ነሐሴ 22 ፣ 2013

ኢትዮጵያ ወዴት...?

City: Bahir Darፖለቲካ

በኢትዮጵያ ሐገረ መንግስት ወቅታዊ ሁኔታ ለተደቀነባት የመፍረስ የስጋት አደጋን የሁኔታ ትንተናዎች ውስጥ የምናገኛቸው ተያያዥ ተግዳሮቶች እና አስቻይ ሁኔታዎች በርካታ ናቸው። እነዚህ የሚገፋፉ ኃይሎች የውስጠ ፖለቲካው ተቋማዊ አሰራርና...

Avatar: Ayele Addis
አየለ አዲስ

Ayele Addis is an award winner Journalist, Journalism, Trainer, Researcher, and Media & Communication Development Consultancy for Thomson Reuters' Foundation, Africa News Channel, Amhara Media, and Journalists Association. Ethiopian Mass Media Action (EMMA News), ARMA Media Production.Woldia University and Bahir Dar University and founder of Journal of Ethiopian Media and Communications.

ኢትዮጵያ ወዴት...?

በኢትዮጵያ ሐገረ መንግስት ወቅታዊ ሁኔታ ለተደቀነባት የመፍረስ የስጋት አደጋን የሁኔታ ትንተናዎች ውስጥ የምናገኛቸው ተያያዥ ተግዳሮቶች እና አስቻይ ሁኔታዎች በርካታ ናቸው። እነዚህ የሚገፋፉ ኃይሎች የውስጠ ፖለቲካው ተቋማዊ አሰራር እና ውጫዊ ብለን ለሁለት ከፍለን እናየዋለን።

እነዚህ ሐገር አፍራሽ የይሆናል ኩነቶች እውን ሊሆኑ የሚችሉት እነዚህ የሚገፋፉ ኃይሎች አንዱ ከሌላው ጋር በሚኖረው መደጋገፍና ግጥምጥሞሽ ነው ሲል በ2012 ዓ.ም የብልፅግና ፓርቲ ያካሄደው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የግምገማ ለከፍተኛ አመራሩ የተዘጋጀው ሰነድ ያመለክታል። የአገሪቱን የወደፊት ቁመና በመወሰን ረገድ ቢያንስ ሶስት መሰረታዊ የሚገፋፉ ኃይሎች ሐገሪቱን ለማፍረስ የሐገሪቷን ፈተና እንደሆኑ መለየት ይቻላል፡፡ እነዚህም ‹‹አንደኛ በፓርቲው አመራር መካከል ሊኖር ይገባው የነበረው አገራዊ የጋራ እሴት መዳከሙና መሸርሸሩ የፈጠረው የብሔር ጽንፈኝነት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ከመጣው የሕዝብ ቁጥር ጋር ያሻቀበው የሥራ ፈላጊ ወጣት ብዛትና የኑሮ ውድነት እያባባሰ የመጣው የኢኮኖሚ ቀውስ ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ በብሔር ጽንፈኝነት መሠረት ላይ ቆሞ የኢኮኖሚ ቀውስ ሲያይል ጸንቶ መቆም ያልቻለው ድርጅታዊና መንግሥታዊ የሥራ ተልዕኮ አፈጻጸም መሽመድመድ ናቸው።››

ብልፅግና በቀዳሚ ሰነዱ ኩነት አንድ ብሎ የሐገሪቱ ፈተና ያስቀመጠው የእርስ በርስ እልቂት ነው፡፡ “የብሔር ጽንፈኝነትና የሃይማኖት ግጭቶች ይጦዛሉ፤ የኢኮኖሚ ቀውስ ይባባሳል፤ ድርጅታዊና መንግሥታዊ ተቋማት ይፈረካከሳሉ፤ በመጨረሻም የእርስ በርስ እልቂት ይከሰታል” ሲል ገምግሟል፡፡ (ብልፅግና፣ 2012)

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በርካታ ኃይማኖቶችና ብዙ አመለካከቶች ያሉባት ሀገር ነች። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታና በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊኖር የሚችለውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ስንመለከተው የብሔር ጽንፈኝነት የሀገሪቱ ዋነኛ ፈተና ነው።

