ሰኔ 29 ፣ 2014

ፈውስ የተቸሩ መዳፎች በባህር ዳር

City: Bahir Darጤናየአኗኗር ዘይቤ

በባህር ዳር ከተማ በወጌሻነታቸው ታዋቂነትንና ተወዳጅነትን ያተረፉት ሃጂ ኑሩ ካሴ (አባ አልቃድር) ከ40 አመታት በላይ አገልግለዋል።

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

ፈውስ የተቸሩ መዳፎች በባህር ዳር
Camera Icon

ፎቶ፡ አብነት ቢሆነኝ

በባህር ዳር ነዋሪዎች ዘንድ “አባ አልቃድር” ተብለው ይታወቁ የነበሩት አንጋፋው ሀጂ አልቃድር ሙሐመድ ከተማዋ ገና መንደር ሳለች፣ በአፄ ኃይሌስላሴ የመጀመሪያዎቹ ንግስና ወቅት የኖሩ ናቸው። ሃጂ አልቃድር እንደዛሬው ከተማው ሳይደምቅ፣ መንገዱ ሰፍቶ በተሽከርካሪ ሳይጨናነቅ፣ ነዋሪውም እንደአሁኑ ሳይበዛ በከተማው የከበሩ ነጋዴ እንደነበሩ የዕድሜ ባለፀጎች ይናገራሉ።

ሀጂ አልቃድር ከንግድ ስራቸው ጎን ለጎን በመጋዘናቸው ውስጥ የሰውነት ክፍል እክል ገጥሞት ለሚመጣ ሰው በመዳፋቸው ብቻ በመዳሰስ የጎበጠውን ሲያቃኑ፣ የተሰበረውን ሲጠግኑ በወጌሻነት ብዙ አመታትን አሳልፈዋል። ይህንንም የፈውስ አገልግሎት በነፃ ሲሰጡ እንደኖሩ ቀደምት የከተማው ነዋሪዎች ያስታውሳሉ።

ሃጂ አልቃድር ከዚህ አለም በሞት ከተለዩ አስርት አመታት ቢያልፉም ስማቸውን እና ተግባራቸውን አንስቶ እስከዛሬ የዘለቀ ተተኪ ግን አግኝተዋል። ተተኪው ሃጂ ኑሩ ካሴ ሲሆኑ በባህር ዳር ነዋሪዎች ዘንድ ግን የሚታወቁት በሞያ አባታቸው በአባ አልቃድር ስም ነው።   

አንጋፋው አባ አልቃድር በህይወት እያሉ ለንግድ ስራቸው አጋዥ እንዲሆን የቀጠሩት የያኔው ወጣት ኑሩ ካሴ (የዛሬው የእድሜ ባለፀጋ ሀጂ ኑሩ ካሴ) በእሳቸው መጋዘን ውስጥ በመስራት የእለት እንጀራውን ያገኝ ነበር። ጉልበታቸው እየደከመ እንደሆነ የተረዱት አባ አልቃድር ይህን አስፈላጊ ሙያ በስጋ ለሚዛመዷቸው ዘመዶች እና ልጆቻቸው አላስተላለፉትም። ይልቁኑም ቀልባቸው ለአረፈበት ሰራተኛቸው ኑሩ ካሴ መክረው እና አስጠንተው በሂደት አወረሱ። 

ሀጂ ኑሩ ካሴም ከዛሬ አርባ ዓመት በፊት በደንብ ተረድተው፣ ከሙያ አባታቸው ከአባ አልቃድር ከአደራ ጋር የተረከቡት የወጌሻነት ሙያ እስካሁኑ የእድሜ ዘመናቸው የሚታወቁበት ስራ ሊሆን በቃ።  

ሃጂ ኑሩ ሁሴን (አባ አልቃድር)   ፎቶ፡ አብነት ቢሆነኝ

ወጌሻነቱን የጀመሩ ዘመን በመጋዘኑ የተለያዩ ስራዎችን እየሰሩ በጎን ደግሞ የተጎዳ ሲመጣ ይጠግኑ ነበር። አልፎ አልፎ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ጉዳይ ሲገጥማቸው ታላቁን አባ አልቃድርን እየጠሩ ያግዟቸው እንደነበር ይናገራሉ። በጊዜ ሂደት ግን ለሙያው ባላቸው ፍላጎት ከታላቃቸው አባ አልቃድር በበለጠ እሳቸው በስራው ላይ ብዙ ጊዜ ማሳለፍ እንደጀመሩ ያስታውሳሉ።

