የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ከመንግሥታዊ ሳንሱር እስከ የእርስ-በእርስ ቁጥጥር

Avatar: Ayele Addis
አየለ አዲስሐምሌ 27 ፣ 2013
City: Bahir Darሚድያ ወቅታዊ ጉዳዮች
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ከመንግሥታዊ ሳንሱር እስከ የእርስ-በእርስ ቁጥጥር

የመገናኛ ብዙኃን ቁጥጥር ስራ ከመነሻው ለዚሁ ተግባር ተብሎ እንደዛሬው ለብቻው በተቋቋመ ድርጅት ውስጥ የሚካሄድ አልነበረም፡፡ በሌሎቹ ድርጅቶች ውስጥ ከሌላ የስራ ዘርፍ ጋር እየተያያዘ ሲሰራ እንደነበር የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰነድ ያስረዳል፡፡

በመጀመሪያ ጊዜ የሳንሱር ስራ ይከናወን የነበረው በ1934 ዓ.ም. በተቋቋመው በጽሕፈት ሚኒስቴር ወስጥ ነበር፡፡ የፕሬስና የማስታወቂያ ክፍል ኃላፊነት ማስታወቂያና ኢንፎርሜሽን ስራ ማከናወንና የመንግስት ማተሚያ ቤቶችና ጋዜጦችን መቆጣጠር ነበር፡፡ በጋዜጦች ቁጥጥር ስራ ውስጥ የሳንሱር ተግባር ይከናወን ነበር፡፡ ይህ በጽሕፈት ሚኒስቴር ስር ይከናወን ነበረው የሳንሱር ስራ በ1935 ዓ.ም. በአዋጅ ታወቀ፡፡ አዋጁ ቲያትርና የሲኒማን ስለመምርመር የወጣ አዋጅ ቁጥር 37/1935 ተብሎ ይታወቃል፡፡

ከ23 ዓመት በኋላ የማስታወቂያና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስልጣንና ተግባር የወሰነው፡፡ ትዕዛዝ ቁጥር 46/1957 ዓ.ም. የሳንሱር ስራ በዚህ ሚኒስቴር ውስጥ ይካሄድ እንደነበር ይገለጻል፡፡ ይህ አዋጅ የሰጠውን ስልጣን መሰረት በማድረግ የማስታወቂያና ቱሪዝም ሚኒስቴር የምርመራ ቦርድ በሚል ስያሜ አንድ የራሱን ቻለ የሳንሱር ክፍል አቋቋመ፡፡

የምርመራ ቦርዱ 4 ክፍሎች የነበሩት ሲሆን፡- እነሱም፡- የሀገር ውስጥ እትሞች ምርመራ የውጭ ሀገር እትሞች ምርመራ፣ የፊልም ምርመራና የቲያትር ምርመራ ክፍል ነበሩ፡፡

በማስታወቂያ ቱሪዝም ሰብሳቢነት የትምህርት ፣የሀገር ግዛት፣ ህዝባዊ ኑሮ እድገት ሚኒስቴሮች፣ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤትና ፖሊስ ሰራዊት ተወካዮች ምርመራ ቦርድ አባል ሆነው እንዲሰሩ ተደረገ፡፡

ከሰኔ 20/19/64 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የምርራ ቦርድ የሚው ስያሜ ቀርቶ “የምርመራ ዋና መምሪያ” ተብሎ እንዲሰራ ተወሰነ፡፡

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከ5 ድርጅቶች ከተውጣጡ የቦርድ አባላት ይካሄድ የነበረው የምርመራ ስራ በምርምር ዋና መምሪያ መደበኛ ሰራተኞች ብቻ እንዲከናወን ተደረገ፡፡ በዚህ አኳኋን እስከ 1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ፍንዳታ ድረስ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ከ1934 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ የሳንሱር ድርጅታዊ መዋቅር ደረጃ በደረጃ እየተጠናከረ እተስፋፋ መጥቷል፡፡ ከዚህ የመዋቅር ጥንካሬና መስፋፋት ጋር አንጻራዊ የሆነ ፖሊሲና የአሰራር እድገትም ታይቷል፡፡

በ1934 ዓ.ም. በጽሕፈት ሚኒስቴር ስር የነበረው የፕሬስና የማስታወቂያ ክፍል ጋዜጦችን ይቆጣጠር እንደነበር ቢገለጽም የሳንሱሩ መምሪያ ፖሊሲ ምን እንደነበር አያታወቅም፡፡ ነገር ግን ከ1 ዓመት በኋላ በ1935 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ ቁጥር 37/1935 በቀጥታ ሳንሱርን የሚመለከት የመጀመሪያ አዋጅ ነበር፡፡ ከወጣበት ጊዜ አንጻር ሲገመገም በቂና ጥሩ እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡ ምን ያህል ብቃትና ስፋት እንዲኖረው የተደረገበት ምክንያት ደግሞ የነበረው ስርዓት የህዝቡን ስሜት ለመቆጣጠር የነበረውን ፍላጎትና ያደረገውን ጥረት ያመለክታል፡፡ በእርግጥ የቁጥጥሩ ዓላማ ስርዓተ ነጸብራቅ ነበርና ለህዝቡ ሳይሆን በህዝቡ ላይ የሚደረግ ነበር፡፡

አዋጁ 10 ነጥቦች ይዟል፡፡ ሳይመረመሩ ለህዝብ መቅረብ የሌላቸውን ነገሮች በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ያልተመረመሩ ነገሮችን ለህዝብ  ማቅረብ የተከለከለ ስለመሆኑና ሊያስከትል የሚችውንም፣ ቅጣት ወስኗል፡፡ ባጭሩ ለምን እንደሚደረግ መግለጽ ይሞክራል፡፡ እነዚህን ነጥቦች አዋጁ እንዴት እንደገለጻቸው መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡

