አደገኛው የውርጃ መድኃኒቶች ሽያጭ

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራውኅዳር 11 ፣ 2014
City: Dire Dawaጤና
አደገኛው የውርጃ መድኃኒቶች ሽያጭ
Camera Icon

Photo: time.com

የጤና ባለሙያዋ ህይወት አሻግሬ ጽንስ የሚያቋርጡ እንክብሎችን ያለማዘዣ እንደሚሸጡ መድኃኒት መደብር ስለመኖሩ መስማቷን ትናገራለች። በድሬዳዋ ከተማ ሳቢያን ቤተሰብ መምሪያ በማገልገል ላይ የምትገኘው ባለሙያዋ በድብቅ የሚሸጡት እንክብሎች “ከሀኪም ትእዛዝ ውጭ ፈጽሞ ተጠቃሚው እጅ መግባት ያልነበረባቸው ነበሩ” ትላለች። ነርስ ገኑ ዳዊቴም በህይወት ሐሳብ ትስማማለች። በኪኒን መልክ ተዘጋጅተው በአፍ የሚወሰዱትን መድኃኒቶች ሐኪም ሳያማክሩ በመጠቀማቸው ምክንያት ከሞት የተረፉ ሴቶችን ገጠመኝ በሥራ አጋጣሚዋ መመልከቷንም ታስታውሳለች። “በተለይ የ‘ሀይስኩል’ ተማሪዎች የዚህ ተግባር አዘውታሪዎች ናቸው” የምትለው ገኑ የመኝታ አገልግሎት በሚሰጥ ‘ፔንስዮን’ ውስጥ ከጓደኛዋ ጋር በመሆን የወሰደችው እንክብል የማያቋርጥ የደም መፍሰስ ያስከተለባትን የ20 ዓመት ወጣት በሥራ አጋጣሚዋ ተመልክታለች።

የፋርማሲ ባለቤት ነው። በዚህ ዘገባ ላይ ስሙ ሳይጠቀስ ሐሳቡን ብቻ እንድንጠቀም ፈቅዷል። “በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ሴቶች በብዛት የሚጠይቁት የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ ኪኒን ነው። በተለምዶ የ72 ሰዓት ተብሎ የሚጠራውን እንክብል በርካታ ሴቶች ቋሚ መከላከያ እያደረጉት ነው። ለውርጃ ተግባር የሚውለውም በብዛት ይጠየቃል። እኛ ቤት ግን ዝም ብለን አንሸጥም” ብሎናል። ሁሉም የተቋሙ ሰራተኞች ማዘዣ ተመልክተው ካልሆነ እንደማይሸጡም ነግሮናል “ሁሉም ፋርማሲ ሕጉን ተከትሎ ይሰራል ማለት አልችልም። ልክ እንደሌሎች ንግዶች ከሕግ ውጭ ተንቀሳቅሶ በፍጥነት ለመክበር ፍላጎት ያለው አይጠፋም” ሲል ሐሳቡን ደምድሟል።

“መድኃኒቶች ዓይነተ ብዙ ናቸው” ያሉን የፋርማሲ ባለሙያ አቶ ዘልዓለም አባቡ ናቸው። በዩኒቨርሳል ሜጂካል ኮሌጅ የፋርማሲ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ አልዓለም በዘመናዊ መልክ ስለሚዘጋጁ መድኃኒቶች በሰጡን ሐሳብ “በአፈጣጠራቸው በደምስር የሚሰጡ፣ የሚቀቡ፣ በእንክብል መልክ የቀረቡ፣ በሽሮፕ የተዘጋጁ ሊሆኑ ይችላሉ። በሀኪም ትእዛዝ ብቻ የሚወሰዱ ወይም ለሆስፒታል አገልግሎት ብቻ የሚውሉም አሉ። በሀኪም ክትትል የሚወሰዱ እና በሀኪም ትእዛዝ ታማሚው በቤቱ የሚወስዳቸውም አሉ። ይህ የሆነው በምክንያት ነው። የተቀመጡ ሕግጋትን መጣስ ራስን አደጋ ላይ መጣል ነው። እስከ ሞት የሚደርስ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል” በማለት ያብራራሉ።

ምክንያቶቹ ምንድናቸው?

