ግንቦት 27 ፣ 2013

የባልደራስ እና የምርጫ ቦርድ ውዝግብ ሂደት

ምርጫ 2013ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

‘ነገ ጠዋት ያልቃል’ የሚል ምላሽ አግኝተናል እንግዲህ ነገ ጠዋት ነው የአባሎቻችንን መወዳደር እርግጠኛ ምንሆነው’’ ሲሉ መልሰዋል።

የባልደራስ እና የምርጫ ቦርድ ውዝግብ ሂደት

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ግንቦት 26 2013 ዓ.ም ባስቻለው አንደኛ የምርጫ ጉዳይ ችሎት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮችን በዕጩነት የመመዝገብ ሂደት መጀመሩን አስታውቋል።

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ከፍተኛ አመራሮች፤ ፕሬዚዳንት አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ አስቴር ስዩም፣ ስንታየሁ ቸኮል እና አስካለ ደምሌን በተመለከተ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እጩ እንዳይሆኑ ሰጥቶት የነበረውን ውሳኔ በመሻር በዕጩነት እንዲመዘገቡ ትዕዛዝ መስጠቱ የሚታወስ ነው። በውሳኔው መሰረት ምርጫ ቦርድ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲፈጽም በደብዳቤ የተጠየቀ ቢሆንም ቦርዱ የፍርድ ቤት ውሳኔን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚቸገር እና ተፈጻሚ እንደማያደርግ በደብዳቤ ምላሽ ሰጥቷል።

ይህንን ተከትሎ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሰኞ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን ለምን መፈጸም እንዳልቻለ ሐሙስ ግንቦት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ አዟል፡፡ ለትዕዛዙ መነሻ የሆነው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ ቦርዱ “አልፈጽምም” ማለቱን ገልፆ እስከሚፈጽም ድረስ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲካሄድ የተወሰነው አገራዊ ምርጫ እንዲታገድለት በደብዳቤ አቤቱታ በማቅረቡ መሆኑን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ 

ይህን አቤቱታ ተከትሎ ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. አዲስ ዘይቤያችን ያነጋገራቸው የኢትዮጲያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት ሶሊያና ሽመልስ ምላሽ ሲሰጡ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 39 (3) ሥር ተደንግጎ እንደሚገኘው፣ የፖለቲካ ዕጩን መለወጥ ወይም መተካት የሚቻለው የዕጩ የምዝገባን በተመለከተ የተዘጋጀው የጊዜ ሰሌዳ ካበቃ በኋላ፣ ከድምፅ መስጫው ቀን አንድ ወር በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን አስታውሰው የተወከሉትና መሥፈርቱን የሚያሟሉት ዕጩዎችን ያካተተ የድምፅ መስጫ ወረቀት ህትመት መጠናቀቁን በመግለፅ ቦርዱ እነ አቶ እስክንድርን እንዲመዘግብ የታዘዘውን ለመፈጸም እንደሚያዳግተው አብራርተው ነበር። ዳይሬክተሯ አክለውም ‘’ቦርዱ ይህንን ማብራርያ ለችሎቱ ሰፋ አርጎ ቢሰጥም ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ቀርበው ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲያስረዱ ጠይቋል” ሲሉ ገልፀውም ነበር።