- በዚህ አዋጅ የጸና ሕግ ከሆነበት ጊዜ በኋላ 15 ቀን ቆይቶ ማናቸውንም ፊልም ቲያትርና ..ቪዲዮ.. ይህም መሰል ልዩ ልዩ ጨዋታ መርማሪ ሳይመረምራቸው በህዝብ ዕንዲታዩ ማቅረብ ኤቻልም፡፡ /4ኛ ቁጥር/

- ማንኛውም ፊልም፣ ቲያትር ቪድዮና ልዩ ልዩ ጨዋታ አስቀድሞ ለጨዋታ መርማሪው ሳይቀርብ ወይም ለጨዋታ መርማሪው እንደቀረበለት ዓይነት ሳይሆን ለህዝብ ሲታይ ይህንኑ የሰሩና ያስተባበሩ በአሰራርም ተከፋይ የሆነ ሁሉ በደለኞች ይሆናሉ፡፡ /9ኛ ቁጥር/

- ይህን አዋጅ የተላለፈ ለዚህም የተመሰከረለት ሰው ከ500 ብር በማይበልጥ መዋጫ ወይም ከ6 ወር በማይበልጥ እስራት ወይም በሁለቱም በገንዘብ መቀመጫ በእስራት ይቀጣሉ፡፡ /10ኛ ቁጥር/

- በጨዋታ መርማሪው ፊልሙን፣ ትያትሩን ቪዲዮውንና ይህንኑ የመሰለውን ልዩ ልዩ ጨዋታ ህዝብና የህዝብን ጸጥታና ንጽህና የሚያበላሽና ብልግና ያለበት መሆኑን መሰረት አድርጎ ነው፡፡ /7ኛ ቁጥር/

የጽሕፈት ሚኒሰቴር በንጉሠነገሥቱ አስፈላጊ ሆኖ በሚታየው ከተማ ሁሉ ጨዋታ መርማሪ መሾም እንደሚችል በአዋጅ ተደንግጓል፡፡ በአዋጁ መሰረት በእያንዳንዱ ፊልም፣ ቲያትር ሪቪውና ስለ ሌሎችም ምርመራ በሚደረግላቸው ጉዳዮች 5 ብር ይከፈል ነበር፡፡

በ1958 ዓ.ም. “የማስታወቂያና ቱሪዝም ሚኒስቴርን” ሥልጣንና ተግባር የወሰነው ትዕዛዝ ቁጥር 46/1958 በኢትዮጵያ ውስጥ ለህዝብ የሚታዩ ትርኢቶችን ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የሚገቡና በኢትዮጵያም ውስጥ የሚታተሙ ጽሑፎች ይዘት ምን መምሰልና ከምን ነገሮች ነጻ መሆን እንዳለባቸው 23 ዓመት ስፋት ከወጣው አዋጅ ቁጥር 27 /1935 በጣም ሰፋ ባለ ሁኔታ ገልጾታል፡፡

- በኢትዮጵያ ውስጥ ለህዝብ የሚታዩ ፊልሞች፣ ቲያትሮች፣ ሌሎችም ህዝብ መደሰቻ ትርኢቶች ሁሉ የህዝብን ግብረ ገብነት የማያበላሹ ወይም የንጉሠነገሥቱን ጸጥታ የማያናጉ መሆናቸውን ያረጋግጣል፡፡

- ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የሚገቡት የታተሙ ጽሑፎች እና በኢትዮጵያም ውስጥ የሚታተሙ ሁሉ የኅብረተሰቡን ግብረ ገብነትን የማያበላሹ ወይም የህዝቡን ጸጥታ የማይጎዱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ኃላፊ ነው፡፡

በወጡት አዋጆችና ትዕዛዞች ላይ ተመስርቶ በውስጥና በውጭ ፖለቲካ እንዲሁም በሞራል ረገድ ሳንሱር ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ ነጥቦች በዝርዝር መመሪያ ቀርበዋል፡፡ እነዚህ መመሪያዎች ያንን ስርዓት ያሳስቡትና ያሳድጉት የነበሩት ጉዳዮችን በግልጽ ያሳያሉ፡፡ የውስጥ የፖለቲካን አስመልክቶ ከተከለከሉት ነገሮች ውስጥ ጥቂቶችን ብቻ እንመለልከት፣

- የንጉሠነገሥትን መሰረታዊ አቋም የሚነቅፍ

- የንጉሠነገሥቱን፣ የንጉሣውያን ቤተሰቦችንና የሚኒስቴሮችን ክብር የሚነካ

- ስራ ፈት፣ ስለ ሴተኛ አዳሪና ስለ ለማኞች ብዛት፡፡

- ስለ አሰሪና ሰራተኛ ግጭት፣ ስለ ተማሪ ሁከት

- ስለ ኑሮ ውድነት፣ ስለ አድማ፣ ስለ መሬት ስሪት

- ስለ ወታደር ደመወዝ፣ ስለ ኢትዮጵያ የኑሮ ደረጃ

- ስለ ኅብረተሰባዊነት /ስለ ሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም/ የሚያብራሩ ጽሑፎች፣ ፊልሞች፣ ቲያትሮች… ወዘተ ትርኢት የተከለከለ ነው፡፡

እነዚህ ከላይ የተተቀሱትን መመሪያዎች ሙሉ በሙሉ በተግባር የሚተረጎሙ ነበሩ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ አዋጅና መምሪያ ወጥቶላቸው በተግባር የማይተረጎሙ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ እነዚህም ህዝብን ሞራል በሚመለከት የሚወጡ አዋጆች መመሪያዎችን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ ለህዝብ የሚታዩ ፊልሞች፣ ቲያትሮች… ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የታተሙ ጽሑፎችና በኢትዮጵያም ውስጥ የሚታተሙ ሁሉ የህዝቡን ግብረ ገብነት የማያበላሹ መሆናቸው መረጋገጥ እንዳለበት በአዋጅ በግልጽ ተቀምጧል፡፡