ሴቶች ሆነ ብለው ጽንስ የሚያቋርጡባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ አስገዳጅ ምክንያቶች በትዳር ውስጥ ለሚገኙ እና ለማይገኙት ልዩ መልክ አላቸው። በዋናነትም ጤና ነክ የሆነ እና ያልሆነ በሚል ይከፈላል። ተጨማሪ ልጅ ባለመፈለግ/በማሳደግ አቅም ማነስ፣ ከትዳር አጋር ጋር በሚፈጠር አለመግባባት፣… በትዳር ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ምክንያቶች ናቸው፡፡ ላላገቡ ሴቶች ደግሞ ከጋብቻ ውጭ በማርገዛቸው ለብቻ ላለማሳደግ የሚለው ይጠቀሳል። አስገድዶ መድፈር ላገቡም ላላገቡም ይሰራል። የጽንሱ አፈጣጠር ችግር ሲኖርበት እና እርግዝነው ለእናትየው ጤና አስጊ ሲሆንም ሐኪሞች ጽንስ ማቋረጥን ሊመክሩ ይችላሉ።

ለምን ተመረጠ?

በፈቃዳቸው ጽንስ የሚያቋርጡ ሴቶች የሕክምና ተቋማትን የማይመርጡበትን ምክንያት በተመለከተ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ከገጠመኛቸው በመነሳት የየራሳቸውን መላምቶች ነግረውናል። ሲስተር ገኑ “ለአስፈላጊ ምርመራዎች ማዘዣ እንጽፍላቸዋለን። እሺ ብለው ይሄዱና አይመለሱም። የተወሰኑት ሴቶች ለምርመራዎቹ በቂ ገንዘብ ስለማይኖራቸው ነው” ብለውናል፡፡

ከገንዘብ እጥረት በተጨማሪ ሂደቱን ለማፍጠን ከመጣደፍ፣ አገልግሎቱ የት እንደሚሰጥ ካለማወቅ፣ ከቤተሰብ ወይም ከሌላ ሰው ዕይታ ለመሰወር፣ የሚያደርሰውን ጉዳት ካለመገንዘብ እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ሴቶች በጤና ተቋማት እንዳይገለገሉ ያደርጋል።

ምርመራዎቹ የደምና የሽንትን ጨምሮ አጠቃላይ ምርመራን ያጠቃልላሉ። ሄፓታይተስ ቢ፣ ሲ፣ coagulogram በዚህ ውስጥ ይካተታሉ። ምርመራዎቹ የጽንሱን እና የእናቲቱን ጤንነት ለማወቅ የሚረዱ ናቸው። የምርመራው ውጤት ቀጣዩን ሂደት ለምረጥ የሚያስችሉ ውሳኔዎች ይተላለፉበታል።

በምን መንገድ ይካሄዳል?

በዚህ ጽሑፍ ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች ነርስ እንደ ቤተሰብ መምሪያ፣ ማሪስቶፕስ፣ የወረዳ ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም ሌሎች የግል እና የመንግሥት ጤና ተቋማት ጽንስ የማቋረጥ ሐሳብ ይዘው ተቋማቱን ለሚያማክሩ ሴቶች ሕጉን ተከትለው አገልግሎቱን እንደሚሰጡ ነግራናለች። ተቋማቱ አገልግሎቱን የሚሰጡት በሴቷ እና በጽንሱ ላይ በርካታ ምርመራዎች ካካሄዱ በኋላ ነው።

የሕግ እና የጤና ተጠያቂነት ከግምት ውስጥ ገብቶ የሚካሄደው ጽንስ ማቋረጥ በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ይካሄዳል። እነርሱም በመድኃኒት እና በህክምና መሳሪያ (ኤም ቪ ኤ) ድጋፍ የሚከወኑት ናቸው። አማራጮቹ የጽንሱን ዕድሜ፣ የሴቷን ጤንነት እና ሌሎች ጉዳዮችን ከግምት በማስገባት በሐኪም ውሳኔ ይሰጥባቸዋል። እንደ ጽንሱ ሁኔታ በቀዶ ጥገና ወይም በመሳሪያ እና በመድኃኒት ጥምረት ጽንስ ማቋረጡ ሊካሄድ ይችላል።

