ግንቦት 17 ፣ 2013

የባልደራስ አመራሮች እስር ቤት ሆነው የምረጡኝ ዘመቻ ማካሄድ እንዲችሉ ፍርድ ቤትን ፈቃድ ጠየቁ

ምርጫ 2013ወቅታዊ ጉዳዮች

የፖርቲውን የሕዝብ ግንኙነት አዲስ ዘይቤ አነጋግሯል።

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

የባልደራስ አመራሮች እስር ቤት ሆነው የምረጡኝ ዘመቻ ማካሄድ እንዲችሉ ፍርድ ቤትን ፈቃድ ጠየቁ

ግንቦት 16 2013 ዓ.ም የሰበር ሰሚ ችሎት በእስር ላይ የሚገኙትን የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ከፍተኛ አመራሮች በመጪው ሀገራዊ ምርጫ በዕጩነት ተመዝግበው መወዳደር እንደሚችሉ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ በዛሬው የችሎት ውሏቸው ካሉበት እስር ቤት ሆነው የተለያዩ የምርጫ ቅስቀሳ ሂደቶችን እንዲያደርጉ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ጠየቁ።

አመራሮቹ ጥያቄውን ለፍርድቤት ያቀረቡት በአቶ ስንታየሁ ቸኮል አማካይነት ሲሆን፤ የፖርቲው የሕዝብ ግንኙነት ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት አመራሮቹ የጠየቁት ከእስር ቤት ሆነው መግለጫዎች እንዲሰጡ እና የተለያዩ የቅስቀሳ ወረቀቶችን እንዲበትኑ እንዲፈቀድላቸው ነው፡፡ በጥቅሉ “ከውስጥ ወደ ውጭ” በተወካዮቻቸው በኩል የምርጫ ቅስቀሳዎችን እንዲያደርጉ ነው ብለዋል፡፡

ጥያቄውን ያቀረቡት እስክንድር ነጋን ጨምሮ የአምስት ተከሳሾችን መደበኛ የክርክር ሂደትን ለመመልከት ለተሰየመው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ-ሽብር እና ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ነው።

ችሎቱ በዛሬ ውሎው በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የተቆጠሩ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን የአሰማም ሂደት በሚመለከት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ተመልክቶ ሂደቱን ለመወሰን እንደተሰየመ ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ግንቦት 4 በዋለው ችሎት፤ የዐቃቤ ሕግ በምስክሮች ላይ ይደርሳል የሚላቸውን ተጨባጭ የደህንነት ስጋቶች ለከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ጉዳዩ ክርክር እንዲደረግበት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ የከፍተኛው ፍርድ ቤት በዛሬው ውሎው፤ የዐቃቤ ሕግ የደህንነት ስጋቶች የሚላቸውን በሬጅስትራር በኩል ሐሙስ ግንቦት 19 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲያቀርብ እና ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ የሚያስገባው ማመልከቻ የሚደርሳቸው የተከሳሽ ጠበቆች ደግሞ መልሳቸውን ለሰኞ ግንቦት 23 አዘጋጅተው ለችሎት እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ቀጠሮ በመሰጠቱ ቅር የተሰኙት የተከሳሽ ጠበቆች፤ በቀላል ነገሮች ቀጠሮ እየበዛ ተከሳሾች እየተጉላሉ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። “ስንጠብቅ የነበረው ክርክር እናደርጋለን ብለን ነበር” ሲሉም ተደምጠዋል። ነገር ግን ፍርድ ቤት ሁለቱም ወገኖች በትዕግስት እንዲጠብቁ ጠይቆ ጉዳዩን በአጭር ጊዜ ይቋጫል ሲል ለጠበቆች ቃል ገብቷል።

በዛሬው የችሎት ውሎ ላይ አራቱም የባልደራስ ተከሳሽ አመራሮች በአካል መገኘታቸውንና አመራሮቹን ወክለው የተናገሩት አቶ ስንታየሁ ቸኮል፤ ፍርድ ቤቱ ይሄን ሁሉ ጊዜ እነሱን ለማዳመጥ ለሚያደርገው ጥረት ምስጋና ማቅረባቸውን አዲስ ዘይቤ ማጣራት ችላለች።  

“ለብዙ ጊዜ የተገፋውን የአዲስ አበባ ህዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ በመረጠው እንዲተዳደር የበኩላችሁን እንድትወጡ ስንል እንጠይቃለን” በማለት አቶ ስንታየሁ በርከት ያሉ የፓርቲያቸው ደጋፊዎች በተገኙበት ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ችሎቱ ተጠናቅቋል።

አስተያየት