መጋቢት 7 ፣ 2015

በአማራ ክልል ከ90 የሚበልጡ የመንግስት ሰራተኞች በሙስና መከሰሳቸው ታወቀ

City: Bahir Darፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

በክልል ደረጃ የፀረ ሙስና ኮሚቴ ከመቋቋሙ በፊት ከ70 በላይ ጥቆማዎች ለኮሚሽኑ ደርሰው የነበረ ሲሆን ኮሚቴው ከተቋቋመ በኋላ ግን በጥቆማ መስጫ ሳጥን የደረሱ ጥቆማዎች ከ12 አይበልጡም

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

በአማራ ክልል ከ90 የሚበልጡ የመንግስት ሰራተኞች በሙስና መከሰሳቸው ታወቀ

በአማራ ክልል 92 የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ በአጠቃላይ 132 ሰዎች በሙስና ወንጀል ተከሰው የቅጣት ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ታወቀ። በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ጥፋተኛ መሆናቸው ተረጋግጦ የቅጣት ውሣኔ የተላለፈባቸው አመራሮች “ከስድስት ቀበሌዎችና ከአስራ አንድ ወረዳዎች” እንደሆኑ የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ አለምሸት ምህረቴ ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመላክተው በሙስና ወንጀል ተከሰው የቅጣት ውሳኔ ከተላለፈባቸው ውስጥ 41 የቀበሌ፣ 34 የወረዳ፣ 8 የዞን፣ 9 የክልል በድምሩ 92 የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም ሌሎች 40 በተለያየ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ናቸው።

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ጥፋተኛ ተብለው የቅጣት ውሳኔ ከተላለፈባቸው የክልሉ አመራሮች መካከል ብዙዎቹ በክልሉ የመንግስት መዋቅር የሚሰሩ ባለሙያዎች መሆናቸውን አዲስ ዘይቤ ከመረጃ ምንጮቿ ለማወቅ ችላለች።
የፌደራል መንግስት ባሳለፍነው ህዳር ወር መጀመሪያ “ሙስና በሀገሪቱ ተስፋፍቷል" በማለት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ እንዲቋቋም መደረጉን ተከትሎ ክልሎችም መሰል ኮሚቴዎችን እንዲያቋቁሙ መደረጉ ይታወሳል። የአማራ ክልልም ሀገራዊ የፀረ ሙስና ትግሉን ለማገዝ በሚል የክልል ፀረ ሙስና አስተባባሪ ኮሜቴ አቋቁሟል።

የተቋቋመው ኮሚቴ በክልሉ ውስጥ በ3 ቦታዎች ማለትም በአማራ ክልል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ በክልሉ ፍትህ ቢሮ እና በአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ቢሮዎች የጥቆማ መስጫ ሳጥን ማስቀመጡን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፀረ ሙስና አስተባባሪ ኮሚቴው አባል እና ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሀብታሙ ሞገስ ገልፀዋል።

እንደ ኮሚሽር ሀብታሙ ገለጻ “ኮሚቴው ከመቋቋሙ በፊት በክልል ደረጃ ከ70 በላይ ጥቆማዎች ለኮሚሽኑ ደርሰው ምርመራቸው ተጠናቆ ክስ እንዲመሰረት ለአቃቢ ህግ የተላለፈ ሲሆን ኮሚቴው ከተቋቋመ በኋላ ግን በጥቆማ መስጫ ሳጥኑ የተሰጡ ጥቆማዎች ከ12 አለመብለጣቸውን ለማወቅ ተችሏል” ብለዋል።

ኮሚሽነሩ በክልሉ ከተንሰራፋው የሙስና ወንጀሎች አንጻር በክልል ደረጃ ለተቋቋመው ክልላዊ ኮሚቴ የተሰጡ ጥቆማዎች በቂ አለመሆናቸውን ገልፀው ህዝቡ ምርመራ ለማካሄድ አመቺ የሆኑና በበቂ ማስረጃ የተደገፉ ጥቆማዎችን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። 

ነዋሪዎችም በክልሉ በተቀመጡ ጥቆማ መስጫ ሳጥኖች፣ በዞን ከተሞች በተቋቋመው የፀረ ሙስና አስተባባሪ ኮሚቴ፣ እንዲሁም በነፃ የስልክ መስመር 9427ን በመጠቀም በአካልም ሆነ በስልክ ጥቆማ መስጠት እንደሚቻል የክልሉ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሀብታሙ ሞገስ አክለው ገልፀዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በተካሄደው የአማራ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ከምክር ቤት አባላት ሙስና በክልሉ ስለመስፋፋት ለተነሱ ጥያቄዎች የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ ህብረተሰቡ ሙስናን አምርሮ ለመዋጋት ከመንግስት ጋር በቅንጅትና በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የተቋቋመው ኮሚቴ የሚወስዳቸውን እርምጃዎችና እንቅስቃሴውን በተመለከተ በየጊዜው ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ፕሬዝዳንቱ የገለጹ ቢሆንም የአማራ ክልል የፀረ ሙስና ኮሚቴ ግን በተከታታይ በሚዲያ መረጃ የመስጠት ውስንነት እንዳለበት ተመላክቷል። 

በፌዴራል ደረጃ የተቋቋመው የፀረ ሙስና አስተባባሪ ኮሚቴ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጠው መግለጫ እስካሁን በብሔራዊ ደረጃ 759 ጥቆማዎች የደረሱ ሲሆን ለክልሎች ደግሞ 2 ሺህ 16 ጥቆማዎች በድምሩ 2 ሺህ 785 ጥቆማዎች መድረሳቸውን አሳውቋል። በህዝብ ጥቆማ የተሰጠባቸው የሙስና ወንጀሎች በአብዛኛው ከገቢዎች፣ ከመንግሰት ግዥ፣ መሬት ነክ ጉዳዮችና ፋይናንስ ጋር የተያያዙ ሲሆን ከነዚህ የሙስና ወንጀሎች መካካል በብሔራዊ ደረጃ 640 ተከሳሾች በ81 የክስ መዝገቦች ክስ እንደተመሰረተባቸው ያሳያል።

አስተያየት