ነሐሴ 9 ፣ 2014

በክረምት የእርሻ ስራ ላይ የሚነገሩ የስነ ቃል ግጥሞች

City: Dessieየአኗኗር ዘይቤማህበራዊ ጉዳዮች

የስነ ቃል ግጥሞች ለገበሬው ኃሳቡን የመግለጽ፣ የመንገር፣ የማነቃቃት፣ የማስተማር፣ የማሳወቅ፣ የማዝናናት ሚና ያላቸው ሃብቶቹና ገጠመኙን ማድመቂያ ጌጦቹ ናቸው

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በክረምት የእርሻ ስራ ላይ የሚነገሩ የስነ ቃል ግጥሞች
Camera Icon

ፎቶ፡ ኢድሪስ አብዱ (አዲስ ዘይቤ)

ሐምሌና ነሀሴ በሃገራችን ክረምት አርሶ አደሩ ዝናቡን፣ ጭቃውን፣ ብርድና ቆፈኑን ተቋቁሞ ጠንክሮ የሚያርስበት ወቅት ነው። በስራ መብዛትና በአየሩ ሆኔታ ምክንያት መሰላቸት እንዳይሰማው እና ድካሙን ለማስወገድ  

ከሚጠቀመው ዘዴ አንዱ በስነ ቃል ማንጎራጎር ነው። 

“በሬ ሆይ፤ በሬ ሆይ” ብለው ካላረሱ፤

አሁን የት ይገኛል ስንዴው እና ገብሱ። 

ሃምሌ ነሐሴ ያልከሰበ (ያላረሰ) ሰው፣

ሞፈር ቀንበሩን ቀሚስ ያልብሰው።

በተለይ ደግሞ በክረምቱ የእርሻ ስራ ላይ በሬዎቹን እያሞገሰ፣ ሰነፎች ለስራ እንዲነሱ እየቀሰቀስ፣ እራሱንና መሰል ታታሪዎችን እያደነቀና እያበረታታ ስራውን በብቃት ሲያከናውን ይውላል። በዚህ ወቅት ከሚነገሩት የስነ ቃል ግጥሞች መካከል በወሎ አካባቢ የሚነገሩትን የአዲስ ዘይቤ የደሴ ሪፖርተር በዚህ መልኩ አጠናቅሮ ለማቅረብ ሞክሯል።

እስከ ገደሉ ስር እርሻውን እረሱ፣

አቦል ጀባ ሲባል ይቸግራል ቁርሱ።

አንተ ተኝተህ እኛ ስናረስ፣

አጭደን ከምረን ምርት ስናፍስ፣

ከስንፍና እንቅልፍ አንተ ስትነቃ፣

መስከረም ነጋ ክረምት አበቃ

ሲል አርሶ አደሩ ክረምቱን በትጋት ማረስ ከርሃብ እና ከችግር እንደሚያድን ውብ በሆነ ስነ ቃል ይገልጻል። ለእርሻ ስራ ወሳኝ የሆነውን የክረምቱን ወቅት በስንፍና ማሳለፍ፤ በቀጣይ ለሚመጣው ጊዜ ለችግር የሚዳርግ የሞኝነት ተግባር መሆኑን ይናገራል፤ ያስተምራልም።   

ሞኜ ሆይ ተላሌ ሆይ፣ 

መማር ከማር አይበልጥም ወይ?

ጤፍ እንጀራ በርጎ፣

አዋዜ ጣል አርጎ አይጎርሱ፣

እንዲህ እንዲህ አርገው ካላረሱ . . . እያለ ጠንክሮ የሰራ ጎተራው ሞልቶ የጣፈጠ ለመብላት እንደሚችል ዘመን ተሻጋሪ በሆነ የስነ ቃል ኃብቱ ይገልጻል። በሌላ በኩል የራሱን የስራ ብርታት እና ጎበዝ ገበሬነት እያንጎራጎረ በመንገር ጎተራው ሙሉ በመሆኑ ብድር እንደማይጠይቅም መልዕክቱን ያስተላልፋል።    