ይሁን እንጂ ይህን የመሳሰሉት አዋጆች ሆኑ መምሪያዎች በጽሑፍ ይኑሩ እንጂ በተግባር የተተረጎሙ አልነበሩም፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ የሚታዩት ፊልሞችና ከውጭ የሚገቡት እትሞች ስለ ሽርሙጥና፣ ስለ ሌብነት፣ ስለ ስካርና፣ ሌሎችም ህዝብ ሞራል ስለሚያላሽቁ ነገሮች በሰፊው የሚያቀርቡ እንደነበሩ በቂ ማስረጃዎች ይገኛሉ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት እነዚህ ነገሮች ጎጂ መሆናቸው አልታወቀም ብሎ ወይም መከልከሉ ስለ ነገሮች ሳይሆን፣ የነበረው ስርዓት ህዝቡን ሞራል መበላሸት ይፈልግ ስለነበር ነው፡፡

በአድሀሪው ስርዓት ውስጥ አዋጅና መምሪያ በተግባር ለመተግበር የሚያስችሉ ጠቅላላ ሁኔታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያሻስል ከምርመራ ታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡ 

በ1934 በጽሕፈት ሚኒስቴር ስር በአንድ ክፍል ውስጥ ከሌሎች ስራዎች ጋር ተደርቦ ይሰራ የነበረው ሳንሱር ስር በ1958 በቦርድ፣ በ1964 በዋና መምሪያ ደረጃ በተዋቀረ ድርጅት ራሱን ችሎ እንዲካሄደ ተደርጓል፡፡   

በአመራርም ሆነ በሌላ ደረጃ በሳንሱር ውስጥ ይሰሩ የነበሩት ሰራተኞች በጥንቃቄ ይመረጡ እንደነበር ይነገራል በየጊዜው በሳንሱር ውስጥ ይሰሩ የነበሩት ሹሞች ታማኝነታቸው ከስርዓቱ ብቻ ሳይሆን በግልም በስርዓቱ ቁንጮ ላይ በሚገኙት ባለሥልጣኖችም የታወቀ መሆን እንደነበረባቸው በጊዜው የታሰሩ ሰዎች ያናገራሉ፡፡

ሳንሱር በቦርድ መስራቱ ከቀረ በኋላ ተጠሪነቱ በቀጥታ ለሚኒስቴሩ ሆኖ በመረዳት ሚኒስቴር ይመራ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ የሳንሱር ስር ንጉሱንና በንጉሱ አካባቢ የነበሩትን ባከስልጣኖች ይጨምር እንደነበር በጊዜው የነበሩ ሰዎች ያስታውቃሉ፡፡ ይህም የነበረው ስርዓት ህዝቡን በድንቁርና ለመግዛት ምን ያህል ይጥር እንደነበር ያሳያል፡፡

ሳንሱር በዘመነ ደርግ ከ1964-68 ድረስ በምርምር ዋና መምሪያነት ስራውን ያከናውን ነበር፡፡ በ1969 መምሪያ መሆኑ ቀርቶ በአገልግሎት ደረጃ እንዲዋቀርና ተጠሪነቱም ለቋሚ ተጠሪ እንዲሆን ተጠሪነቱም ለቋሚ ተጠሪ እንዲሆን ተደረገ፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ አብዮት ፍንዳታ ጋር አብሮ በተከሰተው የስነ-ጥበባት እድገት ምክንያት ምርመራ ስራ ቀድሞ ታቶ ባልታወቀ ሁኔታ ስለሰፋ ቅድመ አብዮት በ4 ክፍሎች ይሰራ የነበረው ሳንሱር ከ1970 ጀምሮ 2 ዋና ክፍሎች ከፍቶ በ2 ዋና ክፍሎችና በ4 ክፍሎች ተዋቀረ፡፡

ከአብዮቱ በፊት እና በኃላ ሳንሱር ለኢትዮጵያ መሪ የፖለቲካ ስርዓት ያገለግል ነበር፡፡ ይህም ስርዓት በሳንሱር ፖሊሲ ያገለገለ ከዚያ ስርዓት፣ በመነጨለት ፖሊሲና መምሪያ ነበር፡፡ አብዮት ፈንድቶ አዲስና ተራማጅ ስርዓት ሲተካና ሳንሱርም በዚህ አዲስ ስርዓት ውስጥ ለመስራት ሲነሳ የአዲስ ስርዓት ነጸብራቅ የሆነ አዲስ ፖሊሲና መመሪያ ማግኘቱ አስፈላጊና ግድም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የምርመራ አገልግሎት አብዮታቸው ያወጣቸውን ስር ነቀል ፖሊሲዎች ተከትሎ ስራውን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ዛሬ የሚሰራባቸው ልዩ ልዩ መመሪያዎች ለውጥ ሲመጣ ወዲያው የተገኙ ሳይሆኑ ከኢትዮጵያ አብዮት ሂደት እድገትና ስፋት ጋር ቀስ በቀስ የተገኙ የዳበሩና የተሸሻሉ ናቸው፡፡

ከአብዮታችን ፍንዳታ በኋላ በመመሪያዎቹ ጥቂት ወራቶች ውስጥ የዓዲሱ ስርዓት ነጸብራቅ የሆኑ መመሪያዎች ማግኘት ባለመቻሉ የምርመራ አገልግሎት ተግባር አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነበር፡፡ ለውጡን ተከትለው ሀገሪቱን ባጥለቀለቋት የሀገር ውስጥና የውጭ ከተሞች፣ ፊልሞች፣ ስዕሎች፣ ፓስተሮችና ሙዚቃዎች ላይ ሐገሪቱ ከምትከተለው ስርዓት አንጻር ውሳኔዎችን ለመስጠት ከባድ ችግር ነበር፡፡ ችግሩን ያከበደው የመመሪያዎች ለመኖር ብቻ ሳይሆን ሰራተኞች ለአዲሱ ስርዓትና ሳይንስ አዲሶች በመሆናቸው ጭምር ነበር፡፡

