ሐምሌ 13 ፣ 2014

ድሬዳዋ ያበቀለቻት የገጽ ቅብ ባለሙያ (ሜክአፕ አርቲስት) ምህረት ኤሊያስ

City: Dire Dawaባህል ኪነ-ጥበብ

ምህረት “የእግር እሳት” ድራማን እና 'እስክሽር' የተሠኘውን የሳያት ደምሴን ሙዚቃን ጨምሮ ከ 30 በላይ ማስታወቂያና ፊልሞች ላይ ተሳትፋለች

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

ድሬዳዋ ያበቀለቻት የገጽ ቅብ ባለሙያ (ሜክአፕ አርቲስት) ምህረት ኤሊያስ
Camera Icon

ፎቶ፡ አርቲስት ምህረት ኤሊያስ (በእግር እሳት ቀረጻ ላይ)

በትወና ጥበብ በተለይም በትያትርና በፊልም ስራ ላይ የተዋንያንን የፊትና የገጽ እይታ በማጉላት ረገድ የሜክአፕ (የገጽ ቅብ) ባለሙያው ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። በዚህ ዘርፍ እየሰሩ ካሉት በጣት ከሚቆጠሩ የሜክአፕ (የገጽ ቅብ) ባለሙያዎች ውስጥ አንዷ የሆነችው ምህረት ኤልያስ ከአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ጋር ቆይታ አድርጋለች።   

በድሬዳዋ ከተማ 'ገንደቦዬ' ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ተወልዳ ያደገችው ሜክአፕ አርቲስት ምህረት ኤልያስ፤ ከአፀደ ህፃናት እስከ መሰናዶ ያለው ትምህርቷን በድሬዳዋ ተከታትላለች። ትምህርቷን በመቀጠልም ከጎንደር ዩኒቨርስቲ በሶሾሎጂ የትምህርት ዘርፍ ተመርቃለች። ከዩኒቨርስቲ ስትመለስ የሜክአፕ ትምህርት ቤት በመግባት መሰረታዊ የውበት ሜክአፕ ትምህርት ተማረች።

ምህረት እንድምታስታውሰው የ10ኛ ክፍል የሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰደች በኋላ በነበረው ክረምት ነበር የመጀመሪያ ስራዋን በፔፕሲ ማስታወቂያ ላይ በመሳተፍ የጀመረችው። “የ12ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ድሬዳዋ ላይ በአርቲስት ሰለሞን ቦጋለ ዳይሬክት የሚደረግ 'የራስ መንገድ' የተሰኘ ፊልም ይሰራ ነበር። እዛ ፊልም ላይ ወተት የምትሸጥ የሀረርጌ እንስት ሆኜ ሰራሁ። በወቅቱ ሜክአፕ የሚሰራው ተስፋዬ ወንድማገኝ የሚባል ባለሙያ ነበር። እሱ ሲሰራ ሳይ ሞያውን በጣም ወደድኩት፤ እናም ያ አጋጣሚ ነው ወደዚህ ሙያ እንድገባ ምክንያት የሆነኝ” ስትል ለሞያው እንዴት ፍቅር እንዳደረባት ምህረት ትናገራለች። 

ምህረት 'የእግር እሳት' በተሰኘውና የጉማ አዋርድ ተሸላሚ የነበረው የቴሌቭዢን ተከታታይ ድራማ ላይ በዋና ሜክ አፕ አርቲስትነት ስኬታማ ስራ ሰርታለች። በዚህም ስኬት መነሻነት አሁን ላይ 'በስንቱ' የሚል ተከታታይ የቴሌቭዢን ድራማ በአብሪኮም መልቲ ሚዲያ ጋር እየሰራች ትገኛለች። ሌላው 'እስክሽር የተሰኘውን' የድምጻዊ የሳያት ደምሴን የሙዚቃ ክሊፕ እንዲሁም ከ 30 በላይ ማስታወቂያዎችና አጫጭር ፊልሞች ላይ በሜክአፕ አርቲስትነት አሻራዋን አስቀምጣለች። 

