ነሐሴ 28 ፣ 2013

የሕዝብ ግንኙነቶች ሥራ መረጃን ማፈን ወይስ ማዳረስ?

City: Bahir Darሚዲያ ማህበራዊ ጉዳዮች

አሁንም ድረስ መረጃ የማግኝት ችግር ለኢትዮጵያ ሚዲያ ፈተና እና የዜጎች የዘወትር ጥያቄ ከመሆን አልወጣም። የመረጃው ረሃብ ያጠቃቸው ሚድያዎች ነገሮችን ዕያዩ የሚያልፉ፣ አልያም የተናገሩትን የሚያጥፉ ናቸው።

Avatar: Ayele Addis
አየለ አዲስ

Ayele Addis is an award winner Journalist, Journalism, Trainer, Researcher, and Media & Communication Development Consultancy for Thomson Reuters' Foundation, Africa News Channel, Amhara Media, and Journalists Association. Ethiopian Mass Media Action (EMMA News), ARMA Media Production.Woldia University and Bahir Dar University and founder of Journal of Ethiopian Media and Communications.

የሕዝብ ግንኙነቶች ሥራ መረጃን ማፈን ወይስ ማዳረስ?

በመረጃ ፍርሃት፣ በመደበቅ አባዜ፣ በተጠያቂነት እጦት፣ ደጃፍን ከፍ አድርጎ በሚያጥር ስነ-ልቦና፣ ግልፅነትን ባዳፈነ ምስጢራዊነት፣ በተሸሸገ አመጋገብ፣ በተቆለፈ ካዝና እና መረጃ፣ በስሚ-ስሚ ጭምጭምታ ወሬ የተገነባ ማኅበረሰባዊ ስርዓታችን መረጃን ከህዝብ በመደበቅ በግምት እንዲኖር ማህበረሰቡን ተጠራጣሪ የሚያደረግ፣ ሞጋችነትን እና መረጃ የማጥራትን ዕድል የነፈገ ነው፡፡ 

የመረጃው ረሃብ ያጠቃቸው ሚድያዎች ነገሮችን ዕያዩ የሚያልፉ፣ አልያም የተናገሩትን የሚያጥፉ ናቸው፡፡ ዛሬ ከፍተኛ የሆነ የሐገሪቱ የሕግ አስፈፃሚ የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ሳይቀር መረጃ በማጣራት፣ ሃቅን በማጥራት የተጠመደው የግልፅኝነት እና ምላሽ ሰጭነት ችግር የዋጠው አስተሳሰብ በሁሉም አቅጣጫ በመንሰራፋቱ ነው፡፡

አሁንም ድረስ መረጃ የማግኝት ችግር ለኢትዮጵያ ሚዲያ ፈተና እና የዜጎች የዘወትር ጥያቄ ከመሆን አልወጣም። አሁን ኢትዮጵያን እየፈተናት ያለው የመረጃ ብክለት፣ መረጃን ማሳሳት፣ መረጃን ማዛባት፣ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ፣ ወዘተ ውስጥ ሀገሪቱ የገባቸው ከመረጃ አቅርቦት ችግር በመነጨ ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህሩ አቶ ጌታነህ መኳንንት ይጠቅሳሉ፡፡

የቀድሞው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የአሁኑ የባህር-ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ሃሰን ኡስማን በበኩላቸው የኮሚዩኒኬሽን ባለሞያዎች ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ያላቸው ግንኙነት ድክመት ያለበት እና የተለያዩ ምክንያቶች በመደርደር ማለትም” እገሌን አስፈቅዱ፣ ደብዳቤ ፃፉ፣ ስብሰባ ላይ ነን፣ ቀጠሮ ከተያዘ በኋላም ላጣራና ሌላ ጊዜ ላሳውቅህ…” በማለት መረጃ በጭራሽ ላለመስጠት ምክንያት እየሰጡ የመረጃ ርሃብ እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።

