ነሐሴ 19 ፣ 2014

የአዲስ አበባ የህግ ምሩቃንን ያገለለው የስልጠና እና ስራ ዕድል

City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮች

የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ የሆኑት የአዲስ አበባ ነዋሪ የህግ ምሩቃን በከተማቸው የማይሰጠውን የቅድመ ሥራ ስልጠና ለመውሰድ ስልጠናው ወደሚሰጥባቸው ወደ ሌላ ክልል ከተሞች ለመሄድ ይገደዳሉ

Avatar: Kalayou Hagose
ኻልኣዩ ሓጎሰ

ኻልኣዩ ሓጎሰ የህግ ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን ይፅፋል። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የአዲስ አበባ የህግ ምሩቃንን ያገለለው የስልጠና እና ስራ ዕድል
Camera Icon

ፎቶ፡ ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ

የኢትዮጵያ ፍትህ ስርዓት አዳዲስ የህግ ምሩቃንን በዳኝት እና በዐቃቤ ህግነት አሰልጥኖ የመቅጠር ልምድ አዳብሯል። የዚህ ስልጠና ዋና ዓላማ ሰልጣኞች በከፍተኛ ትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት እና ክህሎት እንዲያሳድጉ እና በቀጥታ የፍትህ ስርዓቱን ከመቀላቀላቸው በፊት የተግባር ልምምድ እንዲያገኙ ማስቻል ነው። 

የፍትህ አካላት የቅድመ ስራ ስልጠና ማዕከላት ካሏቸው ክልሎች ውስጥ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልል እና የጋምቤላ ክልሎች ይገኙበታል። 

ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ የሆኑና ዲግሪያቸውን ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች በህግ ያገኙ ምሩቃን “በአዲስ አበባ የፍትህ አካላት የቅድመ ስራ ስልጠና ተቋም ስለሌለ ዓቃቤ ህግ ወይም ዳኛ ሆኖው መሥራት እንዳልቻሉ” ይናገራሉ።          

ዊንታና ሐብቶም ከአራት ዓመት በፊት ከዲላ ዩኒቨርስቲ በህግ ዲግሪዋን ያገኘች ስትሆን ዓቃቤ ህግና ዳኛ የመሆን ጥልቅ ፍላጎት አላት።

የቅድመ ሥራ ስልጠና  ለመውሰድ አዲስ አበባ የስልጠና ተቋም ባለመኖሩ ዓቃቤ ህግ ወይም ዳኛ የመሆን የቆየ ህልሟን ለማሳካት ወደ አማራ ክልል ለመሄድ መገደዷን ትናገራለች። ሆኖም ስልጠናውን ለመውሰድ የነዋሪነት መታወቂያ ስለሚጠይቅ ያሰበችውን የቅድመ ስራ ስልጠና ሳትወስድ ቀርታለች። 

ዊንታና ሁኔታውን ስታስረዳ “ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ የህግ ምሩቃን የግል ተቋም ወይም ሌላ የመንግስት መስሪያ ቤት ካልሆነ በስተቀር ዓቃቤ ህግ ሆነ ዳኛ የመሆን ዕድል የላቸውም፣ ይህም ከአቅም ማነስ ጋር የተያያዘ ሳይሆን አዲስ አበባ ነዋሪዎቿን የሚታሰለጥንበት የራሷ የሆነ የቅድመ ስራ ስልጠና ተቋም ስለሌላት ብቻ ነው” ትላለች።  

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ ከዛሬ አራት ወር በፊት ግንቦት 13 ቀን 2014 ዓ.ም የህግ ባለሙያዎችን በዝውውር አወዳድሮ ለመመደብ ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ለውድድር ሄዳ “የቅድመ ስራ ስልጠና አልወስድሽም” በሚል ምክንያት ከውድድር ዉጭ እንዳደረጓትም ገልጻልናለች። 

“ማስታወቂያው ከወጣ በኋላ ወዲያዉኑ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የቅድመ ሥራ ስልጠናን እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ተገቢ እንዳልሆነና እንደሚያስጠይቅም ጭምር ቢሮው ድረስ ሄደን ብናሳውቃቸውም መልስ አልሰጡንም” ትላለች ዊንታና።

ከአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ በተጨማሪ አዲስ አበባ ከንቲባ ፅ/ቤት፣ የአዲስ አበባ የሰው ሀብት ልማት ቢሮ እና አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ መብታቸውን ለመጠየቅ እንደሄዱ የምትናገረው ዊንታና ቢሮዎቹ ችግሩ እንዳለ ቢያምኑም መፍትሄ ግን እንዳልሰጧቸው ገልጻልናለች።  

“የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ እንደ ሌሎች ክልሎች ለነዋሪዎቹ መፍትሔ ማምጣት ሲገባው በተቃራኒው የቅድመ ስራ ስልጠና እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ችግሩ ይበልጥ እንዲባባስ እያደረገ ነው” ስትል ዊንታና ምሬቷን ገልፃለች።

በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናትና አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው ሄዋን ይርጋም ዲግሪዋን በህግ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ አግኝታለች።

ሄዋንም እንደ ዊንታና በተመሳሳይ ሁኔታ በአዲስ አበባ የፍትህ አካላት የቅድመ ስራ ስልጠና ተቋም ባለመኖሩ ከተመረቀች በኋላ ዓቃቤ ህግ፣ ዳኛ ብሎም ጠበቃ የመሆን ፍላጎቷን ማሳካት ተስኗታል።

“ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ በ2012 ዓ.ም (ማለትም ወ/ሮ ፍሬህይወት ኃላፊ በነበሩበት ጊዜ) በጉዳዩ ላይ ጥያቄ አቅርበን መብታችን እንደሆነና በቅርቡ እንደሚስተካከል ነግረውን ነበር፤  ይሁን እንጂ እስካሁን ምንም  የተስተካከለ ነገር የለም” ትላለች ሄዋን። 

በቀደሙት ጊዜያትም ሆነ አሁን አዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ እያደረገው ያለው ነገር ተመሳሳይ እንደሆነ በማስረዳት፣ የሚመለከተው አካል አቤቱታቸውን ሰምቶ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጥ እንደሚገባ ሄዋን በአፅዕኖት ትናገራለች። 

“በዚህ ችግር ምክንያት ዓቃቤ ህግ ወይም ዳኛ ለመሆን የነበረኝ ትልቅ ተስፋ ጨልሟል፤ ህግ ያጠና የአዲስ አበባ ነዋሪም  ህገ-መንግስታዊ መብቱ እየተጣሰ ነው። የቅድመ ሥራ ስልጠና እንደ ግዴታ እየተወሰደ በመሆኑ በከተማችን እንኳን በዓቃቤ ህግነትም ሆነ በዳኝነት ተቀጥረን  መስራት ባለመቻላችን የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል” ስትል ሄዋን ኃሳቧን ታጋራለች። 

የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ የሆኑት የአዲስ አበባ ነዋሪ የህግ ምሩቃን ከምርቃታቸው በኋላ በከተማቸው የማይሰጠውን የቅድመ ሥራ ስልጠና ለመውሰድ ስልጠናው ወደሚሰጥባቸው ወደ ሌላ ክልል ከተሞች ቢሄዱም በነዚህ የክልል ከተሞች ስልጠና ለማግኘት የነዋሪነት መታወቂያና ቋንቋ እንደ ቅድመ ሁኔታ በመቀመጡ ስልጠናውን ማግኘት ሳይችሉ ይቀራሉ። እነዚህ የክልል ከተሞች ከአዲስ አበባ የሚሄዱ ተመራቂዎች ከክልሉ ነዋሪ ውጪ እድሉን እንደማይሰጡና ቅድሚያ ለክልሎቹ ተመራቂዎች እንደሆነም ይነገራቸዋል።

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አሰፋ መብራቴ አዲስ አበባ የራሷ የተለየ የፍትህ አካላት ማሰልጠኛ ተቋም እንደሌላት አምነው ይህ ግን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከህግ ትምህርት ቤት ተመርቀው ሲወጡ ዳኛ ወይም ዐቃቤ ህግ ሆነው ከመስራት የሚያግዳቸው ነገር አይደለም ይላሉ። 