አብዮታዊ ኢትዮጵያ መምሪያ ሶሻሊዝም መሆኑን ይፋ ሆኖ የታወቀው ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት መለስተኛ ፕሮግራም በተግባር ላይ ከዋለ በኋላ ምርመራ አገልግሎት በመመሪያ በኩል የነበረበት ችግር ይፋ ባደረጋቸው ፖሊሲ ላይ ተመስርቶ ክፍሉ ላይ ልዩ መመሪያዎች በበላይ አካል እያስደነቀ ስራውን ያለ ብዙ ችግር ማከናወን ችሏል፡፡

በ1973 የማስታወቂያና መርሃ ብሄር ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ፖሊሲ መምሪያ ተዘጋጅቶ ከጸደቀና በተግባር ላይ ከዋለ ጀምሮ ምርመራ አገልግሎት ስራውን ለመፈጸም ጊዜ በተሸለ ሁኔታ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ የፖሊሲ መምሪያ ውስጥ የምርመራ አገልግሎት ከኢትዮጵያ አብዮት ፍንዳታ ወዲህ እንደየሁኔታው በየጊዜው የተከተላቸው ፖሊሲ መመሪያዎች በአንድ ላይ ተጠቃለው ይኖራሉ፡፡

በዘመነ ደርግ የወታደራዊ አገዛዝ የምርመራ አገልግሎት መምሪያ ከዚህ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች ይይዛል፡፡

1.  የምርመራ አገልግሎት በአዋጅ ለሚኒስቴሩ ከተሰጠው ተግባርና ሀላፊነት ከኢሰፓአኮ በሚተላለፍለት መመሪያ፣ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም አቢዮቱ ከደረሰበት ደረጃና ከጊዜው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በማስታወቂያና መገናኛ ብዙኃን ሚኒሰቴር ስር ከሚተዳደሩ የኢንፎርሜሽን አገልግሎቶች በስተቀር፣

ሀ. በጋዜጦች፣ በመጽሔት በመጻህፍት፣ በበራሪ እትሞች በትያትርና በፊልሞች፣ በምልክቶች፣ በንድፎች፣ በቅርጾች፣ በፎቶ ግራፍና ስዕሎች የሚገለጹት ሀሳቦች፣ አስተያቶችና ሀተታዎች የሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ መሰረታዊ መመሪያ የመንግሥቱን አቋም የማይቃወም እንዲሁም የህዝቡን ሞራልና መልካም ባህል የማያበላሹ መሆናቸውን እያረጋገጠ እንዲሰራጩ ይፈቅዳል፡፡

ለ. በኢትዮጵያና በውጭ ታትመው የሚገቡት በጋዜጦች፣ በመጽሔት በመጻህፍት፣ በበራሪ እትሞች በትያትርና በፊልሞች፣ በምልክቶች፣ በንድፎች፣ በቅርጾች፣ በፎቶ ግራፍና ስዕሎች ወዘተ የሰውን መሰረተ እኩልነት የሚያከብሩ፣ የብሄረሰቦችን እኩልነት የሚጠብቁ ፣ በሀይማኖት፣ በጾታና በመሳሰሉት ባህሪያት የመብት ልዩነት የማይፈጥሩ መሆናቸውን ያረጋግጣል፡፡

2.  በውጭ ሀገር በፊልሞች፣ በቲያትሮች፣ በንድፎች በቅርጾች፣ በስዕሎች፣ በምልክቶች፣ በጋዜጦች፣ በመጽሔቶች፣ በጽሐፍት፣ በበራሪ እትሞችና በመሳሰሉት፣ ስለ ኢትዮጵያ ትክክለኛና እውነተኛ ያልሆኑ ዜናዎች፣ ሁኔታዎችና መግለጫዎች ታትመው ሲወጡ እንዳይሰራጩ አግዶ ለበላይ ያስታውቃል፡፡ 

3.  ማናቸውም የጽሑፍ፣ የስዕል፣ የቅርጻ-ቅርጽ፣ የፊልም፣ የቲያትርና የመሳሰሉት ምርመራ በሚደረግበት ጊዜ ቢያንስ 3 አባሎች በሚገኙበት ኮሚቴ በከፍተኛ ጥንቃቄ ተመርምሮ በአንድ ድምጽ ወይም በድምጽ ብልጫ አስተያየታቸውን ካቀረቡ በኋላ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡

4.  ቲያትርና መድረክ ነክ ዝግጅት በመጀሪያ ጽሑፉ በንባብ ከተመረመረ በኋላ ከነ ሙሉ ዝግጅቱ በመድረክ ላይ ተመርምሮ ይፈቀዳል፡፡

5.  የምርመራ አገልግሎት ጽሑፍ፣ ስዕል፣ ቅርጻቅርጾችን ወይም ፊልምን አስመልክቶ አስተያየትና ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ ፈጽሞ የሚከለከሉትን ወይም ታርመው ለህዝብ የሚቀርቡትን እንደዚሁም የእድሜ ክልል ገደብ የሚደረግባቸውን የሚያስገነዝብ የመመዘኛ ነጥቦች ይኖረዋል፡፡

የምርመራ አገልግሎት ስራ የርዕዮተ ዓለም ቁጥጥር ስራ ነው፡፡ ከመንግስታዊ ስርዓት በድንገት  ወደ አዲሱ እና ተራማጁ ስርዓት ተሻግሮ ስር ነቀልነትና በፍጥነት በሚጓዘው አቢዮታዊ ስርዓት የሚመራ የኮሙኒኬሽን ፖሊሲ እና ሕግ ነበር፡፡

ሰራተኞቹ የማሌ ሳይንስ ብልጭታ ከማየታቸው በፊት በቀድሞው ስርዓት ይወገዙ የነበሩ የውጭ እትሞች፣ ፊልሞች ሙዚቃዎች፣ ስዕሎች ወዘተ ከለውጡ ጋር ሀገሪቱን አጥለቅልቋታል፡፡ እነዚህን ልዩ ልዩ ስራዎች አንብቦ፣ተመልክቶና አዳምጦ ውሳኔ ለመስጠት በዛ ወቅት ሰራተኛ ሊኖራቸው ያልቻለው የማሌ ሳይንስ እጅግ አስፈላጊ ነበር፡፡

