የመብራት መቆራረጥ የፈተናቸዉ ነዋሪዎች

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታነሐሴ 13 ፣ 2013
City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮች
የመብራት መቆራረጥ የፈተናቸዉ ነዋሪዎች
Camera Icon

Photo: Addis Fortune

ወ/ሮ እጥፍወርቅ ኪዳኔ አየር ጤና አካባቢ ዳቦ በመጋገር እና ማከፋፈል ሥራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን  የመብራት መቆራረጥ በስራቸዉ ላይ ትልቅ ችግር እየፈጠረ አንደሚገኝ ይናገራሉ።

“በተለይ ክረምት ሲመጣ ለኔ ፈተና ነው የሚሆንብኝ በዚህ ወቅት መብራት በተደጋጋሚ ስለሚጠፋብን ያዘጋጀነዉን ሊጥ እስከ መድፋት ደርሰን እናዉቃለን” በማለት ሀሳባቸዉን የሰጡን አጥፍወርቅ ደንበኞቻቸውንም በአግባቡ ማስተናገድ አለመቻላቸውን  በመጥቀስ “ትዕዛዝ ለሚሰጡን ደንበኞች ትዕዛዛቸውን በጊዜው እንዳናደርስ መሰናክል ሆኖብናል በዚህም ከብዙ ደንበኞቻችን ጋር ተቆራርጠናል” ሲሉ ያነሳሉ።

በዚህም ምክንያት ገቢያቸው እንዳሽቆለቆለ ያስረዳሉ “ኑሮዉ ተሰርቶም አልገፋ ባለበት ጊዜ መብራቱ ደግሞ ሌላ ራስ ምታት ሆኖብናል፥ በዛ ላይ ደግሞ የመብራት ክፍያ የተጋነነ መሆኑ ምንም ግልፅ አይደለም ” ሲሉ የመብራት ታሪፍ ከአጠቃቀማቸው ጋር አለመጣጣሙን ያነሳሉ።

አዲስ አበባ ላንቻ አካባቢ አነስተኛ የወንዶች የውበት ሳሎን ከፍቶ የሚተዳደረው ወጣት ቤካ ጎርፉ በመብራት መቆራረጥ የንግድ ስራቸዉ ከሚስተጓጎል ሰዎች አንዱ ነዉ። በዚህ የሥራ ዘርፍ ላይ ለአራት ዓመት እንደቆየ የነገረን ይህ ወጣት፣ በመብራት ሳቢያ ምንም ሥራ መሥራት እንዳልቻለ ያስረዳል።

“ወይ እንደበፊቱ ፈረቃ ከሆነም ይንገሩንና የማይኖርበትን ቀን ካወቅን ከትራንስፖርት ወጪም ሆነ ደንበኛን አጓጉል መጉላላት ውስጥ ከመክተት እንድናለን ” ይላል።

መብራቱም የኮሮና ወረርሽኝ ተጨምሮ በስራዉ ላይ መቀዛቀዝ አንዳጋጠመዉ እና መብራት በማይኖርበት ሰዓት ለጊዜ፣ ለገንዘብ እና ለጉልበት ኪሳራ እየዳረገዉ አንደሚገኝ ያስረዳል፡፡ 

የጸጉር ቤት ስራ ከመብራት ዉጭ በሌላ ምንም አይነት የሀይል አማራጭ ሊሰራ አንደማይችል የሚገልጸዉ ቤካ በመብራት ምክያት በርካታ ደንበኞቹ እየራቁት አንደሆና ይህም ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንደጋረጠበት ይናገራል፡፡

ሌላው ያነጋገርናቸው የፒያሳ ቅርንጫፍ ባንክ ማናጀር ዱባለ ግርማ በበኩላቸው “የመብራት መቆራረጡ ነገር ኖርማል እስኪመስል ድረስ ተለምዷል፣ የመብራት ሃይል መስርያቤት ራሱ እዚህ አጠገባችን ሆኖ ከኛ እኩል ጄኔሬተርን አብርተው መጠቀምን እንደ ኖርማል ተቀብለው ለአቤቱታ የይሻሻላል መልስ ብቻ መስጠታቸው ጉዳት ሆኖ ቀጥሏል።” ይላሉ

