ነሐሴ 14 ፣ 2013

የወጣቶች መዝናኛ የሌላት ከተማ

City: Dire Dawaማህበራዊ ጉዳዮች

በርካታ ነዋሪዎቿ የትላንት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዋን ከዛሬ ጋር በማነጻጸር “ድሬዳዋ አንቀላፍታለች” ይላሉ፡፡ ለአባባላቸው በማስረጃነት የሚጠቅሱት የበርካታ ፋብሪኮች መገኛና ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ መናኸሪያ እንደነበረች በመጥቀስ ነው፡፡

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

የወጣቶች መዝናኛ የሌላት ከተማ

በርካታ ነዋሪዎቿ የትላንት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዋን ከዛሬ ጋር በማነጻጸር “ድሬዳዋ አንቀላፍታለች” ይላሉ፡፡ ለአባባላቸው በማስረጃነት የሚጠቅሱት የበርካታ ፋብሪኮች መገኛና ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ መናኸሪያ እንደነበረች በመጥቀስ ነው፡፡ ከ70 ዓመታት በላይ በከተማዋ የኖሩት ወ/ሮ ዋጋዬ ከበደ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡትም ሆነ ተወልደው ያደጉባት ወጣቶች የነበራቸውን የሥራ ቅልጥፍና አንስተው አይጠግቡም፡፡ “ጊዜው ወጣቶች በሱስ ያልናወዙበት ነው፡፡” የሚሉት አዛውንቷ “ድሬዳዋ ንጹህ፣ ለሥራ እና ለለውጥ ተጉዘው ጥሪት የሚጨብጡባት፣ በማስተር ፕላን የተገነባች ነበረች” በማለት ትላንትን ያስታውሳሉ፡፡ ምስል ከሳች ገለጻቸው ዓመታትን ወደ ኋላ አስጉዞ ደማቁን የከተማዋን እንቅስቃሴ እና የቀልጣፋ ወጣቶቿን ትጋት በዐይነ ህሊና ያስቃኛል፡፡  

የከተማዋ በጎ ገጽታ በአብዛኛው አሁን የለም፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ባለው የሥራ አጥ፣ የነዋሪ እና የሱሰኛ ትውልድ ተተክቷል፡፡ ሞቃታማ የአየር ንብረቷ እና ነዋሪዎቿ የሚከተሉት ቀላል የአኗኗር ዘይቤ ሱስና ሱሰኝነት ለመስፋፋቱ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ የሚጠቅሱ በርካቶች ናቸው፡፡ በተጨማሪነትም ወጣቶች ጤናቸውን ጠብቀው፣ እውቀትና ችሎታቸውን እያዳበሩ ጊዜ የሚያሳልፉበት ከሱስ የጸዳ አካባቢ አለመኖሩ ዋነኛው ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ ለኢኮኖሚው መዳከም ደግሞ የባቡር አገልግሎቱ መቋረጥ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ቀደምት ነዋሪዎቿ ይናገራሉ፡፡