ጤና መኮንን ሱራፌል ደመቀ በድሬዳዋ ከተማ አዲስ ከተማ ጤና ጣቢያ ውስጥ ያገለግላል። ጽንስን ለማቋረጥ ስለሚያገለግሉ እንክብሎች የጠየቅነውን ሲመልስ “‘ሜፊፕሪስቶን’ እና ሚሶፕሮስቶል የሚባሉ ሁለት ዓይነት ጽንስ ማቋረጫ እንክብሎች አሉ” በማለት ይጀምራል። ማብራሪያውን ሲቀጥል “የ‘ሜፊፕሪስቶን’ሥራ ጽንሱ ለማደግ የሚያስፈልጉትን ሆርሞኖች መገደብ ነው። ‘ሚሶፕሮስቶል’ ደግሞ የማህጸን በርን በመክፈት ንጥረ ነገሮቹ እንደሚወጡ ያደርጋል። ውጤታማ የጽንስ ማቋረጥ ለማካሄድ ሁለቱም እንክብሎች በ48 ሰዓታት ልዩነት ሊወሰዱ ይገባል። በጋራ የሚወሰዱት የአንደኛውን ጉድለት አንደኛው ስለሚሞላ ነው” ብሎናል።

በጤና ተቋማት ውስጥ በሚገኙ መድኃኒቶች በፈቃዳቸው ጽንስ ማቋረጥ የሚፈልጉ ሴቶች ለአገልግሎቱ ተብለው ከሚዘጋጁ መድኃኒቶች በተጨማሪ ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ መድኃኒቶችንም ሲጠቀሙ ይስተዋላል። በቁጥር የበዙ መድኃኒቶችን በአንድ ጊዜ በመውሰድ፣ ልዩ ልዩ መድኃኒቶችን ቀላቅሎ በመውሰድ ጽንሱን ለማቋረጥ የሚሞክሩ ሴቶች መኖራቸውን አስመልክቶ የጠየቅናቸው ባለሙያዎቹ “አደገኛ ሙከራ ነው” ይላሉ። ያልተጠበቀ የከፋ የጎንዮሽ ጉዳት ስለሚያስከትል ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን ተግባር ስለመሆኑ ነግረውናል።  

የሚያስከትለው ጉዳት

“አገልግሎቱ በጤና ተቋማት ውስጥ ሲሆን የሚያስገኘውን ጥቅም ከጤና ተቋም ውጭ ሲሆን ያሳጣል” የምትለው ሲስተር ገኑ “ኪኒኑ እንደ ራስ ምታት ወይም የሕመም ማስታገሻ አይደለም። የሐኪም የቅርብ ክትትል ያስፈልገዋል” ስትል አጽንኦት ሰጥታ ነግራናለች። ሲስተር ዲቦራ በበኩሏ “በጤና ተቋማት ውስጥ ሲሆን ሴቷ በቀጣይ ሕይወቷ ማድረግ የሚገቧትን ጥንቃቄዎች ከሀኪሙ ትረዳለች” ያለች ሲሆን፤ ጽንስ ማቋረጥን ሁሉም የጤና ባለሙያ የሚሰራው ሳይሆን በመስኩ ልዩ ስልጠና የወሰደ ባለሙያ እንደሚከውነው ነግራናለች። ሴቷም ግንኙነት መቼ እንደምትጀምር፣ ስለ ኢንፌክሽን፣ ከማኅጸን ስለሚወጡ ፈሳሾች እንድታውቅ ይደረጋል። እንደ ሲስተር ዲቦራ ገለጻ ብዙዎች ከጽንስ መቋረጥ በኋላ የእርግዝና ጊዜአቸው እንደሚቆይ ቢያስቡም በአንድ ሳምንት ውስጥ ድጋሚ የማርገዝ ዕድል አላቸው።

ሕጉ ምን ይላል?