የብሔር ጽንፈኝነት ለዘመናት በመንግሥት መዋቅር ድጋፍ ጭምር በልሂቃን እየተቀነቀነ የተገነባ እንጂ የአጭር ጊዜ እድሜ ያለው ጥያቄ አይደለም። አሁን በለውጡ ሂደት የተፈጠረን ቀዳዳ እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም የግለሰብ የፖለቲካ ነጋዴዎች የብሔር ጽንፈኝነትን በሕዝቡ ውስጥ ዘልቆ ገብቶ ገዥ ሐሳብ እንዲሆን ማድረግ ከቻሉ ሀገሪቱን ወደ መሰነጣጠቅ ሊወስዷት ይችላሉ፡፡ ምንም እንኳን የብሔር ጽንፈኝነት በአገሪቱ ላይ የእርስ በርስ እልቂት አደጋ የጋረጠ ቢሆንም ይህ የሚገፋፋ ኃይል ብቻውን የሐገሪቱ ክስተት  አንድነትን ሊያመጣ እንደሚችል እንደ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት እና የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰፊ ማብራሪያዎች ማስታወስ እንችላለን። ይልቁንም ያለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መባባስ፣ ሥር እየሰደደ የሄደው የዝርፊያ ልማድ ጠንክሮ መቀጠል እና የሥራ ተልዕኮ አፈጻጸም መሽመድመድ ሲደመሩበት አገሪቷን ወደ እርስ በርስ እልቂት ይወስዳታል ሲሉ አቶ ልደቱ አያሌው "አሃዳዊ ሥርዓት እና ብሔር ተኮር ፌድራሊዝም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሒደት በፅንሰ-ሐሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ተፈትነው ወድቀዋል" ሲሉ ባብራሩበት ፅሁፋቸው ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህ ከሚገፋፉን ኃይሎች መካከል ግን የብሔር ጽንፈኝነት ፊታውራሪ ሆኖ እናገኘዋለን። በመቀጠል ደግሞ የኢኮኖሚ ቀውሱ ይከተላል።

ኩነት አንድ ከተፈጠረ በተሰነጣጠቁ የወረዳ፣ የዞንና የክልል ግዛቶች ትንንሽ መንግሥታት ይፈጠራሉ። እነዚህ ትንንሽ መንግሥታት ደግሞ ወደ ለየለት ትርምስና ጦርነት ውስጥ በመግባት በሀገሪቷ ታይቶ የማይታወቅ እልቂት ሊከሠት ይችላል። በአናቱ ላይ የብሔር አቀንቃኞች ብሔርተኝነትን እንደ ነዳጅ ይጠቀሙበታል።

ኢትዮጵያ ለዚህ ክፉ ዕጣ ከተዳረገች መሰነጣጠቋና የእርስ በእርስ ጦርነቶቿ ማቆሚያ አይኖራቸውም፡፡ የዚህ ምክንያቱ የሀገሪቱ መሠረታዊ ሥሪትና ያለችበት ሁኔታ የባልካናይዜሽንና የዘር ፍጅት ሰለባ ከሆኑ ሌሎች ሀገራት በእጅጉ የተለዬ ስለሆነ አይደለም። ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ልዩ የሚያደርጋት ታሪካዊ ሂደቶችን ያሳለፈች ሀገር ናት። በዚህም ምክንያት የታሪኳን ውስብስብነት ያክል የተወሳሰበና መውጫ ከሌለው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ልትገባ ትችላለች። ውስብስብነቱን ከሚፈጥሩትና ከሚያጠናክሩት ዋነኛ ምክንያቶች መካከልም፡-

1ኛ. አሁን የተካለለው የወረዳ፣ የዞንና ክልል ወሰን የብሔሮችን መብት ለማስከበር በሚያመች መልኩ ለአስተዳደር የተካለለ እንጂ ከድርጅታችን በፊት የነበረና የሚታወቅ ድንበር አልነበረም። በእርግጥ የብሔር ጥያቄ ፖለቲከኞች የፈጠሩት ተራ ጉዳይ ሳይሆን አፋጣኝ መልስ የሚሻ ጉዳይ እንደ ነበር አያከራክርም። ኢትዮጵያውያን በአንድ ሀገር የኖርን ሕዝቦች ነን፤ እርስ በርሳችን በብዙ ነገሮች ተሠናስለናል፤ ተዛምደናል። በዚህም የተነሣ ይህን ሕዝብ እዚያ እና እዚህ ብሎ ለመለየት አስቸጋሪ ነው። ሌላ በኩል የብሔር መብት ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የማይችል ቢሆንም ብሔርን ከወሰን መጨመርና መቀነስ ጋር አስተሣሥሮ ማየት ግን ዴሞክራሲያዊ አመለካከት አይደለም።

