የንብ ቀፎን የሚቆጣጠር ስማርት ቴክኖሎጂን ያስተዋዋቀው የፈጠራ ሀሳብ

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታነሐሴ 10 ፣ 2013
City: Addis Ababaቴክንግድ
የንብ ቀፎን የሚቆጣጠር ስማርት ቴክኖሎጂን ያስተዋዋቀው የፈጠራ ሀሳብ

ምዕራብ ኢትዮጵያ ወደ ምትገኘው መቱ ከተማ በስራ ጉዳይ በተገኘሁበት አጋጣሚ ገበያ ውስጥ ማር ገዝቼ ወደ አረፍኩበት ቦታ እስክመለስ ድረስ የሀገራችንን የንብ አናቢዎች አንግልት አሰብኩት የሚለዉ የ27 ዓመቱ  የኮምፒዩተር ኢንጅነሪንግ ምሩቅ ወጣት አብይ ታዲዮስ ይህም ለአዲስ የፈጠራ ሀሳብ እንዳነሳሳዉ ይናገራል። 

“ከዚያም “አናቢ” ብለን የሰየምነውን የንብ አነባብ እና ማር ምርት ባህልን የሚያዘምን ቴክኖሎጂ ለመስራት መንቀሳቀስ ጀመርኩ” ይላል፡፡

በኢትዮጵያ ንብ ማነብ ባህላዊ እና እጅግ ልፋት የሚጠይቅ ስራ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ችግሩ እና ልፋቱ የሚመጣው ከቴክኒክ እጥረት መሆኑን የተገነዘቡት አብይ እና ባልደረቦቹ ንብ አንቢዎች እና ማር አምራቾች ውጤታማ በሆነ መንገድ የማያቋርጥ የማር አቅርቦት እንዲያቀርቡ ያስችላቸዋል ብለው ያመኑበትን ቴክኖሎጂ ይፋ አደረጉ።

ይህ ግብርና ተኮር የሆነው የፈጠራ ቴክኖሎጂ በዋናነት የሚያተኩረው የንብ ማነብ ባህልን ከማሻሻል ባለፈ የአሠራር ወጪን ለመቀነስም ጭምር ነው። 'አናቢ' ስማርት ቴክኖሎጂን በንብ ቀፎዎች ላይ የሚገጠምና በቀፎዉ ውስጥ የሚከናወነዉን ሂደት በተመለከተ ለአንቢዉ መረጃ የሚሰጥ መሳሪያ ያለዉ ሲሆን አንቢዉ ንቦቹ ያሉነትን ሁኔታ፤ የማሩን ደረጃ፤ አና ሌሎች መረጃዎችን በቀላሉ በስልኩ መቆጣጠር የሚያስችል ነዉ፡፡

በዚህም የመንጋውን እና የማር ምርትን ሁኔታ ለመከታተል የሚረዳ ከበይነመረብ ጋር የተገናኙ ዳሳሾች በንብ ቀፎዎች ውስጥ ተጭነው የማር ምርት ሂደቱ ምን ላይ እንዳለ፣ ንቦቹ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ፣ ንግስቷ ንብ ከቀፎው መውጣቷን እንዲሁም ተመሳሳይ ኡደቶችን ንብ አንቢው ቀፎው ጋር መሄድ ሳይጠበቀበት ባለበት ሆኖ በኢንተርኔት መከታተል እንደሚችል መስራቹ አስረድቶናል።

እንደ አብይ ገለጻ አንቢዎች በዚህ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ከሆነ በአማካይ የ 30 በመቶ ዕድገት ማግኘት ይችላሉ። ፈጠራው የንብ ቀፎዎች አያያዝ እና ባህላዊ አሰራር የሚያስከትሉትን ተግዳሮቶች ለመቋቋም እና ክፍተቶችን ለመሙላት ታስቦ ወደ ስራ መግባቱን አዉቀናል።