ጽንስ ማቋረጥን በተመከለተ በጤና ባለሙያዎች እና በሲቪል ማኅበራት፣ በሀይማኖት ሰዎች እና በመብት ተሟጋቾች መካከል በሁለት ጎራ የተከፈሉ ዓለም አቀፋዊ ክርክሮች አሉ። ‘ሴቷ ያልፈለገችውን ጽንስ ማቋረጧ ትክክል ነው’ የሚሉት ደጋፊዎች በአንድ ወገን ‘ድርጊቱ ሰውን ከመግደል እኩል ነው’ የሚሉ ተቃዋሚዎች በሌላ ወገን ጎራ ለይተው ይከራከሩበታል። የዓለም ሐገራትም ገሚሶቹ ድርጊቱን ሲፈቅዱ ገሚሶቹ ከልክለዋል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሐገራት በዋናነት ቢከለክሉም በልዩ ሁኔታ ፈቅደዋል።

ጽንስ ማቋረጥ የሚፈቀድባቸውን ሁኔታዎች የሚያብራራው የፌደራል የወንጀል ሕግ አንቀጽ 521 “በህክምና ሙያ በተፈቀደ የጊዜ ገደብ ውስጥ በህክምና ተቋም” መሆን እንደሚገባው ያስቀምጣል። ይህ እንዲሆን ግን ጽንሱ የተፈጠረው በመደፈር ወይም በዘመድ መካከል በተደረገ የግብረ ስጋ ግንኙነት ምክንያት ከሆነ፣ የእርግዝናው መቀጠል በእናቲቱ ጤንነት ወይም በጽንሱ ህይወት ላይ አደጋ የሚያስከትል ከሆነ፣ ጽንሱ ሊድን የማይችል ከባድ ጉድለት ያለው (ዲፎርምድ) ከሆነ ወይም እርጉዟ የአካል ወይም የአዕምሮ ጉድለት ያለባት በመሆኗ የሚወለደውን ለማሳደግ የህሊናም ሆነ የአካል ዝግጁነት ሳይሆራት ሲቀር ነው።

የሕግ ባለሙያው አቶ ተመስገን አሰፋ “ይሁን እንጂ የአፈጻጸም ክፍተት ያለ ይመስላል” ይላሉ። “ለማስወረድ ጤና ተቋማት የመጣችው እንስት ቃሏ ይታመናል እንጂ በምስክር ወይም በምርመራ እውነትነቱ አይረጋገጥም። ለምሳሌ የጸነስኩት ተደፍሬ ነው የምትልን ሴት ምስክር አትጠይቃትም። ቃሏን ብቻ ነው የምታምነው። ስለዚህ ለዋሾዎችም እድል ይሰጣል ማለት ነው” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአንቀጹ ከተጠቀሱት ሁኔታዎች ውጭ እርግዝናን ማቋረጥ ለቅጣት እንደሚዳርግ ሕጉ አስቀምጧል። የራሷን ጽንስ ሆነ ብላ የምታቋርጥ ሴት በቀላል እስራት፤ እንድታቋርጥ የሚያስችላትን መሳሪያዎች ያቀበለ ወይም በማናቸውም ሁኔታ የደገፈ፣ በተባባሪነት ተካፋይ የሆነ ግለሰብ በቀላል እስራት፤ ድርጊቱ የተፈጸመው እርጉዟ ፈቃድ ባልሰጠችበት ወይም ፈቃድ መስጠት በማትችልበት ሁኔታ ከሆነ ወይም ዛቻ፣ ማስገደድ፣ ማታለል ከታከለበት፣ በማታለል ወይም ጽንሱ እንዲቋረጥ የፈቀደችው ድርጊቱ የሚያስከትለውን ውጤት ማወቅ በማትችልበት ጊዜ መሆነ ቅጣቱ ከሦስት እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሆነ ተገልጿል።

Author: undefined undefined
ጦማሪዝናሽ ሽፈራው

Zinash is Addis Zeybe's correspondent in Dire Dawa.