ግንቦት 1 ፣ 2014

የዓሳ ማስገሪያ ‘ዝግ ወቅት’ ባለመከበሩ በጣና ኃይቅ የተፈጠረው ከፍተኛ የምርት እጥረት

City: Bahir Darማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

የአሳ ማስገር ዝግ ወቅት ማለት በዓሳዎች የተፈጥሮ ርቢ ወቅት በደንብ መራባት እንዲችሉ ያንን ጊዜ ምንም አይነት የዓሳ ማስገር ስራ ሳይሰራ ማሳለፍ የሚገባበት ወቅት ማለት ነው

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

የዓሳ ማስገሪያ ‘ዝግ ወቅት’ ባለመከበሩ በጣና ኃይቅ የተፈጠረው ከፍተኛ የምርት እጥረት
Camera Icon

Credit: Michael Adinew

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዓሳ ተመጋቢው ቢጨምርም በአንፃሩ የጣና ሃይቅ ከስፋቱ አንፃር የሚጠበቅበትን የዓሳ ምርት እየሠጠ አለመሆኑን አዲስ ዘይቤ ካነጋገራቸው በሃይቁ ዙሪያ ከሚገኙ አሳ አስጋሪዎች መረዳት ችሏል። 

አቶ አበበ ፋንታሁን የክልሉ የእንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የዓሳ ቴክኖሎጂ ባለሙያ ሲሆኑ በጣና ሃይቅ በቂ የዓሳ ምርት አለመኖሩን ይናገራሉ። ሃይቁ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ የምርት ዕጥረት እያሳየ መሆኑን ገልጸው በተለይ እንደሌሎች ሃይቆች በቅዝቃዜ ወቅት እጥረቱ ቢባባስም በሌሎች ወቅቶችም በቂ ምረት አይገኝም ብለዋል።

ባለሙያው እንደሚናገሩት በዓሳ ሀብት ልማት አስተዳደር ውስጥ ለዓሳ ማስገር ዝግ የሆኑ ወቅቶች አሉ። “እንደ ጣና ሃይቅ ተጨባጭ ሁኔታ ከግንቦት አጋማሽ እስከ ሃምሌ አጋማሽ ያለው ጊዜ የዓሳ ርቢ ወቅት በመሆኑ በሃይቁ ላይ ዓሳ ማስገር አይመርከርም” ይላሉ።

በጣና ሃይቅ የሚገኙ ህገ ወጥ ዓሳ አስጋሪዎች በእነዚህ በተከለከሉ ወቅቶች ዓሳ ስለሚያሰግሩ ሃይቁ በቂ ምርት አንዳይሠጥ እንደሚያደርጉት በመግለፅ የችግሩን መሰረታዊ ምክንያት አቶ አበበ ያስረዳሉ። 

የጣና ሀይቅ ዙሪያን ከሚያዋስኑት አስር ወረዳዎች የተውጣጡ ከአምስት ሽህ በላይ ዓሳ አስጋሪዎች ይገኛሉ። ይህ ማለት አልፎ አልፎ ለመዝናናት እና ለሌሎች ጉዳዮች ዓሳ የሚያሰግረውን ሳይጨምር ነው። እነዚህ ሁሉ አሳ አስጋሪዎች ህጉን አክብረው ካልሰሩ በሃይቁ ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት ባለሙያው ህገ ወጥ ዓሳ አስጋሪዎች በዓሳ ምርቱ ላይ ሁለት አይነት ተፅዕኖ እንደሚኖራቸው ይናገራሉ። 

አንደኛ ዓሳ ማስገር በተከለከለበት የዓሳ ዕርባታ ወቅት ዓሳ ማስገራቸው በምርት ዕድገቱ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ሲኖረው ሁለተኛ ደግሞ አብዛኞቹ አስጋሪዎች “ከደረጃ በታች የሆነ ማስገሪያ መረብ ስለሚጠቀሙ ለምግብነት ያልደረሱ ትናንሽ ዓሳዎችን በርቢ ወቅት ማስገራቸው ተገቢ አይደለም” ይላሉ አቶ አበበ። 

እንደ ባለሙያው ገለጻ ይህ ህገወጥ ድርጊት በሃይቁ የዓሳ ምርትና ምርታማነት ላይ ቀጥተኛ የሆነ የጎላ ተፅዕኖ እያስከተለ ይገኛል።

አቶ መሃመድ ኡመር በባህር ዳርና ሌሎች የውሃ ምርምር ማዕከላት ውስጥ የዓሳ ግብርና ተመራማሪ ሲሆኑ የአቶ አበበን ሀሳብ ይጋራሉ። “ለምርቱ መቀነስ መሰረታዊ ችግር የዓሳ ማስገር ዝግ ወቅት አለመከበር መሆኑ ሲሆን ይህም በርቢ ላይ ያሉ ዓሳዎች በዝግ ወቅቱ በሚካሄድ ዓሳ ማስገር ይጠፋሉ” ብለዋል።

ተመራማሪው ሙያዊ ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ “በተለምዶ ለምሳሌ ቆሮሶ ዓሳ በሳይንሳዊ መጠሪያው /Nile Tilapia/ በርባታ ወቅት ወይም ዕርባታውን ሳይጨርስ በመሰገሩ እራሱን እስከ አንድ ሽህ ወደሚጠጋ ቁጥር ሊያራባ ይችል የነበረውን ዕድል ያሳጣዋል” በማለት ይገልፃሉ። ይህ የዓሳ ዝርያ በጣና ሀይቅ የሚገኝ ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመጥፋት ላይ እንደሚገኝ  ተመራማሪው ይጠቁማሉ።

