የካቲት 16 ፣ 2015

መሬት ያለግንባታ ፈቃድ ያስረከበው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ቅሬታ ቀርቦበታል

City: Bahir Darየአኗኗር ዘይቤወቅታዊ ጉዳዮች

በማህበር የተደራጁ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ሲሰጣቸው በማስረጃ የተደገፈ ፍተሻ ተደርጎ ተረጋግጦ ቢሆንም አሁን በድጋሜ ለማጣራት በሚል ሰበብ መታገዳቸውን ቅሬታ አቅርበዋል

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

መሬት ያለግንባታ ፈቃድ ያስረከበው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ቅሬታ ቀርቦበታል
Camera Icon

(ፎቶ በአብነት ቢሆነኝ- የቤት ማህበር አባላት ቅሬታ አቅራቢዎች)

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እንደተቀሩት የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከሰተበትን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስ ነዋሪዎች እንደገቢ አቅማቸው እንዲደራጁ አማራጮች በመቅረባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተደራጅተዋል። ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በባህርዳር ከተማ በማኅበር ተደራጅተው ቦታ ለማገኘት የሚጠባበቁ በርካታ ማኅበራት መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። 

እነዚህ ማህበራት የሚጠበቅባቸውን መስፈርት አሟልተው ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በከተማ አስተዳደሩ እውቅና ተሰጥቷቸዋል። እውቅና ከተሰጣቸው ማህበራት መካከል 9 ሺህ 913 ነዋሪዎች በ469 ማህበራት ተደራጅተው በዘንዘልማ ሳይት 150 ካሬ ሜትር ቦታ አግኝተዋል። ሌሎች 185 ማህበራት ደግሞ በ3 ሺህ 806 ነዋሪዎች ተዋቅረው በመሸንቲ ሳይት እያንዳንዳቸው 200 ካሬ ሜትር ቦታ ያገኙ ሲሆን በድምሩ 13 ሺህ 719 የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ከወራት በፊት በርካታ ውጣ ውረድ አልፈው ቦታ ተሰጥቷቸዋል።

የተሰጣቸው ቦታ እያንዳንዱ የማህበር አባላት የተሰጣቸውን ቦታ ለይተው ቢያውቁም እስካሁን የግንባታ ፈቃድ አልተሰጣቸውም። የከተማ አስተዳደሩ ቦታ ያለአግባብ የወሰዱ ሰዎች በመኖራቸው አጣራለሁ በሚል ምክንያት እንዳገዳቸው ለአዲስ ዘይቤ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

አቶ እንድሪያስ ይብሬ በ2006 ዓ.ም በማኅበር ተደራጅቶ በ2010 ዓ.ም ማህበራቸው እውቅና ማግኘቱንና ከዓመታት ጥበቃ በኋላ በጥቅሉ ለቤት ማህበር ቁጠባና የመሬት ካሳ 160 ሺህ ብር በላይ ካወጣ በኋላ ቦታ ማግኘቱን ይናገራል። እንደ አቶ እንድሪስ ማብራሪያ ማህበራት በ2010 ዓ.ም ዕውቅና ሲሰጥ የአባላት ማስረጃዎች ፈትሾ ትክክለኛ መሆናቸውን አረጋግጦ ነው ዕውቅና የሰጠን ይላሉ። 

በሌላ በኩል እንደገና ቦታ ሊሰጥ ሲል በ2014 ዓ.ም ከወራት በፊት ማስረጃዎችን እንደአዲስ እንዲያስገቡ በመጠየቁ አስፈላጊውን ሁሉ መስፋርት አሟልተው ቦታ ከወሰዱ በኋላ “የእያንዳንዱን ሰው ማስረጃ አጣራለሁ በማለት ዕገዳ መጣል ወቅቱን የጠበቀ አይደለም” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል።

የአቶ እንድሪያስ እጣ ፋንታ ብዙዎች የተጋሩት ቅሬታ እንደሆነ የአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ዘጋቢ ያነጋገራቸው የማኅበር አባላት መረዳት ችለናል። 

በሌላ በኩል ቦታ ከደረሳቸው ሰዎች መካከል ለሌላ ሰው አሳልፈው የሸጡ መኖራቸውን አዲስ ዘይቤ ቦታ ገዝተናል ከሚሉ ሰዎች ማረጋገጥ ችላለች። በዚህም ቦታቸውን የሸጡ ሰዎች በሚደረገው ማጣራት ቦታውን የሚቀሙ ከሆነ ችግር ላይ እንወዳይወድቁ ስጋት ውስጥ ገብተዋል። 

በሌላ በኩል ወ/ሮ ፍቅርተ ይስማው የከተማ አስተዳደሩ “አሁን አጣራለሁ በሚል የጣለው እገዳ መሰራት በነበረበት ጊዜ ያልተሰራ ከመሆኑ በተጨማሪ ማህበራችሁ በ2010 ዓ.ም ዕውቅና ሲያገኝ ያቀረባችሁትን ማስረጃ እንደገና አፅፋችሁ አምጡ” ማለት አሳዛኝ ነው በማለት ቅሬታዋን ነግራናለች።