ዳቦ በመጋገር የሚተዳደሩትን ወ/ሮ እጥፍወርቅን ጨምሮ ሌሎች ያነጋገርናቸው በመብራት ላይ ጥገኛ የሆነ በስራ ላይ የተሰማሩት ሰዎች ሁሉ ይህን ይመሰክራሉ። ከምግብ ማብሰያነት ጀምሮ ለዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች የሚዉለዉ የመብራት ሃይል በሚያጋጥመዉ መቆራረጥ ምክኒያት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ቁሶችን እንዲቃጠሉ ማድረጉ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከደንበኞቹ ቅሬታ ይቀርብበታል፡፡

በሀገሪቱ የአገልግሎት አቅርቦት ከፍተኛ ቅሬታ የሚቀርብበት የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ራሱ በዘንድሮው አመት ብቻ በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ከ18ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ በላይ ውሃ ማምረት እንዳልቻለ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ አቶ እስጢፋኖስ ብስራት ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። “ይህን ሃይል ለመተካት በዚህ ዓመት ከ426,000 ብር በላይ ነዳጅ ለጄኔሬተር ወጪ አድርገናል። ይህም ሆኖ ግን ጄኔሬተሩ በቀን 8 ሰዓት ብቻ በመስራቱ ህብረተሰቡ ለውሃ ችግር መዳረጉን ቀጥሏል” ብለዋል።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን በብቸኝነት የሚያቀርበው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፓሬሽን እንደመሆኑ እና የመብራት መቆራረጥን ለመቀነስ የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎችን እየሰራ አንደሚገኝ በተደጋጋሚ ቢገልጽም አሁንም እነዚህ ቅሬታዎች አልቆሙም። አገልግሎቱ የደንበኞችን ዕርካታ ካለማሟላቱ በተጨማሪ ተገልጋዮች የሚከፍሉት ታሪፍ እየጨመረ መሄዱ ተገቢ አይደለም ሲሉ ብዙዎች ያነሳሉ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ይህን የደንበኞች የዕርካታ መጠንን ለመለካት ይረዳው ዘንድ በ2011 ሕዳር ወር ላይ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ባስጠናው ጥናት፣ በአገራችን ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል በተለያየ ምክንያት እንደሚቋረጥ እና ችግሮቹ ታውቀው ለመፍትሄው እንደሚሰራ መገለፁ ይታወሳል፡ በጥናቱም መፍትሄ ላይ መደረሱን ጠቅሶ በ2013 ዓ.ም አጋማሽ ችግሮቹ እንደሚቀረፉ ገልጾ ነበር። 

ችግሮቹ ይቀረፋሉ የተባለባት ዓመት እየተጠናቀቀ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ “ፕሮጀክቱ ምን ላይ ደረሰ? የተገልጋዩስ ቅሬታ ምላሽ የሚያገኘው እንዴት ነው?” ስትል አዲስ ዘይቤ በአዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ስራ አስኪያጅ በቀለ ክፍሌን አነጋግራለች።

ሥራ አስኪያጁ የጥናቱ ውጤት በኃይል መቆራረጥ ላይ የተገልጋዩ ሕብረተሰብ ቅሬታ በጣም ከፍተኛ እንደነበረ  ማሳየቱን አስታዉሰዉ  ይሁን እንጂ በአሁን ወቅት በዛ ጊዜ በጥናቱ ተዳሰው የነበሩት የቴክኒክ ችግሮች ሙሉ በሙሉ መቀረፋቸውን እና አሁን ላይ የሚያጋጥሙት የመብራት መቆራረጦች ከተቋሙ የቴክኒክ ችግር ከመሆን ይልቅ የሀገሪቱ ሃይል እና የአቅርቦት መጠን አለመመጣጠን መሆኑን ስራ አስኪያጁ ያስረዳሉ። በተጨማሪም በጥናቱ እንዲሰሩ በተወሰነው መሰረት 66 ኪሎ ቮልትን ጨምሮ ከ132-230 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመሮች ተገንብተዋል።

