መስከረም 11 ፣ 2015

የ14ኛ ጊዜ የሎተሪ እድለኛው አቶ መሃመድ አብደላ

City: GonderLifestyle

"በህይወትና በሎተሪ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም"

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የ14ኛ ጊዜ የሎተሪ እድለኛው አቶ መሃመድ አብደላ
Camera Icon

ፎቶ፡ ጌታህን አስናቀ

በጎንደር ከተማ አራዳ ክ/ከተማ ቅዳሜ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መኖሪያቸውን ያደረጉት አቶ መሃመድ አብደላ ለ14 ጊዜ የሎተሪ እድለኛ የሆኑ በኢትዮጵያ ብቸኛው ግለሰብ ናቸው። በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ደረጃ ለበርካታ ጊዜ የሎተሪ እጣ እድለኛ በመሆን ቀዳሚ የሆኑት እሳቸው እንደሆኑ ወ/ሮ ማንጠግቦሽ የኋላ፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ብሄራዊ ሎተሪ ጽ/ቤት ሃላፊ አረጋግጠዋል።  

በከተማዋ በሚገኙ ሎተሪ አዟሪዎችና የሎተሪ እጣ እድል ሞካሪዎች ዘንድ እንደ ትልቅ ተስፋ የሚታዩት አቶ መሃመድ “የእሳቸው እድል ጥሩ ነውና ለእኔም ይደርሰኝ ዘንድ በእሳቸው እጅ ይቆረጥልን” በሚል እምነት ካሉበት ድረስ መተው ሎተሪ የሚቆርጡ እንዳሉ ሰምተናል።      

አሁንም በልብስ መኪና ስፌት የሚተዳደሩት አቶ መሃመድ አብደላ ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ እድል ለእሳቸው እንደጎረፈ ይናገራሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ የ500 ብር እድለኛ በመሆን ቤታቸውን ያንኳኳው ይህ ታዕምረኛ የሎተሪ እጣ በ 2007 ዓ.ም 75 ሺህ ብር አሸናፊ አድርጓቸዋል።

በ1954 ዓ.ም የተመሰረተው የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር በ2015 ዓ.ም 61ኛ አመቱን ይዟል። 

የብሄራዊ ሎተሪ የመጀመሪያው እጣ 50ሺህ ብር የነበረ ሲሆን በ 2004 ዓ.ም በአስተዳደሩ 50ኛ አመት ላይ ከፍተኛው እጣ 5 ሚሊዮን ብር ነበረ። በ60ኛ አመቱ በ2014 ዓ.ም ደግሞ 20 ሚሊዮን ብር ደርሷል። 

የሎተሪ ትኬት ዋጋ በ1954 ዓ.ም 25 ሳንቲም ነበረ። ከ2014 መጨረሻ ወራት ድረስ ከፍተኛው የአንድ ሎተሪ ትኬት የሽያጭ ዋጋ 100 ብር ደርሷል። በዚህ ዲጂታል ዘመን ደግሞ በስልክ ቴክስት በማድረግ ሎተሪ መግዛት ተችሏል።

አቶ መሃመድ አብደላ ከብር 500 ጀምሮ እስከ 75 ሺህ ድረስ በተለያዩ ጊዜያቶች አስራ አራት ጊዜ በመሸለም በአስተዳደራቸው ቀዳሚውን ስፍራ የያዙ እድለኛ ደንበኛቸው እንደሆኑ የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር የጎንደር ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ማንጠግቦሽ የኋላ ይናገራሉ። 

ጥር 13 ቀን 1977 ዓ.ም የመጀመሪያ ሎተሪ እድለኛ የሆኑት አቶ መሃመድ አብደላ የ500 ብር እጣ የደረሳቸው ሲሆን ከሶስት አመት ቆይታ በኋላ መጋቢት 18 ቀን 1980 ዓ.ም በመደበኛ ሎተሪ 7ሺህ ብር እንዲሁም በአንድ አመት ልዩነት ውስጥ ሃምሌ 27 ቀን 1981 ዓ.ም 50 ሺህ ብር እንዲሁም ታህሳስ 07 ቀን 1982 ዓ.ም 50 ሺህ ብር በመደበኛ ሎተሪ ደርሷቸዋል።