ለዚህ ዘገባ ያነጋገርናቸው ወጣቶች በሚኖሩባት ድሬዳዋ ከተማ ከሦስት የማይበልጡ ጤናማ መዝናኛዎች እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ ወጣቶቹ ከጠቀሷቸው ጤናማ መዝናኛዎች ውስጥ “ፓፓ” አንዱ ነው፡፡ ፓፓ እንደ ‘ፑል’ እና ‘ጆተኒ’ ያሉ የቤት ውስጥ መጫወቻዎች ያሉት የወጣቶችና የሕጻናት የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ መዝናኛ ነው፡፡ በቅርብ ሳቢያን ማደያው አካባቢ 02 ቀበሌ የተከፈቱት ሁለት “ጌም ዞኖች”ም ወጣቶች ለሱስ ተጠቃሚነት ሳይጋለጡ የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉባቸው መዝናኛዎች እንደሆኑ ነግረውናል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ነዋሪዎቿ ሥራ አጥ ለሆኑባት ከተማ በሦስት የመዝናኛ ስፍራዎች ብቻ የተገደበችበትን ምክንያት ጠይቀናል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ጌቱ ተገኝ በከተማዋ 38 ቀበሌዎች የሚገኙባቸውን አራት የገጠር ክላስተሮችን ጨምሮ በ9 ቀበሌዎች በድምሩ 17 ለወጣቶች መዝናኛ እንዲሆኑ የተሰናዱ ወጣት ማዕከላት ስለመኖራቸው ይናገራሉ፡፡ “ይሁን እንጂ” ይላሉ ኃላፊው “ይሁን እንጂ አብዛኛዎቹ በአሁን ሰዓት አገልግሎት አይሰጡም፡፡ በተቻለ መጠን በየቀበሌው በሚገኙት ወጣት ማዕከላት አስፈላጊ ግብአቶችን ለማሟላት ጥረት ተደርጓል፡፡ የተጓደሉትን ቁሳቁሶች ለማሟላትም እቅድ ተይዟል” ብለዋል፡፡ የተወሰኑት ወጣት ማዕከላት የኢንተርኔት አገልግሎት፣ ፑል፣ ዴስ-ቲቪ፣ መጽሐፍት እንደሚገኙና ቀበሌ 05 ውስጥ ያለው ሁለገብ የወጣቶች ማዕከል አሁንም አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ነግረውናል፡፡ የቀበሌ 03 ወጣት ማዕከል ደግሞ 1 ቴሌቪዥን እና 40 መጻሕፍት መሰረቁን ጠቅሰው ወጣቱ ንብረቶቹ የራሱ መገልገያዎች መሆናቸውን አውቆ እንዲጠብቃቸው አጋጣሚውን ተጠቅመው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ወጣቶች ስልቹነት የሚያጠቃቸው፣ አዳዲስ ነገሮችን የሚፈልጉ እንደመሆናቸው ባህርያቸውን ያገናዘበ መዝናኛ እንደሚያስፈልጋቸው የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ ወጣቶችን ታሳቢ አድርገው የሚንቀሳቀሱ መዝናኛዎች በየጊዜው ራሳቸውን የሚያሻሽሉ መሆን ይገባቸዋል፡፡

የመኖርያ ሰፈሩ በድሬዳዋ ከተማ ፖሊስ መሬት አካባቢ የሆነው ወጣት መኮንን ኃይሌ የመዝናኛ ሥፍራዎች ጊዜ ማሳለፊያ ብቻ ተደርገው መታሰባቸው ስህተት እንደሆነ ያምናል፡፡ እንደ ወጣቱ ገለጻ የመዝናኛ ስፍራዎች ወጣቶችና ሕጻናት የነገ ተሰጥኦአቸውን የሚፈልጉበት መሆን ይገባዋል፡፡ “በሌሎች የዓለም ሀገራት ወጣቶች ፈጠራዎቻቸውን የሚያሻሽሉባቸው፣ ከመደበኛው ትምህርት ባሻገር ያሉ የግል ተሰጥኦዎቻቸውን የሚያዳብሩባቸው መዝናኛዎች አሉ፡፡ የእኛ ሐገሩ የትም ብትሄድ ተመሳሳይ ነው፡፡ እንደ መዝናኛ የሚቆጠረው ፑል፣ ኳስና ጌም ነው” ይላል፡፡ ተወልዶ ያደገባትን ድሬዳዋ ከተማን እድገትና የመዝናኛ አማራጮቿን አስመልክቶ የቀረበለትን ጥያቄ ሲመልስ የከተማዋን የቀድሞ ዘመናዊነት በማስቀደም ነው፡፡