ለአያሌ ዘመናት ሀሳብ የመግለጽ መብታቸውን ተገፈው የኖሩት ድርጅቶች፣ግለሰቦች፣ ቲያትሮች፣ ሙዚቃዎች፣ ስዕሎች እንደ እንጉዳይ አፈሏቸው፡፡ በዛ ወቅት የምርመራውን ስራ በሚገባ ለማከናወን የማሌ ሳይንስ ብቻ ሳይሆን ወቅታዊ ሁኔታወችንም ማወቅ ያስፈልግ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ አብዮት ጥቅም አንጻር የእያንዳንዱን የፖለቲካ ቡድን አቋም ማወቅና በተተሰለፈው ትግል ውስጥ የዕለቱን ተጨባጭ ሁኔታና እንቅስቃሴ ማወቁ አስፈላጊነት ነበር፡፡

ይሁን እነጂ የአገልግሎት ሰራተኞች በየግላቸው ከሚያውቁት ኢንፎርሜሽን ውጪ የፖለቲካ ቡድኖችን አቋምና የየወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታ ከየጥንስሱ የሚጠቁም ኢንፎርሜሽን ማግኘት አይቻልም ስለነበር የተለያዩ ፖለቲካ ቡድኖችን አቋም የሚያንጸባርቁትን እትሞችና ሌሎች ስራዎች ያለ ችግር መገምገም አይቻልም ነበር፡፡

ይህን በመሰለው አስጨናቂ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የምርመራ አገልግሎት ደረጃ ያለውና የስራ የትግል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የምርመራ አገልግሎት የስራ ጠባዩ ስለሆነ በውስጡ የተሰለፉት ሰራተኞች ስለ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ፍልስፍናና ስለ ወቅታዊ ሁኔታዎች የማወቅ ግዴታ ነበረባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይ ከሰራተኞቹ ውስጥ የአቢዮታችን ሙሉ ደጋፊዎች የሆኑት ጥረታቸውን ከፍ አድርገው ሳይንሱን በማጥናትና የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታዎች በጥንቃቄ በመርመር ጠቃሚ የሆኑ የስራና የትግል አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

የመደብ ትግል ነውና በአንጻሩም በአቢዮቱ ያልተደሰቱ ጥቂት ሰራተኞች ነበሩ፡፡ ግን ብዙ ችግር ከመፍጠራቸው በፊት በሰራተኛው ትክክለኛ ትግል በየጊዜው ተወግደዋል፡፡

የአገልግሎቱን የስራና የትግል አስተዋጽኦ በ2 ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡ በመጀመሪያ የኢትዮጵያን አብዮት ለመቀልበስ የተነሱ ጸረ አብዮት ቡድኖች ሊያራምዱ ከሞከሩት የሀሳብ ስርጭት ጋር የተደረገው ትልም ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ አብዮት ፍንዳታ በኋላ ብዛት ያላቸው መጽሔቶች፣ ጋዜጦችና ልዩ እትሞች ይታተሙ ነበር፡፡ ከዚህም ውስጥ አንዱ “ጎህ” የተባለው መጽሔት የቀንደኛው የኢትዮጵያ አብዮት ተፎካካሪ ኢህአፓ  ፓርቲ ልሳን ነበር፡፡ ይህ መጽሔት በህጋዊ መድረክ በኩል አልፎ ይታተም ስለነበር የምርመራ አገልግሎት እየቀረበ መፈቀድ ነበረበት፡፡ የሰራተኞቹ የንቃት ደረጃ በፈቀደለት መሰረት ምርመራ አገልግሎት በመጀመሪያ ደረጃ በየጊዜው የመጽሔቱ አዘጋጆች ያቀረቧቸውን ጸረ ሳይንስ ጽሑፎች እንዳይታተሙ በማድረግ በጸና አቋም ታግሏል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ጽሑፎቻቸው እየታገዱባቸው  ስለተቸገሩ አዘጋጆቹ በረቀቀ መንገድ በልባስ ስዕሎች አማካኝነት ያንኑ ጸረ አብዮት መልዕክታቸውን ማስተላለፍ ሲጀምሩ ከተወሰኑ ሙከራዎች በኋላ መጽሔት ያለ ሽፋን ስዕል እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም አገልግሎቱ ባደረገው ትግልና አቢዮታው መንግስት በወሰደው ቆራጥ እርምጃ መሰረት ጎህ መጽሔት መስከረም 20 ቀን 1969 ዓ.ም. ሊታገድ ችሏል፡፡

በዛን ወቅት ጽሑፎቻቸው በታረሙና በተከለከሉ ቁጥር የመጽሔት አዘጋጆችና ደጋፊወቻቸው 5ና 6 እየሆኑ በትጥቅ በመምጣት ለምን ታረምንና ተከለከልን የሚሉ ጥያቄዎችን ከጉልበትና ከሀይል አንጻር ይሰነዝሩ ነበር፡፡ ይህም በመርማሪዎች ላይ ተጽዕኖ ያደርግ ነበር፡፡ ግለሰብ መርማሪዎች እንዳይጋለጡ ታስቦ የተመረመሩ ጽሑፎችን ና ውሳኔዎችን ከመዝገብ ቤት እንዲረከቡ በተደረገበት ጊዜም ምርመራ አገልግሎት ውስጥ በነበሩት አብዛኞዎች አማካኝነት ማን እንደከለከለ ጥቆማ ይደረግላቸው ስለነበር የአገልግሎቱ ሰራተኞች ከስጋት ሊድኑ አልቻሉም ነበር፡፡

