ግንቦት 11 ፣ 2014

በባህር ዳር ከተማ ቦታ ከወሰዱ ባለሃብቶች መካከል 79 በመቶው ወደ ስራ አልገቡም

City: Bahir Darወቅታዊ ጉዳዮችንግድ

በአለፉት ዓመታት በባህር ዳር ከተማ ቦታ ከወሰዱ 664 ባለሃብቶች መካከል 142 ብቻ ግንባታቸውን ጨርሰው ወደ ማማረት አንደገቡ ተነገረ፡፡

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

በባህር ዳር ከተማ ቦታ ከወሰዱ ባለሃብቶች መካከል 79 በመቶው ወደ ስራ አልገቡም
Camera Icon

Credit: Social media

በአለፉት ዓመታት በባህር ዳር ከተማ ቦታ ከወሰዱ 664 ባለሃብቶች መካከል 142 ብቻ ግንባታቸውን ጨርሰው ወደ ማማረት አንደገቡ ተነገረ፡፡ እንደ ባህር ዳር ከተማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሪፖርት የባህር ዳር ከተማ በአለፉት ዓመታት ለ664 በላይ ባለሀብቶች 602.99 ሄክታር መሬት ቢያስተላልፍም 21 በመቶው (142) ብቻ ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ምርት ማምራት ስራ መግባታቸው ይገልፃል፡፡ በተመሳሳይ በመሰረተ ልማት እና ተያያዥ ችግሮች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ልማት ያልገቡ 273 ፕሮጀክቶች አንደሚገኙ በሪፖርቱ ተገልፃል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አዲስዘይቤ ያነጋገራቸው የባህር ዳር ከተማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ፅ/ቤት ኃላፊ በለይነህ ምትኩ ገለፃ ፕሮጀክቶች ወደ ማምረት ያልገቡበት ምክንያት የመሰረት ልማት ችግር ፣ የብድር አቀርቦት ችግር ፣ ባለሃብቶች ቶሎ ገንብቶ ወደስራ ለመግባት ፍላጎት ማጣት  እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ ይላሉ፡፡

በዚህም በከተማው ግንባታቸው ከተጠናቀቀ ፕሮጀክቶች መካከል "69 የመንገድ 27 የውሃ እና 170 የመብራት ወይም የኃይል ችግር አለባቸው" ያሉ ሲሆን በሌላ በኩል ምርት በማምረት ላይ ከሚገኙ ድርጅቶች የመሰረተ ልማት ችግር ያለባቸው ሲሆን በዚህም 10 የመንገድ ፣ 2 የውሃ እና 23 የመብራት ወይም የኃይል ችግር የገጠማቸው በመሆኑ በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርት ስራ ያልግቡ ናቸው ብለዋል ኃላፊው፡፡

የኮርፖሬሽን ፅ/ቤት ኃላፊ በለይነህ ምትኩ በከተማ የሚገኙ ፓርኮች ወደስራ ለአለመግባታቸው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም በአለፉት ዘጠኝ ወራት በከተማዋ የሚገኙ ግንባታቸው የተጠናቀቀ 20 ፕሮጀክቶች በውጭ ምንዛሬ ችግር ወደስራ አለመግባታቸውን ገልፀዋል፡፡

በባህር ዳር ከተማ የባህር ዛፍ ዘይት ለማምረት ከዓመታት በፊት 10 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ መወሰዳቸውን እና ግንባታ መጀመራቸውን የተናገሩት "የማርኮን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት" ስራአስኪያጅ አበበ ታደሰ ግንባታ ቢጠናቀቅም የመሰረተ ልማት እና የወጭ ምንዛሬ እጥረት ወደ ምርት መግባት እንዳልቻሉ ይገልፃሉ፡፡

በሌላ በኩል በባለሃብቶች የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ በአለፉት ዘጠኝ ወራት 72 ባለሃብቶች ወደ ግንባታ መግባት ባለመቻላቸው መሬታቸው መነጠቁን እና ለ32 ባለሃብቶች ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን የባህር ዳር ከተማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ፅ/ቤት ኃላፊ በለይነህ ምትኩ ገልፀዋል፡፡

እንደ በላይነህ ምትኩ ማብራሪያ ከተማዋ በጀት ችግር ምክንያት የመሰረተ ልማት ለሟሟላት መቸገሩን ተናግረው ከተማ አሰተዳደሩ በአለው ውስን በጀት ለሟሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የበጀት ችግሩ አንዲፈታ በክልሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን በኩል ተደጋጋሚ ጥያቄ መቀረቡን ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ ግንባታቸውን አጠናቀው ለመካዝን ክራይ ወይም ለሌላ አገልግሎት በአዋሉ ባለሃብቶች በተመለከተ በላይነህ ምትኩ ግንባታቸውን ጨርሰው ለሌላ አገልግሎት እያዋሉ ያሉ ባለሃብቶችን በተመለከተተ መረጃው አንደሌላቸው ተናግረው ወደፊት ክትትል እንደሚደረግ  ተናግረዋል፡፡

በተያያዘ የክልል አንዱሰትሪ ፖርኮች ኮርፖሬሽን የዘጠኝ ወር ሪፖርት አንደሚያሳየው በአጠቃለይ በክልሉ ቦታ ተቀብለው ወደ ልማት ከገቡ 1552 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወስጥ 18 በመቶው (283) ብቻ ወደ ማምረት ስራ መግባታቸውን  ያሳያል፡፡

በክልሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን የህዘብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በልስቲ ወርቅ ማብራርያ በክልል የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ የግል ባለሃብት ፓርኮች ወደ ማማርት ያልገቡባቸው መሰረታዊ ችግሮች በኮርፐሬሽኑ በኩል ተለይተዋል በዚህም "ባለሃብቶች ትክክለኛ ፕሮጀክቶችን አቅርቦ ወደ ማምርት ከመግባት ይልቅ መሬት ወስዶ ብድር ለመውሰድ መፈለግ፣ የባለሃብቶች የፋይናስ አቅም ውስን መሆን፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በቂ የብድር አቅርቦት ችግር እና የግንባታ ማቴሪያል የዋጋ ንረት" በክልሉ በባለሃብቶች ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ምርት ስራ ለአለመግባታቸው በምክንያትነት ይገለፃል ብለዋል፡፡

እንደ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገለፃ ባህር ዳርን ጨምሮ በክልሉ ለሚገኙ የኢዱስትሪ መንደሮች መሰረት ልማት ለሟሟላት የክልል መንግስት የበጀት ችግር በተላይ ዘንድሮ ያለ በመሆኑ አንደተቸገሩ ተናግረው የፌድራል መንግስት የበጀት ድጋፍ ማድርግ ስለሚጠበቅብት ጥያቄ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ ለኢ.ዜ.አ እንደገለፁት በአጠቃላይ በክልሉ በኃይል እጥረት ወደ ስራ ያልገቡ ከ200 በላይ ፕሮጀክቶች እስከ ሰኔ 30/2014ዓ.ም ድረስ ወደስራ ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ  ነው ብለዋል።

አስተያየት