የአቶ መሃመድ አብደላ እድል በእነዚህ ብቻ አላበቃም። እስከ ከፍተኛው የብሄራዊ ሎተሪ እጣ ድረስ ቤታቸውን አንኳኩቷል።

“በህይወትና በሎተሪ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም” በሚል መርሃቸው ሁሌም በየአመቱ ሎተሪ እየቆረጡ በ1983 ዓ.ም ባሉት ወራቶች ሶስት ጊዜ ሎተሪ ደርሷቸዋል። መስከረም 5 ቀን 1983 ዓ.ም 12ሺህ ብር በመደበኛ ሎተሪ ፣ ጥቅምት 17 ቀን 1983 ዓ.ም 7ሺህ ብር በመደበኛ ሎተሪ እንዲሁም የካቲት 10 ቀን 1983 ዓ.ም 12ሺህ ብር በመደበኛ ሎተሪ አግኝተዋል።

ነሃሴ 1 ቀን 1984 ዓ.ም 20ሺህ ብር በመደበኛ ሎተሪ፣ ታህሳስ 1 ቀን 1986 ዓ.ም 7 ሺህ ብር በመደበኛ ሎተሪ፣ ነሃሴ 06 ቀን 1987 ዓ.ም 12ሺህ ብር በመደበኛ ሎተሪ፣ ሃምሌ 13 ቀን 1999 ዓ.ም 15ሺህ ብር በሎቶ ሎተሪ አሸንፈዋል።

ጥቅምት 2000 ዓ.ም 500 ብር በሎቶ ሎተሪ እና መስከረም 1 ቀን 2001 ዓ.ም 500 ብር በሎቶ ሎተሪ ከደረሳቸው በኋላ ከፍተኛ ብር ያገኙበት እጣ ታህሳስ 2007 ዓ.ም 75,000 ብር በመደበኛ ሎተሪ ደርሷቸዋል።

የብሄራዊ ሎተሪ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ንዋይ በ2014 በታተመው መፅሄት ስለ ሎተሪ ሲናገሩ "ሎተሪ ብዙ ገፅታዎች አሉት። በመጀመሪያ ገፅ የሎተሪ ትኬት የሆነ የዕድል ጨዋታ ነው። የእጣ ቁጥሮችና የሽልማት መጠኑን የያዘ ትኬት ወይም ወረቀት ነው። ግን ሎተሪ ወረቀት ብቻ አይደለም። ሚናው ከወረቀትነት፣ ከትኬት የገዘፈ የእያንዳንዳችንን ህይወት የመለወጥ ሁነኛ ሚና አለው " ይላሉ። 

የሎተሪው ሌላው ገፅታው ተስፋና የብዙዎች የለውጥ መንገድ ነው። ደንበኛው የሎተሪ ትኬትን ከገዛበት ሰከንድ ጀምሮ ትኬቱ ህይወትን የመለወጥ አቅም አለው። ጥዋት ከተከራየበት ቤቱ የወጣ ደንበኛ እረፋዱ ላይ የቪላ ባለቤት፣ ወደ ጉዳዩ በታክሲ የሄደ ደንበኛ አመሻሹ ላይ የአውቶሞቢል እድለኛ ፣ከቤቱ ሲወጣ የ አንድ መቶ ብር ኖት ብቻ የያዘ ደንበኛ ወደ ቤቱ ሲመለስ የ 20 ሚሊየን ብር ዕድለኛ የማድረግ አቅም አለው። ዕድለኛውን ባለሃብት አድርጎ እራሱን ፣ቤተሰቡንና ሃገሩን የመርዳት ዕድል ይሰጠዋል ይላሉ አቶ ቴዎድሮስ ንዋይ። 