ብሔርን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ አደረጃጀትና እንቅስቃሴ በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥም የቅርብ ጊዜ ክሥተት ነው። በአጠቃላይ ከ60ዎቹ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛ ማጠንጠኛ ከብሔር ይልቅ አካባቢያዊነት ነበር። በቀደመው ዘመን ደግሞ በሰው ልጆች ታሪክ የግጭትም ሆነ የፖለቲካ አሰላለፍ ዋነኛ ምንጭ ኃይማኖት ነበር። ከዚያም ሲያልፍ በመሪዎች የግዛትና የአስገባሪነት ዐቅም ልክ የተመሠረቱ አካባቢያዊነቶች ናቸው።

በሀገሪቱ መጠነ-ሰፊ የህዝብ እንቅስቃሴዎችና የማስገበር ዘመቻዎች በየጊዜው ሲካሄዱ ስለኖሩ የሃይማኖት፣ የብሔር እና የአካባቢያዊነት መሥመሮች የተደበላለቁና ወጥነት የሌላቸው ነበሩ። ከአንድ ቦታ ፈልሶ ሌላ ቦታ ሠፍሮ ለተከታታይ ትውልድ ከመቶ ዓመታት በላይ መኖር የተለመደ ነው። ነባር ሕዝቦች ቋንቋና ባሕላቸው በሚያጎራብቷቸው ከአንድ በላይ የሆኑ ኃያል ሕዝቦች ቋንቋና ባሕል ተጽእኖ ስር በመውደቅ አሻሚ ማንነት መፍጠራቸው የታሪክ ሂደት ነው። ከአንድ በላይ ለሆኑ አንዳንድ ብሔሮችም በነባር ቦታቸው ካለው ሕዝባቸው ቁጥር ያልተናነሰ የብሔሩ አባል በመላ ሀገሪቱ ተበትኖ ይኖራል።

በመሆኑም በአንድ በኩል የብሔሮች የመሬት ጉዳይ ለብዙ ታሪካዊ ንትርኮች፣ ፍልስፍናዎች፣ በተስፋፊዎች ተፈናቅያለሁ እና የተበድያለሁ እሰጥ አገባዎች የተጋለጠ ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል የሃይማኖትና የአካባቢያዊነት ግጭቶች አመች ሁኔታ ሲያገኙ ሊፈነዱ ይችላሉ። ይህም ሁኔታ ኢትዮጵያን በብዙ የብሔር፣ የሃይማኖትና የአካባቢ ስብጥሮች የተከፋፈለች ሀገር ያደርጋታል። የክፍልፋዮችና የስብጥሮች መብዛት ደግሞ ምንም እንኳን ለጦርነት መቀስቀስ ያለው ሚና ዝቅተኛ ቢሆንም ጦርነት አንዴ ከተቀሰቀሰ በኋላ ፍጅቱን በማባባስ፣ ማለቂያ ቢስ በማድረግ እና ወደዘር ፍጅትነት በመቀየር ረገድ ግን ትልቅ ሚና ይጫወታል። ሐገሪቱ አሁንም ክልል እና ዞንን ከሚጠይቁ የፖለቲካ ሽፋን ቁማርተኞች አልተላቀቀችም፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ግጭቶች የሚነሡት ከክፍልፋይ መብዛት ይልቅ በጥቂት ቡድኖች መካከል ባለ የጽንፈኝነት አመለካከት ነው። ይሁን እንጂ ግጭቶቹ አውዳሚና አሰቃቂ የሚሆኑትና የዘር ፍጅቶችን የሚፈጽሙት ክፍልፋዮች ሲበዙ ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያ በጥቂት የጎበዝ አለቆች ፉክክር መካከል በሚነሣ ጠብ ማለቂያ ወደሌለው ዕልቂት ልታመራ ትችላለች።  

2ኛ. ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች ሀገር በመሆኗ የሕዝቦች ትሥሥር በቅኝ ገዢዎች ከፋፋይ አጀንዳ አልተስተጓጎለም። ለምሳሌ ጣሊያኖች በአዲስ አበባ ላይ ቀለምን መሰረት ያደረገ ከፋፍሎ የማስፈር የከተማ ዕቅዳቸውን ሕዝቡ በእምቢ ባይነት ጥሶ በመደባለቅና አብሮ በመኖር አክሽፎታል። ቅኝ ገዢዎች በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ሲገነቡት የኖሩት ከፋፋይ አጀንዳ በብሔሮች መካከል የፈጠረው የረጅም ጊዜ ጥላቻና ቁርሾ በኢትዮጵያ ውስጥ ጎልቶ የሚታይ አይደለም። የጥላቻ ንግግሮችና ዝንባሌዎች ቢኖሩም እንኳን በልሂቃን ደረጃ ያሉ እንጅ በሌሎች ሀገራት እንዳየነው በሕዝብ መካከል ተካረው የሚስተዋሉ አይደለም።

