ጎንደርን በጨረፍታ

Avatar: Ghion Fentahun
ግዮን ፈንታሁንነሐሴ 12 ፣ 2013
City: Gonderባህል ቱሪዝም ታሪክ
ጎንደርን በጨረፍታ

ጎንደር ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ 656 ኪ.ሜ. እንዲሁም ከአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር 175 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኝ በቀደምት ዘመናት የነገሥታት መናገሻ የነበረች ታሪካዊ ከተማ ናት። በ17ኛውና 18ኛው መ.ክ.ዘ የተሰሩ ታሪካዊ ቅርሶቿ የከተማዋ መገለጫዎች ናቸው። ታሪካዊ ቅርሶቿ የቱሪስቶች መዳረሻ ለመሆን አብቅቷታል። በታሪክና በባህል ነፀብራቅነቷም ትታወቃለች፡፡ የጎንደር ከተማ ዋነኛ የቱሪስት መስህብ የሆኑት አብያተ መንግስታትና አብያተ ክርስቲያናት በወርቃማው ዘመኗ የኢትዮጵያ ነገሥታት ያሰሯቸው ናቸው፡፡ አብያተ መንግሥታቱ በከተማው መሃል በሚገኘው ከፍተኛ ስፍራ ላይ ይገኛሉ። አብያተ መንግሥታቱ የተሰሩት ከድንጋይ፣ ከእንጨትና ከኖራ ሲሆን የጥንት ኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ረቂቅነትን ያንፀባርቃሉ፡፡ የፋሲል ግንብ የኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ አሻራ ያረፈበት ግንባታ ነው። አገራችን የራሷ ግብረ-ሕንፃ አሰራር እንደነበራት በዓለም የመሰከረውን ግብረ-ሕንጻ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /UNESCO/ እ.ኤ.አ ጥቅምት 1979 ዓ.ም. በዓለም ቅርስነት ሊመዘግበው ችሏል፡፡

ጎንደር አፄ ፋሲለደስ የቆረቆራት የነገስታት ከተማ እንደሆነች  የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። የነገስታት መናገሻ እንድትሆን በአፄ ፋሲለደስ ብትመረጥም ከአፄ ፋሲለደስ ቀደም ብሎ ሰው የሚኖርበት አካባቢ እንደነበር ታሪካዊ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ። ጎንደር የሚለው ስያሜ በአፄ አምደ ፅዮን ዜና መዋዕል (1307-1337 ዓ.ም.) ተጠቅሶ ይገኛል። ጎንደሮች ማርያምና ጊዮርጊስ የሚባሉ ቤተ-ክርስቲያኖች ጎንደር ዘመናዊ ከተማ ሆና ከመመስረቷ አስቀድመው የነበሩ መሆናቸውም ጎንደር ከአፄ ፋሲለደስ የቀደመ ታሪክ እንዳላት መገንዘብ ይቻላል።

ጎንደር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለምአቀፍ ደረጃ ስመ ገናና መሆን የጀመረችው ግን በአፄ ፋሲለደስ ዘመነ-መንግስት ለመናገሻ ከተማነት ከተመረጠች ማግሥት ጀምሮ ለመሆኑ አሌ አይባልም። በተለይም በአባቱ በአፄ ሱሲንዮስ ዘመን ቅሬታ የነበራትን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅሬታ በመፍታት፣ በአባቱ የንግሥና ዘመን አብባ የነበረችውን የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ወደ ጎን በመግፋታቸው ከሀገር ውጭ ስሟ በደጉም በክፉም እንዲነሳ አድርጓታል። በተለይም አፄ ፋሲለደስ ከሚሲዮናውያን ጋር የገቡበት እሰጥ-አገባ ጎንደር ከኢትዮጵያ አልፋ በዓለም ላይ ስሟ ደጋግሞ እንዲነሳ አድርጓል።

አፄ ፋሲለደስ ጎንደር የከተማ ቅርፅ እንድትይዝና ዘመናዊ አኗኗር እንድታዳብር ከማድረግ ባለፈ በኪነ-ሕንፃ ተጠቃሽ ከተማ እንድትሆን ብርቱ ጥረት ያደረገ ንጉሥ ነው። በዚህ ጥረቱም ጎንደር እስከ 1855 ዓ.ም. ድረስ የኢትዮጵያ መዲና ሁና እንድታገለግል መሰረቱን ጥሏል። አሁን በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ አስደማሚ የኪነ-ሕንፃ ውጤቶችን በመገንባትም ፈር ቀደጅ ንጉሥ ነበር።