ከፊልሙ ስራ በተጨማሪ ሙሽራና የተለያዩ ዝግጅቶች ያለባቸውን ሰዎች ሜክአፕ ትሰራለች። ሜክአፕ አርቲስት ምህረት በምን መልኩ አሁን በምትገኝበት ደረጃ ላይ እንደደረሰች ስትናገር “የተለያዩ ፊልሞችን በማየትና በኦንላይን የሚሰጡ ተከታታይ ትምህርቶችን በመማር እራስን በማሳደግ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ የሞያ ዘርፍ ትምርቱ አይሰጥም ” በማለት ታስረዳለች። በተጨማሪም ሜካፖችን፣ የመስሪያ ቁሳቁሶች እና ንጥረ ነገሮችን በቀላሉ አለማግኘት በራሱ ስራውን እንደሚያከብዱት ታስረዳለች። 

ሜክአፕ አርቲስት ምህረት ስለ ስራው ስታስረዳ “የሜክአፕ ስራ በሰው የፊት ቆዳ ላይ እና በአካል ላይ የሚሰራ እንደመሆኑ መጠን ሰዎች አምነው ራሳቸውን እንዲሰጡ የምንይዛቸው ቁሳቁሶች ጥራት ያላቸው መሆን ይጠበቅባቸዋል። በአብዛኛው ለፊልም አገልግሎት የምንጠቀምባቸው ንጥረ ነገሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ስለማይመረቱ ከውጪ ሰው ሲመጣ ጠብቀን አልያም እንዲላክልን አድርገን ነው የምናገኘው” ስትል ከሚገጥማት ተግዳሮቶች አንዱን ታስረዳለች።

በዚህ ሙያ በስፋት ለመስራት ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ መጥተሽ ስትስሪ ያጋጠሙሽ ፈተናዎች ምን ነበሩ ብላ አዲስ ዘይቤ ለጠየቀቻት ጥያቄ ምህረት ስትመልስ “ለመጀመሪያ ጊዜ ምንም ነገር ሳይኖር አዲስ አበባ ለመኖር መወሰን ስጀምር ነው ገና የህይወት ፈተናዎች ማየት የጀመርኩት። ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ። ራሴን ሙሉ ለሙሉ ችዬ ለመቆየት እንዲሁም ከለመድኩት የአኗኗር ዘይቤ የተለየ ስለሆነ ትንሽ ከብዶኝ ነበር” ስትል መልሳለች። 

ምህረት እንደምትገልጸው ከሆነ በዚህ የሞያ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልግ ሰው መሀበራዊ ሚዲያን በመጠቀም እራሱን እያሳደገ ይመጣል እንጂ አዲስ አበባም ላይ ሆነ ክልሎች ላይ ትምህርቱ አይሰጥም። በጥበብ ዙሪያ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በትንሹም ቢሆን ወደሞያው ለመግባት የሚያንደረድራቸውን ትምህርት የሚያገኙት አዲስ አበባ በመምጣት ነው።

“በዚህ የሙያ ዘርፍ ብዙ መስራት የሚችሉ ፍላጎቱ ያላቸው ነገር ግን ድሬዳዋ ላይ በአርት ዙሪያ ትምህርት ቤቶች ባለመኖራቸው ያልወጡ ብዙ ሰዎች አሉ” ስትል ሜክአፕ አርቲስቷ ትናገራለች። በእንደነዚህ አይነት የትምህርት ዘርፎች አጫጭር ስልጠናዎች መሰጠት ቢችሉ ወደሙያው መግቢያ እድል ሊከፍት እንደሚችል ኃሳቧን አካፍላናለች። 

“በዚህ የሙያ ዘርፍ ያለን የድሬደዋ ልጆች ለጥቂት ቀናት የሚቆዩ ስልጠናዎችን መስጠት ብንጀምር ያ እያደገ መምጣት ይችላል ብዬ አስባለሁ። እኔም በቅርቡ ከአስተዳደሩ ጋር በመነጋገር ለጥቂት ቀናት የሚቆይ ስልጠና የመስጠት ኃሳብ አለኝ። በእርግጥ ገና እኔም እየተማርኩ ነው ግን እስካሁን ያወቅኳትን ለሀገሬ ልጆች ማካፈል እፈልጋለሁ” በማለት ኃሳቧን ደምድማለች።

አስተያየት