በአፍሪካ የተካሄዱ አሰቃቂ የዘር ፍጅቶች ሁሉ የቅኝ ግዛት ውጤት ናቸው። በአህጉራችን ቅኝ ገዢዎች አስቀድመው በሕዝቡ መካከል ያሠመሩት የጥላቻ መሥመርን መሠረት አድርገው በህዝቦች መካከል ግጭቶች ተነስተዋል፤ በርካቶችም ለእልቂት ተዳርገዋል። በእኛ ሀገር ሁኔታ ግን ይህ ዓይነት የጥላቻ መሥመር የለም። የብሄር ሊህቃኖች መሠሪ መጣጥፎችንና መጽሐፎችን በመጻፍ አጀንዳውን ሊያሰርፁብን ቢሞክሩም በሕዝባችን መካከል ይህ ዓይነት ጥላቻ አልተፈጠረም።

በሕዝቡ መካከል ጥላቻና ቁርሾ አለመኖሩ ለሀገራችን ሰላምና አንድነት አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ የብሔር ነጋዴዎች የጥላቻ መርዝ መርጨታቸውንና በስግብግብነት ሀገር ማመሳቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ የእኛ ፍጅት ከሌሎቹም የሚከፋ ይሆናል። ምክንያቱም ሕዝቡ መካከል ግልጽ መሥመር ስለሌለና የሚፋጀው ወገንም በቅጡ ስለማይተዋወቅ፣ በተጨማሪም ሕዝቡ እጅግ ስለተዋለደ ትርምስምሱ ለምናብ የሚከብድ ነው። የቤተ ዘመድና የቤተሰብ ፍጅት ቅርጽና ውል በሌለው መልኩ መከሠቱ የማይቀር ነው።

የብሔር ፍጅቱ ራሱን ችሎ የሚከሠት ላይሆን ይችላል። በተለይም በቀጥታ በተደራጀና በተሰላ አኳኋን ከተካሄዱት የብሩንዲ፣ የሩዋንዳ ወይም የአይሁዶች ሆሎካስት ጋር የሚመሳሰል አይሆንም። ይልቁንም በሀገራት መካከል በሚደረግ ጦርነት ውስጥ በሲቪሎች ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዳለው ሁሉ ብሔርን ሰበብ ያደረጉ ጦርነቶችም ዐቅም ሲያንሳቸውና ጥላቻው እየከረረ ሲመጣ ሲቪል ወደማጥቃት ይዘዋወራሉ። ይህም ጦርነትን ተከትሎ የሚፈጸመው ጦርነት መር የብሔር ፍጅት ቀስ በቀስ ሙሉ ለሙሉ ወደ ዘር ፍጅት ሊያድግ ይችላል።

እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ነገር የእርስ በርስ ጦርነቱና የዘር ፍጅቱ በአንድ በኩል ተመጋጋቢ ቢሆንም በሌላ በኩል ተገፈታታሪ ናቸው። በጦርነት ውስጥ የተጋጣሚዎቹ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ዐቅማቸውም የጦርነቱን ሁኔታ ስለሚወስነው ብዙ ትጥቅና ገንዘብ ባላቸው ወገኖች መካከል እጅግ አውዳሚ ጦርነት እንጅ የዘር ፍጅት የመኖሩ አጋጣሚ አነስተኛ ነው። በሌላ በኩል ትጥቅና ገንዘብ ካጠራቸው ደግሞ ጦርነቱ ወደ ዘር ፍጅት የማደጉ አዝማሚያ ከፍተኛ ይሆናል። በሀገራችን ሁለቱም አጋጣሚዎች ተፈራርቀው የመከሠታቸው ዕድል ከፍተኛ ነው። 

ስለዚህም በአንድ በኩል ልሂቃን የሚዘሩት ጥላቻና የስግብግብነት ፖለቲካ በሌላ በኩል የሀገሪቱ ታሪክ ድብልቅና የራስ ገዝነቱ ጉዳይ በቃል ከምንለው በላይ ውስብስብ በመሆኑ የባልካን ሀገራት ዕጣ ፈንታ (ባልካናይዜሽን)፣ የብሔር ፍጅት፣ እና የጎረቤቶቻችን ዕጣ ፈንታ በአንድ ላይና በተሰባጠረ መልኩ ሊከሠትብን ይችላል። ይህም ደም መፋሰሱ እጅግ ኢ-ተገማችና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ ገብነት እንኳን የማይመች ያደርገዋል።