“ከጅቡቲ የሚመጣውን የባቡር መስመር ተከትሎ የተመሰረተችው ድሬዳዋ ከፍ ያለ የንግድ እንቅስቃሴ ነበራት፡፡ ድሬዳዋ እና ኤርትራ ራሳቸውን ለመለወጥ የሚፈልጉ ሰዎች ለሥራ ፍለጋ የሚመርጧቸው ነበሩ፡፡ ከተማዋ ወደ ላይ ማደጓን አቁማ ወደታች ማደግ የጀመረችው ይህ እንቅስቃሴ ሲቋረጥ ነው፡፡ የወጣት ነዋሪዎቿ ቁጥር መብዛት፣ የብዛታቸውን ያህል የትምህርትና የመዝናኛ አማራጮች አለመኖር፣ ሞቃታማ መሆኗ ደግሞ የሱሰኛውን ቁጥር እንዲጨምር አድርጎታል ብዬ አምናለሁ” ብሎናል፡፡ እንደ ወጣት መኮንን ማብራሪያ እንደ ሌሎች የሐገሪቱ ከተሞች የሆቴል፣ የሪዞርት እና ሌሎች ጊዜ ማሳለፊያ እና ማረፊያ ቦታዎች ቁጥር ማነስ ኢኮኖሚውን ብቻ ሳይሆን የወጣቱን ሞራልም አዳክሟል፡፡ ሁኔታው ከስራ አጥነት እና ከወጣቶች መዝናኛ እጥረት ጋር ሲዳመር ወጣቱ ሱሰኛ ቢሆን አስገራሚ እንደማይሆን ያብራራል፡፡

ጽጌ ገብረየስ የተባለችው ከድሬዳዋ ከተማ ተወልዳ ያደገች የ23 ዓመት ወጣትም በመኮንን ኃይሌ ሐሳብ ትስማማለች፡፡ ድሬዳዋ ከተማን ተከትለው የተቆረቆሩ በእድሜ የሚያንሷት ሌሎች ከተሞች እድገት ከድሬዳዋ ሊበልጥ የቻለበት ምክንያት ብላ ያስቀመጠችው የነቃ እና ከሱስ የጸዳ ትውልድ ለማፍራት የሚሆኑ የመዝናኛ ሥፍራዎችና የሥራ አማራጮችን ማነስ ነው፡፡ በተከታይነትም “ነፍስ ካወቅኩ ጀምሮ ያየኋቸው አመራሮች ወጣቱን ምርታማ ለማድረግ በሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ላይ ሲሳተፉ አላጋጠመኝም” በማለት ሐሳቧን ትደመድማለች፡፡

የስነ-ልቦና ባለሙያዋ ዮርዳኖስ ደስታ “መዝናኛ እንደየሰዉ ፍላጎት፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ሐይማኖት፣ የትምህርት ደረጃ እና ሌሎችም በርካታ ምክንያቶች ይለያያል” ትላለች፡፡ ነገሯን በምሳሌ ስታስረዳ “ለምሳሌ እግርኳስ በርካታ የዓለም ሰዎች የሚከታተሉት መዝናኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እግርኳስ የማያዝናናቸው ወይም የማይወዱ ሰዎችም አሉ፡፡ መጽሐፍ፣ ፊልም፣ የእግር ጉዞ፣ ሙዚቃ፣ ጸጥታ፣ ከሰዎች ጋር ማውራት፣ ማብሰል በጣም ብዙ ነው፡፡ ሁሉም እንደ ባህሪው እና ፍላጎቱ የሚዝናናበት ነገርም ይለያያል” ብላናለች፡፡ ሁሉንም ሰው መቶ በመቶ የሚያስደስት መዝናኛ ቦታ መክፈት አዳጋች መሆኑን ያነሳችው ባለሙያዋ አማራጮች መኖር እንዳለባቸው ታስቀምጣለች፡፡ መዝናኛ ሥፍራዎች ሁሉ ተመሳሳይ ገጽታ እና ይዘት ከሚኖራቸው ይልቅ ልዩ ልዩ ቢሆኑ ለተጠቃሚዎች ምርጫ ብቻ ሳይሆን አማራጭም መሆን ይችላሉ የሚል ሐሳቧን አጋርታናለች፡፡