ቀጥሎም በሀይማኖት ጥላ ስር በመካነ እየሱስ ድርጅት ተቆጣጣሪነት ይታተም የነበረው ብርሀን መጽሔት ከጎህ በኋላ ጎህን ተክቶ ሊሰራጭ የሞከረ የገዥው ፓርቲ (“ጸረ አብዮት”) መጽሔት ነበር፡፡ ይንን መጽሔት በየደረጃው ለመቆጣጠር ተሞክሮ ከጸረ አቢዮቱ ፕሮፖጋንዳው ሊታገስ ባለመቻሉ በመጨረሻ መጋቢት 23 /1973 ከህትመት ታግዷል፡፡ 

በህዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ዋና ማደራጃ ታተም የነበረው “ሰረገላ” ወርሃዊ ጋዜጣ ቀስ በቀስ የለየለት የፖለቲካ ተቃውሞ ይመራ የነበረ “ጸረ አብዮት” ተብሎ በተፈረጀ ሚና ይዞ ስለተገኘ የካቲት 1975 እትም በኋላ እንዲቆም ተደርጓል፡፡

በህትመት መልክ ከቀረቡት እነዚህ ለናሙና ያህል ተጠቀሱ እንጂ በጸረ-አብዮት ይዘታቸው የሚታረሙና የሚከለከሉ ጽሐፍቶች ፣ መጽሔቶች፣ ጋዜጦች፣ ቲያትሮች፣ ፊልሞች፣ ስዕሎች፣ ሙዚቃዎች፣ ቁጥር እጅግ ብዙ ነው፡፡

በተለይ የኢትዮጵያ አብዮት ፍንዳታ ተከትለው ሀገር ወስጥ እንዲገቡና እንዲሰራጩ ጥረት ይደረግላቸው የነበሩት ልዩ ልዩ የምዕራባውያን እትሞች ቢሰራጩ ኖሮ አቢዮቱን ለማቆም ባይችሉም ጉዳት ያደርሱ ይችላሉ የሚል ግምት መንግስት አስቀምጦ ነበር፡፡

የምርመራ አገልግሎት 2ኛው ምዕራፍ የስራና የትግል አስተዋጽኦ፣ አቢዮታዊ ይዘት ያላቸው ግን ስነ ጥበባዊ ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ ስራዎች እየታረሙና እየተሸሻሉ ለህዝበ እንዲቀርቡ በማድረግ ረገድ የሰጠው ድጋፍ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

“የመደብ ጥቅማቸው የተነካባቸው የኪነ ጥበብ ሰዎች ብዕርና ብሩሻቸውን ለኢትዮጵያ አብዮት ማንሳት ሲሳናቸው፣ በምትካቸው የኢትዮጵያን አብዮት የሚደግፉ ብዕሮችና ብሩሾች ፈለቁ፡፡” ሲል የደርግ ዘመንን የ10 ዓመታት የሚዲያ ጉዞ የገመገመው ሰነድ ተቃውሞን በማገድ ከድጋፍ ወገን ማሰለፍ መቻሉን ይጠቅሳል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ አቋሙና ፍላጎቱ ቢኖራቸውም፣ የርዕዮተ ዓለማዊ ዓመለካከት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ነበሩ፡፡ የምርመራ አገልግሎት አቅሙ በፈቀደ መሰረት እነዚህን ከመደገፍና ከማበረታት አልዘለለም፡፡

ከዚህ በላይ የቀረቡ ማስረጃዎች ለናሙና የቀረቡ እንጂ ሁሉም ሚዲያዎች በሚያቀርቧቸው ዜና፣ ሀተታ፣ ልዩ ዝግጅትና ፕሮግራሞች ሁሉ ህዝባዊና አቢዮታዊ ወገናዊነታቸው በሚገባ አንጸባርቀዋል፡፡ ሁሉም ዝግጅት ለሶሻሊስት ስርዓት ግንባታ በሚል መፈክር ስር በመሰለፍ የማስታወቂያና መርሀ ብሄር ሚኒስቴር ሰፊው ህዝብ ለብሄራዊ አንድነት ለህልውናው በጋራ እንዲሰለፍ አቢዎታዊው መንግስት በየወቅቱ የሚያወጣቸውን አዋጆች መግለጫዎችና መመሪያዎች በሚገባ የሚያስተጋባ እና ለተግባራዊ እንቅስቃሴ ክንዱን እንዲያጠነክር የሚያግዝ መሳሪያ ነበር፡፡

እያንዳንዱ ሚዲያ ከአነስተኛ ዜና አንስቶ ስከ ልዩ ፕሮግራም ድረስ የሚያቀርባቸው ዝግጅቶች ሁሉ መደባዊ ይዘት እንዲኖራቸው በ66 የተጀመረውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ እንዲያጠናክሩ፣ አዲሲቷን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት አጋዥ ሀይል ሁኖ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡

በዚህም መሰረት የማስታወቂያና መገናኛ ብዙኃን ሚኒስቴር በዚያን ወቅት ከሶሻሊስት ሀገሮች ጋር የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር አሰራሩን ፍጹም ሶሻሊስታዊ ለማድረግ አይነተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ከሶቭየት ህብረት፣ ከጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ከየመን ህዝባዊት ሪፐብሊክ ህብረት፣ ከቬትናም፣ ከኩባ፣ ከችኮዝላቫኪያ፣ ከኮሪያ ህዝባዊ ሪፐብሊክ፣ ከዩ ጎዝላቪያ፣ ከሀንጋሪና ከሌሎች የሶሻሊስት ሀገሮች ሚዲያ ጋር ስምምነት ውል በመፈራረም የፕሮግራምና የዜና ለውጦችን በማድረግ ላ ነው፡፡ በዚህም ለሰፊው ህዝብ ዜናዎችን ልዩ ልዩ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ አዘል ፕሮግራሞችን በማቅረብ ስለ ዓለም ህብረተሰብ ተጨባጭ ሁኔታ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው አድርጓል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን የእርስ-በእርስ ቁጥጥር በኢትዮጵያ አዲስ ለውጥ