የአሳ ማስገር ዝግ ወቅት ማለት በዓሳዎች የተፈጥሮ ርቢ ወቅት በደንብ መራባት እንዲችሉ ያንን ጊዜ ምንም አይነት የዓሳ ማስገር ስራ ሳይሰራ ማሳለፍ የሚገባበት ወቅት ማለት ነው። ይህ በሁሉም የውሃ አካላት አካባቢ የተለመደ አሰራር ነው። ነገር ግን የውሃ አካሉ ምንም አይነት የዓሳ ምርት እጥረት ከሌለበት የአሳ ማስገር ዝግ ወቅት ላያስፈልግ ይችላል። የውሃ አካላቱ አንደሚገኙበት አካባቢ ዓሳ ማስገር የሚከለከልበት ወቅትም የተለያየ ሊሆን ይችላል።

አብዮት እንዳለው ከአስር ዓመት በላይ በጣና ሐይቅ ላይ አሳ በማስገር ስራ ተሰማርቶ ራሱንና ቤተሰቡን እያስተዳደረ ይገኛል። ዓሳ በጣና ሃይቅ እንደልብ እንደማይገኝ የሚናገረው አብዮት ለዚሀም ምክንያቱ “ህገ-ወጥ ዓሳ አስጋሪዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው ነው” ይላል። እንደ አብዮት አስተያየት እነዚህ አስጋሪዎች ለምግብነት ያልደረሱና የርቢ ወቅታቸውን ያልጨረሱ ዓሳዎችን በማስገር ምርቱ አንዲቀንስ ያደርጋሉ።

“ልምድ ያለው ዓሳ አስጋሪ ስለ ዓሳ ማስገር ዝግ ወቅት እና ምን አይነት መረብ መጠቀም እንዳለበት ግንዛቤው አለው ብዬ አምናለሁ” ይላል አብዮት። ነገር ግን አብዛኛው ዓሳ አስጋሪ በሀይቁ ዙሪያ የሚኖር በመሆኑና ሌላ አማራጭ የገቢ ምንጭም ስለሌለው በህገወጥ ተግባሩ ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ አብዮት ይናገራል።     

ችግሩን ለመቅረፍ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት በተመለከተ ህገ-ወጥ ዓሳ አስጋሪዎችን ወደ ህጋዊ አሰራር እንዲመጡ በማህበራት የማደራጀት ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉ የዓሳ ቴክኖሎጂ ባለሙያው አቶ አበበ ይገልፃሉ። የክልሉ የእንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ በተጨማሪም ወደ ህጋዊ አሰራር ያልገቡትን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራም ያከናውናል። ቁጥጥሩ የሚደረገው በሃይቁ ዙሪያ ከተሰማሩ ሰራተኞች እና ህጋዊ አስጋሪዎች ጋር በመተባባር እንዲሁም በሀይቁ ዙሪያ በአካል በመገኘት ነው። 

የዓሳ ግብርና ተመራማሪው አቶ መሃመድ ኡመር በበኩላቸው፣ ባህር ዳር ዓሳ እና ሌሎች የውሃ ውስጥ ምርምር ማዕከል  በውሀ ጥራት እና በዓሳ ዝርያዎች ላይ ሰፊ ምርምር እያደረገ እንደሚገኝ ያስረዳሉ። በዚህም ዋና የምርምር ትኩረት የተሰጠው ጣና ሃይቅ በመሆኑ ዝርያቸው በመጥፋት ላይ ያሉ የዓሳ ዝርያዎችን በሰው ሰራሽ መንገድ በማራባት፣ ማለትም የአሳ ጫጩት ከሃይቁ ውጭ በማራባት እና ወደ ሃይቁ በተደጋጋሚ በመጨመር ችግሩን የመቀነስ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ መሃመድ ይገልፃሉ።

በተጨማሪም የማስገሪያ መረቦች ከውጭ የሚመጡ በመሆናቸው የጥራትና ደረጃ መመዘኛ መስፈርት ቢዘጋጅላቸው መልካም መሆኑን ባለሙያው ምክራቸውን ለግሰዋል። ለተለያየ የዓሳ ማስገር ስራ የሚውሉ መረቦች ያሉ ሲሆን ህገወጥ አስጋሪዎች የሚጠቀሙት መረብ መጠኑ አነስተኛና ዝቅተኛ ጥራትና ደረጃ ያለው በመሆኑ እድገታቸውን ያልጨረሱ ትንንሽ አሳዎችን ይይዛል።

የጣና ሀይቅ ለቱሪስት መዳረሻ ሆኖ ከማገልገሉ በተጨማሪ በሀይቁ ዙሪያ ለሚገኙ ከአስር በላይ ወረዳዎች በዓሳ ግብርና ተጠቃሚ እያደረገ አንደሚገኝ ከክልሉ የእንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፌያ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። 

ወደ 27 የሚሆኑ የዓሳ ዝርያዎችን የያዘው የጣና ሃይቅ ካሉት ዝርያዎች ወደ 20 የሚሆኑት ሀገር በቀል ናቸው። በተባበሩት መንግስታት የምግብና ግብርና ድርጅት (FAO) መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ካላት የውሃ አካላት የሚገኘው የአሳ ምርት ከፍተኛውን መጠን ምርት በቀዳሚነት የሚያስገኙት ጣና፣ ዝዋይና ላንጋኖ፣ ጫሞ እና አባያ ሃይቆች ሲሆኑ ከነዚህም 1000 ቶን ዓሳ የማምረት አቅም በመያዝ ጣና ሃይቅ ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል።   

አስተያየት