መጋቢት 9 ፣ 2014

“ጥረት ኮርፖሬት” በጦርነቱ ከግማሽ ቢልዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሞብኛል አለ

City: Bahir Darዜና

የድርጅቱ የኮምዩኒኬሽን ሲንየር ኦፊሰር አቶ ውድነህ ገዛኸኝ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት “ሙሉ ለሙሉ በወደሙት ሦስት ድርጅቶች ውስጥ በማገልገል ላይ የነበሩ ከ400 በላይ ቋሚ እና ጊዜያዊ ሰራተኞች ከሥራ ገበታ ውጭ ሆነዋል።

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

“ጥረት ኮርፖሬት” በጦርነቱ ከግማሽ ቢልዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሞብኛል አለ
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሚዲያ

“ጥረት ኮርፖሬት” በጦርነቱ ምክንያት በአማራ ክልል የሚገኙ ሦስት ኩባንያዎቹ ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን አስታወቀ። ከወደሙት በተጨማሪ ሌሎች ስድስት ኩባንያዎች በተለያየ መጠን ጉዳት ደርሶባቸል ተብሏል።   

የድርጅቱ የኮምዩኒኬሽን ሲንየር ኦፊሰር አቶ ውድነህ ገዛኸኝ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት “ሙሉ ለሙሉ በወደሙት ሦስት ድርጅቶች ውስጥ በማገልገል ላይ የነበሩ ከ400 በላይ ቋሚ እና ጊዜያዊ ሰራተኞች ከሥራ ገበታ ውጭ ሆነዋል። የቀደመ ስያሜውን ወደ “ንጋት የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት” እንደቀየረም ኃላፊው ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

በሦስቱ ድርጅቶች ብቻ ከ230 ሚልዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት በኪሳራ የተመዘገበ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በጦርነቱ ምክንያት ከ527 ሚልዮን ብር በላይ የሚገመት ሐብት ወድሟል።

ሙሉ ለሙሉ በመውደማቸው ከሥራ ውጭ የሆኑት ኩባንያዎች “የጃሪ የተፈጥሮ ምንጭ ውሃ”፣ “የጁ የማር ውጤቶች ማቀነባበሪያ”፣ “ወልዲያ አትክልትና ፍራፍሬ” መሆናቸው ተነግሯል። በተለያየ መጠን መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸው በፈጣን ጥገና ወደ ሥራ የገቡት ደግሞ “ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ”፣ “ዋልያ ቆርኪ ፋብሪካ”፣ “አምባሰል የንግድ ስራ ድርጅት የምስራቅ አማራ ቅርንጫፍ”፣ “ቢ.ዲ.ሲ ኮንስትራክሽን”፣ “ተላጀ ጋርመት”፣ “ጥቁር ዓባይ የትራንስፖርት ድርጅት” ስለመሆናቸው አቶ ውድነህ ነግረውናል።

እንደ አቶ ወድነህ ማብራሪያ በወደሙት ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው ሲያገለግሉ የቆዩ ሰራተኞች ቀድሞ ይሰሩበት ከነበረ ድርጅት ጋር የሚመሳሰል ምርት ወደሚያመርቱ ተቋማት ተመድበው እንዲሰሩ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። “ዘላቂው መፍትሔ የወደሙትን ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ መመለስ ነው። ያንን ለማሳካትም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው” የሚሉት ኃላፊው በጦርነቱ ወቅት የተዘረፉ ማሽኖች መኖራቸውንም ተናግረዋል “በሦስቱም ድርጅቶች ውስጥ የነበሩት ማሽኖች ያልተወሳሰበ ስሪት ያላቸው፣ በቀላሉ መንቀሳቀስ የሚችሉ በመሆናቸው ለአጥፊው ቡድን የዘረፋ ተግባር ተመችተዋል” ብለዋል።

በ2013/14 ከአለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 49 በመቶ ብልጫ በማሳየት 463.8 ሚሊየን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝቻለሁ ያለው የቀድሞው “ጥረት ኮርፖሬት” ተጠሪነቱ ለአማራ ክልል ምክር ቤት እንዲሆን መደረጉ ይታወሳል። የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ በብአዴን ባለቤትነት እና መሪነት መተዳደሩ ቀርቶ የክልሉ ሕዝብ እንዲሆን ተወስኗል። ውሳኔውን ተከትሎ “ንጋት የዘላቂ በጎ አድራጎት ድርጅት” በሚል ስያሜ ሥራውን በመቀጠል ላይ ይገኛል። 

ባለፉት 3 ዓመታት ብቻ በ7 ቢሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ያደረገው፤ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአገልግሎት፣ በግብርና፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኮንስትራክሽን እና ማማከር ዘርፎች የተሰማራው ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከ13 ቢልየን ብር በላይ ሐብት አለው።

የድርጅቱ ዓመታዊ ሪፖርት ዕንደሚያሳየው "ንጋት የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርችት” በግሉ 15 ከአጋር ድርጅቶቹ ጋር 4 በድምሩ 19 ኩባንያዎችን ያቀፈ ሲሆን በጥናት ሂደት ላይ የሚገኙ ሌሎች 6 ፕሮጀክቶችም አሉት።

አስተያየት