ይህን የማጣራት ስራ እንዲሰራ ከተማ አስተዳደሩ ያቋቋመው ኮማቴ አገልግሎት አሰጣጡ ፈጣን ካለመሆኑ በተጨማሪ በመስኮት ማስረጃዎችን ከመቀበል ውጭ ዶክመንት በሟሟላት ሂደት የገጠመንን ችግር ለማድመጥ ፈቃደኛ አይደሉም ያሉት ደግሞ ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢ አቶ ዝናቡ ታደሰ ናቸው።

አቶ ዝናቡ በንግድ ስራ የሚተዳደሩ ሲሆን በ2010 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ በበላይ ዘላቀ ክፍለ ከተማ ገቢዎች ፅህፈት ቤት ግብር የከፈሉበትን ማስረጃ አሁን ፋይሉን አስወጥቶ ለማፃፍ በክፍለ ከተማው ከዓመታት በፊት በደረሰው ቃጠሎ ማስረጃዎች በመውደማቸው ፋይል አውጥተው ማፃፍ እንደማይችል ተነግሮኛል ይላሉ። 

ቅሬታቸውን ለከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ቢያቀርቡም በ2010 ዓ.ም የከፈልክበትን ደረሰኝ ካለመጣህ አንፅፍም ተብያለሁ ሲሉም አቶ ዝናቡ ታደሰ ገልፀዋል። ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ አጣሪ ኮሚቴው የገጠማቸውን ችግር ለመስማት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

አቶ ማስረሻ በላይ ከ13 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የተደራጁባቸው 598 ማህበራት የመሰረቱትን የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ውስጥ አመራር  ሲሆኑ “የከተማ አስተዳደሩ ያቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ህጋዊ መሰረት የለውም፣ የመሬትን ጉዳይ የማጣራት ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው ለሌላ አካል ነው” ይላሉ። 

በሌላ በኩል መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ቦታ እስኪሰጥ ድረስ ለስምንት ዓመታት በቅርበት ሲሰራ የነበረ ቢሆንም አሁን አጣሪ ኮሚቴ ከተማ አስተዳደሩ ሲያቋቋም እውቅና እንደሌለው እና እንዳልታሰተፈ ይናገራሉ። የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል አቶ ማስረሻ በላይ አሁን ከተማ አስተዳደሩ የጀመረው የማጣራት ስራ ወቅቱን የጠበቀ አደለም ምክንያቱም ከተማ አስተዳደሩ የእንያንዳንዱን አባላት ዶክሜንት (መረጃ) አጣርቸ ጨርሻለሁ ብሎ እውቅና በ2010 ዓ.ም ሰጧል ማጣራት በተመለከተ ያኔ መጨረስ ነበረበት ይላሉ።

የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው አመራር የሆኑት አቶ ማስረሻ እንደሚገልፁት “በማህበራት ተደራጀተው ቦታ የወሰዱ አካላት መስፈርቱን አሟልታችኋል ተብለው ለዓመታት ጠብቀው ቦታ ተሰጥቷቸዋል፤ አሁን የተሰጣቸውን ቦታ ቢነጠቁ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የመውሰድ መብት አላቸው” ብለዋል። የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የማጣራት መብት ያለው ቢሆንም የተወሰኑ ሰዎች ህጋዊ ሳይሆኑ ቦታ ወስደዋል በተባሉ ሰዎች ምክንያት ሌሎች በርካታ የማህበር አባላት አብረው መጉላላት እንደሌለባቸው አፅንኦት ተሰጥቷል። 

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ወደዚህ የእግድ እና የማጣራት ስራ ለመግባት መነሻ የሚሆኑ በ2014 ዓ.ም የቦታ ምሪት ተጠቃሚ የሆኑ  ነዋሪዎችን በተመለከተ እና ከማህራት አደረጃጀት ጋር ተያይዞ ጥቆማዎችና አስተያቶችን እንደደረሱት ይገልፃል። በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ የደረሱትን ጥቆማዎችና አስተያየቶች የሚያጣራ ኮሚቴ እንዳቋቋመ አስታውቋል። ተቋቋመ የተባለው ኮሚቴ አሰራርም ከእያንዳንዱ የማህበር አባላት መረጃዎችን በአካል በመቀበል እና በማጣራት ለሚመለከተው ክፍል ማስተላለፍ መሆኑን አስተዳደሩ ገልጿል። 

አጣሪ ኮሚቴው የማህበሩ አባላት በ2010 ዓ.ም ማህበራቱ ዕውቅና ሲያገኙ ያቀረቧቸውን የቀበሌ መታወቂያ፣ በተደራጁበት ወቅት የሰሩበት ተቋም የስራ ልምድ እንዲሁም አባላቱ ዕውቅና ከማግኘቱ በፊት (ከ2010 ዓ.ም በፊት) የተደራጁበትና የቆጠቡበት የባንክ ደረሰኝን የመሳሰሉ ማስረጃዎችን እመረምራለሁ ማለቱ ተነግሯል።   

በ'መኖሪያ ቤት ሕብረት ስራ ማኅበራት ማደራጃ መመሪያ ቁጥር 28/2009' መሰረት በመኖሪያ ቤት የሕብረት ስራ ማኅበራት የዕውቅና ምስክር ወረቀት በተሰጠ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የቤት መስሪያ ቦታ እንደሚሰጥ መመሪያው ይደነግጋል። ይህ ካልሆነ ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት መውሰድ አንደሚቻል መመሪያው ላይ በግልፅ ተቀምጧል። 

አስተያየት