አንጋፋው አባ አልቃድር የምድር ቆይታቸውን ጨርሰው ወደ ማይቀረው ሲሄዱ ሀጂ ኑሩ ካሴ ይህን አገልግሎት በቤታቸው መስጠት ጀመሩ። የመጋዘኑም ስራ በመቋረጡ መደበኛ ስራቸው አድርገው ያዙት። የከተማውም ነዋሪ ተተኪውን ወጌሻ ባለፉት ተወዳጅ የሞያ አባታቸው ስም “አባ አልቃድር” ይሏቸው ጀመር። 

በዚህም የተነሳ ሀጂ ኑሩ እና ቤተሰባቸው ለከተማው ነዋሪ ከሞያ አባታቸው ከአባ አልቃድር ጊዜ ጀምሮ ለልጅ ልጅ የዘለቀ አበርክቶት አላቸው። በማንኛውም ሰዓት ደጃቸው የደረሰ ተጎጂ፣ ሀኪሙ የለም ወይም መብራት ጠፍቷል የሚሉ መልሶች ሳይሰጡት የፈውስ አገልግሎታቸውን ማግኘቱን የከተማው ነዋሪዎች የሚመሰክሩት ነው።

የሰው ልጅ የአኗኗር ዘይቤ ለአካል ጉዳት ሊዳርጉ በሚችሉ እንቅስቃሴዎች የተሞላ ነው። ከዘመናዊ ህክምና ይልቅ ባህላዊው ከሚመረጥባቸው የጤና እክሎች መካከል በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚከሰቱ ስብራት እና ወለምታ ቀዳሚዎቹ ናቸው። 

በሀገራችን ባህላዊ ህክምና የራሱ አደረጃጀት እና የአሰራር ስርዓት ቢጎለውም ለጤናው ዘርፍ አበርክቶው ብዙ ነው። በባህላዊ መንገድ ከሚሰጡ ህክምናዎች መካከል የተሰበረን ወይም የወለቀ የሰውነት ክፍል በማሸት ማስተካከል የተለመደ ነው።

ታሪካቸውን ለመሰነድ ቤታቸው በተገኘን ጊዜ ሃጂ ኑሩ (አባ አልቃድር) የተለመደውን ስራቸውን በፈገግታ በተሞላ እና በጨዋታ መንፈስ ሲያካሂዱ ለመታዘብ ችለናል። የእጅ ውልቃት ገጥሞት ደጃቸው የተገኘን ታካሚ አዋዝተው እያወጉ የወለቀውን እጅ ወደ ቦታው በድንገት ሲመልሱት ታካሚው ድንገት የህመም ድምፅ ቢያሰማም ተገቢውን ህክምና ግን አግኝቷል።

አቶ ድረስ ይርጋ በባህር ዳር ከተማ ተወልደው፣ አድገውና ቤተሰብ መስርተው ይኖራሉ። አቶ ድረስ ልጆቻቸውም ሆኑ ወዳጆቻቸው ተመሳሳይ እክል ሲገጥማቸው ከዘመናዊ ህክምና ይልቅ ወደ ሃጂ ኑሩ እንደሚመጡ አጫውተውናል። ቀድሞ አገልግሎቱ በነፃ ይሰጥ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ድረስ ከዘመናዊ ህክምና ዋጋ ጋር ሲነፃፃር ይህ አሁንም የነፃ አገልግሎት ማለት ነው ይላሉ።

“ሀጂ ኑሩ (አባ አልቃድር) ለከተማው ነዋሪዎች ባበረከቱት አገልግሎት ልክ በአስተዳደሩ እውቅና አልተቸራቸውም” የሚሉት አቶ ድረስ በርካታ ትውልዶችን ደከመኝ ሳይሉ ቤተሰባቸውን ሁሉ አስተባብረው እዚህ ግባ በማይባል ገንዘብ ሲያገለግሉ የኖሩትን ወጌሻ በከተማው ህዝብና አስተዳደር ስም በይፋ ማመስገን ይገባል ይላሉ። 

