ሚያዝያ 1 ፣ 2014

የአማራ ክልል የግል ኮሌጆች ከ10 የሚበልጡ የትምህርት መስኮችን እንዳናስተምር ተከልክለናል አሉ

City: Bahir Darዜና

የቴክኒክና ሙያ ስልጠናዎችን እየሰጡ የሚገኙት ተቋማቱ እገዳው ተማሪዎች የሚፈልጉትን የትምህርት መስክ በግል ተቋማት እንዳያገኙ የሚገድብ ነው ብለዋል።

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

የአማራ ክልል የግል ኮሌጆች ከ10 የሚበልጡ የትምህርት መስኮችን እንዳናስተምር ተከልክለናል አሉ
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሚዲያ

ከ10 በሚበልጡ ተፈላጊ የትምህርት መስኮች ስልጠና እንዳይሰጡ መከልከላቸውን በአማራ ክልል የሚገኙ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስታወቁ። የቴክኒክና ሙያ ስልጠናዎችን እየሰጡ የሚገኙት ተቋማቱ እገዳው ተማሪዎች የሚፈልጉትን የትምህርት መስክ በግል ተቋማት እንዳያገኙ የሚገድብ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል የግል ኮሌጆች ማኅበር ዋና ጸሐፊ አቶ አማረ ህሩይ ማኅበሩ የክልሉ የሥራ እና ሥልጠና ቢሮ በተወሰኑ የትምህርት መስኮች ላይ የተጣለውን እገዳ እንደሚቃወም ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። በተጨማሪም ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች በተለየ በክልሉ በሚንቀሳቀሱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ብቻ የተተገበረው ክልከላ እንዲነሳ ጠይቀዋል።

የባህርዳር ከተማ ነዋሪ የሆነችው ተማሪ መታደል ታደሰ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ባለማምጣቷ በግል ኮሌጆች አካውንቲንግ ለመማር ብታቅድም እንዳልተሳካላት ትናገራለች። “እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎችም ተማሪዎች አሉ” የምትለው ተማሪዋ አካውንቲንግ፣ የሰው ኃይል አስተዳደር፣ ሰርቬይንግ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መማር የሚፈልጉ ተማሪዎች ኮሌጅ በማጣታቸው የማይፈልጉትን የትምህርት መስክ ለመመዝገብ እንደተገደዱ ነግራናለች። “ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆቹ የሚሰጡን ምላሽ እነዚህን ፊልዶች እንዳናስተምር ታግደናል የሚል ነው” ብላለች።

በአማራ ክልል የሥራ እና ክህሎት ቢሮ የተቋማት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙላው አበበ በበኩላቸው “የትምህርት መስኮች በተማሪዎች ፍላጎት ብቻ አይከፈቱም” ይላሉ። "የገበያ ጥናትን መሰረት ማድረግ ያስፈልጋል። ባለሙያ የሚመረተው ኢኮኖሚው የሚፈልገው የሰው ኃይል ተጠንቶ ነው" ብለዋል።

ኮሌጆች የሚያስተምሯቸው የትምህርት መስኮች የሚወሰኑት በየ5 ዓመቱ በሚካሄድ የገበያ ጥናት እንደሆነ ዳይሬክተሩ አብራርተዋል። “በጥናቱ መሰረት የትምህርት መስኮች አሁን ያላቸው እና ወደፊት የሚያስፈልጋቸው የሰለጠነ የሰው ኃይል ይለያል። የትምህርት መስኮች የሚከፈቱት በዚህ ሂደት አልፈው፤ የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው” ያሉ ሲሆን፤ ክልሉ የሚፈልገውን የሰው ኃይል አስልቶ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ላይ ጊዜዊ እገዳ ሊጥል እንደሚችልም ነግረውናል።

በተጨማሪም የግል ኮሌጆች ማኅበር ሊቀመንበሩ “ክልከላው በአማራ ክልል ብቻ ያለ ነው” የሚለውን ቅሬታ በተመለከተ ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ “ክልሎች ይህንን ዓይነት አሰራር እንደማይከተሉ ጠቅሰን ያቀረብነው ጥያቄ ሳይመለስ ኃላፊው በመልቀቃቸው ችግሩ እስካሁን አልተፈታም” ብለዋል። የትምህርት መስኮችን የሚወስነው የገበያ ጥናቱ ውጤት መሆን እንዳለበት በቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂው ላይ በግልጽ መቀመጡን አንስተዋል። "ጥናቱ ድንበር ተሻጋሪ ሙያዎችን ማለትም ማክሮ ኢኮኖሚው በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚፈልጋቸውን ከግምት ያስገባ ነው" ብለዋል። ችግሩን ለመቅረፍም ጥናቱ በፌደራል ደረጃ እንዲካሄድ ጥያቄ ማቅረባቸውንም ሰምተናል። “ጥናቱ በክልል ብቻ የተወሰነ መሆኑ እና ወደ ሌሎች ክልሎች ተጉዞ የመቀጠርን ዕደል መዘንጋቱ ዋነኛ ችግሩ እንደሆነ ጠቅሰዋል። “ጥናቱ ኢኮኖሚው የሚፈልገውን የስራ እድል ብቻ ሳይሆን የተማሪዎችን የግል ፍላጎት ያማከለ ሊሆን ይገባል” ብለዋል።

“ተማሪዎች መሰልጠን የፈለጉትን ሙያ ብቻ ማሰልጠን ተገቢ አደልም” የሚል አቋም ያላቸው አቶ ሙላው ለአባባላቸው ምክንያት ያሉትን ሲያስቀምጡ “ኢኮኖሚው ሚፈልገውን፣ ተማሪውን ብሎም ከተማዋን እና ሐገሪቱን የሚጠቅመውን መስክ መለየት የመንግሥት ኃላፊነት ነው” ብለዋል። 

ከአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንዲያመለክተው በክልሉ 83 የግል እና 113 የመንግሥት ኮሌጆች ይገኛሉ። እንደ ቢሮው እምነት በክልሉ የሚገኙት ተቋማት የመማር ፍላጎት ያለውን ሁሉንም ተማሪ የማስተናገድ አቅም አላቸው።

በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተለያዩ የሙያ መስኮች የሚሰለጥኑ ተማሪዎች ከስልጠና መስካቸው አንጻር “ሀርድ” እና “ሶፍት” በሚል በሁለት ይከፈላሉ። የጤና፣ የቢዝነስ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች “ሶፍት” በሚለው ምድብ ውስጥ ይገኛሉ። “ሀርድ” በተሰኘው ዘርፍ ውስጥ ደግሞ ማኑፋክቸሪንግ፣ አውቶመካኒክ እና መሰል ዘርፎች ይካተታሉ። በጥናቱ መሰረት “ሶፍት” በሚለው ምድብ ውስጥ የተዘረዘሩት መስኮች የሰፋ የስራ እድል የላቸውም ተብሏል።

በትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ያላመጡ በቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ በግልፅ ተቀምጧል። ከዚህ ጋር በተገናኘ በበፌደራል ደረጃ የዲፕሎማ ደረጃ የስልጠና መስኮች ቢከለከሉም በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ከደረጃ 1 - 5 በተለያዩ ሙያዎች ስልጠና አንደሚሰጥ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል።

አስተያየት