በሌላ በኩል ‘’የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔን አልቀበልም ማለት እንዴት ይታያል?’’ ብለን የጠየቅናቸው የሕግ ባለሙያ ውብሸት ሲመልሱ "በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ያልተባሉ ሰዎችን በወንጀል ተጠርጥረው በማረፊያ ቤት ስላሉ ብቻ ‘የምርጫ ተወዳዳሪ እጩ አድርጌ አልመዘግብም’ ማለቱና ‘የመምረጫ ካርዶችን ስላሳተምኩ’ ሚል ምክንያት መስጠቱ  ከሕግ አተረጓጎም አንጻር ግር ያሰኛል። እንደ ክሱ ጥፋተኛ ተብለው እስራት ከተፈረደባቸው (ከታሠሩ) እና በምርጫ ውድድሩ አሸንፈው የምክር ቤት አባል ከኾኑ፣ ሕጉ ግልጽ መፍትሔ አለው - የማሟያ ምርጫ። ምርጫ ቦርድም ማድረግ ያለበት ይሔንኑ ነው። የማሟያ ምርጫ የምክር ቤት አባል የኾነ ሰው በሞት ሲለይ፣ በወንጀል ተከሶ ሲታሠር፣ ውክልናው ሲነሳ ወዘተ እንደሚደረግ ሕጉ ይደነግጋል።’’ ሲሉ የሕግ ባለሙያ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አቶ ያሬድ ኃ/ማርያም በበኩላቸው “እርግጥ ነው ቦርዱ በርካታ ዝግጅቶችን ባጠናቀቀበት በዚህ ወቅት የሚነሱ አዳዲስ ጉዳዮች ችግር ይፈጥሩበት ይሆናል። ሆኖም ይህን ለፍርድ ቤት አስረድቶ ወሳኔው ላይ በክርክር ወቅት ዳኞችን ማሳመን ሳይችል ቀርቶ በሰበር ችሎት ከተወሰነበት በኋላ ግን የፍርድ ቤቱን የመጨረሻ ውሳኔ አልቀበልም ማለት አይችልም። እንዲህ ያሉ ምላሾች ነገ ከምርጫው ጋር በተያያዘ አለመግባባቶች ቢፈጠሩ ወደየትኛው አካል ሊኬድ ነው የሚል ጥያቄ ማስነሳታቸው ስለማይቀር በደንብ ሊታይ ይገባል።’’ ብለው ነበር። 

           ይህንን እና መሰል ውዝግቦችን ሲያስነሳ የቆየው ክርክር በዛሬው ችሎት ምላሽ አግኝቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ለችሎቱ እንደተናገሩት የባልደራስ ፓርቲ ቀደም ሲል አስመዝግቧቸው በነበሩ ዕጩዎች ምትክ ለምርጫ እንዲቀርቡለት የሚፈልጋቸውን ግለሰቦች እንዲያሳውቅ በተቋማቸው በኩል ጥያቄ ቀርቦለት ማሳወቁን ገልፀዋል፡፡ የባልደራስ ፓርቲ ጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ በበኩላቸው ይህንኑ ለፍርድ ቤቱ ሲያብራሩ ‘’ምርጫ ቦርድ የዕጩዎችን ምዝገባ ለመፈጸም እንዲያስችለው ባልደራስ በተተኪነት የሚያቀርባቸውን ዕጩዎች ፎቶግራፎች እንዲያቀርብ ተጠይቆ ለቦርዱ መስጠቱን” አሳውቀው ‘’ሆኖም ማረጋገጥ የምንችለው የዕጩዎችን ሰርተፊኬት ስንቀበል ነው” ብለዋል።

“የዕጩዎች ሰርተፊኬት የመስጠት ሂደት ቦርዱ በ30 ደቂቃ ማከናወን የሚችለው ነገር ነው። ነገር ግን አላደረገውም” ሲሉ በችሎቱ ማብቂያ ላይ ለፍርድ ቤቱ ቅሬታቸውን ያሰሙትን የፓርቲውን ጠበቃ አቶ ሔኖክ አክሊሉ ያገኙትን ምላሽ ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ የዕጩዎች ሰርተፊኬት የመስጠት ሂደት በምን ያህል ጊዜ ሊያልቅ ይችላል ብሎ ፍርድ ቤቱ  የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋን መጠየቁን እና  ‘ነገ ጠዋት ያልቃል’ የሚል ምላሽ አግኝተናል እንግዲህ ነገ ጠዋት ነው የአባሎቻችንን መወዳደር እርግጠኛ ምንሆነው’’ ሲሉ መልሰዋል።

ከዚሁ ጋር አያይዞ ቦርዱ የፓርቲው አመራሮች ለሚወዳደሩባቸው ቦታዎች፤ ቀደም ሲል አሳትሟቸው የነበራቸውን ወደ 1.3 ሚሊዮን የሚጠጉ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እንዲቃጠሉ ትዕዛዝ ማስተላለፉንም ገልጿል። 

አዲስ ዘይቤ ‘’ይህ ውሳኔ ከምርጫው ቀን ጋር በተያያዘ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ይኖራል ወይ?’’ ስትል ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርባ ‘’ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ አውጥተን ይህን ውሳኔ ተፈፃሚ ስናደርግ ይህን እና መሰል የምርጫ ሂደቶች የማይስተጓጎሉበትን ሁኔታዎች ታሳቢ በማድረግ በመሆኑ እንዲህ አይነት ስጋት የለም’’ የሚል ምላሽ አግኝታለች።

አስተያየት