ሀጂ ኑሩ ካሴ እንደሚሉት አባ አልቃድር በህይወት እያሉ ለረጅም ጊዜ አገልግሎቱን የሚሰጡት በነፃ ነበር፤ ነገር ግን ከአባ አልቃድር ሞት በኋላ እሳቸው ቀደም ሲል ሲሰሩት የነበረውን ስራ አቋርጠው ሙሉ ለሙሉ ወደህክምናው በመግባታቸው የግድ ለመኖር ሁለት ብር እያስከፈሉ ቀጥለዋል።  

ሀጂ ኑሩ (አባ አልቃድር) አሁን በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ አንድ በሚገኙበት ቤት ውስጥ ለአርባ ዓመታት በቀን በአማካኝ ከ10-15 ሰው ሲያስተናግዱ ኖረዋል። ነገር ግን ሀጂ ኑሩ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በኖሩበት ከተማ በስማቸው አይጠሩም በስማቸው አይታወቁም። ስማቸውም ሆነ መጠሪያቸው የሙያ አባታቸው አባ አልቃድር ነው። አገልግሎቱን ፈልጎ የመጣ ሰው አድራሻ ቢጠፋው የአባ አልቃድር ቤት ወዴት ነው ብሎ ጠይቆ ያገኛቸዋል።

በከተማው ሁሉም “አባ አልቃድር” ይላቸዋል እሳቸውም በዚህ እንደማይከፉ ይናገራሉ። “በመንገድ ድንገት የሚያገኘኝ ወይም ህክምና ፈልጎ ቤቴ የሚመጣ ሰው አባ አልቃድር ብሎ የፈጣሪ ሰላምታ ይሰጠኛል” ይላሉ በኩራት። 

ሀጂ ኑሩ ካሴ (አባ አልቃድር) በዚህ ሁሉ ዘመን አገልግሎታቸው በተለይ “ከገጠር አካባቢ መጥተው ተፈውሰው ሲሄዱ እረካለሁ” ያሉ ሲሆን በተለይ አንድ ዓመት ሙሉ የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ተስፋ ቆርጦ የነበረን ሰው ታሪክ አይረሱትም። 

ሰውየው ከደቡብ ጎንደር የመጣ አርሶ አደር ሲሆን ከዚያ በፊት በዘመናዊ ህክምና ተስፋ ቆርጦ ረዘም ላለ ጊዜ በቤቱ የቆየ ነበር። የሀጂ ኑሩን ባህር ዳር መኖር ሰምቶ ወደ እሳቸው ቤት ይመጣል። በደረሰበት ጉዳት ተዘርግቶ አልታጠፍ ያለ እግሩን ለአንድ ወር በአብሽ እና በቀርከሀ አስረው፣ በእሳቸው አገላለጽ "አጅለው" ማስተካከላቸውን ተርከውልናል። ፈውስ ከአገኘው አርሶ አደር ጋርም ለረጅም ጊዜ ወዳጅ ሆነው ይጠያየቁ እንደነበር አጫውተውናል። 

“በስራዬ ገንዘብ ባስቀድም ኖሮ ዛሬ ባለፀጋ ነበርኩ” የሚሉት ሀጂ ኑሩ ፈውስ በተቸረ መዳፋቸው ለሰዎች ባበረከቱት መልካም አስተዋጽኦ ፈጣሪ ይከፍለኛል የሚል ተስፋ አላቸው።       

ሀጂ ኑሩ ካሴ (አባ አልቃድር) በቀድሞው በጌምድር ክፍለ ሀገር (በአሁኑ ጎንደር) በ1944 ዓ.ም በዓርብ ገበያ እንደተወለዱ አጫውተውናል። ነገር ግን በሞያቸው የታወቁትና ስምም ያፈሩት ባህር ዳር ውስጥ ነው። በዕድሜያቸው መጀመሪያ የንግድ ስራ ቢከውኑም አሁን ግን መሉ በሙሉ በወጌሻነት ስራቸው ላይ አተኩረዋል። 

የሰባ ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ ሃጂ ኑሩ ባለትዳርና የሶስት ሴቶችና አራት ወንዶች ልጆች አባት ናቸው። 