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ ፍትህ ቢሮ የስራ ልምድ የሌላቸው የህግ ምሩቃንን ሲቀጥር የቅድመ ስራ ስልጠና በመስጠት እንደሆነ ኃላፊው ይናገራሉ።  “ይህ የተደረገውም  ሰልጣኞች  ስልጠናው ለመውሰድ ካላቸው ፍላጎት እና ለፍትህ ስርዓቱ ካለው ጠቀሜታ አንጻር በመሆኑ አዲስ አበባ የራሷ የሆነ የፍትሕ አካላት ማሰልጠኛ ተቋም ባይኖራትም ከፌደራል የፍትህ እና የህግ ምርምር ተቋም በመቀናጀት ስልጠናው እየሰጠን መጥተናል፣ አሁንም እንሰጣለን። በመሆኑም ተቋም አለመኖሩ ችግር የሚያስነሳ ጉዳይ አይደለም” በማለት አቶ አሰፋ ያስረዳሉ።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተለያዩ የፍትህ አካላት ማሰልጠኛ ተቋማት ማስታወቂያ ሲያወጡ በግላቸው ስልጠናውን ወስደው ፍትህ ቢሮ የቅጥር ማስታወቂያ ሲያወጣ መወዳደር እንደሚችሉ እና እድሉም ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ኃላፊው አክለው ገልጸዋል። ይህ እንዳለ ሆኖ “አዲስ አበባ የራሷ የሆነ የፍትህ አካላት የቅድመ ሥራ ማሰልጠኛ ተቋም እንዲኖራት ቅድሚያ ሰጥተን እየሰራን ነው” በማለት አቶ አሰፋ ነግረውናል።

ከላይ እንደተገለፀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ ግንቦት 13 ቀን 2014 ዓ.ም የህግ ባለሙያዎችን በዝውውር አወዳድሮ ለመመደብ ማስታወቂያ አውጥቶ እንደነበር እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለቢሮው ጥያቄ አቅርበው ነበር። 

ይህን ዝዉዉር በተመለከተ አቶ አሰፋ ሲመልሱ ቢሯቸው አዲስ ሰራተኛ እንዳልቀጠረ እና የዝዉዉር ምደባው የቢሮውን ህግ እና ደንብ መሰረት አድርጎ የተክናወነ እንደሆነ ይናገራሉ። 

“ቅጥር ቢሆን የቅድመ ሥራ ስልጠና እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡ ትክክል ላይሆን ይችል ነበር፣ ግን እኛ ያደረግነው ቅጥር ሳይሆን ዝዉውር ነው። ዝውውር ላይ ደግሞ ደንቡ ተወዳዳሪዎቹ የቅድመ ስራ ስልጠና የወስዱ መሆን እንዳለባቸው በግልጽ ያስቀምጣል” ይላሉ።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በአንድ የፌደራል የፍትህ እና የህግ እንስቲቲዩት ውስጥ በቅድመ ስራ ስልጠና ላይ የማስተባበር የዳበረ ልምድ ያላቸው የህግ ባለሙያ ስለችግሩ ሲናገሩ “አንድ የህግ ምሩቅ የቅድመ ስራ ስልጠና ካልወሰደ በቀጥታ ወደ ፍትህ ስርዓቱ የመቀላቀል እድሉ ጠባብ ነው፤ ይህን ደግሞ ካለኝ ልምድ ልረዳ ችያለው” ይላሉ።

አንድ የህግ ባለሙያ አስፈላጊውን ስልጠና ካልወሰደና የተግባር ልምምድ ስልጠናው ከሌለው ደግሞ በዓቃቤ ህግነት ወይም በዳኝነት ተቀጥሮ የመስራት አድሉ ጠባብ እንደሆነ ባለሙያው ያስረዳሉ። ይህም በመሆኑ ብዙ ጊዜ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የቅድመ ስራ ስልጠና የሚወስዱበት ተቋም ስለሌለ ዐቃቤ ህግ ወይም ዳኛ ሆነው የመስራት እድላቸው ዝቅተኛ እንደሆነም ያምናሉ።  

ባለሙያው ለዚህ ችግር መፍትሄ ይሆናሉ ያሏቸው ሁለት ነገር ያስቀምጣሉ። የመጀመርያው እንደ ሌሎች ክልሎች አዲስ አበባም የራሷ የሆነ የህግ የቅድመ ስልጠና ማዕከል በአዋጅ ማቋቋም የሚል ነው። 

ለአዲስ አበባ የራሷ የሆነ ማሰልጠኛ ተቋም የማቋቋም ጉዳይ ብዙ ጊዜ በበጀት ጉዳይ እና በአንድ ከተማ ሁለት የማሰልጠኛ ማእከል አያስፈልግም የሚል ክርክር የሚነሳበት እንደሆነ በመግለጽ ማሰልጠኛው ባይቋቋም እንኳን አዲስ አበባ የፌደራል መንግስት መቀመጫ እስከሆነች ድረስ ነዋሪዎቿ በፌደራል የፍትህ አካላት ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ ገብተው ስልጠናውን እንዲወስዱ ሊፈቀድላቸው ይገባል በማለት ሁለተኛ ያሉትን መፍትሄ አስቀምጠዋል። 

አስተያየት