በፌደራል፣ ክልል/ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የህዝብ ግንኙነት መዋቅሩ ለሚዲያ መረጃ ምላሽ ሰጪነት ጥናት ያተኮረ ያልታተመ ዳሰሳዊ ጥናት ላይ እንዲህ ብሏል፡፡ “ለሚዲያዎች ግብአት የሚሆኑ ወቅታዊ መረጃዎችን ከመዘገብ አኳያ ዘገምተኛና ዝቅተኛ ነው፡፡ ባለሙያዎቹ መረጃ የሚሰጡት መረጃ መስጠት ስራቸው መሆኑን አውቀው ሳይሆን እየተለመኑ ነው፡፡ ድርጊታቸውንም እንደ ትልቅ ውለታ ቆጥረው የተጋነነ ምስጋና ይጠብቃሉ” በተጨማሪም በተወሰኑት ላይ የመረጃ ጥራት ጉድለት ይታያል፡፡ የዳሰሳ ጥናቱ በተጨማሪም የህዝብ ግንኙነቶቹ፡- ስለተቋማቸው ያላቸውን ግንዛቤ አነስተኛነት፣ መረጃን በአግባቡ አደራጅቶ የመያዝ ችግሮች መስተዋላቸውን፣ መረጃ ለመስጠት ከመትጋት ይልቅ ሂደቱን ለማደናቀፍ ምክንያቶች መደርደር እንደሚቀናቸው አንስቷል፡፡

የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅን ጠንቅቀው ባለማወቃቸው የተነሳ በመንግሥት እጅ የሚገኝ መረጃ የህዝብ ሀብት መሆኑና ህዝቡም መረጃ የማግኘት መብት እንዳለው መዘንጋት፣ መረጃ መስጠት ግዴታ መሆኑን መዘንጋት፣ መረጃ መስጠትን ከጥቅም ጋር ብቻ ማያያዝ፣ የሚከለከሉና የማይከለከሉ መረጃዎችን ለይቶ ያለማወቅ፣ ለጋዜጠኞች የተቀመጠን ከለላ ተግባራዊ አለማድረግ፣ ክፍተቶች በሚያጋጥሙበት ወቅት ለአደጋ ተጋላጭ መሆናቸው በብዛት በምላሽ ሰጪዎች ከተጠቀሱት መካከል ናቸው። በተጨማሪም፣ የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት ቻርተር ተግባራዊ አለመሆን እንደ ችግር ተነስተዋል።

የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ዋናው መሰረታዊ ችግር በቅደም ተከተል የቢሮክራሲ አሰራር፣ የሙያና የአቅም ብቃት ማነስ መሆናቸውን ጥናቱ ዓሳይቷል። በቀውስ ጊዜ የኮሚዩኒኬሽን ክፍሉ ለሚዲያዎች በሚሰጠው መረጃ ችግሮች ተከስተው ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ መረጃ ለህዝቡ እንደሚሰጥ (ማስተካከያ እንደሚደረግ) ምላሻቸውን አስቀምጠዋል።

የ2013 ዓ.ም. የመረጃ ነፃነት ቀንን በተመለከተ የኢትዮጵያ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ በስጡት መግለጫ እንደተብራራው በሀገራችን የመረጃ ነጻነት አዋጅን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በርካታ ተግዳሮቶች ተደቅነዋል፡፡ በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 29 እና በመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ክፍል ሦስት የተደነገገው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የመረጃ ነጻነት መብት እውቅና ቢያገኝም፤ ፖለቲካው እንደ ግብርና እና ጤና ያልሰለጠነና ያለዘመነ መሆኑ (ዴሞክራሲን ማልማት አልቻልንም) ዴሞክራሲ ሽቅብ የሆነባት ሀገር ናት ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በአዋጁ ላይ ያሉ የሕግ ክፍተቶች (ተጠያቂነትን በግልጽ አልተቀመጠም፣ የተቀመጡትም ቢሆኑ የመገኛኛ ብዙኃንን ከግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑ) በመንግሥት አካላት ውስጥ ያሉ ችግሮች የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትን ጨምሮ የተቋማት የበላይ ኃላፊዎች በየደረጃው ላሉ ም/ቤቶች ሪፖረት በሚያቀርቡበት ወቅት የመረጃ ነጻነት አዋጅን አተገባበር አካተው እንዲያቀርቡ በአዋጁ ላይ በግልጽ ቢቀመጥም ም/ቤቱ እስከዛሬ ጠይቆ አያውቅም ብለዋል፡፡ 

ሕግ አውጭው አካል ለክትትልና ድጋፍ ወደ ተቋማት በሚሄዱበት ጊዜም የስራቸው አካል አድርገው ቁጥጥር አያደርጉም፡፡አስፈጻሚ አካላት የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ለሚንስትሮች ም/ቤት ሪፖረት ሲያቀርቡ ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተው አካተው አያውቁም፡፡ የኢትዮጵያ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ እንደሚሉት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ከወጣበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን አንድም ጠቅላይ ሚንስትር ከመረጃ ነጻነት አዋጅ አፈጻጸም አንጻር ለም/ቤት ሪፖረት አቅርቦ አያውቅም፤ ም/ቤቶችም ጠይቀው አያውቁም፡፡