“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስኳር በሽታ ተጠናውቶኝ አቅሜ እየደከመ ይገኛል” ይላሉ ሀጂ እንደወትሮው በሙሉ አቅማቸው አለመስራታቸውን ሲገልፁ፡፡ በዚህም ምክንያት ይህን የተከበረ ሙያ ለትውልድ ማስተላለፍ ስለሚያስፈልግ ከአሏቸው ልጆች መካከል ኡመር ኑሩን መርጠው እያስተማሩት እንደሆነ ነግረውናል።

ኡመር ኑሩ የአባቱን ፈለግ ተከትሎ እየሰራ ሲሆን በህክምና ሙያ ባይሆንም የዩኒቨርስቲ ምሩቅ በመሆኑ ወደፊት ከእሳቸው በተሻለ ሙያውን ሊያሳድግ እንደሚችል ተስፋ ጥለውበታል።

የሀጂ ኑሩ (አባ አልቃድር) ቤተሰብ ያለፈበትን መንገድ በሰነድ መልክ የመመዝገብ እና ስራውን የማዘመን ችግር ቢጫነውም ለመገመት የሚያዳግት እክል የገጠማቸው ወገኖቹን ለዘመናት አገልግሏል። ከከተማዋ ነዋሪዎች በቤተሰብ ቢያንሰ አንድ ሰው በዚህ ቤተሰብ እጅ ተዳሷል። በጥቅሉ የዚህ ቤተሰብ ስም ለባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ከህፃን እስከ አዋቂ ቅርብ ነው።

ባሳለፉት ረጅም የአገልግሎት ዘመናቸው ሀጅ ኑሩ ካሴ (አባ አልቃድር) አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ ማስታወቂያ አስነግረው፣ አድራሻችን እዚህ ይገኛል የሚል ማስታወሻ ለጥፈውም አያውቁም። ነገር ግን በተግባራቸው ቤታቸው ጀምበር ወጥታ እስትገባ በወረፋ ይሞላል።  

በዚህ አንደ መኖሪያም ሆነ  አንደ ሀኪም ቤት በሚያገለግለው ቤት ውስጥ ከህፃን እስከ ከአዋቂ፣ ከመደበኛው ሰው እስከ ባለስልጣን፣ ከድሃ እስከ ባለፀጋ ተገኝቶ ተፈውሷል። 

ሀጂ ኑሩ ካሴ (አባ አልቃድር) ከዓመታት በፊት በረከት ያደለኝ የሚሉትን አጋጣሚ አጫውተውናል። “ስማቸውን በጊዜ እርዝማኔ የረሳሁት የእስልምና ሀይማኖት አባት ከደቡብ ጎንደር አካባቢ ታጅበው እግራቸው ወልቆ ለሶላት አስቸግሯቸው ኖሮ መጡ፤ እኔም ከብዙ ልፋትና ድካም በኋላ እግራቸውን ወደ ቦታው መልሼ አስተካከልኩላቸው” እያሉ ሲነግሩን ፊታቸው ላይ ትካዜና ፈገግታ የተቀላቀለበት ስሜት እየተነበበ ነው። የሀይማኖት አባቱም አመስግነው ሂሳብ ሊከፍሉ እጃቸውን ሲዘረጉ ሃጂ ኑር “ዱአ” ወይም ፀሎት እንጂ ገንዘብ ጥሩ አልቀበልም ስላሏቸው ዱአ እንዳደረጉላቸው ያስታውሳሉ። እንደ ሀጂ እምነት ያን ቀን የተደረገላቸው ጸሎት እስከዛሬም አብሯቸው አለ፤ ይህንንም “ያኔ በረከታቸው እንዳደረብኝ ይሰማኛል” በማለት ይገልጹታል። 

ሀጅ ኑሩ ካሴ ከአባ አልቃድር በተረከቡት ሙያ ከአርባ ዓመት በላይ የባህር ዳርን ነዋሪዎች አገልግለው በዚህም የመምህራቸውን ስም ወርሰው እስካሁን ዘልቀዋል። ከዚህ ሁሉ ዓመት አገልግሎት በኋላ አቅማቸው ሲደክም ለልጃቸው ስራቸውን ቢያወርሱም አሁንም በሚችሉት ሁሉ ታካሚዎችን ይረዳሉ። የሃጂ እና ቤተሰቦቻቸው አገልግሎት ለባህር ዳር እና አካባቢዋ ነዋሪዎች ከልጅ ልጅ የዘለቀ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ።

አስተያየት