“በሀገራችን የንብ ማነብ ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ የማደግ አቅም እንዳለው አምናለሁ። በሀገር ውስጥ ፍጆታ መጨመር እንዲሁም በተለያዩ ደንበኞች እና ድርጅቶች ወደ ውጭ በመላክ የማር ፍላጎት እየጨመረ ነው።” የሚለው አብይ ሀገሪቱ ያላት የተፈጥሮ ሃብት እንዲሁም የሰው ሀብቷ በማር ብዛት ውስጥየማር ምርቷን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ግልጽ ነው ሲል ይናገራል። 

ከዚህ ጋር በተያያዘ አዲስ ዘይቤ “ፈጠራው ከኢንተርኔት ጋር የተጎዳኘ እንደመሆኑና የሀገራችን አብዛኛው ንብ አንቢ ደግሞ በአብዘሀኛ ከከተማ ውጭ የሚኖር ሰው በመሆኑ ቴክኖሎጂውን የሚጠቀሙበት መንገድ ታስቦበታል ወይ?” ስትል ለጠየቀችው ጥያቄ “እኛ መጀመርያ የምንገናኘው እነዚህን ንብ አንቢ ገበሬዎች አቅፈው ከሚሰሩ ኩባንያዎች ጋር ሲሆን ለገበሬዎቹ የሚሰጡ ስልጠናዎችን እና ግንዛቤ ማስጨበጫዎች ላይ ከነዚህ ድርጅቶች ጋር በመጣመር የምንሰራ ይሆናል።” ሲል አቢይ መልሷል።

ከተመሰረተ አንድ አመትን ያስቆጠረው ‘አናቢ’ የሙከራ ጊዜውን በስኬት አጠናቆ በአሁን ሰዓት ከሁለት ድርጅቶች ጋር ተጣምሮ ስራውን የጀመረ ሲሆን ከእቅዶቹ መካከል በምሥራቅ አፍሪካ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የንብ ማነብ ሰራተኞችን ለመድረስ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዘመናዊ ቀፎዎችን በመስራት ትላልቅ እና የተራቀቁ የአገልጋይ ስርዓቶችን በማከራየት የአገልግሎት አቅምን ለማሳደግ መስራት አንዱ ነው።

በኢትዮጵያ በተለይም በገጠሩ አካባቢ የሚስተዋለው የኢንተርኔት ፍጥነት ችግር ፈጠራዉን ለመጠቀም አንዱ ተግዳሮት መሆኑን አብይ ይናገራል። በሌላ በኩል የፋይናንስ ተደራሽነትም ትልቅ ፈተና መሆኑን ጠቅሶ “የእኛ ራዕይ ወደ አህጉሪቷ መስፋፋት ሆኖ ሳለ ምርታችንን ለገበያ ለማቅረብ የሚፈለገው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚፈለገውን ድጋፍ ማግኘት ካልቻልን ለስራው ስጋት ይሆንብናል” ብሏል።

በሌላ በኩል ኩባንያው ተደራሽነቱን ለማስፋት በተለያዩ የኅብረት ሥራ ማህበራት ውስጥ ያሉ የንብ ምርምር ማዕከሎችን በማግኘት ፈጠራውን እያስተዋወቁ መሆናቸውንም ከመስራቹ ሰምተናል።

“ይህ ስራ የኔ ጥረት ብቻ አይደለም የተባባሪ መስራች ጓደኛዬ እና የሁሉም ባልደረባዎቼ ትብብር ጥምር ውጤት ነው።” ሲል የስራውን ሂደት የነገረን አብይ አክሎም እሱም ሆነ ባልደረቦቹ በሶስት አመት ውስጥ ትርፋማ ለመሆን እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጿል።

Author: undefined undefined
ጦማሪንግስት በርታ

Nigist is working as a reporter and content creator at Addis Zeybe to explore her passion for storytelling. She has Bsc. in medical laboratories & BA in media and Communications.