የርስ በርስ ቁጥጥር በአንድ አገር ውስጥ የሚዲያ ተቋማት እና ባለሙያዎች ሁሉም አካላት ከሕግ በታች መሆናቸውንና በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን የሚያመለክት በጋራ የሙያ መግባባያ ላይ የተመሰረተ የሙያ መመሪያ ጽንሰ ሐሳብ ነው። የመገናኛ ብዙኃን የርስ በርስ ቁጥጥር የሚያረጋግጥ ስርዓት መገንባት ዜጎች በኃይለኞች በተለይ በሚዲያ አካላት እንዳይጠቁ ዋስትና ይሰጣል። በተመሳሳይም የመገናኛ ብዙኃን በውጫዊ እና ውስጣዊ ተፅኖ ፈጣሪዎች ማለትም እንደ መንግስት፣ ማስታወቂያ አስነጋሪዎች፣ አርታኢዎች የሚዲያ ባለቤቶች  የሚያደርሱትን ተፅኖ እንዳይደርስባቸው ያስችላል፡፡

በሚዲያዎች የርስ በርስ ቁጥጥር ከሌለ፣ የመንግስት ተቆጣጣሪ አካላት የሚጨቁኑበት እና ነፃነትን የሚነፍጉበት፣ የሙያው ገለልተኛነት የሚቀጨጭበት እና አድሎ፣ ኢፍትሃዊነት፣ ሚዛናዊ ያልሆነ አሠራር የነገሠበት ሁኔታ ይፈጠራል። የኃይል ባለቤት የሆነው መንግሥትም፣ ኃይሉ በሕግ የተገደበ እና ስልጣን የሚያጋራበት እድል እንዲፈጠር የሚያደርገው የሚዲያዎች የርስ በርስ ቁጥጥር መኖር ነው፡፡ የመንግሥት ሚዲያን የመቆጣጠር ስልጣን በሕግ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የርስ በርስ ቁጥጥር ካልተላለፈ ትልቅ አደጋ ነው፤ የሳንሱር እና የመረጃ ገዳቢነት ምንጩም ይኸው ነው። በዚህ መሰሉ ሁነት ውስጥ ደግሞ ሁለንተናዊ የጋዜጠኞችን ነፃነት ማስመዝገብ አደጋች ይሆናል፡፡

በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 34 ላይ "የመገናኛ ብዙኃን የእርስ በእርስ ቁጥጥር" ማለት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በፈቃደኝነት ላይ ተመስርተው የሚገዙበትን፣ የሙያ ሥነ-ምግባርና የመልካም አሰራር ደንብ የሚያወጡበት፣ የዘርፉን የሙያ ብቃት የሚያሳድጉበትና የተጠቃሚውን ኅብረተሰብ ቅሬታዎች የሚያስተናግዱበትን አሠራር በመዘርጋት ራሳቸውን ለሕዝቡ ተጠያቂ አድርገው እርስ በእርስ የሚተራረሙበት ሒደት ነው።

የሙያ ነፃነትን በማረጋገጥ ሂደት የሕግ የበላይነትና በሕግ መግዛት ፈጽሞ የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል። ጥቂት ሰዎች፣ ምናልባት የአገሪቱ መሪ ወይም የመሪው ታማኞች ወይም ደግሞ ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮች ሚዲያውን ሕግ እያወጡ የሚገዙበት፣ እነሱ ግን በሕግ የማይጠየቁበት ስርዓት ሊኖር አይገባም። የመገናኛ ብዙኃን የርስ በርስ ቁጥጥር ውስጥ የሕጉ ዓላማ ሙያውን እና ሙያተኞችን ከኃይለኞች፣ ከጉልበተኞች በተለይ ከመንግሥት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ ህዝቡን በታማኝነት እና በወገንተኛነት ማገልገል ነው።

በሌላ መልኩ የመገናኛ ብዙኃን የርስ በርስ ቁጥጥር የፍትሕ ስርዓት ቀዳሚ በር ነው፡፡ ጥቂት የሚዲያ ተቋማት አጀንዳ ብቻ በኢፍትሃዊነት እንዳይቀርብ እና አሳሳች ዘገባዎች እንዳያቀርቡ በጋራ ሙያውን ባማከለ እና በሙያው ባለቤቶች ይሁንታ በተሰጠው ሕግ መመራት ነው። ፍትሐዊነት እንዲሰፍን ሁሉም ጋዜጠኛ ለራሱ የሙያደህንነት ሲል በጋራ ለሙያው መመሪያዎችን ለማክበር የቆመ መሆን አለበት። ለመከበር ብቻ ሳይሆን ለማስከበርም የበኩሉን ማድረግ ይኖርበታል። የመገናኛ ብዙኃን ፍትህን በራስ እጅ ሳይሆን በሙያው ገለለተኛ አካላት ፍትህ  እንዲፈፀም መጣር ይገባል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ከተደረገ በሀገራችን የሚሰተዋሉት ዋልታ ረገድ ፅንፈኝነት፣ ስር የሰደደ የፖለቲካ ጥገኝነት፣ አድሏዊነት እና የሙያ እምነት ማጣት እንዲነግስ መንገድ ይጠርጋል።

የኢ-ፍትሃዊነት ጥግ በደረሰበት፣ ሰሚ መንግስት ባልነበረበት ወቅት ለነጻነት፣ ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲ ብዙ ዋጋ ተክፍሏል። ብዙሃኑ ዋጋ የከፈሉበት ትግል ውጤት ማስገኘት በጀመረበት ወቅት ከዚያ በተቃራኒ መጓዝ የተከፈለውን ዋጋ ማውረድ ይሆናል። በነጻነት ለመኖር ነጻነትን ማጣጣም፣ ከነጻነት ጋር የሚመጡ ኃላፊነቶችንም ጠንቅቆ መረዳት እና ለዚህም ለመገዛት መትጋት ያሻል። 