አፄ ፋሲለደስ መዲናቸውን በጎንደር እንዲያደርጉ የተለያዩ ገፊ ምክንያቶች እንደነበሯቸው በጎንደር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ አበበ ታደግ ይናገራሉ። «የጎንደር መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ ራስን ከጠላት ለመከላከል የተመቸ መሆኑ፣ ዙሪያ ገባውን ለመቆጣጠር የሚያስችል አማካኝ ቦታ ላይ መገኘቷ፣ ምቹ የአየር ጠባይ የታደለች መሆኗ፣ ለመጠጥ እና ለንጽህና መጠበቂያ የሚሆኑ ወራጅ ወንዞች እና ምንጮች በብዛት መገኘታቸው፣ ንጉሡ ላሰቡት ግንባታ የሚሆኑ ግብዓቶች በቅርብ መገኘታቸው፣ በወቅቱ ንጉሡ በነበሩበት የጎርጎራ አካባቢ ህዝቡን ካስቸገረው የወባ በሽታ የፀዳ አካባቢ መሆኑና ለንግድ እንቅስቃሴ ምቹ መሆኑ" ከብዙ በጥቂቱ ለከተማዋ መቆርቆር  ምክንያቶች ናቸው ይላሉ የታሪክ መምህሩ።

ጎንደር ከተማ ሁለት ክፍለ-ዘመን በዘለቀ የመናገሻ ከተማነቷ አስራ አራት ነገሥታትን አስተናግዳለች። ጎንደር ከተማ የሚገኙ የወቅቱ የሥልጣኔ አሻራዎች ኪነ-ሕንፃ፣ ኪነ-ጥበብ፣ እደ-ጥበብ፣ የንግድ እንቅስቃሴ፣ ሕግና ስርዓት ማቆም ከተማዋን ዘመናዊ የማድረግ የአፄዎቿ መገለጫዎች ተደርገው ይወሰዳሉ።

ጎንደር ከተማ ታሪክ የማይሽራቸው የጥበብ ውጤቶች መገኛ መሆኗ የቱሪስቶችን ቀልብ በቀላሉ የምትስብ ከተማ አድርጓታል። የታሪክ መምህሩ አቶ አበበ ታደግ የጎንደርን መካነ ቅርስነት ያብራራሉ። "ከተማዋ በጎርጎሮሳዊያን የዘመን አቆጣጠር በ1636 በአፄ ፋሲል የተገነባውን የፋሲል አብያተ መንግሥትን ጨምሮ በርካታ ቅርሶችን በጉያዋ ይዛለች፡፡ የፋሲል ግንብ የሚገኝበት እጥር ግቢ 12 ቢሮዎች፣ 6 አብያተ-ክርስቲያናት ሌሎች በተመሳሳይ የስነ-ሕንፃ ጥበብ የተገነቡ ቀደምት ሕንፃዎችን አካቶ የያዘ ነው፡፡ የአፄ ፋሲል፣ የአፄ ዮሃንስ (ፃዲቁ)፣ የልጅ እያሱ (የአፄ አድያም ሰገድ ልጅ) የአፄ ዳዊት፣ የአፄ በካፋና የእቴጌ ምንትዋብ (ብርሃን ሞገስ)፣ የቋረኛው ኢያሱ ቤተ-መንግሥቶች በውስጡ ይዟል። በሌላ በኩል የአፄ ፋሲል የመዋኛ ገንዳ፣ እቴጌ ምንትዋብ ያስገነባችውና ድንቅ የስነ-ሕንፃ ጥበብ ያረፈባት የቁስቋም ቤተ ክርስትያን፣ አድያም ሰገድ ኢያሱ ያስገነቡትና የኢትዮጵያውያን የስዕል ጥበብ የታየባት ጥንታዊቷ የደብረብርሃን ሥላሴ ቤተክርስትያን፣ አፄ ፋሲል ያሰሯቸው ጎንደርን ከአጎራባች ከተሞች ጋር የሚያናኟት ሰባቱ ድልድዮች፣ የዓባይን መነሻ ለማወቅ በመሻት ጎንደር የከተመው የስኮትላንዳዊው ጀምስ ብሩስ መኖሪያ እና ሌሎች ቅርሶችን አቅፋ የያዘች ድንቅ ከተማ ናት" የታሪክ መምህሩ "ጎንደርን ጎብኝቶ በወርቃማ ዘመኗ የነበረው የኪነ-ሕንፃና ኪነ -ጥበብ የደረሰበትን ደረጃ ተገንዝቦ አለመደመም አይቻልም" ይላሉ። 

ጎንደር ከተማ በአፄ ፋሲለደስ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ከተቆረቆረች ጀምሮ የከተሜነት መለያዎቿ ከፍ በማለቱ "ጎንደር - የከተሞች እናት" ተብላ እስከመጠራት ደርሳለች። ከጎንደር ቀድመው ለተመሰረቱትም ይሁን ከእርሷ ዘግይተው ለተቆረቆሩት የኢትዮጵያ ከተሞች ምሳሌ ሆናለች።

