ሐምሌ 16 ፣ 2013

መቋጫ ያላገኘው የመተከል እልቂት

City: Benishangul-Gumuzሰላም እና ደህንነትፖለቲካኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮች

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በምትገኘው መተከል ዞን በርካታ የጭካኔ ተግባራት ተፈጽመዋል። ይህ ጉዳይ ያበቃ ቢመስልም ግን የነዋሪዎቿ እንግልት እና ስቃይ ግን ዛሬም እንደቀጠለ ነው።

መቋጫ ያላገኘው የመተከል እልቂት

ከአዲስ አበባ በ550 ኪ.ሜ.፣ ከክልሉ ዋና ከተማ አሶሳ ደግሞ በ400 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በምትገኘው መተከል ዞን በርካታ የጭካኔ ተግባራት ተፈጽመዋል። በጅምላ ከመቀበር እስከ የተናጥል ግድያ፣ በስለት አንገት ከመቁረጥ እስከ የሰውን ልጅ ሆድ እቃ መበተን፣ የንጹሀን ሰዎችን ጥሪት ከማቃጠል እስከ ቤተሰብ መበተን፣ በርካታ የጭካኔ ድርጊቶች ተፈጽመዋል። አስደንጋጩ ክስተት ቤተሰብን ያለ አሳዳጊ አስቀርቷል፣ የቤተሰብ አባላትን በታትኗል፡፡ የመተከል ዞን የሰላም ማጣት ችግር በገሀዱ ዓለም ይታያሉ ተብለው የማይገመቱ ክስተቶችን ዐሳይቶናል። ክስተቱ የመገናኛ ብዙኃን የየዕለት ትኩረት የመሆኑ ነገር ያበቃ ቢመስልም የነዋሪዎች እንግልት እና ስቃይ ግን ዛሬም እንደቀጠለ ነው።

መተከል ትላንት

ከሐገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ የሁሉም ብሔር ተወላጆች በፍቅር የሚኖሩባት መተከል ዞን ተወዳጅ እንደነበረች በርካቶች ምስክርነታቸውን ይሰጡላታል፡፡ አሁን ላይ የቀድሞ ውበቷ ረግፎ የሚመለከቱ ታዛቢዎች ሐዘን እና ቁጭት ይፈራረቁባቸዋል፡፡ ብዙ እንቅስቃሴ የማይታይባት፣ ጸጥታ የነገሰባት ሆናለች፡፡

የመተከል ዞን ዋና ከተማ ግልገል በለስ ሲሆን የ110ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የተፋሰሱ አካላት፣ የአፍሪካ ሕብረት እና የአውሮፓ ሕብረት ሳይቀሩ በትኩረት የሚመለከቱት የህዳሴ ግድብ መገኛ ናት፡፡ ከርሰ ምድሯም በወርቅ፣ በእምነ-በረድ፣ በከሰል ድንጋይ እና በሌሎች የከበሩ ማዕድናት የበለጸገ ነው፡፡ በእርሻ ስራ ላይ ለመሰማራት ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚጓዙ ባለ ሐብቶችም ቀዳሚ ምርጫቸው ነች፡፡ መሬቷ የዘሩበትን ያበቅላል፡፡

“ነዋሪዎቿ ኢትዮጵያዊ መገለጫቸውን ያልሸረሸሩ ናቸው” የሚለው አባባል ብዙዎችን የሚያስማማ ነው፡፡ በስራም ሆነ በመዝናኛ ሕዝቦቿን የመመልከት እድል የገጠመው ሁሉ እንግዳ ተቀባይ፣ ያለውን ለማካፈል የማይሰስት ሕዝብ እንዳለ መስክሯል፡፡

መተከል ዛሬ

እንደ ሩቅ እና እንደ ብርቅ በመነገር ላይ የሚገኙት ጥሩ ነገሮች ዛሬ የሉም፡፡ ከከርሰ ምድር ማእድኗ ለመቋደስ ‹ኢንቨስት› የሚያደርጉ ባለሐብቶች ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ ዛሬ ላይ ለትርፍ የሚጓዙባት ሳትሆን ህይወትን ለማትረፍ የሚርቋት ሆናለች፡፡ ነዋሪዎቿ በግጭቱ ቁጥራቸው 2ሺህ 7መቶ በላይ የሚገመት ንጹሀን ሽማግሌዎች፣ እናቶች፣ ታዳጊዎች፣ ጡት ያልጣሉ ጨቅላ ህጻናት፣ ሀገር ተረካቢ ወጣቶችና ተማሪዎች ተሰውተዋል። ከ100ሺህ በላይ ነዋሪዎች ሀብታቸውን አጥተው ተፈናቅለዋል፡፡ ከ2ሺህ 5መቶ በላይ ሰዎች መሞታቸው መኖራቸው ሳይረጋገጥ ጠፍተዋል፡፡ ማሳቸው ጾሙን አድሮ ምጽዋት ጠያቂ ሆነዋል፡፡ ክስተቱ 2ኛ ዓመቱን ሊያስቆጥር ጥቂት ጊዜያት ብቻ ይቀሩታል፡፡