 “መዝናናት ማለት አካላችንም ሆነ አዕምሮአችን እረፍት የሚያገኝበት መሆን አለበት፡፡ ጤናማ ያልሆኑ ልክ እንደጫትና መጠጥ ያሉ የመዝናኛ ዓይነቶች በማግስቱ ሙሉ ለሙሉ የእረፍት ስሜት እንዲሰማን የማያደርጉ ጤናማ ያልሆኑ የመዝናኛ ዓይነቶች ናቸው፡፡ በከተማችን ድሬደዋ ጤናማ የሚባሉ የመዝናኛ ዓይነቶች በሚፈለገው ብዛትና የጥራት ደረጃ ቢነር ኖሮ ወጣቱ አማራጭ ስለሚያገኝ ሱስ በሚያስይዙ የመዝናኛ ዓይነቶች የመጠመድ እድሉ ይቀንስ ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ወጣቱ ጤናማ የሆኑ መዝናኛ ስፍራዎችን ባለማግኘቱ ከኅብረተሰቡ ያገኛቸውን የመዝናኛ መንገዶች እንዲመርጥ ያደርገዋል፡፡” ስትል ገልጻለች፡፡ 

 “ናሳ (NASA) በፈጠራ ችሎታ ላይ ለረጅም ጊዜያት ባደረገው ጥናት (Longitudinal test) መሰረት ቁጥራቸው 1,600 የሚሆኑ እና እድሜያቸው በ4 እና 5 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ህፃናት መካከል 98% የሚሆኑት “የፈጠራ ክህሎት” (”Creative genius”) እንዳላቸው የጥናቱ ውጤት ሲጠቁም እነዛው ህፃናት ላይ ከአምስት ዓመት በኋላ በተደረገ ጥናት ደግሞ 30%ቱ ብቻ ተመሳሳይ ደረጃ ያለው ውጤት ያስመዘገቡ መሆኑ ተገልጿል፣ እንደገና ከአምስት ዓመት በኋላ በተደረገ ጥናት ደግሞ 12%ቱ ብቻ ናቸው የፈጠራ ክህሎት እንዳላቸው የተረጋገጠው፡፡ ይሄው ጥናት በተመሳሳይ በአዋቂዎች ላይ ሲሰራ 2%ቱ ብቻ ከፍተኛ የፈጠራ ክህሎት ደረጃ ላይ እንዳሉ ለማወቅ እንደተቻለ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡

ይህ 98% የነበረው “የፈጠራ ክህሎት” ወዴት የሄደ ይመስላችኋል ህፃናት እድሜያቸው 17 ዓመት እስከሚደርስ ድረስ ከማኅበረሰቡ በሚደርስባቸው (ቤተሰብንም ይጨምራል) ጫና ይቀበራል እንጂ፤ ይህም ማለት 150,000 ጊዜ አሉታዊ ቃላቶችን (እንቢ፣ ተው፣ ተቀመጥ፣ አይቻልም፣ አይሆንም…ወዘተ) ሲሰሙ በተቃራኒው አዎንታዊ ቃላቶችን (እሺ፣ አድርግ፣ ተጫወት፣ ውሰድ…ወዘተ) 5,000 ግዜ ብቻ በዙሪያቸው ካሉ ቤተሰብ፣ መምህራን በአጠቃላይ ከማኅበረሰባቸው መስማት የሚችሉት፡፡ 

‹‹ስለዚህም ወጣቶችም በአቅሪያባቸው ጤናማ መዝናኛዎች ካልኖሩ ማኅበረሰቡ ያቀረበላቸውን የመዝናኛ መንገዶች ይጠቀማል›› ትላለች የስነ ልቦና ባለሙያዋ ዮርዳኖስ። 

የድሬደዋ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ሰሚራ ሁሴን ሱስ ወደሚያስይዙ የመዝናኛ ዓይነቶች ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሊገቡ እንደሚችሉ ትናገራለች። ከነዚህም መካከል ወጣቶች በተለያዩ ምክንያቶች ድብርት ውስጥ በሚገቡበት ወቅት ከድብርት ለመላቀቅ መዝናናትን ስለሚመርጡና መዝናኛዎቹ በየጊዜው እራሳቸውን የሚያዘምኑ እና ወጣቶችን ሊስቡ የሚችሉ የመዝናኛ ስፍራዎችን ካላገኘ ማኅበረሰቡ ውስጥ በስፋት የሚገለገሉበትን የመዝናኛ ዓይነት እንደ አማራጭ እንዲወስደው ሊያደርገው ይችላል ስትል ሀሳቧን ታጋራለች፡፡ 

