ጥቅምት 20 ፣ 2014

የቴሌኮም አገልግሎቶችን የሚሰጥ ማሽን ሥራ ሊጀምር ነው

City: Addis Ababaቴክዜናወቅታዊ ጉዳዮች

የኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያ ደንበኞች መሰረታዊ የሆኑ አራት የቴሌኮም አገልግሎቶችን ራሳቸውን ማስተናገድ የሚያገኙበትን  “Self Service Kiosk Machine” በመባል የሚታወቅ አዲስ ማሽን ለማስተዋወቅ በተለያዩ ቦታዎች ሙከራ ላይ ነው።

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

የቴሌኮም አገልግሎቶችን የሚሰጥ ማሽን ሥራ ሊጀምር ነው

የኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያ ደንበኞች መሰረታዊ የሆኑ አራት የቴሌኮም አገልግሎቶችን ራሳቸውን ማስተናገድ የሚያገኙበትን  “Self Service Kiosk Machine” በመባል የሚታወቅ አዲስ ማሽን ለማስተዋወቅ በተለያዩ ቦታዎች ሙከራ ላይ መሆኑን አዲስ ዘይቤ ተመልክታለች።

ይህ የግል አገልግሎቶችን ማግኛ ማሽን አዲስ ሲም ካርድ ለማውጣት፣ የጠፋ ሲም ካርድን ለማውጣት፣ የስልክ አገልግሎት ክፍያን ለመፈጸም እንዲሁም የአየር ሰዓትን ለመግዛት የሚያስችል ሲሆን በመጀመርያው ዙር በአዲስ አበባ ከተማ ለአገልግሎት ተደራሽነት ምቹ ይሆናሉ ተብለው በተመረጡ አስር ቦታዎች ላይ ለመትከል እቅድ የተያዘ ሲሆን በአሁን ሰዓት ሶስት ቦታዎች ላይ ተተክሎ የሙከራ ስራ እየተካሄደበት እንደሚገኝ ከኢትዮ ቴሌኮም ኮሚዩኒኬሽን ክፍል ዋና ሃላፊ መሳይ ውብሸት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ማሽኑ ለሙከራ ከተተከሉባቸው ሶስቱ ቦታዎች መካከል የመጀመርያው ወደ ቸርችል ጎዳና በሚወስደው መንገድ ከሊሴ ገብረማርያም አጠገብ በሚገኘው የኢትዮ ቴሌኮም የሽያጭ ማዕከል የሚገኝ ሲሆን፣ የተቀሩት ሁለቱ ቦሌ መድሃኒዓለም አካባቢ በሚገኙ ሁለት የገበያ ማዕከል ህንጻዎች ላይ ይገኛሉ።

ማሽኑ ለአገልግሎቱ በጥሬ ገንዘብ ክፍያ እንዲቀበል ተደርጎ የተሰራ ሲሆን ሲም ካርድ ለማውጣት የሚያስፈልገውን መታወቂያ ማንበብ የሚችልበት አሰራርም ተካቶበታል።

የደንበኞችን አገልግሎት የተቀላጠፈ እና ፈጣን ያደርጋል ተብሎ የታመነበት ይህ መሳርያ የተመረተው ከሀገር ውጪ በሚገኝ የቴክኖሎጂ አምራች ድርጅት መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ የድርጅቱን ማንነት እና በአጠቃላይ የወጣበት ወጪ ኢትዮ ቴሌኮም ማሽኑን አስመርቆ ይፋ በሚያደርግበት ወቅት እንደሚገለጽ ሃላፊው ጠቅሰዋል።

ከቴክኖሎጂው አዲስነት ጋር በተያያዘ አዲስ ዘይቤ የባለሙያ አስተያየታቸውን የጠየቀቻቸው በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ፋሲካ ቤተማርያም ሲያብራሩ “ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እያደገ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ እንደዚህ ያሉ ራስን በራስ ማስተናገድ የሚያስችሉ ማሽኖች ወደ ሀገር ውስጥ መምጣታቸው የሚጠበቅ ነገር ነው፣ እንዲያውም በቴሌኮም አገልግሎት ብቻ መገደብ የለበትም ሌሎች ከደንበኛ ጋር ፊት ለፊት የሚያገናኙ ተቋማትም ይህን መከተል ይኖርባቸዋል” ይላሉ።

ከሌሎች የዓለም ሀገራት ልምድ በመነሳት የሚሰጠውን ጥቅም ሲያብራሩም፣ ማሽኖቹ ሕዝብ እንደ ልብ በሚያገኛቸው ቦታዎች ላይ ስለሚተከሉ ያለምንም ሰዓት ገደብ የሽያጭ ቦታዎችን ወረፋ ሳይጠብቁ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉ ሲሆን በዚህ መንገድ የሚሰጠው ለደንበኞችም ሆነ ለተቋማት የጋራ ጥቅም ይሰጣል ብለዋል።

ከዚሁ ጋር አያይዘው ቴክኖሎጂው ወደ አዳጊ ሀገር ሲመጣም የራሱን ስጋት ይዞ ይመጣል ሲሉ ያስረዳሉ “በሀገራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ያለውን ኤቲኤም ማሽን ስንመለከት በተደጋጋሚ እየተበላሹ አገልግሎት መስጠት ሲያቆሙ የምናስተውልበት አንዱ ምክንያት የአጠቃቀም እውቀት ማነስ መሆኑ አያጠያይቅም” በማለት አንድ ኩባንያ እንዲህ ያሉ ማሽኖችን ሲያስተዋውቅ ‘ትራያል ኤንድ ኢረር’ ብለን የምንጠራውን እቅድ አብሮ ይዞ መምጣት እንደሚኖርበት እና በዛ መንገድ ኪሳራን እና ትርፍን በጥሩ መልኩ ለማስተናገድ እንደሚያመች ምክራቸውን ያስቀምጣሉ።

በሌላ በኩል “ኩባንያዉ ደንበኞች በራሳችዉ አገልግሎት የሚያገኙበት ማሽኖችን ሲያስተዋውቅ የሰው ሃይልን የመቀነስ እቅድ ይኖረው ይሆን ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄ የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ሃላፊው ሲመልሱ “ይህን ማሽን ለተገልጋዮች ለማቅረብ ስናስብ ዋነኛው አላማችን አድርገን የተነሳነው የደንበኛን ፍላጎት ማርካትን እና የደንበኞቻችንን ቁጥር ማብዛትን ነው፣ በመሆኑም ስራውን የሚያሳድግ እና በዘርፈ ብዙ መልኩ የሚያበዛ ቴክኖሎጂ ከመሆኑ አንጻር በሰው ሃይልም እያደግን ብንሄድ እንጂ መቀነስ የሚለው ጉዳይ ቅንጣት አያሳስብም” ሲሉ አስረድተዋል።

በመሆኑም ቴክኖሎጂ የማያቆም ሂደት መሆኑን በማንሳት ድርጅቱ በቴክኖሎጂ በበለፀገ ቁጥር ሰራተኞችም የሚያድጉበትን ሁኔታ ሊያስቡ እንደሚገባ እና ሊያበረታቱት እንደሚገባ ተናግረዋል።