የዋጋ ተመንና ቁጥጥር ያልበገረው የድሬዳዋ ኑሮ ውድነት

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራውነሐሴ 28 ፣ 2013
City: Dire Dawaኢኮኖሚ
የዋጋ ተመንና ቁጥጥር ያልበገረው የድሬዳዋ ኑሮ ውድነት
Camera Icon

Illustration: Addis Zeybe

በሁለት አሃዝ ሲንከባበል የከረመው የዋጋ ንረት በባለፈው ወር 26.4% በማስመዝገብ በባለፉት ዓመታት ከተመዘገቡት አሃዞች ከፍተኛው ደረጃ ላይ ደርሷል። በመላው ኢትዮጵያ በሸቀጦች ላይ ዕየታየ ያለው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የግለሰቦች፣ ከፍ ሲልም የባለሙያዎችና የመንግሥት ስጋት ሆኗል።

ክስተቱን ከወቅታዊው ፖለቲካዊ ሁነት ጋር የሚያገናኙት በርካታ ናቸው። ዊንስተን ቸርቺል “ፖለቲካ ጨዋታ አይደለም፤ ኃይለኛ ቢዝነስ እንጂ” ያለውን ለዚህ አባባላቸው በማጣቀሻነት ያቀርባሉ። “ትልቁ ኃይል የገንዘብ ኃይል አይደለም፤ የፖለቲካ ኃይል እንጂ” የሚለው ደግሞ ዋልተር አኔንበርግ ነው፤ የፖለቲካው አለመረጋጋትና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ግጭት ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ዋነኛ ምክንያት እንደሚሆን የፖለቲካ ምሁራን በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡

በድሬደዋ ዩንቨርሲቲ ፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና ተመራማሪ አቶ ሱራፌል ጌታሁን ‹‹የሀገር ውስጥ ግጭት ከኑሮ ውድነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው›› ይላሉ፡፡ አያይዘውም በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነት ሰው ሰራሽ ሊሆን እንደሚችል ይገልፃሉ፡፡ በግጭት ወቅት የኑሮ ውድነት የሚጠበቅ ቢሆንም በዚህ መንገድ አይደለም ባይ ናቸው፡፡

“የሸቀጦት ዋጋ እለት በእለት በሚያሻቅብበት በዚህ ወቅት እየጨመሩ ለሚገኙት ሸቀጦች መለያ/ዘርፍ ማበጀት ከባድ ነው፡፡ ግጭቱ ከሚገኝበት አካባቢ ውጭ የሚመረቱ፣ ከውጭ ሐገራት የማይመጡ፣ የትራንስፖርት እጥረት በሌለበት ሥፍራ የሚገኙ፣… እነዚህ ሁሉ ተወደዋል፡፡ ‹ይህ ስለሆነ ይህ ሆነ› ለማለት የሚያስችል ሁኔታ የለም፡፡ አሁን ላይ ልንደርስበት የምንችለው ድምዳሜ ‹‹ሁኔታው ሰው ሰራሽ ነው›› የሚለውን ብቻ ነው፡፡ ባንኮች የማይንቀሳሰሱ ንብረቶችን ይዘው ማበደር ሲያቆሙ የዶላር የጥቁር ገበያ ዋጋ መቀነሱ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡

"ሰው በኢኮኖሚ ሲዳከም የመኖርያ መንደሩን ጥሎ ይወጣል። እንደዚህ ዓይነቱ ከስተት ደግሞ በከተሞች ላይ ማኅበራዊ ቀውስ ያስከትላል። የሚበላው ያጣ ሕብረተሰብ ደግሞ ወደ ተቃውሞ እና ሽብር መሄዱ ተጠባቂ ነው። የዚህ ምልክት አሁንም ዕየታየ ነው" ሲሉ የገለፁት ባለሞያው አሁን የሚስተዋለው የኢትዮጵያ ጦርነት በሦስት መልኮች አሉት፡፡ እሱም በሚዲያ፣ በግንባር እና በኢኮኖሚ የሚካሄድ ጦርነት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የኑሮ ውድነት የተከሰተው በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚደረግ ጦርነት ሲሆን አጋጣሚውን በመጠቀም የኢኮኖሚው ዘርፍ ተዋናዮች ሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነት እንዲከሰት የሚያደርጉበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድ ስርአት ዲጂታላይዝ ስላልሆነ ለሕገ-ወጦች በር ይከፍታል፤ ስለዚህ ለሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነት ለመጋለጥ ቅርብ ነው ብለዋል፡፡