ያርሳል ያሳርሳል ያወጣል እዳሪ፣

ሚስቱን አይላትም ሂጂ ተበደሪ።

አረንዛ ገፊ ሰርዶ ቅልቅል፣

ሻሽ የመሰለ ማኛ ሚያበቅል።

ማረሻው ሀዲድ ሞፈሩ ወይራ፣

ሰርዶ አራጋፊ እንደ ጨጓራ።

ማረስ ነው እንጅ ሸከኬም ቢሆን፣

አንድ ቃጤ እህል መቶ ብር ሲሆን። 

እዚህ ላይ አንዳንድ ቃላትን ግልጽ ለማድረግ ያህል፤ “አረንዛ” ማለት ውስጡ ረግረግ የሆነ ውሃማ መሬት ሲሆን “ቃጤ” ማለት ደግሞ ከአክርማና ስንደዶ የሚሰራ ትንሽ ሰሃን መሰል የስፌት እቃ ነው። “ሸከኬ” ሲባል ደግሞ ለማረስ አሰቸጋሪ የሆነ የአፈር ዓይነትን ለመግለጽ በወሎና በአካባቢው ህዝብ ዘንድ የተለመዱ ቃላት ናቸው። 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተመሰረተው በእርሻ ላይ መሆኑ የሚታወቅ ነው። የእርሻ ስራው ባለመዘመኑ በዝናብ እና በበሬ ጫንቃ ላይ ተንጠልጥሎ ለዘመናት ዘልቋል። ለአርሶ አደሩም የኑሮው ዋስትና ለሆነው የእርሻ ስራው ዋና ረዳቶቹ በሬዎቹ ናቸው። አርሶ አደሩ እንደ አንድ የቤተሰብ አባል የሚቆጥራቸው በሬዎቹን ቡሬ፣ ሶረን፣ ቦራ፣ መጋል እያለ ስም ያወጣላቸዋል። ታድያ በእርሻ ስራ ወቅት በሬዎቹን በስማቸው እየጠራ በስነ ቃሉ ያሞጋግሳል፤ ያደንቃል።

መጋል ከሶረን ሲተባበሩ፣

ማ'በል የመታው ይመስላል ፈሩ፡፡

በወይፈን በጊደር ካልተፍጨረጨሩ፣

የጎተራ ሌባ ያደርጋል መንደሩ።

በሬው ጀገነ ሞፈሩ ሰላ፣

ገለባበጠው ቅብቅቡን ሁላ።

በሬው ሰጋጊ ማረሻው ወጊ፣

የቤቱ ጌታ  ምርት አረግራጊ።

አርሶ አደሩ በሬውን እንደ ቤተሰቡ አባል ብቻ ሳይሆን፤ እንደ ቅርብ ጓደኛም እያዋራ፣ ሲያጠፋም እየተቆጣ ከዚህ ካለፈም መግባባት እስኪችሉ ድረስ በጅራፍ ይገርፋል። በሬውም መሬቱን ፈንቅሎ በማረስ ታዛዥነቱን ያሳያል። በዘህ ጊዜ አርሶ አደሩ ልዩ ልዩ ስነ ቃሎችን እያነሳሳ የእርሻ ስራውን ያከናውናል። 

ተው መጋል ተው ቦራ፣

አንተና እኔ አለን መሃላ፣

እኔም ላልገርፍህ አንተም ላትላላ።

ካረሱም አይቀር ሞፈር ከበሱ፣

ሲያደናግር ነው ባቄላ ገብሱ።

ፎቶ፡ ኢድሪስ አብዱ (አዲስ ዘይቤ)

ሰማይ በደመና ተሸፍኖ ጉርምርምታ ሲያሰማ፣ ምድር በዝናብ ረጥባ በአረንጓዴ ስትሸፈን፣ የክረምቱ ጭጋግ እና ቆፈን ከእረኞች ጅራፍ ጩኸት ጋር ሲደማመር ልዩ የክረምት ድባብ ይፈጥራል። እናም አርሶ አደሩ በዚህ ድባብ ታጅቦ የመጭውን የመኸር ምርት ውጤታማነት እያሰበ ከሌላው ጊዜ በተለየ በሥራ የሚተጋበት ወቅት ነው። ይህንን የስራና የእርሻ ዝግጅት ወቅትም በስነ ቃሉ ሳያስበው አያልፍም።  

ሰኔ ግም ሲል ሃምሌ ሲያገሳ፣

አከናናቢ ጎድጓዳ ማሳ።

የበሬው ዳኛ የበሬው ምሁር፣

አቆላላፊ ክምር በክምር።

በክረምት ወቅት የዝናቡ ጊዜ ሳያልፍ ጠንክረው ማረስና መዝራት ካልቻሉ በበጋው ለችግር መጋለጥ የማይቀር ነው። ሰነፉ አርሶ አደር የእርሻ ጊዜ ሳያልፍበት ጠንክሮ እንዲያርስና የስራ ክቡርነትን እንዲረዳ ትጉህ አርሶ አደሩ በስነ ቃል እያዋዛ ይነግረዋል።

ሲሞላው እህል ቀዬ አውድማህን፣

መጣ አባ ቢድራ ሊሰጥህ ልጁን።

በበጋ እንዳይሰራ ፀሐይ እየፈራ፣

በክረምት እንዳያርስ ዝናብ እየፈራ፣

ልጁ “እንጀራ” ሲለው በጅብ አስፈራራ።

እንደ ሌሎቹ ጠንካራ አርሶ አደሮች መሬቱን በወቅትና በአግባብ አርሶና ዘርቶ ምርት ያልሰበሰበ ገበሬ 'ርቦኛል' ያለውን ልጁን ምግብ በመስጠት ፈንታ በጅብ ቢያስፈራራው ረሃብ ነውና ከማልቀስ አይመለስም። ታዲያ ለዚህ ችግሩ ሰው ደጅ ሄዶ እህል ልመና መቆሙ አይቀሬ ይሆንበታል። በዚህም በላይ በየሰርጉ፣ በየደቦውና በየሰንበቴው ላይ በስነ ቃል መሰደብ፣ መተቸቱ የሰርክ ዕጣ ፈንታው ሆኖ ይቀራል። ጥፋቱን አውቆ ከስህተቱ እንዲማር የጠንካራ ገበሬን የልፋት ውጤት በእንጉርጉሮ ይነግሩታል።