በአንድ ወቅት በምስራቅ አፍሪካ ከ500 ሺ ሰዎች በላይ በጫት ንግድ ተሰማርተው ይገኛሉ የሚል መረጃ እንዳገኘች የገለፀችው ሰሚራ ይህ ሁሉ ሰው በዚህ የንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩት ብዙ ደንበኛ ቢኖራቸው ነው እንደሀገርም ስለመዝናናት ያለን አመለካከት የተንሻፈፈ ስለሆነ ነው ብላ ታምናለች፡፡ 

“የመዝናኛ ማእከሎች ስፖርትን፣ ቴክኖሎጂን እና መጽሐፍትን የመሳሰሉ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያማከለና ከጊዜው ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል መሆን አለበት” ስትል ሰሚራ ሀሳቧን አብራርታለች፡፡ 

ወ/ሮ ትግስት ከበደ የነምበርዋን ነዋሪ በአካባቢዋ ስለነበረው የወጣት ማእከል ስታብራራ በፊት ላይብረሪ፣ፑልና ጆተኒ የተሟሉለት እንደነበርና ወጣቶችም በሚገባ ይጠቀሙበት እንደነበርና በአሁን ሰአት ግን ተዘጋግቶ ለወጣቶች ያን ያህል አገልግሎት እንደማይሰጥ ትናገራለች፡፡

ህይወት ካሳሁን የተባለች የድሬደዋ ነዋሪ እንደሀገር የመዝናኛም ሆነ የሁሉም ነገር ማእከል አዲስ አበባ ብቻ እንደሆነችና በክልሎች የስራ እድልና የመዝናኛ ማእከላትን ለማግኘት ከባድ ስለሆነ እነዚህን ነገሮች ለማግኘት በብዛት ወጣቶች ወደአዲስ አበባ እንዲፈልሱ ያደርጋቸዋል ትላለች። 

አብዛኛው የድሬደዋ ወጣት ዩንቨርሲቲ ገብቶ ሲወጣ ስራ ለመፈለግ ወደአዲስ አበባ ይጓዛል ምክንያቱም የተሻለ የስራ እድል የሚገኘው እዛ ነው ለመዝናናትም ቢሆን የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ መዝናኛዎች በድሬደዋ ውስጥ ውስን እንደሆኑ ገልፃለች ህይወት፡፡

ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ሰዎች ለተለያዩ ክበባት ትኩረት መስጠት ቢችሉ፣ ሱስ ውስጥ የገባ ሰው ህክምና የሚያገኝበት እና ከሱስ እንዲወጣ የሚደረግበት መንገድ ትኩረት ቢሰጠው፣ ለቲያትር፣ ለስፖርት እንዲሁም በየቀበሌው የሚገኙ ወጣት ማዕከሎችን ከጊዜው የሚራመድና ወጣቱን ሊስብ የሚችል እንዲሁም ወጣቱን በዕውቀት ሊገነባ የሚችል እንዲሆን ትኩረት ሰጥተው ቢሰሩበት መልካም ነው ሲል ሀሳቡን የገለፀው ምትኩ ዓባይነህ የተባለ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ነው፡፡ 

በቀጣይ ወጣት ማዕከሎቹ የወጣቱ እንደሆኑ እንዲያስብና ከወጣቱ እኩል የሚራመድ ወጣት ማዕከልን ለመገንባት ከወጣት ማኅበር እንዲሁም ከወጣቶች ሊግ ጋር በአንድነት ለመስራት እንደታሰበ የሚናገሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ተገኝ ናቸው፡፡ አቶ ተገኝ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ የመዝናኛ ማዕከላቱን ሥራ ከማስጀመር ባለፈ አካባቢያቸውን ሳቢ ከማድረግ አንጻር ብዙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

አስተያየት