መጋቢት 22 ፣ 2015

በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን የፀጥታ ስጋት በመኖሩ ከድሬዳዋ ወደ ጅቡቲ የሚወስደው አስፓልት መንገድ ተዘጋ

City: Dire Dawaፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮችንግድ

በአካባቢው በተፈጠረ አለመረጋጋትና የሰላም እጦት ሳቢያ ከድሬደዋ ወደ ጅቡቲ የሚወስደው መንገድ በመዘጋቱ በእለት ተእለት ህይወታቸው ላይ ከፍተኛ ጫና መፈጠሩን የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን የፀጥታ ስጋት በመኖሩ ከድሬዳዋ ወደ ጅቡቲ የሚወስደው አስፓልት መንገድ ተዘጋ
Camera Icon

ምስል ኢትዮ ስፖርትስ

“ከጅቡቲ ወደብ ጋር የሚያገናኘውን የአስፓልት መንገድ ለመዝጋት እና ሁከት ለመፍጠር ሙከራዎች ተደርገዋል” በሚል የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ የሦስት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ከ10 በማያነሱት ላይ ደግሞ ከባድ የመቁሰል አደጋ መድረሱን በስልክ ያነጋገርናቸው የአይሻ ከተማ ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

ይህንን ተከትሎም በዞኑ አብዛኛው አካባቢዎች ውጥረትና አለመረጋጋት በመፈጠሩ ከድሬዳዋ ወደ ጅቡቲ የሚወስደው አስፓልት መንገድ መዘጋቱን አዲስ ዘይቤ ከአካባቢው ማህበረሰብ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

“ተወልደን ካደግንበትና በቋሚነት ከምንኖርበት መፈናቀላችን አግብባ አይደለም” ሲሉ አስተያየታቸውን ለአዲስ ዘይቤ የገለፁት አቶ ጣሂር ዲረኔ የተባሉ ነዋሪ “የአፋር ክልል ከተሞች ከሆኑት ከገርበኢሴ፣ ኡንድፎ እና አደይቱ ከተሞች በታጠቁ ኃይሎች በደረሰባቸው ጥቃት ወደ ሲቲ ዞን መሰደዳቸውን” ይገልፃሉ።

በእንስሳት የግጦሽ ሳርና በውኃ ሳቢያ ይከሰት የነበረው ግጭት ተባብሶ የሰብዓዊ ቀውስ እያስከተለ የሚገኝ ሲሆን ለበርካታ ንፁሀን ዜጎች ግድያ፣ አካል ጉዳት እና ዝርፍያ ምክንያት መሆኑንም ተፈናቃዬች ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል። “በአይሻ ከተማ በጊዜያዊነት የተጠለሉ በሺዎች የሚገመቱ ተፈናቃይ ወገኖች እየደረሰባቸው ያለው ጥቃት እንዲቆም” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። 

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ቀን ድረስ “መንገዱ ከተዘጋ ከስድስት ቀናት” ማለፉን ጠቅሰው ይህም ከድሬዳዋ ወደ ደወሌ በየዕለቱ አትክልት እየወሰዱ በመሸጥ በሚተዳደሩ ሰዎች ላይ ጫና እንደፈጠረባቸው ወ/ሮ ለይላ ዱሬ የተባሉ ነጋዴ ለአዲስ ዘይዜ ገልፀዋል።

ለሲሚንቶ ማምረቻነት የሚያገለግል ማዕድን ግብዐት በምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ ለሚገኙ ፋብሪካዎች የሚያቀርቡት አቶ ኢዲሪስ አደን ሸረዋ በበኩላቸው “በዞኑ በተከሰተው ግጭትና የሰላም እጦት ሳቢያ” በስራቸው ላይ ከፍተኛ መስተጓጎልና ኪሳራ እያጋጠማቸው እንደሆነ ነግረውናል።

ስማቸው እንዲገለፅ ፈቃደኛ ያልሆኑና በሲቲ ዞን የሚንቀሳቀሰው የሳርዳ የፖለቲካ ፓርቲ የቀድሞ ከፍተኛ አመራር እንደሚሉት ደግሞ “በዞኑ የሰው ህይወትን የሚቀጥፉ ግጭቶች መደጋገም፣ ከፍተኛ ጥፋትን የሚያስከትሉ አለመረጋጋቶች መስተዋል እና በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጭንቀት መብዛት ከምጣኔ ሀብታዊና ከማኅበራዊ ጫና በዘለለ ከባድ ሀገራዊ ፈተናዎችን ሊያስከትል ይችላል” ሲሉ ስጋታቸውን ለአዲስ ዘይቤ አጋርተዋል።

በሶማሌ ክልል ከሚገኙት 11 ዞኖች አንዱ የሆነው የሲቲ ዞን 12 ወረዳዎች ያሉት ሲሆን ዞኑ ከአፋር ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ከረጅም ጊዜ አንስቶ በሁለቱ ክልሎች በሚገኙት አርብቶ አደር ህዝቦች መካከል በግጦሽና በውሃ ሀብት ይገባኛል ጥያቄዎች ሳቢያ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ሲቀሰቀሱ መመልክት አዲስ አለመሆኑን ከአካባቢው ነዋሪዎች ያገኘናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።

አስተያየት