እንደሌሎቹ የሃገሪቱ ክፍሎች ሁሉ የዋጋ ንረት ከፍቶ የታየባት የድሬዳዋ ከተማ ችግሩን ለመፍታት በምክትል ከንቲባው የሚመራ ግብረ-ኃይል አቋቁማለች። ግብረ-ኃይሉም ባፉት ሳምንታት በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ ያልተገባ ጭማሪ በማድረግ የዋጋ ግሽበት እንዲከሰት ያደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ፣ በማወያየትና የዋጋ ተመን በማውጣት የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ማስቻሉን አስተዳደሩ ማሳወቁ ይታወሳል። ሆኖም ግብይቱ በተቀመጠው አግባብ እየተካሄደ አለመሆኑን ነዋሪዎች ይገልፃሉ። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ የተወሰደው የማስተካከያ እርምጃ ውጤት በተግባር ዕንደማይታይ ይናገራሉ።

የድሬደዋ አስተዳደር አላስፈላጊና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ያደርጋሉ ባለቸው ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል፡፡ ለዚህም ማሳያ እንዲሆን በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉና ምርት የደበቁ 396 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን ገልጾአል፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ ከነጋዴው ማኅበረሰብ ጋር ውይይቶች በማዘጋጀት እልባት የመስጠት ስራዎችን መከወኑን የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር ገልፀዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር አስተዳደሩ እርምጃ በመውሰድ ማስተካከያ ማድረጉን ቢገልፅም የተሻሻለ ነገር አለመኖሩን ነዋሪዎች ይገልፃሉ፡፡ ነጃት ሁሴን የተባለች የድሬደዋ ነዋሪ የዋጋ ማረጋጊያው ከተተገበረ በኋላ እቃ ለመግዛት ወደገበያ አምርታ የገጠማትን ትናገራለች፡፡ ‹‹ሱቆቹ የዋጋውን ተመን ለጥፈዋል፤ነገር ግን የሚጠየቁትን ሸቀጥ አልቋል ወይም አልገባም ይላሉ›› ብላናለች፡፡

በአሁን ሰዓት በተለይ የስኳርና የዘይት ጉዳይ እንዳሳሰባትና እንደተቸገረችም በቁጭት ገልፃለች፡፡ የከተማዋ ነዋሪ መተባበር እንደሚገባውና በዋጋ ቁጥጥሩ ምክንያት ሸቀጦችን በማያቀርቡ ነጋዴዎች እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማጋለጥ እንደሚገባው ጠቁማለች፡፡ ከሌሎች ክልሎች አንፃር የድሬደዋ ህዝብ በእነደነዚህ ዓይነት ጉዳይ ላይ ቸልተኛ እንደሆነና ለሕግ አሳልፎ መስጠት ላይ ክፍተት እንዳለበት ገልፃ ጊዜው ሁሉም ግለሰብ የማጋለጥ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባና ነጋዴውም የዋጋ ንረቱን ከማባባስ ተግባሩ እንዲቆጠብ ጠይቃለች፡፡

በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ያለው የዋጋ ንረት በተለይ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩትን የሀሪቱን ዜጎች ብርቱ ፈተና ውስጥ ከቷቸዋል። በተለይ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ የእህል፣ የጥራጥሬና የአትክልት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሄድ በኅብረተሰቡ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው፡፡ ይህ የዋጋ ንረት ቀጥተኛ ተፅእኖ ካደረሰባቸው ነዋሪዎች መሃከል ወ/ሮ ሰውነት ምንዳዬ እና ቤተሰቦቻቸው ይገኙበታል። በድሬደዋ ገንደቆሬ ገበያ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ሰውነት እንጀራ በመሸጥ ልጆቻቸውን እያስተዳደሩ እንደሚገኙ የገለፁ ሲሆን “የጤፍ ዋጋ በመናሩ ምክንያት አንድ እንጀራ አስር ብር እየሸጥኩ እገኛለሁ፡፡ በኑሮ ውድነቱ ምክንያት የገበያው ሙቀት ቀንሷል፡፡ ሸማቾች ወደገበያ እየመጡ አይደለም ስትል ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች፡፡ መጪው መስከረም እንደመሆኑ የ5ልጆቿን ዩኒፎርም፣ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችና ወርሃዊ ክፍያ ለመሸፈን ሐሳብ ውስጥ መውደቋን ገልጻ፡፡ ወጪውን በቀላሉ የምትወጣው ባለመሆኑ ልጆቿን ከግል ወደ መንግሥት ለማዘዋወር መወሰኗን አብራርታለች፡፡