የእርስ-በእርስ ቁጥጥር ጅማሮ

በወርሃ የካቲት እና ሐምሌ 2013 ዓ.ም. የተሻሻለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ዓ.ም. በፀደቀበት ዕለት እና ማግስት መርሳ ሚዲያ ተቋም የተሰኘው ግበር ሰናይ ድርጅት ከፎዮ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ድጋፍ ጋር በመተባባር (ims-fojo) በኢትዮጵያ ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን የርስ በርስ ቁጥጥር ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከባለደርሻ አካላቶች ጋር የምክክር፣ የጥናት ምርምር፣ የፓናል ውይይቶች እያቀረበ የህትመት ውጤቶችን በይፋ አቅርቧል፡፡

በዚህ የሐገሪቱ ሚዲያዎች አዲስ ለውጥ ብለው በመዘገቡት ስነ ስርዓት ላይ መርሳ ሚዲያ ተቋም ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሄኖክ ስማእግዜር እንደተናገሩት “በአስገዳጅ ሕግ ላይ ያልተመሰረተ የመገናኛ ብዙኃን የጋራ ቁጥጥር ስርዓት መዘረጋቱ የሐገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ራሱን በራሱ እንዲቆጣጠር እድል ይሰጣል፡፡ የተጋጋለ ብሄርተኝነት፣ የማኅበረሰብ ግጭት እና የዜጎች መፈናቀል የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሽግግር በተደጋጋሚ እየፈተነ ያለ ጉዳይ ቢሆንም ሃገሪቱ ለበርካታ የማኅበረሰብ አደረጃጀቶች ፈቃጅና አካታች የሆነ ምህዳር በመፍጠር ላለፉት ሶሰት ዓመታት በዴሞክራሲ ሽግግር በማለፍ ላይ ትገኛለች፡፡”

የቀድሞው የብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ድንቁ “የመገናኛ ብዙኃን ቅሬታዎችና የቅሬታ አስተናጋጆች አለመመጣጠን፣ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን የርስ በርስ ቁጥጥር ሰርዓት ላይ ያሉ ምልከታዎች” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅኁፍ እንዳሰፈሩት “ቁጥራቸው የማይናቅ የመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ኢቢሲን ጨምሮ ሌሎች የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት አባል አይደሉም፡፡ የመገናኛ ብዙኃን በሚጠራቸው ስብሰባዎች አባል ብንሆን ምን እንጠቀማለን በሚል የግል ጥቅም እንጅ የእርስበርስ ስርዓት ግንባታን በማምጣት ለህዝብ የሚኖራቸውን ወገንተኛነት የሚደራጀበት እድል አላዩም፡፡ ይህም በግንዛቤው ረገድ አሁንም ድረስ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ታምራት ኃይሉ በበኩላቸው አሁንም ድረስ ምክር ቤቱ ላይ ለሚነሱ አደረጃጀት እና ቁመና ችግሮች አባል መሆን የሚገባቸው የሚዲያ አካላት ያላቸው ተሰታፎ ዝቅተኛነት ያነሳሉ፡፡   

የምክር ቤቱ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መንቃት ይገባቸዋል ሲሉ አሰተያየታቸውን የሚሰጡት ወ/ሪት ፋሲካ ታደሰ ከኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር ባቀረቡት ፅሁፍ እንዳሉት “የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ከተቋቋመ አራት ዓመታት በላይ ቢሞላውም የተሰጠውን ስልጣን እና ተግባር በማስከበር ረገድ እንዲሁም የሚዲያዎችን የርስ በርስ ቁጥጥር ግቡን እንዲመታ ያለበትን ኃላፊነት ለመወጣት በተለይም ሊመለከታቸው የሚገቡ በሚዲያ ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ተቀብሎ በማስተናገድ ረገድ ወደ ስራ አልገባም” ሲሉ ይገልፃሉ፡፡  

የኢትዮጵያ የሚዲያ ሕግ ሪፎርም ቡድን መሪ አቶ ሰለሞን ጎሹ በበኩላቸው “የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000፣ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/1999፣ እና የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008ን ጨምሮ የመገናኛ ብሁኃን ሕጎች ከመፅደቃቸው በፊት በረቂቅ ደረጃ ሳሉ ጀምሮ አወዛጋቢ እንደነበሩ ይታወሳል። ሕጎቹ ታውጀው በሥራ ላይ ሲውሉ በይዘታቸውም ሆነ በአተገባበራቸው አወዛጋቢነታቸው ጨምሯል። በተለይም ሕጎቹ “መሰረታዊ የዜጎችን መብቶች ለማጣበብና ዘርፉን ለማዳከም ምክንያት ሆነዋል” በሚል ብዙ ትችት ሲቀርብባቸው ቆይቷል። ከዚህም በመነሳት፣ መንግሥት እነዚህን ሕጎች መልሶ በመፈተሽና ችግሮቹን በመለየት ለመገናኛ ብዙኃን ዘርፉ የርስ በርስ ቁጥጥርን በሚደግፍ መልኩ በገልፅ በሕግ ደረጃ ተረቆ በምክር ቤት ዋስትና ተሰጥቶት ወጧል፡፡”

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ም/ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋየ ዋነኛዎቹ የመገናኛ ብዙኃን የርስ በርስ ቁጥጥር በኢትዮጵያ ሚዲያ ፖሊሲ፣ እና አዋጆች እውቅና የተሰጠው በመሆኑ ዘርፉን ባለሙያው እንዲመራው ለመስራት ባለስልጣኑ ዝግጁነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

Author: undefined undefined
ጦማሪአየለ አዲስ

Ayele Addis is an award winner Journalist, Journalism, Trainer, Researcher, and Media & Communication Development Consultancy for Thomson Reuters' Foundation, Africa News Channel, Amhara Media, and Journalists Association. Ethiopian Mass Media Action (EMMA News), ARMA Media Production.Woldia University and Bahir Dar University and founder of Journal of Ethiopian Media and Communications.