በአፍሪቃ ቀንድ ካለው አጠቃላይ ምስቅልቅል ጋር ሲደመር ጉዳዩ እጅግ ውስብስብ ይሆናል። ይህም የባልካን መንግሥታት ተበጣጥሰው ሁሌም በጦርነትና በእልቂት ሲያሳልፉ “ጦርነት ባሕላቸው ነው” የሚሉ ጥናታዊ ጽሑፎች እስከመቅረብ የደረሰባቸውን ዕጣ ፈንታ እንድንጋራ ያደርገናል። በተለይም የቀጣናውንና የሀገራችንን የተፈጥሮ ሀብት ለመቀራመት የሚሹና በኢትዮጵያ መበተን ላይ ጥቅማቸውን የሚያሰሉ ሀገራት እንደፈለጉ ሲጫወቱብንና እሳቱን እፍ እያሉ ዘላለም ሲያባሉን ይኖራሉ።

የእኛን ሁኔታ ከጎረቤቶቻችንም ይሁን ከባልካን መንግሥታት የባሰ ኢ-ተተንባይ የሚያደርገው የብሔሮች ትሥሥር፣ ግልጽ ያልሆነ የራስ ገዝነት ታሪክ እና በከፊል የተገነባው ሀገረ መንግስት ጉዳይ ነው። በከፊል የተገነባ ሀገረ መንግስት ላይ የሚደርስ መሰነጣጠቅ የሚፈጥረው ፍጅት ለአእምሮ የሚከብድ ነው። ከዚህ ሁሉ ባሻገር ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና የብዙ የማሕበረሰብ ማንነቶች ስብጥር ሀገር በመሆኗ የእርስ በርስ እልቂቱ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም።

በመሆኑም አሁን እየተስተዋሉ ያሉት በየቦታው የሚቀጣጠሉት ግጭቶችና ቁርሾዎች የሚባባሱና አክራሪ ብሄርተኞችም የእሳት ጨዋታቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ ገዥው መንግስትም ይህን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ቁርጠኝነትና መራራነት ካላሳዬን ሀገሪቱ ፍሙ በማይጠፋ የእርስ በርስ ዕልቂት ልትነድ ትችላለች። ዕልቂቱ በሁለትና ሦስት ተዋናዮች መካከል የሚካሄድ ሳይሆን እርስ በርሱ የተቆላለፈና አሁን ምልክቱን እንደምንመለከተው ያለ በየቦታው እንደ እሳተ ገሞራ የሚፈነዳ ይሆናል።

ችግሩ የበለጠ አሳሳቢ የሚሆነው በእንደኛ ዓይነት በብሔር ጽንፈኝነት እጅ ከወርች በተጠረነፈ ሀገር ውስጥ ለውይይት እጁን እና አዕምሮውን የሚዘረጋ ፖለቲከኛ እና ህዝብ ማገኘት ያስፈልጋል፡፡ ፖለቲከኞች ጦርነትን ህዝባዊነት አድርገው ነጋሪት የሚጎስሙ ወገኖች ሐገሪቱን ይበሏታል የሚለው ፍራቻ ብቻ ሳይሆን በቂ አሁናዊ ትንበያም ነው። የብሔር ፖለቲካ በጦዘባቸው ሀገራት አንዱና ዋነኛው ፈተና ልሂቃኑ ዴሞክራሲን በአፋቸው ቢያነበንቡም ለዴሞክራሲ ዝግጁ አለመሆናቸው ነው። ስለሆነም የችግሩ ቤንዚንም ሆነ ማጥፊያ መፍትሔው ዴሞክራሲ ነው። በአንድ በኩል ዴሞክራሲ ለፖለቲካ ተፋላሚዎች የብጥብጥ ዕድል ስለሚከፍትላቸው ወደ ዕልቂት ሊያመራ ይችላል። በሌላ በኩል ግን ችግሩን እንደምንም ተቆጣጥሮ በብልሃት ማለፍ ከተቻለ ዴሞክራሲ የሐገራችን የመጨረሻም የመጀመሪያም መንገድ ነው።

ከእልቂት እንዴት እናመልጣለን? ወቅታዊውን ፖለቲካ ከእናንተ የመፍትሄ ሃሳብ አሰተያየት ጋር አዋህደን በሌላ ጥንቅር እንመለሳለን፡፡

አስተያየት