“በአብዛኛው አሁን ከተማው ውስጥ እየተከሰተ ያለው በብልሽት ምክንያት  የሚፈጠር የኃይል መቋረጥ ነው።” የሚሉት ስራ አስኪያጁ ለብልሽቶቹ በሀገሪቱ የሚከናወኑትን ከፍተኛ የግንባታ ሂደቶች እንደምክንያት ያነሳሉ። በተጨማሪም በምስሶዎች ላይ የሚያጋጥም የመኪና ግጭት፣ የዛፍ መውደቅ፣ በግንባታና መንገድ ሥራዎች ወቅት ከሚከሰት የኤሌክትሪክ ሽቦ መቆረጥ ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ አደጋዎች መብራት ለረጅም ሰዓት እንዲቋረጥ ምክንያት መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ።

ስራ አስኪያጁ ተቋሙ በወሰዳቸው መፍትሄዎች የቴክኒክ ችግሮች መቀረፋቸዉን ቢያስረዱም አሁን ላይ የሚታየው ተደጋጋሚ መቆራረጥ እና በበርካታ ዘርፎች ላይ እያሳደረው ያለው ተፅዕኖ ከታሪፉ መጨመር ጋር ተደራርቦ ያለውን ስሞታ በመጥቀስ “የቴክኒክ ችግር ተቀርፎ ከሆነ ምናልባት ከሃይል እጥረት ጋር የተያያዘ ችግር ይኖር ይሆን?” ስትል አዲስ ዘይቤ ላነሳችው ጥያቄ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የውጭ ግንኙነት ሃላፊ ምስክር ነጋሽ ማብራርያ ሰጥተዋል።

“ከሃይል ጋር በተያያዘ ምንም እጥረት እንደሌለብን እናረጋግጣለን። ይሁን እንጂ የሀገሪቱ የሃይል አቅርቦት ጠያቂ አካላት እልፍ ሆነው ሳለ ሀይሉን የምናከፋፍልባቸው ጣቢያዎች በቁጥር ትንሽ መሆናቸው አለመመጣጠን ችግር ሆኖብናል” ይላሉ።

በሌላ በኩል የታሪፉን ቅሬታ አዘል አስተያየት በተመለከተ ሲያብራሩ  “ቅሬታው ተገቢነት ያለው ቢሆንም ለደንበኞች በተደጋጋሚ ለማሳወቅ የሞከርናቸው አዳዲስ አሰራሮች ስላሉ ነው ታሪፉ ከፍ ያለው” በማለት የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ ታሪፍ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለተወሰኑ ዓመታት ጭማሪ ተደርጎበት እንደሚቀጥል መስርያ ቤቱ ያሳወቀ መሆኑን እና ህዝቡ በፊት የለመደውን ታሪፍ መለወጡን ሊገነዘብ ይገባል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሃላፊው እንደሚሉት ታሪፉ ማሻሻያ ያስፈለገው ተቋሙ ስራውን ለማሻሻል እና ያሉበትን ዉስንነቶች በማስተካከል የሀይል ስርጭቱን ያለመቆራረጥ ለማከፋፈልና በደንበኞች የሚነሱ ቅሬታዎችን በበፍታት የተሻለ አገልግሎት ለማቅረብ አንደሆነ ይናገራሉ፡፡  

እንደ ወ/ሮ እጥፍወርቅ ኪዳኔ ያሉ የመብራት መቆራረጥ የፈተናቸዉ የከተማዋ ነዋሪዎች ግን በመብራት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተስፋ የቆረጡ ይመስላል፡፡ 

“የመብራት ጉዳይ ይሻሻላል ብየ አልጠብቅም፡፡ ሁልጊዜ የሚሰጥ ምክኒያት አንጂ እስካሁን መሬት ላይ የወረደ መፍትሄ አላየሁም” ይላሉ፡፡

Author: undefined undefined
ጦማሪንግስት በርታ

Nigist is working as a reporter and content creator at Addis Zeybe to explore her passion for storytelling. She has Bsc. in medical laboratories & BA in media and Communications.