲባ የሚሆነው ሰው በክልሎች አሸናፊ የሆነው ፓርቲ እጩ አቅርቦ ምክር ቤቱ ሲያፀድቀው እንደሆነ ገልፀው ከንቲባ ለመሆን የመጀመሪያው መስፈርት የምክር ቤት አባል መሆን እንደሆነ ያስረዳሉ። በየጊዜው ስልጣናቸውን የሚለቁት ከንቲባዎች የጀመሩትን ፕሮጀክት ሳይጨርሱ እንዲለቁ እና በስፋት ወደ ክልል አመራርነት እንዲሄዱ መደረጉ ስለሚፈጥረው ጫና የጠይቅናቸው የጎንደር ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ “ከንቲባዎች ወደ ክልል መሄዳቸው ይጠቅማል እንጂ ጉዳት የለውም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል። 

ጎንደርን በከንቲባነት የመሩ ሰዎች ወደ ክልል መዋቅር መግባታቸው የከተማዋን ችግር ስለሚያውቁ ችግሩን ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት በሚያውቁት ልክ የበለጠ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ እና የክልሉን አቅም ለማጠናከር እንደሚያግዙ አፈ ጉባኤው አቶ ፀጋው አዘዘ ይገልፃሉ። 

የከንቲባዎችን የቆይታ ጊዜ የሚደነግግ ህገ ደንብ ባይኖርም ቢያንስ አምስት አመት ማገልገል እንደሚገባና ጎንደርን ባስተዳደሩ ከንቲባዎች በከተማዋ ውስጥ የተሰሩ መናፈሻዎች፣ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ ለውስጥ የተሰሩ መንገዶች እንደምሳሌ ቀርበዋል። 

የጎንደር ከተማ ምክር ቤት የማህበራዊ፣ ሴቶች እና ህፃናት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ስለሺ መስፍን በበኩላቸው ጥንታዊቷ ጎንደር የቱሪዝም ከተማ እንደመሆኗ በልማት አልበለፀገችም ብለው፣ “ከንቲባ ቶል ቶሎ መቀያየሩ ለከተማዋ መሰረተ ልማት ወደኋላ መቅረት አንዱ ምክንያት ቢሆንም ከንቲባው ብቻ ሳይሆን በስር ያሉ ዘርፎች ስራዎች እንዲጓተቱ አድርገዋል” ብለዋል። 

አንድ ከንቲባ የጀመረውን አጠናቆ ለመጨረስ ቢያንስ ከአራት እስከ አምስት ዓመት በስልጣን ላይ ሊቆይ ይገባ ነበር የሚሉት አቶ ስለሺ መስፍን፣ ከንቲባዎች ከእነሱ በፊት የነበረ አስተዳዳሪን የሚተቹበት አጋጣሚ መኖሩን አስታውሰው “በመመካከር ቢሰራ ኖሮ ጎንደር ከተማ እንደጥንታዊነቷ እና የቱሪዝም ከተማነቷ የበለፀገች ከተማ ትሆን ነበር” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። 

የከተማው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ፀጋው አዘዘ በበኩላቸው ጎንደር በመሰረተ ልማት ወደኋላ እንድትቀር ካደረጓት ምክንያቶች መካከል በሃገሪቱ ያጋጠመውን ጦርነት እንደአንድ ችግር ይጠቅሳሉ። ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ አፈ ጉባኤ የሆኑት አቶ ፀጋው ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ጎንደርን ያስተዳደሩት አቶ ተቀባ ተባባል የገቢያ መነቃቃት፣ የከተሞች ፎረም እና ባዛር እንዲጀመር ማድረጋቸውን ይገልፃሉ። 

ከህዳር 2013 እስከ ጥቅምት 2014 ዓ.ም ያገለገሉት አቶ ሞላ መልካሙ የጎንደር ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ምንጭ የሆነው የአንገረብ ግድብ ከአገልግሎት ጊዜው በማለፉ ውሃ እንዳይቋረጥ ማድረጋቸው እንዲሁም ከህዳር 2014 እስከ የካቲት 2015 ዓ.ም በስልጣን ላይ የቆዩት አቶ ዘውዱ ማለደ ደግሞ “በጦርነት መካከል ሆነው ሃገራችንን ለጠላት ሳያስደፍሩ ማቆየታቸው”ን አፈ ጉባኤው አስረድተዋል።

ምንም እንኳ እነዚህ በፍጥነት የሚቀያየሩት ከንቲባዎች ወደ ክልል በመሄድ የክልሉን አቅም እያሳደጉ ነው ቢባልም ጎንደር ከተማ ላይ ግን ከሰሩት መሰረተ ልማት ይልቅ ያልሰሩት ገዝፎ እንደሚታይ ነዋሪዎቹ እና ለጉብኝት የሚመጡ እንግዶች የሚመሰክሩት እውነታ ሆኗል። 

በፌደራል እገዛም ይሁን በክልሉና በከተማው በጀት ተመድቦላቸው መሰረተ ድንጋይ የተጣለላቸው በርካታ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ዳዋ በልቷቸው መቅረቱ ህዝቡን አስቆጥቷል። አዲስ ዘይቤ ከዚህ ቀደምም የህብረተሰቡን ጥያቄ ተከትላ ጎንደር ከተማ ባልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች እና በመሰረተ ድንጋይ መጨናነቋን ዘግበን ነበር።  

ከታህሳስ 1998 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2000 ዓ.ም ድረስ አቶ መጋቢው ጣሰው፣ ከሰኔ 2000 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 2004 ዓ.ም አቶ ሃብታሙ ገነቱ፣ ከታህሳስ 2004 ዓ.ም እስከ የካቲት 2008 ዓ.ም አቶ ጌትነት አማረ፣ ከመጋቢት 2008 ዓ.ም እስከ ሃምሌ 2010 ዓ.ም አቶ ተቀባ ተባባል፣ ከሃምሌ 2010 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 2012 ዓ.ም ድረስ ሙሉቀን አዳነ (ዶ/ር) ተሹመው ጎንደርን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል። 

አቶ ማስተዋል ስዩም፣ አቶ ሞላ መልካሙ እንዲሁም በቅርቡ በአዲስ ሹመት ወደክልል መዋቅር የተወሰዱት አቶ ዘውዱ ማለደ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ቆይተዋል። በመጨረሻም ከህዳር 2014 ዓ.ም እስከ የካቲት 2015 ዓ.ም አቶ ዘውዱ ማለደ ተሸመው ሲያገለግሉ ቆይተው ስልጣናቸውን ለቀው ወደ ክልል መዋቅር የገቡ ሲሆን ይህ ፅሁፍ እስከታተመበት የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ከተማዋ ያለከንቲባ ትገኛለች። 

አስተያየት