ጎንደር ለሁሉም የምትሆን ከተማ ተደርጋ መመስረቷን ፒያሳ መጽሐፍ ሲገዙ ያገኘናቸው አቶ ማንደፍሮ ገዛኸኝ ይናገራሉ። "በጎንደር የሚገኘው የወለቃ ቤተ-እስራኤላዊያን የእደ-ጥበብ መንደር ጎንደር የሁሉም ከተማ እንደነበረች ጠቋሚ ነው። በዚህ መንደር የሚኖሩ ቤተ-እስራኤላውያን በእደ-ጥበብ ሙያ የታወቁ ሰለነበሩ አፄ ፋሲለደስ ቤተ-መንግሥታቸውን ሲያሰሩ እንደተሳተፉ ይነገራል፡፡

ቤተ-እስራኤላውያን ለጎንደር ሥልጣኔ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበረም የማይዘነጋ ነው፡፡ በሌላ በኩል ጎንደር የሲራራ ነጋዴዎች መዳረሻ የንግድ ማዕከል በነበረችበት ወቅት በርካታ የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች በከተማዋ አዲስ ዓለም በሚባለው የመኖርያ መንደር ይኖሩ እንደነበር ይወሳል፡፡ አዲስ ዓለም በዘመኑ "ነጋድራስ" የሚባለው ማዕረግ የሚሰጣቸው ሰዎች የሚገኙበት የተዋበ ሰፈር እንደነበርም አባቶቻችን ነግረውናል፡፡ ጎንደር ለቀዳሚዎቿም ለተከታዮቿም ኢትዮጵያዊ ከተሞች የከተሜነት ባህሪን ያስተማረች ታሪካዊ ከተማ ነች" በማለት አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ አቶ ማንደፍሮ።

ጎንደር ከተማ በውስጧ ከሚገኙ ድንቅ ታሪካዊ ቅርሶቿ ባሻገር በአቅራቢያዋ በርከት ባሉ የቱሪስት መዳረሻዎች የተከበበች መሆኗ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሌላ ሀገር ዜጎችም በሩቅ የምትናፍቅ ድንቅ ከተማ ነች። የጉዛራ ቤተ-መንግሥት (እንፍራንዝ)፣ የአፄ ሱስንዮስ ቤተ መንግሥት (ደንቀዝ ዛንተራ፣ ጎርጎራ)፣ ደብረሲና-ማርያም (ጎርጎራ)፣ አልጣሽ ፓርክ (ቋራ)፣የሊማሊሞ ሰንሰለታማ ተራራ (ደባርቅ)፣ ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የኮሶየ የተፈጥሮ ገጽታ (Natural Scene)፣ ጣና ገዳማት፣ ደበረ-ምጥማቅ(ደጎማ)፣ ባህሪ ግንብ (ጠዳ) -ጎንደር ዙሪያ፣ ዞዝ አምባ (ሀሙሲት)፣ በአፄ ፋሲል የተሰሩ ጥንታዊ ድልድዮች (ጎባጢት)፣ የጉና ማራኪ የተራራ ገፅታ (ደብረ-ታቦር)፣ ቆማ ፋሲለደስ (እስቴ)፣ የአውራምባ ማኅበረሰብ (ወረታ)፣  ቅዱስ ያሬድ ገዳም፣ ደረስጌ ማሪያም፣ ወርቅ አምባ ፍልፍል ዋሻ፣ ወይ ብላ ማርያም፣ ማኅበረ-ሥላሴ ገዳም ከብዙ በጥቂቱ በጎንደር ዙሪያ የሚገኙ የጎብኝዎችን ትኩረት የሚስቡ መዳረሻዎች ናቸው።

"ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በድምቀት እየተከበረ የመጣው የጥምቀት በዓል የጎንደርንና አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻነት በአወንታዊ መንገድ አሳድጎታል።" የሚለን ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነው ሰለሞን አዲሱ ነው። ሰለሞን "የኮቪድ-19 መከሰትና ወቅታዊው የፖለቲካ ትኩሳት በቱሪዝም ኢንደስትሪው ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተፅዕኖ ቢኖርም ጎንደር አሁንም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኝዎች ተመራጭ ከተማ ከመሆን አላገዳትም።" ይለናል።

ይህ የስህበት ማዕከልነቷ በተለያየ ዘመን በተዋቡ ቃላት ተሞካሽቷል። የዓባይ ወንዝ መነሻውን ለማወቅ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጎንደር ከትሞ የነበረውና በጎንደር ቆይታው መጽሐፈ ሄኖክን ዘርፎ በመሰወር የሚታማው ጀምስ ብሩስ ጎንደርን በገለፀበት መንገድ ነገራችንን እንቋጭ። "ፈረንሳያዊ ሆኖ ፓሪስን ያላየ ኢትዮጵያዊም ሆኖ ጎንደርን ያላየ ከእናቱ ማህፀን ጀምሮ የተረገመ ነው!"

Author: undefined undefined
ጦማሪግዮን ፈንታሁን