አስፈጻሚ አካላት ወቅታዊ መረጃ ለመገኛኛ ብዙኃን በወቅቱ ስለማይሠጡ ህዝቡ ለማኅበራዊ ሚዲያ እና ለጥላቻ ንግግሮች ተጋላጭ ሆኗል ያሉት የኢትዮጵያ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዳይሬክተር በግለሰብም ደረጃ በየተቋሙ ለሚቀርቡ የመረጃ ጥያቂዎች ምንም ሕጋዊ መሰረት በሌለበት አኳኋን ክልከላዎች ይደረጋሉ ሲሉ አንሰተዋል፡፡ በመንግስት በኩል ለመረጃ ነፃነት የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን፣  ዓመታዊ ሪፖርቶች ወቅቱን ጠብቀው በግልፅነት ይፋ አለመሆናቸው፣  በየተቋማቱ ቀደም ሲል ይደረጉ የነበሩ የህትመት ስራዎች መዳከም፣ በብዙ የመንግስት ተቋማት የመረጃ ማዕከላት አለመደራጀታቸውና ያሉትምት መዳከማቸው፣ በአደረጃጀት፡-የተማከለ መረጃ የሚሰጥ መንግስታዊ ተቋማት መፍረሳቸውና፣ የመንግስት ተቋማት የህዝብ ግኑኝነት ሙያተኞች ኃላፊነት ሲሰጣቸው የተቋማቱን ገጽታ ለመገንባት ታሳቢ በመደረጋቸው እና በተጠያቂነት ችግር መረጃ ለመስጠት መፍራታቸው፣ የተቋማቱ የበላይ ኃላፊዎችም አሁን ያለውን ሀገራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነጻ ገለልተኛ እንዲሁም ፕሮፌሽናል ሆነው በአዲስ መልክ እንዲደራጁ አለማድረጉ፣ በፌደራል ደረጃ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መፍረሰን ተከትሎ ወደታች ያለው የሕዝብ ግንኙነት መዋቅር መፍረስ እና መዳከም፣ የሚዲያ አካላት የጋራ ሀገራዊ አጀንዳ እንዳይኖራቸው ጭምር አድርጓል ሰሉ ገልፀዋል፡፡

በክልል ደረጃ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ ያለመወርቅ አጋዥ በበኩላቸው መረጃ ለመስጠት የምንፈራው በቅርብ አለቃቸው የሚደርስባቸውን ተፅእኖ እና ግምገማ፣ የስራ እድገት እና ዋስትና ስጋት ስለሚሆናቸው መሆኑን ይገራሉ፡፡

“በተመሳሳይ ሁኔታ መረጃ አስፈሪ ነው፡፡ ከትንሽ ማስታወሻ ጀምሮ ለህዝቡ ለማድረስ የመስሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ ማወቅ አለበት አለበለዚያ ስራህንም፣ ደረጃህንም ታጣለህ፣ ይህን ያደረገው ደግሞ ራሱ መንግሥት ነው፡፡ እኔ ለግል ሚዲያ መረጃ ሰጠህ ተብሎ በጣም መንገላታት የደረሰበት ባለሙያ አውቃለሁ፡፡ ያንን ዕያየህ መቸም መረጃ ስጠኝ ብትለኝ እኔም የለኝም” ያለው የመረጃ አሰተዳደር ባለሙያ የሆነው ደረጀ ገድፍ ነው፡፡

ደረጀ መረጃን ግልፅ የሚያደርግ ሀገር አቀፍ አሰራር እና አሰገዳጅ ሁኔታ ካልተቀመጠ፣ ሐገሪቱ ሁልጊዜም በመረጃ ደህነት ትቀጥላለች ያለው ባለሙያው፣ እንኳንም መረጃ ለዜጎች እና ለሚዲያ በግልፅነት መስጠት ቀርቶ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ስራ ወይም ቦታ ሲቀየሩ መረጃ አጥፍተው እንደሚሄዱ መታዘቡን ተናግሯል፡፡

ዶክተር እንዳለ ኃይሌ በበኩላቸው “የመረጃ ነጻነት መብት ሌላ ሦስተኛ ወገን እንዲያስከብርላቸው የመፈለግ ዝንባሌዎች በሀገራችን ይታያል ያሉ ሲሆን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለCGTN መረጃ ቢከለክል CNN እና BBC ናቸው፡፡ የበለጠ የሚጮሁት በእኛ ሁኔታ ግን ይህ የለም፡፡ መረጃ የተከለከለ ሚዲያ የከለከለውን አካል በየደረጃው በሚመለከታቸው አካላት እንዲጠየቅ አለማድረግና መረጃ ሊሰጡን ስላልቻሉ ማካተት አልቻልንም የሚለውን ብቻ በመዘገብ በዝምታ ማለፍ አሁንም መረጃ ሰጭዎች መረጃ የሚከለክሉ አካላትን የሚያበረታታ አካሄድ ነው፡፡ 

በመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 በተመሳሳይ ከግለሰብ ህይወት ወይም አካላዊ ደህንነት፣ ከሀገር ደህንነት አንጻር የተጣሉ ገደቦችን በስመ ነጻነት ስም ሲጣሱ ይስተዋላል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ እንዲሻሻልና በምትኩ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን የሚፈታ አዋጅ ጸድቆ ስራ ላይ እንዲውል የክትትል ስራ እየተስራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የመረጃ ነጻነት በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 29 እና በመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ሕጋዊ እውቅና አግኝቷል፡፡ በመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ክፍል ሦስት የተደነገገ የመረጃ ነፃነት ሕጉን እንዲያስተገብርና ተፈፃሚነቱን እንዲከታተል ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ‘መረጃን ለሕዝብ ይፋ ማድረግን’ አስመልክቶ አዋጅ አዘጋጅቷል፣ በተመሳሳይም መረጃ ለማግኝት በሚያስፈልግ ወጭ የክፍያ ተመንና ተገቢነትን በተመለከተ የተዘጋጀ ደንብ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ፀድቋል፡፡ በሌላ በኩል ‘የመረጃ ሰርተፊኬት መስጠትን የተመለከተ ደንብ እንዲሁም ‘ምስጥራዊ መረጃ ምደባና ጥበቃን’ የተመለከተ ደንብ ረቂቅ ተዘጋጅተው በሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ሁሉ የሕግ ማዕቀፎች ወጥተው በመገናኛ ብዙኃን ሕግ ማዕቀፍ የሥራ ቡድን በርካታ ችግሮችን ይፈታል የተባለ አዲስ የመረጃ ነፃነት ረቂቅ ሕግ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመርሳ ሚዲያ ኢንስቲትዩት  አዘጋጀነት ውይይቶችን እያካሄደ ይገኛል፡፡ 

የመገናኛ ብዙኃን ሕግ ማዕቀፍ የሥራ ቡድን ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሰለሞን ጎሹ በባህርዳር በነበራቸው የአዋጁ ማስተዋወቂያ መድረክ ላይ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ መንግሥት የአስተዳደር ባህል በአብዛኛው ሚስጢራዊ መሆኑ ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀምንና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ማስከተሉን በመረዳት፤ የሕዝብ ጥቅምን የሚመለከቱ ጉዳዮች ግልፅ እንዲደረጉና ውይይት እንዲደረግባቸው፤ መንግሥትና የግል አካላት ለግለሰቦችና ለመገናኛ ብዙኃን መረጃን ተደራሽ እንዲያደርጉ የሕግ ግዴታ በመጣላቸው እና የሕዝብ ተሳትፎንና የሥልጣን ባለቤትነትን የማረጋገጥና እንዲሁም ግልፅነት፤ ተጠያቂነትና ውጤታማነት የሰፈነበት የመንግሥት አሰራርንና መልካም አስተዳደርን ለማጠናከር በመወሰን፤ የሰብዓዊ መብቶችን ለማረጋገጥ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል መልካም ግንኙነትን ለመገንባትና ሙስናን ለመዋጋት የመረጃ ነፃነትን ማረጋገጥ ያለውን ከፍተኛ ሚና በመገንዘብ፣ በስራ ላይ ያለውን የመረጃ ነፃነት ሕግ በማሻሻል የሕዝቡን መረጃ የማግኘት ፍላጎቱን በሚያንጸባርቅና መብቱን ይበልጥ ለመጠበቅና ለማራመድ በሚያስችለው አዲስ ሕግ መተካቱ አስፈላጊ በመሆኑ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55 (1) መሰረት የመረጃ ነፃነት አዋጅን ብቻ የሚመለከት እና ይህንን የሚመራ ተቋም እንዲመሰረት የሚያግዝ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡

የመረጃ ነጻነት ቀን በ74ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በየዓመቱ መከበር እንዳለበት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) መስከረም 28 ዓለም አቀፍ የመረጃ ነጻነት ቀን ወይም International Day for Universal Access to Information እንዲሆን ተወስኗል፡፡ በዓሉ በመጭው መስከረም 2014 በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ6ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ ተከብሮ እንደሚውል ይጠበቃል፡፡

አስተያየት