በአጠቃላይ በ14 ጊዜ የሎተሪ እጣዎች እድለኛ በመሆን ከ250,000 ብር በላይ የደረሳቸው አቶ መሃመድ በሎተሪ እድለኛ ሆነው ባገኙት ገንዘብ መኖሪያ ቤት እንደሰሩበት ፣ ሚኒባስ መኪና እንደገዙበት እንዲሁም ልጆቻቸው ወደ ውጭ ሃገር እንደላኩበት ነግረውናል። ቤታቸውን እንደማስታወሻም እንደሚጠቀሙበት አጫውተውናል። 

የሎተሪ እጣ ሳይደርሳቸው በፊት በልብስ ስፌት ሙያ ትዳራቸውን ይመሩ እንደነበረ የተናገሩት አቶ መሃመድ አብደላ የሎተሪ እጣ ከደረሳቸው ወዲህ ደግሞ የተሻለ እና መልካም የሚባል ህይወት እየኖሩ እንሚገኙ አጫውተውናል።

በጋዝ የምትሰራው የልብስ ስፌት መኪናቸውን እስከዛሬ ያልተውት አቶ መሃመድ አብደላ ከስራ ወዳድነታቸው አንፃር እንዲሁም ብር የማይጠገብ መሆኑን እየገለፁ የልብስ ስፌት መኪናዋ መስራት እየቻለች ቦዝና መቀመጥ የለባትም በሚልና ለቀን ማስመሻም ትሆናቸው ዘንድ እየተገለገሉባት እንደሚገኙ ነግረውናል። 

የመጀመሪያው የብሄራዊ ሎተሪ የእጣ አወጣጥ ስነስርዓት የተካሄደው በ1954 ዓ.ም በጃንሜዳ ነበር። በዚህም የቀድሞ የኤርትራ ሃማሴን አውራጃ አምስት ነዋሪዎችን በ50 ሺህ ብር እድለኛ አድርጓል። በእንቁጣጣሽ፣ በዝሆን፣ በትንሳኤ፣ በእድል እንዲሁም በገና ስጦታ ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያንን ተስፋ ከመስጠት አልፎ የሚሊዮን እድለኛ የማድረግ፣ ህይወት የመለወጥ ታሪክ ሰርቷል። 

ከብዙ ሚሊዮን ህዝብ ጋር ተፎካክረው የመረጡት የእድል ቁጥር በተደጋጋሚ ወደ እሳቸው በር ያንኳኳበትን ሚስጥር አቶ መሃመድ ሲናገሩ "በህይወትና በሎተሪ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም" በሚለው እምነታቸው ያለማሰለስ ስለሚቆርጡ እንደሆነ ነግረውናል። 

ከጎንደር ብሄራዊ ሎተሪ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ባገኘነው መረጃ ከአቶ መሃመድ አብደላ በተጨማሪ በጎንደር ዙሪያ ቆላድባ ከተማ የሚገኙ አቶ እርዚቅ ፍሬው የሚባሉ ግለሰብ ለሶስት ተደጋጋሚ ጊዜ ሎተሪ ድርሷቸዋል፤ 2 ሚሊዮን ብር ፣ 800 ሺህ ብር እና የቡና መፍጫ ደርሷቸዋል። 

የጎንደር ከተማ ሎተሪ አዟሪዎች አቶ ሙሃመድ አብደላን እንደቤተሰብ ያውቋቸዋል። በእሳቸው እጅ እንዲቆረጥላቸው የሚፈልጉ እጣ ሞካሪዎችም ለረጅም አመታት ያለምንም ተስፋ መቁረጥ ወደ አቶ መሃመድ አብደላ መሄዳቸውን እስካሁን ድረስም እንዳላቋረጡ አጫውተውናል።

በሙከራቸውም በእሳቸው እጅ ሎተሪ ተቆርጦላቸው እጣ የደረሳቸው እንደሚኖሩ ይናገራሉ። “እጣ ከደረሰኝ ለእርሰዎ አካፍለዎታለሁ ወይም መጥቼ አመሰግነዎታለሁ ብለው ቃል በመግባት ያስቆርጡኝና በዛው ይጠፋሉ፤ ማን እንደደረሰው ለይቼም አላውቅም” በማለት ነግረውናል። 

አስተያየት