የኑሮ ውድነት ከአቅማቸው በላይ የሆነባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በብዛት ዕንደሚታዩ የሚያስረዱት የድሬደዋ ነዋሪ አቶ ብስራት ኃይሉ በዚህ ከቀጠለ ሕብረተሰቡን ወደ ተስፋ መቁረጥ እንዳይገፋው ሰግተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት ብዛት ያላቸውን ሸቀጦች ወደ ገበያ በብዛት በማስገባት በአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ የተሰማሩ አካላትን ውሳኔ ሰጭነት ከመሀል አውጥቶ አምራቹና ተጠቃሚው የሚገናኙባቸው መንገዶች ላይ አተኩሮ እንዲሰራ አቶ ብስራት ኃይሉ ይመክራሉ።

"እኔ የችርቻሮ ነጋዴ ነኝ፤ ከሕብረተሰቡ ጋር በቀጥታ እገናኛለሁ፤ እኛ ደግሞ ከጅምላ አከፋፋዮች እንገዛለን። እኛ እነርሱን ስንጠይቅ፣ የጨመረው ከላይ ነው ይሉናል፤ ግልጽ የሆነ ምክንያት የለም። እኔ አሁን ይህንን የሕዝብ ምሬት መስማት አቅቶኝ ሥራዬን እያቆምኩ ነው" ይላሉ ሰኢዶ አካባቢ ጉልት ቸርቻሪ የሆኑት ወ/ሮ እመቤት ጉልላት በሁሉም እቃዎች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ 'ዶላር ስለጨመረ ነው' ሲባል ከመስማት ውጪ ምክንያቱ ይህ ነው ብሎ የሚናገር የለም ስትል ገለፃለች፡፡          

"ሃገር ውስጥ የሚመረቱ እንደ ሽንኩርት፣ ጤፍ፣ ቲማቲም የመሳሰሉት ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል፤ ከዚያ ባሻገር ከውጭ የሚገቡ እንደ መዋቢያ ምርቶች፣ አልባሳት የመሳሰሉትም ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል" ስትል የምትገልፀው ወ/ሮ ኑኑሽ በቀለ ምናልባትም ከዓለም አቀፍ ወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የንግድ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዛቸው፣ እንደ ወትሮውም በቀላሉ መጓጓዝ ባለመቻሉ የአቅርቦት እጥረት ማጋጠሙ ለዋጋ ጭማሪ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ግምቷን ሰንዝራለች ከዚህም ባሻገር አሁን ሀገሪቷ ላይ ያለው ያለመረጋጋት ለዋጋ ንረቱ ዋነኛ ምክኒያት ሊሆን ይችላል ብላለች፡፡"ሽንኩርት በአስራዎቹ ብር ደረጃ ነበር የምንገዛው፥ አሁን ወደ አርባ ብር ደርሷል፤ ቲማቲምም አሁን በማስታጠቢያ ሰባና ሰማኒያ ይላሉ ከዚህም የተነሳ አጠቃቀማቸውን ለማስተካከል መገደዳቸውን ትናገራለች ጤፍ ከ4300 በላይ እየሆነ ነው። ዘይት ድሮ መንግሥት ያቀርብ ነበር፤ አሁን ግን አያቀርቡም፤ ስለዚህ ከነጋዴ እየገዛን ነው። ዋጋው ጨምሯል። የመንግሥት ሰራተኛ የሆነ፣ ደሞዙ አነስተኛ የሆነ፣ ቤተሰብ ያለው በጣም እየተቸገረ ነው።" ብላለች።