የሁሉም የዞኑ እና የክልሉ ህዝብ ተደጋጋሚ ጥያቄ የውጥንቅጡን ጊዜ ማብቂያ የሚናፍቅ ነው፡፡ ምንም እንኳን ጉዳዩ ፖለትካዊ ይዘት ያለው ቢመስልም መልኩን ቀይሮ ብሄርን፣ አከባቢንና የቆዳ ቀለምን መሰረት አድርጎ የሚፈመው ጥቃት የእርስ በእርስ ጦርነት አስመስሎታል።

ከባድ እልቂት ያስከተለው ግድያ እንዴት ተጀመረ ለሚለው ጥያቄ የአካባቢው ነዋሪዎች ሲመልሱ ማኅበራዊ ሚድያው የማነሳሳት እና የማባባስ ሚናውን እንደሚወስድ ይናገራሉ፡፡ እንደ ታዛቢዎቹ ገለጻ የመተከል ዞንን ‹ጂኦግራፊያዊ› አቀማመጥ የማያውቁ፣ ስለ ህዝቦቿ መስተጋብር ምንም ዐይነት ግንዛቤ የሌላቸው ሰዎች የግጭቱን እሳት ለኩሰዋል፡፡ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ በሐገር ሰላም እና በሰዎች ሕይወት ላይ ቆምረዋል ስለተባሉት ሰዎች ሁሉም የየራሱ አረዳድ አለው፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በጋራ የሚስማሙበት ጉዳይ ግን አነሳሾቹ ብዙኃንን የማይወክሉ መሆኑን ነው፡፡ በብሄር ካባ ተከልለው ለግል ጥቅማቸው የሚተጉ ስለመሆናቸው የሚበዛው አስተያየት ሰጪ ሐሳብ ነው፡፡

በዚህ መልክ የተጀመረው የመተከል ግጭት በሽፍታ ቡድኖች እስከ መደራጀት ደርሶ በየጫካው በመመሸግ ከህፃን እስከ አዋቂ ጾታና ዘርን ሳይለይ ለመናገር በሚከብድ ሁኔታ ዜጎች ወጥተው ሳይመለሱ አስክሬናቸው በየጫካው እንዲበሰብስ ሆኗል።

የህዝብ ተሽከርካሪዎችን ጫካ ላይ በማስቆም ሙሉ ተሳፋሪውን በስለትና በመሳሪያ ከመጨፍጨፍ ጀምሮ በተናጠል በእርሻ ማሳዎች ላይ ያሉትን አርሶ አደሮች፣ ከዚህም ባለፈ ንፁሀን ዜጎችን ቤታቸው እንደተቆለፈባቸው የተቃጠሉበት ዘግናኝ ግድያዎች ተፈዕሞበታል።

ኮማንድ ፖስት

በኮማንድ ፖስት የሚመራው የመተከል ዞን የፀጥታ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ የዞኑን እንቅስቃሴ ቢያስቆምም በኮማንድ ፖስቱብርቱ ትግል በርካታ የሽፍታ ቡድኑ አባላትን በመደምሰስ እጃቸውን እንዲሰጡ ቢደረግም ቀሪዎቹ ግን ዛሬም ከመግደል አልቦዘኑም።

በዚህ ኮማንድ ፖስት ከተሠሩ መልካም ስራዎች መካከል የሽፍታ ቡድን አመራሮች ከክልሉ መንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት እንዲፈራረም እና ሕብረተሰቡ ወደ ቀድሞው ሰላሙ እዲደመለስ የተደረገው ጥረት የሚጠቀስ ቢሆንም ይህም ውጤት ማሳየት አልቻለም።

የሽፍታው ቡድን ካቀረባቸው መደራደርያ መስፈርቶች መካከል ቀዳሚው የሥልጣን ቦታ እንዲሰጥና በተለያዩ የክልሉ መቀመጫዎች ላይ ቦታ እንዲሰጣቸው ሲሆን ይህ ተፈፃሚ እንዲሆን የክልሉ መንግሥት ከሽፍታው አመራሮች ጋር የሰላም ስምምነት ተፈራርሞ ከ100 በላይ የወረዳና የዞን እንዲሁም የክልል የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ቢያስቀምጥም ጉዳዩ ግን ውጤት ሊያመጣ አልቻለም።

ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የሰላም ስምምነት የዞኑን ሰላም ይመልሳል ቢባልም ከዚህ የስምምነት ፊርማ ማግስት በቁጥር ያልተገለፁ በርካታ ንፁሀን ሰዎች በተሽከርካሪዎች ላይ፣ በጫካ፣ በመንገድ እና በቤታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ሞተዋል።

ችግሩን የመፍታት ጥረት

ችግሩ እንዲፈታ ሕብረተሰቡ በተደጋጋሚ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር ዐቢይ እንዲወያዩበት ጠይቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴሩም ወደ ስፍራው በማቅናት ከህዝቡ ጋር ቢወያይም ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ወደ አዲስ አበባ በተመለሱ በሰዓታት ልዩነት ከ150 የሚበልጡ ዜጎች ተገድለዋል።

በተመሳሳይም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከሁለትና ሦስት ጊዜ በላይ ወደ ስፍራው በማቅናት ተወያይተዋል፡፡ የከፍተኛ አመራሮቹ ውይይት የዜጎች ሞት አላስቆመም፡፡ ዛሬም በስፍራው የግድያ ዜና የየእለት ክስተት ነው፡፡

ከዚህ በላይ በመከላከያው የሚመራው የዞኑ ኮማንድ ፖስት በሰላም እጃቸውን ለመንግሥት የሰጡ ከአንድ ሺህ በላይ የሽፍታው ቡድን አባላትን ለሁለት ሳምንታት የተሀድሶ ስልጠና ቢሰጥም ዞኗ ግን ዛሬም እንደ ትላንቱ ሰሏሟ ሊመለስላት አልቻለም።

ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ የሚገኘውን ግድያ ለማስቆምና ለመከላከል የሀገር መከላከያ ሰራዊት ህዝቡን በባህላዊ መንገድ በማስታረቅ ሊፈታው ሞክሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ተደጋጋሚው ጥረት እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ያልተሳኩ ሙከራዎች ሳይሳካ ቀርቷል፡፡  

አልሆን ሲል ሚሊሻዎችን መልምሎ በማሰልጠን ቢያስታጥቅም ከጊዜ በኋላ አብዛኛው ሚሊሻ በተናጠል እየተገደለ የታጠቀውን መሳርያ ተቀምቷል። ይህም አልሆን ሲል አዲስና ነባር የታጠቁ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳርያቸውን እንዲመልሱ ተደረገ። ይህ ጉዳይ ደሞ ይባስ ብሎ ሕብረተሰቡን ለከፋ ስጋት ከመዳረግ ውጪ ውጤት ሊያሳይ አልቻለም።

በአጠቃላይ አማራጭ ይሆናሉ የተባሉ አማራጮች ሁሉ በዞኑ ተሞክረዋል። ግን ዛሬም የመተከል ዞን ሰላሟን አላገኘችም፣ ንጹሃን ሳይገደልበት ያደረበት ቀን የለም ማለት ይቻላል።

ወደፊትስ

ከ150 ሺህ በላይ የሚገመቱ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከሥራና ከእርሻ ማሳዎቻቸው ተፈናቅለዋል። የምግብ ዋስትና የነበረው ምርታቸው በእሳት ጋይተዋል። ዛሬ ላይ መታረስ የሚገባቸው የእርሻ ማሳዎች ሳይዘራባቸው ፆም አድሯል። ይህ ሁኔታ የሚያሳየው በመተከል ዞን ያሉ ነዋሪዎች በቀጣዩ ጊዜያት ለከፋ ረሀብና ችግር የሚጋለጡ መሆናቸውን ነው።

ይህ ትንበያ የነገውን የቤትስራ ያሳያል፡፡ በጥይት እና በስለት ካለቀው ሰው በላይ በረሃብ የሚያልቅበት ስጋት ከፊት ለፊታችን አለ፡፡ መንግሥት፣ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች እና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግሩ ተከስቶ እሳት ለማጥፋት ከመሮጥ ሳይቃጠል በቅጠል የሚልበትን መላ በጋራ ሊመክር ይገባል፡፡ ከዚህ በፊት የተሞከሩት ሙከራዎች ያጎደሉት ተገምግመው፣ ጥፋታቸው ታርሞ በድጋሚ መፍትሄ ሊፈለግ ግድ ነው፡፡

አስተያየት