ቧልቱን ተውና እረስ ተነስተህ፣

ጎታው ይሙላ ኋላ እንዳያዝህ።

ቧልት ያላበዛ በወቅት ያረሰ፣

ማኛ ከነጩ መርጦ ጎረሰ።

አፍላ ወጣት የሆነ አርሶ አደር በበኩሉ ቀን ከሌት ድካምና ልፋት ውስጥ ሆኖም እንኳን የአይኑን ረሃብ፣ የልቡን እመቤት፣ የነገ የጎጆው አጋር የሆነችውን ሳዱላ ይናፍቃታል። እርሷም ደግሞ ልቧን በፍቅር ያስሸፈተው ጉብል ከመንደሩ ማልዶ ከወጣ ጀምበር ሳያዘቀዝቅ አይመለስምና ናፍቆቱ ሲበረታባት በሬ ጠምዶ በሚያርስበት ስፍራ ተገኝታ አይን አይኑን ታየዋለች። ይሄኔ አርሶ አደሩ ስሜቱን በስነ ቃሉ እንዲህ ይገልጻል፥

በሮችን ጠምጄ እርፉ ሲያንገላታኝ፣

መጣች ግራ ጎኔ ሥራ ልታስፈታኝ።

ተይ በሏት ያችን ሰው አትግባ በስራ፣

ፍቅር ትዝታ እንጂ አይሆንም እንጀራ።

ይህንንም በማለት እርሷን በማየቱ ልቡ መንታ ሆኖ እርሻውን በወጉ ከማረስ እንዳይዘናጋ ወደ ስራው ለመመለስ ራሱን ይገስጻል። በሌላ በኩል ደግሞ እርሷን በማየቱ መደሰቱንና የመስራት ፍላጎቱም በዚያው መጠን መጨመሩን ላለማካድ በዚህ መልኩ ያንጎራጉራል። 

ውብዬን እያየሁ ሆብዬ ሆብዬ፣

ምርቱን ይዤ ገባሁ ገለባውን ጥዬ። 

ገና ወደፊት ለሚመጣው ቀን፣

አልወጣለትም የእርሻው ሰቀቀን።

ገበሬው የክረምቱን የዝናብ ወቅት በመጠቀም አርሶ፣ ዘርቶ፣ አርሞና ኮትኩቶ እንዲሁም ሰብልን ከሚጎዱ እንስሳትና ነፍሳት ጋር ታግሎ ለአጨዳ ያደርሳል። በበጋ ወቅት ምርቱን ሰብስቦ በጎተራው ያስቀምጣል። ያኔ ከራሱና ከቤተሰቡ አልፎ ለሌሎችም ይተርፋል። በዚህም ጠንካራ ገበሬ መሆኑ በተለያዩ ማህበራዊ ሁነቶች ላይ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ይመሰከርለታል፣ ይደነቃል። 

ሰኔና ሃምሌ ግም ግም ሲል፣

የቀኙ በሬ አውጣኝ አውጣኝ ሲል፣

የግራው በሬ አውጣኝ አውጣኝ ሲል፣

ማረስ ነው ደጉ...

የእርፉ ልማም ጎጆ እስኪመስል ።

እገጭ ጓ ሲል መሬት ሲናጋ፣

አራሽ ገበሬ ቆላና ደጋ።

በአርሶ አደሩ ህይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ስነ ቃል የመስክ ተግባር ብቻም ሳይሆን ሰፊ ለሆነው የስነ-ጥበብ ዘርፍ ያበረከተው አስተዋጽኦ የጎላ ነው። አራሹ ገበሬም መዝግቦ ባያስቀምጣቸውም ለተተኪው ትውልድ በቃል እያስተላለፈ እስከ አሁን አቆይቷቸዋል። 

ሀሳብን የመግለጽ፣ የመንገር፣ የማነቃቃት፣ የማስተማር፣ የማሳወቅ፣ የማዝናናት ሚና ያላቸው የስነ ቃል ሃብቶች፤ ለአርሶ አደሩ የእለት ገጠመኙ ማድመቂያ ጌጦቹ ናቸው። እነዚህን ሃብቶች በጽሑፍ በማስቀመጥ ለትውልድ ቢሻገሩ ከስነ ጽሁፋዊ ጠቀሜታቸው በተጨማሪ የአርሶ አደሩን ህይወት፣ ባህልና እሴት ለማወቅ ፋይዳቸው የጎላ እንደሆነ የሰርፉ ባለሙያዎች ያሳስባሉ።

አስተያየት