በድሬደዋ ዩንቨርሲቲ የማርኬቲንግ መምህር የሆኑት ዶክተር ምንግዜም ብርሃን ‹‹የዋጋ ጭማሪው በተለይ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ሸማች በሆነባቸው ከተሞች አካባቢ የዜጎች እለታዊ ኑሮ እንዲከብድ እያደረገው ይገኛል። የምርት ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም፣ በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋትና ጦርነት፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያለው መፈናቀሎች፤ የሥራ አጥ ዜጎች መበራከት፣ የሕዝብ ቁጥር እድገት መጨመር እና የማምረቻ ግብአቶች የዋጋ ንረት ለኑሮ ውድነት መባባሱ እንደምክንያትነት ይጠቅሳሉ። ገበሬው በሰላም እጦት ምክንያት ቢያርስ እንኳ አልጎለጎለም›› የሚሉት ባለሙያው፣ የጎለጎለው መዝራት ሳይችል ሲቀር፣ የዘራ ደግሞ መሰብሰብ አለመቻሉ የእርሻ ምርቶች አቅርቦት እየቀነሰ እንዲመጣ ማድረጉን ይገልጻሉ።

ዶ/ር ምንግዜም አክለውም በርካታ ኢንደስትሪዎችም ከውጪ አገር ግብዓት ስላላገኙ ወይንም በሰላም እጦት ፍራቻ ምክንያት ምርት መቀነሳቸው ወይንም ማቆማቸው ሌላው ለኑሮ ውድነቱ አስተዋጽኦ ካደረጉ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። እነዚህ ማምረት የሚያቆሙ ኩባንያዎች በበዙ ቁጥር ለኑሮ ውድነቱ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የሚገልጹት ዶ/ር ምንጊዜም የውጪ ምንዛሬ እጥረት እና የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ተደራርበው የኑሮ ውድነትን ማባባሳቸውን ይገልጻሉ። 

"ከ2017 እስከ 2021 (እኤአ) የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅም በ54 በመቶ ወርዷል፤ በአጠቃላይ ሲታይ በአስር ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅም በመቶ እጅ ወድቋል" የሚሉት ዶ/ር ምንጊዜም የምግብ አቅርቦትና ሌሎች የዕለት ፍጆታ የሆኑ ምርቶች የብር የመግዛት አቅም በወደቀበት በዚህ ጊዜ ከውጪ ሲገቡ የኑሮ ውድነትን እንደሚያባብሱ ይናገራሉ። 

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያመርቱ አብዛኞቹ ኢንደስትሪዎች ከውጪ በሚገባው ግብዓት ላይ የተንጠለጠሉ በመሆናቸው ይህንን ችግር ለመፍታት ያላቸውን ሚና ማሳነሱንም ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ ዕየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ዘላቂ መፍትሄ ሳያገኝ ከቀጠለ አገሪቷን ውስብስብ ወደ ሆነ ችግር ሊመራት እንደሚችል ባለሙያው ይጠቁማሉ።

ዶ/ር ምንጊዜም ለእነዚህ የመፍትሄ ሀሳብ ያሉትን ሲገልፁ የኑሮ ውድነትን ጨምሮ ለበርካታ የአገሪቱ ችግሮች መነሻ የሆነው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የመጀመሪያው መፍትሄ መሆን እንዳለበት ያመለክታሉ። "ሰላም ከሌለ ኢንቨስትመንት የለም፣ ወደ ውጪ መላክ የለም፣ ምርትን አጓጉዞ ማከፋፈል የለም። ሰላም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መኖር ያለበት ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ መንግሥትና ሌሎች ድርጅቶች አብረው ሆነው መወያየት አለባቸው። ግጭት ከሁሉም ወገን መቆም አለበት" ሲሉ ይመክራሉ። የውጪ ምንዛሬ ላይ በፍጥነት ማስተካከያ መደረግ አለበት፣ በዚህ ሁኔታ አገሪቱ ከቀጠለች አስቸጋሪ የምጣኔ ኃብት ሁኔታ ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ገልፀዋል። ብር የመግዛት አቅሙ ከቀን ወደ ቀን መቀነሱ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መቆም እንዳለበትም ይመክራሉ። አሁን ያለው የውጪ ምንዛሬ ከዚህም ባነሰ በ30 እጅ ወደ ኋላ መመለስ አለበት ይላሉ። አሁን የብርን ዋጋ እንዲወርድ ማድረግ በኢንቨስትመንትም ሆነ በውጪ ንግድ አንጻር ለኢትዮጵያ የሚያመጣው ትልቅ ፋይዳ የለውም ብለዋል።  የህዝቦች የሥራ ባህልም መሻሻል አለበት በማለት ሃሳባቸውን ያጠቃልላሉ።

Author: undefined undefined
ጦማሪዝናሽ ሽፈራው

I graduated from Bahir dar university in the field of journalism and communication, and a reporter at Addis Zeybe in Dire Dawa branch.