ሚያዝያ 30 ፣ 2014

በአማራ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዝርፊያ እንደተፈፀመ ታወቀ

City: Bahir Darዜና

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሰጡት መግለጫ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ እየደረሰ ያለው ስርቆትና ውድመት በመጠንና በስፋት እየጨመረ መምጣቱን አስታውቀዋል

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

በአማራ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዝርፊያ እንደተፈፀመ ታወቀ
Camera Icon

Credit: Amhara Electric Service

የአማራ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክልሉ ከጦርነቱ ቀጠና ውጭ ባሉ አካባቢዎች ብቻ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዝርፊያ እንደተፈፀመበት ታወቀ። 

የአማራ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ማተቤ አለሙ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኤሌክትሪክ የመሰረተ ልማት ዝርፊያ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ተፈፅሟል ያሉ ሲሆን ኪሳራው አገልግሎቱ ከኃይል ሽያጭ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ገቢ ሳይጨምር የተከሰተ ኪሳራ ነው ብለዋል።

በዘረፋ ወንጀሉ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የኃይል መቋረጥ ለቀናት መከሰቱ የታወቀ ሲሆን ኃይል በተቋረጠባቸው ከተሞች በስራ ላይ የነበሩ ፋብሪካዎች ግምቱ ያልታወቀ የምርት ብልሽት እንደገጠማቸውም የኮሚኒኬሽን ኃላፊው አስረድተዋል።

እንደ ኮሚኒኬሽኑ ኃላፊ ማብራሪያ ዝርፊያው የተፈፀመው ከ “ሰብስቴሽን” ተነስተው ወደተለያዩ ከተሞች ኃይል በሚያሰራጩ ከፍተኛ የኃይል አስተላላፊ መስመሮች ላይ ሲሆን በዚህም ምክንያት በክልሉ በሚገኙ በአያሌ ከተሞች ለቀናት የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ እንዲፈጠር ማድረጉንና ተመሳሳይ ዝርፊያዎች የሚያስከትሉት ተፅዕኖም ሰፊ ጉዳትና ኪሳራ እንደሆነ አስረድተዋል።

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዝርፊያው በኤሌክትሪክ  አገልግሎት ባለሙያዎች ጭምር ይፈፀማል ለሚለው የህበረተሰቡ ቅሬታን በተመለከተ አቶ ማተቤ በሰጡት ምላሽ በየትኛውም አካል ለተፈፀመ ዝርፊያ የአማራ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ ከደረሰው አስተዳደራዊ እርምጃ ከመውሰድ በተጨማሪ ለህግ በማቅረብ ለማስቀጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኤሌክትሪክ የመሰረተ ልማት ዝርፊያ ፈፅመው የተገኙ አካላት ላይ በፍትህ ተቋማት አስተማሪ እርምጃ እየተወሰደ ባለመሆኑ ችግሩ እየተባባሰ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ኃላፊው ተናግረዋል። እየተባባሰ የመጣውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዝርፊያ ለመከላከል የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ሊተገበር እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን መንግስት የህግ ማቀፍ ያዘጋጀ በመሆኑ ችግሩን ለመከላከል የህብረተሰቡ ትብብር ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።

በቅርቡ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዝርፊያ ከተፈፀመባቸው መካከል ከባህር ዳር- ከዳንግላ 66KV የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ የብረት ታወር፤ ከባህር ዳር ወደ ጭስ አባይ በሚሄደው ባለ 15KV 720 ሜትር የአሉሚኒም ሽቦ፣ ለሳንጃና አካባቢው ከተሞች ኃይል የሚያሰራጭ ባለ 33KV አገልግሎት መስጫ ማዕከል እና በጎንደር ከተማ በትራንስፎርመር ላይ የተፈፀሙ ዝርፊያዎች አንደሚገኙበት ከአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሚያዝያ 26 ቀን ለ ኢዜአ በሰጡት መግለጫ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ እየደረሰ ያለው ስርቆትና ውድመት በመጠንና በስፋት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው ስርቆቱ የጨመረው ድርጊቱን በሚፈጽሙ ወንጀለኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪ ባለመሆኑ ነው ብለዋል። በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ የሚፈጸመውን ስርቆት ለመከላከል ድርጊቱን በሚፈጽሙ ወንጀለኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪና ተመጣጣኝ ሊሆን እንደሚገባም ተቋማቱ አሳስበዋል።

በዘገባው የፍትህ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አወል ሱልጣን እንዳስረዱት፤ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጡ መሳሪያዎች ላይ የሚፈጸሙ ስርቆቶች በከባድ ወንጀል ያስጠይቃሉ ብለዋል።

በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ የሚፈጸም ስርቆትን ለመከላከልና ተፈጽሞ ሲገኝ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የኢነርጂ አዋጅ ያለ ሲሆን፤ በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ ስርቆት የሚፈጽም ወይም ጉዳት የሚያደርስ አካል በኢነርጂ አዋጅ 810/2006 አንቀጽ 26 እና 29 ተጠያቂ ይሆናል።

የአዋጁ አንቀጽ 26 በማመንጫ፣ ማሰተላለፊያ ወይም ማከፋፈያ ተቋማት ላይ ጉዳት ያደረሰ ማንኛውም ሰው ከ5 እስከ 15 አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም እስከ ብር 50 ሺህ የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ ይደነግጋል።